የሌባ ወሬ – ቀላሉን ያድርግልን !!

16

አዲስ አበባን የሚያሳስባት እንደ ጉድ ይቀፈቀፋል። የንጹህ መጠጥ ውሃው ችግር፣ የትራንስፖርት፣ የኑሮ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የኤሌክትሪክ ሃይል፣ወዘተ ችግሮች ወይ አብረው አልያም የተወሰኑት በጋራ እየሆኑ ይፈትኗታል። ወትሮም ቢሆን ከኪስ ማውለቅ፣ ከቅሚያ፣ከማጅራት መምታትና ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ ስሟ የሚነሳው ከተማዋ፣ቅሚያ እና ዘረፋ በምሽት ብቻ ሳይሆን በጠራራ ጸሀይ የሚፈጽምባት ሆናለች።

በከተማዋ እየተፈጸመ ስላለው ሌብነት አሳሰቢነት ለመናገር ጥናት ማካሄድ እንዲሁም ፖሊስ የሚይዘውን የስርቆት መዝገብ ሄዶ አገላብጡልኝ ማለትም አያስፈልግም። ለዚያውስ መረጃው ሲኖር አይደል።

በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ሽኩቻ መጦፉን ተከትሎ የፖለቲካ ወሬ ብዙውን ድርሻ ቢይዝም የስርቆት ጉዳይ የቡናው፣ የትራንስፖርቱ፣ የስራው፣ ወዘተ ላይ ወሬ ሆኗል። ከቅሚያ ፣ከዝርፊያ፣ኪስ ከማውለቅ፣ በአጠቃላይ ከሌብነት ጋር የተያያዘው ወሬ ቀላል የማይባል ጊዜ እየወሰደ ነው። ጎበዝ ስለአንድ ነገር ሲወራ ያ ነገር አቅራቢያ ላይ ደርሷል ይባልና ወሬው እንዲቆም ሲደረግ አስታውሳለሁ። ስለሌባ ሳወራ አጠገቤ ደርሶ እንዳይሆን ብዬ ነው።

ሌብነት እንደ ቀላል ጉዳይ እየታየ ነው። እንኳን ተረፋችሁ ይባላል እንጂ ይህን ያህል ስትሰረቅ ሞተህ ነበር እንዴ የሚለው ዛሬ አይሰራም። ቁመናውን አይተን ሌባ አይደለም ታንክ አይደፍረውም ያልነው ሰው ተሰርቆ ልናገኘው እንችላለን። ይህን የሚያህል ሰው እንዴት ተሰረቀ ብለን የምንጠይቅበት ዘመን ላይ አይደለንም። የማይሰረቅ የለም።

ምልልሱ ላይ ልዩነት ሊኖር ይችላል። አንድ ጓደኛችን ሞባይል ይሰረቅና ይገዛል፤ አሁንም ይሰረቃል፤ እንደገናም ገዝቶ ይሰረቃል። አሁንስ እኛውና መጡ ሳይሉኝ አይቀሩም ያለው ትዝ አለኝ። ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ እንዳውም በራቸው ላይ ቅሚያ ሲፈጸም የሚስተዋልበት ጊዜም አለ። ፖሊሶቹም ጭ ምር እ የተሰረቁ ነ ው ይ ባላል።

ወገኖቼ በኡኡታ፤በማመልከቻ በአቤቱታ አልሆነምና እንዳው በጨዋታ በጨዋታ መልእክት ቢተላለፍ ብዬ ነው ይህን መጻፍ ውስጥ የገባሁት።

ለጥንቃቄ እንዲረዳ በቅርቡ ከሰማኋዋቸው አንዳንዶቹን ልጠቅስላችሁ። አንድ እናት ውጭ ሀገር ልጅ አለቻቸው። ከልጃቸው ገንዘብ እና እቃ ሁሌም ይላክላቸዋል። መልእክቱ የሚደርሳቸው ልጃቸው ከምትገኝበት ሀገር በመጡ ሰዎች እና በባንኮች እንዲሁም ሀገር ውስጥ ባሉ ሰዎች አማካኝነት ነው።

አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ። ይህ የሆነው ደግሞ ሴትዮዋን በሚገባ ባጠናች ሴት ነው። አንድ ቀን የሆነች ሴትዮ ትደውልላቸውና ልጃቸው ካለችበት ሀገር በቅርቡ መምጣቷን ትገልጽላቸዋለች።

