የህክምና ስነ ምግባርና ስህተት ተኮር ጉዳዮች

46

የሰው ልጅ ከልደቱ እስከ ህልፈተ ሕይወቱ ብዙ የኑሮ ውጣ ውረድ ያጋጥመዋል። ሲወለድ ይህችን ዓለም እያለቀሰ ተቀላቅሎ ሲሞት ደግሞ እየተለቀሰ ይሸኛል። ሲወለድ በደስታና በእልልታ የተቀበሉት ቤተሰቦች ሲሞት በሀዘንና በዋይታ ይሰናበቱታል።

ለሰው የኑሮ መሰናክል ምክንያት ከሆኑት መካከል ወላጅ አልባ መሆን፣ ሥራ አጥነት፣ ሴሰኝነት፣ ሱሰኝነት ፣ጎዳና ተዳዳሪነት እና በሽተኝነት ይጠቀሳሉ። ሰዎች ህክምና ፍለጋ ወደ ተለያዩ ህክምና ሥፍራዎች ይሄዳሉ። አንዳንድ ጊዜ ለመታከም ሄደው በህክምና ስህተት አካላቸው የተቆረጠ፣ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለከፋ በሽታ የተጋለጡ ሰዎች ያጋጥማሉ።

‹‹የህክምና ስህተት ሲከሰት የጤና ባለሙያው የሚከሰሰው በውጤቱ ሳይሆን፣ በተከተለው የህክምና ሂደት ነው›› የሚሉት የህግ ባለሙያው አቶ ሱለይማን ሽጉጤ ፣ባለሙያዎቹ ሙያዊ ነፃነታቸውን ተጠቅመው መሥራት እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ።

አቶ ሱለይማን የህክምና ስህተቶች ከድርጅታዊ፣ ሰዋዊ ፣ከስርአት/ሲስተም/ እና ከታካሚውና ቤተሰቦቹ መረጃ የማስተላለፍ ችግር (contributional error ) ሊመነጩ እንደሚችሉ ይናገራሉ።ለታካሚ ቀዶ ህክምና እየተደረገ መብራት ቢቋረጥ ጄኔሬተሩም ካልሠራና ጉዳት ቢደርስ ችግሩ የህክምና ሲስተም መሆኑን ጠቅሰው፣ ህመምተኛው ለሀኪሙ የተሳሳተ መረጃ ቢሰጥና በዚያው መሰረት ህክምና ሲሰጥ ጉዳት ቢደርስበት ስህተቱ የሀኪሙ ሳይሆን የታማሚው መሆኑን ያብራራሉ።

እንደ አቶ ሱለይማነት ማብራሪያ፤ በመድኃኒት ቤቶች የመድኃኒት ማዘዣ ወረቀት የያዙ ብዙ ደንበኞች ከመጡ ወረቀት ተቀያይሮ የአንዱን መድኃኒት ሌላው የሚወስድበት አጋጣሚ ይፈጠራል። መድኃኒት ገዛሁ ብለው የሄዱት ግለሰብ መድሀኒቱን ሲጠቀሙበት ሊጎዱ ይችላሉ። ተመሳሳይ ችግሮችን ለመቀነስ መድኃኒት ማዘዣው ላይ የኪስ ስልክ ቢፃፍ ችግሩ እንዳይከሰት ለመከላከል ያመቻል። ይህም በስህተት የሌላ ሰው መድኃኒት የወሰዱ ወዲያው በመደወል ተጠርተው ትክክለኛ መድኃኒት እንዲወስዱ ማድረግ ያስችላል።

ጋዜጠኞች የህክምና ስህተቶችን ሲዘግቡ ሚዛናዊ መሆን እንዳለባቸውና በሀኪሙ ችግር ብቻ የተከሰተ አድርጎ መዘገብ ሙያውን ማዳከም መሆኑን ጠቅሰው፣ባለሙያውም ወቀሳ ፍራቻ ከህክምና ርቆ በምርምርና ማስተማር ላይ ብቻ አተኩሮ እንዲሠራ ያደርገዋል ይላሉ።‹‹በጤና ባለሙያዎች የሚታዩ ስህተቶችም ቢኖሩ ወታደሮች የራሳቸው ችሎት እንዳላቸው ሁሉ ለህክምናውም ተመሳሳይ ችሎት ቢኖር ይመረጣል›› ሲሉ የህግ ባለሙያው ይመክራሉ።

እንደ አቶ ሱለይማን ገለጻ፤ የህክምና ስህተቶችን ሀገራዊ ብቻ አድርጎ የማየት እሳቤዎች አሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በህክምና ስህተት ሳቢያ ከ10 ሰው የ4 ሰው ህይወት ያልፋል፡፡በአሜሪካ ብቻ በየዓመቱ 200ሺ ሰዎች በህክምና ስህተት ሳቢያ ይሞታሉ፡፡ ይህም በየቀኑ 547 ሰዎች በህክምና ስህተት እንደሚሞቱ ያሳያል። ከአሜሪካ ህዝብ 84 በመቶው በህክምና የተጎዳ ሰውን ያውቃል።

