ቡናውን ከህገወጥ ግብይት መታደግ ሀገርን መታደግ ነው!

28

ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝባቸውን ምርቶችና ፣ምርቶቹ የሚላኩባቸውን መዳረሻዎች ለማስፋት፣የምርት ጥራትና የመሳሰሉትን በማሻሻል ከምርቶቹ ተገቢውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እየሰራች ትገኛለች፡፡ ሀገሪቱ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጪ መላክ ብትጀምርም ፣አሁንም የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ቡና አጋዥ አገኘ እንጂ የመሪነቱን ስፍራ ያስለቀቀው ግን የለም፡፡ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው አሁንም ቡና ነውና፡፡

ይሁንና ይህን ያህል ፋይዳ ያለው ቡና በአለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው እየወደቀ ከመምጣቱ በተጨማሪ በህገወጥ ግብይት ሳቢያ አደጋ ውስጥ ገብቷል፡፡ ለእዚህም የ2011 በጀት አመት አፈጻጸምን ብቻ መመልከት ይበቃል፡፡ የቡናና ሻይ ባለስልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው በበጀት አመቱ 318 ሺ ቶን ቡና ፣ሻይና ቅመማቅመም ወደ ውጪ በመላክ አንድ ቢሊየን 114 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ቢታቀድም፣መላክ የተቻለው ግን 230 ሺ 764 ቶን ቡና ሲሆን ከዚህም የተገኘው 774 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ፡፡

ለውጭ ምንዛሬ ግኝቱ መቀነስ በምክንያትነት ከተጠቀሱት መካከል አንዱ በአለም ገበያ ከሀገሮች የቀረበው የቡና መጠን ከፍተኛ መሆን አንዱ ሲሆን፣ በዋጋ በኩል ደግሞ የበጀት አመቱ የቡና ዋጋ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ20 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ነው፡፡ እነዚህ አለም አቀፍ ችግሮች ናቸው፡፡

የቡናው ዘርፍ ከእዚህም በተጨማሪ በሀገር ውስጥ በህገወጦች መወረሩም ሌላው ምክንያት ነው:: ቡናው ወደ ውጪ ሲላክ በጉዞ ላይ እያለ ቅሸባ ይፈጸምበታል፡፡ ገዥዎች ዘንድ ሲደርስ ጉድለት እያስከተለ ነው፤ይህም ገዥዎች በኢትዮጵያ ላይ እምነት እንዲያጡ እየተደረገ ነው፡፡

የተለያዩ አካባቢዎችን ቡና ቀላቅሎ ለገበያ ማቅረብም ሌላው የቡናው ዘርፍ ፈተና ሆኗል፡፡ የት ላይ እንደሆነ በትክክል ማወቅ ባይቻልም ቡና እንደሚቀላቀል ግን ባለድርሻ አካላትም ያረጋግጣሉ፡፡በዚህ የተነሳ ገዥዎች የኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎችን ቡና ለመለየት እየተቸገሩ መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡

ሌላው ደግሞ ዋጋ ዝቅ አርገው በመሸጥ የውጭ ምንዛሬውን ሸቀጦችን በመግዛት እና ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የሀገርን ሀብት አለአግባብ በሚጠቀሙ ህገወጥ ነጋዴዎች ተወሯል፡፡ ቡናው ለእቃ በእቃ ንግድ እየዋለ ነው ሲሉ ባለድርሻ አካላት ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡

መንግስት የቡናውን ዘርፍ ችግሮች ለመፍታት እንደሚሰራ በቅርቡ አረጋግጧል፡፡በቡና ምርት ላይ የሚስተዋለውን የኮንትሮባንድ ንግድ እና የተደራጀ ዘረፋ ለመከላከል የሚያስችል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ግብረ ሀይልም አቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ ግብረ ሀይሉ ከግብርና ሚኒስቴር ከጉምሩክ ፣ከፌዴራል ፓሊስና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ነው፡፡ የግብረ ሀይሉ መቋቋም  ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል አንድ እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳልና ይበል የሚሰኝ ነው፡፡