ልጃቸው በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት እንደምትመጣ፣ ቤቱ ተለዋውጦ ማየት እንደምትፈልግ ይህንንም ከእሳቸው ጋር ተነጋግራ ሶፋ ፣ፍሪጅ እንዲገዛ ማዘዟን ትነግራቸዋለች። እቤት ለመምጣት እንደምትፈልግ ትነግራቸውና ቀጠሮም ይይዛሉ።

በቀጠሮው መሰረትም ቤታቸው ትመጣለች። ምኗም ምኗም የማይጠረጠር በ40ዎቹ እድሜ ውስጥ የምትገኝ ናት። እናት የልጃቸውን ደህንነት ይጠይቁና ማስተናገዳቸውን ይቀጥላሉ።

የእሳቸውን ሹሮ ሁሌም ልጃቸው ቤት እንደምትበላ እና በጣምም እንደምታውቀው ትናግራቸዋለች። እሳቸውም ውይ ልጄን ደሞ ለሹሮ ብለው ወዲያው አሰርተው ያቀርባሉ፤ ቡናም ይፈላል። ለግዥውም 40 ሺ ብር እንደሚያስፈልግ ነግራቸው ባንክ ይሄዳሉ ያወጣሉ። ብሩን ትይዝና ኮንትራት ታክሲ ላምጣ ፤እርስዎ ታክሲ ድረስ መሄድ የለቦትም ብላቸው ከአጠገባቸው ትሄዳለች።

እሳቸውም መጠበቃቸውን ይቀጥላሉ። የበላት ጅብም አልጮህ ይላል። የሆነውን በአቅራቢያቸው ለሚገኙ ሰዎች ይናገራሉ። መጭበርበራቸው ይነገራቸዋል። 40 ሺ ብር እንደ ቅቤ ቀለጠ። ነጻነት የኢቢኤሱ እንዴት እንዴት ነው የሚለው፤ አ….ር…ባ ሺ ብ … ር ! ቀለጠ ። ሌብነት እዚህ ደርሷል!!

አንዱ ደግሞ አውቶብስ ተራ አካባቢ አይቶት የማያውቀው ሰው ከመሬት ተነስቶ በእርግጫ እንደመታው በጨዋታ በጨዋታ ነገረን። እንዴት ቢደፍረኝ ነ ው? የ ት አ ባቱ ያ ውቀኛል! ይ ልናም መቺውን አንቆ ይይዛል። ትንቅንቅ ይሆናል። በዚህ መሀል ገላጋይ ነን ያሉ መሀል ይገባሉ። ይገላግሉና በየአቅጣጫው ይሄዳሉ። ተመቺ ቆይቶ ኪሱን ሲዳብስ ሞባይሉ የለም። ማንን ይያዝ። ሰውረን ነው ማለት !!

የሌባ ወሬ ብዙ ያሰማል። አንዳንዶች ደግሞ በአገር አማን በቡጢ ተመትተዋል። ከዚያ በኋዋላ የሆነውን እንደማያውቁት ፤ቆይተው ተረጋግተው ኪሳቸውን ሲዳብሱ ከሞባይል ነጻ ሆነው ራሳቸውን ማግኘታቸው ነው የሚወራው።

በሞተር ይደረግ የነበረው ዘረፋ የከተማ አስተዳደሩ በወሰደው እርምጃ ጋብ ብሏል፤ ተመስገን ነው። ባጃጅ ደግሞ ዋናው የዘረፋ መሳሪያ ሆናለች ይባላል። በተለይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከጀሞ ለቡ ላፍቶ ባለው መንገድ በባጃጅ የሚደረገው ዘረፋ ብዙዎችን እርቃን እያስቀረ ነው። ሞባይላቸውን የሚሰረቁ ጥቂት አይደሉም፤ ከባንክ ወጥተው ባጃጅ የያዙ ጥቂት የማይባሉት ተቀምተዋል፤መዝረፍ የሚፈልጉትን ሰው ከኋላ ወንበር ላይ መሃል ነው አሉ የሚያስቀምጡት። ነቅቶ እንኳ ልውረድ ብሎ እንዳይወራጭ ነው አሉ መሃል ማስቀመጣቸው።

ከዚያ ጉዞ ይጀመርና ተሳፋሪው በፈለገው አቅጣጫ ሳይሆን አሽከርካሪው በፈለገው አቅጣጨ ጉዞ ይጀመራል። የፈለጉት ቦታ ወስደው የፈለጉትን ሁሉ ከወሰዱ በኋላ ውረድና ቀጥ ብለህ ሂድ ፤እጮሃለሁ ወይም ሌላ ነገር አደርጋለሁ ብትል በራስህ ትፈርዳለህ ይባላል።ታሪኩ ያበቃል።