የአደጉ ሀገሮች የህክምና ስህተትን ለመቀነስ እንጂ ለማስወገድ እንደማይችሉ አቶ ሱለይማን ጠቅሰው፣በዓለም ላይ የህክምና ሙያ በስህተት የታጀበ ዘርፍ መሆኑን ይጠቁማሉ።በ1962 የወጣው የፍትሐ ብሄር ሕግ የጤና ባለሙያው የማዳን ዋስትና የለውም እንደሚል በመጥቀስም ፣በዚህ ላይ የጤና ባለሙያው ዋስትና እንዲሰጥ እንደማይገደድም ነው የሚያብራሩት።

በጤና ባለሙያ መስፈርት ቸልተኝነት ከደረጃው ውጪ ህክምና መስጠትና ስነ ሥርዓቱን አለመከተል ነው። የዐይን ሀኪም ኩላሊት ህክምና ላይ ከተሰማራ ቸልተኝነት ሳይሆን ወንጀለኝነት ነው። በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 543 የሌላ ሰውን ሕይወት ጤንነት ወይም ደህንነት የመጠበቅ የሙያ ወይም ሌላ ግዴታ ያለበት የሕክምና ባለሙያ ወይም አሽከርካሪ በቸልተኝነት ሰው የገደለ ከሆነ ከአንድ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ከ3ሺ እስከ 5ሺ ብር ሊደርስ በሚችል ገንዘብ የሚቀጣ ሲሆን ፣ጥፋተኛው ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎችን የገደለ እንደሆነ ቅጣቱ ከአምስት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ10ሺ እስከ 15ሺ የሚደርስ መቀጮ ይሆናል።

ስህተቶች ሲፈፀሙ ከወንጀል ተጠያቂነት በተጨማሪ ፍትሐ ብሄር ህግ የአስተዳደር ተጠያቂነት የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ለተወሰነ ጊዜ ፈቃዱን ማገድ የመሳሰሉት መኖራቸውን አብራርተው፣ይህም የጤና ባለሙያው በሙያው ልኬት ውስጥ እንዲሠራ ያስችለዋል ይላሉ።የጤና አገልግሎት ገበያ ተኮር እና የፖለቲካ ተለጣፊም መሆን የለበትም ዋናው ጉዳይ ታካሚውን በቅንነት ለመርዳት መጣር እንደሆነ የህግ ባለሙያው ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር አዳሙ አዲስ በበኩላቸው የህክምና ስነ ምግባር መርሆዎች መሠረታዊ እና ዓለም አቀፍ መሆናቸውን ያስረዳሉ ። በየትኛውም ቦታ የጤና ባለሙያው የሚሰጠው አገልግሎት መርሆዎች በተከተለ መልክ ሊሄድ እንደሚገባው ጠቅሰው፣ከቦታ ቦታ ከሀገር ሀገር እንደ ተጨባጭ ሁኔታው ዐውዱን በጠበቀ መልክ እንዲሄድ ማድረግ ደግሞ ያስፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ። ምክንያቱም ለምሳሌ በባህል ላይ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለህክምና ያላቸው ግንዛቤ እና የሚጠብቁት ነገር በባህል ውስጥ ያሉ ዕሴቶች አንድ ዓይነት ላይሆኑ ይችላሉ ይላሉ።

‹‹ዓለምአቀፋዊ መርሆዎች እንደተጠበቁ ሆነው ግን ወደ አተገባበር ስንመጣ የት እንዳለን ማንን እንደምናገለግል ማወቅ አለብን። ተጨባጭ ሁኔታዎችን ዐይተን በተመጣጠነ መልኩ መተግበር ይገባል›› ሲሉም ይናገራሉ።

እንደ ዶክተር አዳሙ ገለጻ፤ የስነ ምግባር ትምህርት ያስፈልጋል ትምህርት ማለት የቀለም ወይም የሚፃፍ ትምህርት ብቻ ማንበብ ትምህርት አይደለም ። አስፈላጊ ቢሆንም ትምህርት የምንለው ከቤተሰብና ከአንደኛ ደረጃ ከቤትና ከወላጅ ጀምሮ ነው። ኮርስ ስለወሰደ አንድ ሰው ተማረ ሊባል አይችልም፡፡ እነዚህን አቅጣጫዎች ሁሉ ማየት ያስፈልጋል። ስነ ምግባርን ወደፊት ለማስኬድ የሁሉም ባለድርሻዎች ከቤተሰብ ጀምሮ ወላጆች የእምነት አባቶች የማኅበረሰብ መሪዎች ሀገር ሽማግሌዎች ምሁራን ተሰሚነትና ጥሩ ሚና ያላቸው ሰዎች አስተዋፅኦ ያስፈልገናል። ከፀሀፊያንና ተዋንያን ሁሉ ዕሴት ይመጣል ሁሉም መታየት አለበት ።