የቡናውን ዘርፍ ከእነዚህ ቀበኞች መታደግ ማለት ብዙ ትርጉም አለው፡፡ ሀገሪቱ ለልማቷ የሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሬ ስታስብ እሰራባቸዋለሁ ብላ ከያዘቻቸው ተግባሮች አንዱ የወጪ ንግዱ እንደመሆኑ ቡናው ደግሞ የወጪ ንግዱ ቁልፍ ነው፡፡ ይህ ዘርፍ ተጎዳ ማለት በአጠቃላይ ልማቱ ላይም ሆነ በአገር አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ በመሆኑም የመንግስት እርምጃ ከብዙ ጉዳት በኋላ የተወሰደ ቢሆንም መጪው ጊዜም አለና በአበረታችነቱ ሊጠቀስ ይገባል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ከኢትዮጵያ ህዝብ ከ25 ሚሊየን በላይ የሚሆነው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ህይወቱ ከቡና ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የቡናውን ግብይት መታደግ ማለት ይህን ህዝብ መታደግ ማለት ነው፡፡ ቡና የኑሮው መሰረት የሆነውን አርሶ አደር፣ነጋዴ፣ወዘተ ህይወት መጠበቅ ይሆናል፡፡

አርሶ አደሩ ከቡናው ተገቢውን ጥቅም ካላገኘ ቡናውን በሌላ ሰብል መተካት ውስጥ ሊገባ ይችላል፡ ፡ ይሄ ደግሞ ከቡና ሌላውን ልማት ለማሳለጥ የሚረዳ የውጪ ምንዛሬ ለምትጠበቅ ሀገር ትልቅ ጉዳት ይሆናል፡፡

ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው ምርቶች ቡና 60 በመቶውን እንደሚሸፍን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ቡናዋ ለሚታወቀው ሀገር ጥቅምን አሳልፎ መስጠት በመሆኑም ቡናውን ከህገወጦች ለመታደግ የተጀመረው ጥረት በትኩረት ሊሰራበት ይገባል፡፡

ሀገሪቱ የቡና የወጪ ንግዱ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት የጀመረችው ይህ ጥረት በርካታ ስራዎች ተሰርተው ያፈራቻቸውን ደንበኞች ለመጠበቅ የሚያስችል ስራ የሚሰራበት ሊሆንም ይገባል፡፡ ጥራት ያለውና ተገቢውን ቡና በማቅረብ ደንበኞች ያጡትን አመኔታ ማስመለስ ያስፈልጋል፡፡

በቡናው ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ላኪዎች በሚገባ መፈተሽ ይኖርባቸዋል፡፡ ለሀገር የሚፈይድ ስራ እስካልሰሩና የግል ጥቅማቸውን ብቻ የሚያሳድዱ ከሆኑ በህግ አግባብ እንዲጠየቁ ማድረግ ፣ከስራውም እስከ ማገድ የሚደርስ እርምጃም መወሰድ ይኖርበታል፡፡በቅርቡ በህገወጥ የቡና ነጋዴዎች ላይ የተወሰደው እርምጃም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

ግብረ ሀይሉም ስራው ሰፊ፣ግዙፍና ውስብስብ መሆኑን አውቆ ለውጥ ለማምጣት መረባረብ ይኖርበታል፡፡ በዚህ አካሄድ የህገወጦቹ ሰንሰለት ረጅም ሊሆንም ይችላል፡፡ አሁን የተጀመረው ቁጥጥር የዘገየ ቢሆንም፣ ቀጣዩን የልማት ዘመን በማሰብ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል፡፡

‹‹ሳቁ ላይቀር ላችሁ ምንድን ነው›› እንደሚባለው ከቡና ጥቅም ፈልጎ ህገወጥነትን አለመከላከል ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ቡናውን መታደግ ሀገርን መታደግ ነው፤ ቡናውን ለሀገር ጥቅም ለማዋል ሲባል የሚከፈለው መስዋዕትነት ሁሉ ሊከፍልም ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ነሀሴ 7/2011