ከኪስ ሞባይል ወይም ገንዘብ መስረቅም በስፋት የሚፈጸም ሲሆን፣ይህን አይነቱ ሌብነት ታክሲ ተራ እንደ መገናኛ አውቶብስ ተራና በመሳሰሉት አካባቢዎች አሁንም በስፋት ይፈጸማል። የትራንስፖርት ግፊያ ለእዚህ ምቹ መንገድ ነው።

በጉዞ ላይ እያሉ ኪስዎን የሚያወልቁም በርካታ ናቸው። እንደ መገናኛ ባሉ አካባቢዎች በትርምስ ውስጥ ኪስ፣ ቦርሳ ፣ወዘተ ይበረበራል። ይህ በእንዲህ እያለ ነው ታዲያ አዳዲስ የስርቆት አይነቶች ከተማዋን እየበረበሯት የሚገኙት።

ይህ ሁሉ ሲሆን ፖሊስ አያውቅም አይባልም። ቢያውቅም መፍትሔ ሊሆን አልቻለም፤ሌባ ሞባይል ሲሰርቅ ሊያዝ ይችላል። ሰው ሞባይሉ ከተገኘ ከሌባ ጋር ምን አጓተተኝ ፤ወዲያው ለሚለቁት ምን አለፋኝ እያለ ወደ ክስ አይሄድም።

ለነገሩ ልክሰስ ቢልስ ምስክር ከየት ይገኛል። ምስክርነት ከሚያስከትለው እንግልት በተጨማሪ ሌብነቱ በተደራጀ አግባብ የሚካሄድ እንደመሆኑ ሌባ ቀለበት ውስጥ መግባት ሊከተል ይችላል። ያየውም ቢሆን ነግ በኔን ትቶ መጭ ነው የሚለው።

ማን ይከሰስ! በፍርድ ቤት አሰራር የተማረሩ ጠላቴም አይከሰስ ሲሉ ነው የሚሰማው። አንዳንዶች ደግሞ ከመክሰስ መከሰስ ይቀላል ይላሉ። ይህ ሁሉ ታዲያ ሰው እቃው ከተገኘ ሌባ መክሰስ ውስጥ እንዳይገባ እያረገው ነው። እቃው ባይገኝም አብዛኛው ሰው መክሰስ አይፈልግም፤ ምክንያቱ ደግሞ ፖሊስ ጣቢያ ምልልሱ አድካሚ መሆኑ ነው።

ጎበዝ ተቀምተው ተሰርቀው ቢወራጩ ቢጮኹ ስርቆቱ በቡድን የሚፈጸም ነውና ከየት መጡ ብለው ባላሰቧቸው ሰዎች ተወረርው ሌባ ተብለው እንደ እባብ ሊቀጠቀጡ ይችላሉ። ጓደኛችን ነው አሞት ነው ፤ ልንወስደው ነው የሚሉም አሉ አሉ።

ፖሊስም ለጊዜው ይይዝና ከሳሽ ከሌለ ብሎ ይለቃል። ለማስረጃ እንኳ መመዝገቡን የተተውም ይመስለኛል። አንድ ጓደኛዬ በአይኔ በብረቱ አየሁ ያለውን አጫወተኝ። አንድ ጠብደል ሞባይል ሲሰርቅ ይያዛል። ባለሞባይሉ ሞባይሉን ተቀብሎ ይሄዳል። ፖሊስ ሌባውን ለጊዜው ይይዘዋል፤ይህን የመሰለ ቁመናና ሰውነት ይዘህ እንዴት ትሰርቃለህ፤ሁለተኛ ግን እንዳይለምድህ ብሎ ቢያሰናብተው ምን ይላሉ። ለማስረጃ እንዲሆን ፎቶውን ታሪኩን መታወቂያውን ወዘተ መያዝ እንኳ እንዴት እንዳላስፈለገ እንጃ። ታዲያ ለምን ሌባ አይፈለፈል! ጎበዝ ፖሊሶቻችን ካላስጣሉን ከተማ ለከተማ ቢንጎማለሉ ምን ይጠቅሙናል።