ህክምና የቡድን ሥራ ነው፡፡ የካርድ ክፍል ሠራተኞች፣ ሀኪሞች፣ ነርሶች፣ የሰመመን መርፌ ሰጪዎች ፣የቀዶ ህክምና ሀኪሞች፣ ፋርማሲስቶች ፣ወዘተ የቡድኑ አባላት ናቸው። ታካሚዎች ለህክምና ሲሄዱ የሚፈልጉት “ከፍትፍቱ ፊቱ” የሚለውን ማየት ነው፡፡ የሀኪሙ ገፅታ አቀባበል አነጋገር አዛኝነትና ርህራሄ አክባሪነት ማሳየት ታካሚውን ማበርታት ናቸው።

‹‹ሀኪሙ ለታካሚው ወሳኝ መረጃዎችን መስጠት፣ ለታካሚው የሚረዳውን መሥራት፣ችግሮችን መቀነስ፣ ጎጂ ነገር አለማድረግ፣ ሕመምተኞችን ማክበር፣ መንከባከብ፣ አለማዳላት፣ታማኝነት ማሳየት ይኖርበታል።›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡ሁለንተናዊ የህክምና አገልግሎት ለመሥጠት ህመምተኞች መከበር እንዳለባቸው የሚጠቁሙት ዶክተር አዳሙ፣ ታካሚዎችን ፊት መንሳት ማመናጨቅ ደንበኞች ላይ መጮህ የስነ ምግባር ጉድለት መሆኑን ይገልጻሉ።

በቀደመው ጊዜ ያው በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ የሚሰጥ ትምህርት ባይኖርም፣በህክምና ውስጥ የሚያልፉ ባለሙያዎች ጥሩ ሚና ባላቸው ሰዎች ይታዩ የነበሩ ሰዎችን ተግባራት ይተገብሩ ነበር የሚሉት ዶክተር አዳሙ፣በዛ መልክ የተማሩት ነገር አለ ብለው እንደሚያስቡም ይናገራሉ፡፡‹‹ኮርስ ስላልተሰጣቸው ብቻ አልተማሩም አያሰኝም።አሁንም ይሄንን ሰፋ አድርገን ዐይተን ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን በኑሮ ውስጥም ትምህርት ማግኘት ይቻላል።››ሲሉ ያብራራሉ፡፡

በቅርቡ በቢሾፍቱ በህክምና ስነ ምግባርና ስህተቶች ላይ ያተኮረ ስልጠና ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡የሥልጠናው ዓላማ የኢትዮጵያ ጤና ሕክምና ማኅበር በሕክምና ስነ ምግባር ላይ በአዲስ መልክ ሠፋ ባለ መልኩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡‹‹ስለዚህ ሀኪም ብቻውን የሚሠራው ነገር አይደለም። የህክምና ባለሙያዎች ብቻቸውን የሚሠሩት ሳይሆን በጋራ በቡድን የሚሠራ ነው።››ሲሉ ያብራራሉ::

የመገናኛ ብዙሃን ለኀብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ‹‹በመካከላችን ክፍተት አለ አንዳንዴ ሚዲያውም ህክምናን በተሳሳተ አተያይ ያየዋል፤ ህክምናውም ሚዲያውን በተመሳሳይ መልኩ ይመለከተዋል። ስለዚህ የሚታየውን ክፍተት አጥብበን አብረን መሥራት ይገባናል።››ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡

ዶክተር አዳሙ ዘገባዎች የሚወጡት ሚዛናዊነትን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፣ስልጠናው አብሮ ለመስራት እንዲያስችል መዘጋጀቱን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ወደፊት በህክምና ጋዜጠኝነት ዙሪያ መሪ ጎዳና በኢትዮጵያ እናወጣለን ብለን እናስባለን። ሥልጠና ስናመቻች ጋዜጠኞችን ለማስተማር ብቻ ሳይሆን ከጋዜጦችም ለመማር ጥሩ ግንዛቤ ላይ እንድንደርስ ነው።›› ሲሉ ጠቅሰው፣ይህም ወደፊት የምንሠራቸውን ሥራዎች ተጋግዘን ለመሥራት መነሻ ይሆነናል ብለዋል፡፡ ስልጠናው የህክምና ስነ ምግባርና ለማዳበርና ስህተቶችን ለመቀነስ የህክምና ስህተቶች ሲፈፀሙ የሚሰራው ዘገባ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እንዲሆን ይረዳል ይላሉ።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 7/2011

ኃይለማርያም ወንድሙ