የፖሊስ ነገር ሲነሳ አንድ ነገር በእጅጉ ይቆጨኛል። ለነገሩ ብቻዬን ምን ማድረግ እችላለሁ። የምኖርበት የኮንደሚኒየም መንደር አንድ ወቅት ላይ በሌባ ክፉኛ ይቸገራል። ሌቦች ለሞባይል ሲሉ ሰው ያበላሻሉ። በጩቤ መውጋት ፣ማጅራት መምታት (ሀንግ ማድረግ)፣ ወዘተ ተለምዷል። የተሰጣ ማንሳት በተለይ ጂንስ በወረንጦ ይለቀም ነበር። መኪና አስነስቶ ወስዶ ጎማ እና የተለያዩ የመኪና እቃዎች መውሰድ ተለምዷል። የቆየም ነው።

ነዋሪው ተቸገርን እያለ ነጋ ጠባ ፖሊስ ጣቢያ እየሄደ ያመለክታል፤ በአቅራቢያው ላገኛቸው ፖሊሶችም ይጠቁማል። ጉዳዩ የኮንደሚኒየሙ ማህበር የሁልጊዜ አጀንዳም ይሆናል ፤ዛሬ ደግሞ ብሷል፤

ችግሩ በጣም አሳሳቢ እየሆነ መጣናም ጉዳዩ ወረዳና ክፍለ ከተማ ይደርሳል። በአንድ ወቅት የክፍለ ከተማው እና የወረዳው አስተዳደር ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት አንድ መድረክ ያዘጋጃል። በዚያ መድረክም የፖሊስ አካላት ፖሊስ የመመደብ ችግር የለብንም፤ተረኛ ፖሊሶች በስራ ላይ ቆይተው ትንሽ አረፍ የሚሉበት ፣ነዋሪዎችም ፖሊሶችን ሲፈልጉ የሚያገኙበት ቤት ግን ይዘጋጅልን፤ በተረፈ ሁሉንም ነገር ለኛ ተውት አሉ።

ከዚያም የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ቤት ከ500 ሺ ብር በላይ ወጪ ተደርጎ ተገነባ። ህብረተሰቡ ፖሊስ አለ ብሎ ሲሄድ የተረፈው ድካም ሆነ። ‹‹ወፍ የለም›› ነው ያለው የአራዳ ልጅ ! ፖሊስ የለ፤ቤቱም ኦና ሆኗል፤እንዴት አዲስ ቤት ኦና ይሆናል! ስርቆቱም ባሰበት፤ቅሚያው ለፖሊሱ የሰራነው ቤት በራፍ ላይ ጭምር ቀጥሏል። ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ ነው የተባለው።

ባላገር ትዝ አለኝ ።ድንች፣በቆሎ ፣ ወዘተ አውሬ እየበላ ሲያስቸግረው ሰው የሚመስል ነገር እየሰራ ማሳ ውስጥ የሚያቆመው። የማህበረሰብ ፖሊስ ጣቢያው እንዲያ ሆኗል። ለማስፈራሪያ የቆመ እንጂ ህዝብን የሚያዳምጥ አልሆነም።

በከተማዋ መሰረቅ፣መዘረፍ አሁን አሁን ብዙም የሚያሳስብ መሆኑ እየቀረ ነው። የሚያሳስበው ዝርፊያው፣ ስርቆቱ የተፈጸመበት መንገድ ሆኗል። ሳይደበደቡ፣ ሳይወጉ፣ አካል ሳያጎድሉ መሰረቅ ብዙም ከክፉ ወደ አለመቆጠር ሄዷል። የተሰረቀው ሰው አንድ ድምጽ ቢያሰማ ሊደርስበት ስለሚችለው ችግር አስቀድሞ ስለሚነገረውም እኔ ደህና ብሎ መንገዱን ይቀጥላል።

መመታት.፣ በስለት መወጋት፣ መገደል ወዘተም አለና በሚል የተሰረቀ የተቀማ ሁሉ ብዙም ሳያማርር እቃ ይተካል፤ ነፍስ ግን መተኪያ የለውም እያለ የሆነውን ሁሉ እያቀለለ ተቀምጧል።

ህብረተሰቡም የፖሊስ ምላሽ ባያገኝም ፣ስለጉዳዩ ፖሊስ አያውቅም ብሎ አያውቅም። በእርግጥም ፖሊስ የማያውቀው ነገር የለም። ለእዚህም ነው አንዴ ዘመቻ ሲወጣ አገር ሌባ ሰብስቦ የሚመለሰው። ይህ ግን ሲሆን የሚስተዋለው ህዝቡ በጠየቀ ጊዜ ሳይሆን መንግስት ወይም ፖሊስ በፈለገ ጊዜ ይመስለኛል። የፖሊስ ህዝባዊነት ታዲያ ምኑ ላይ ነው ጎበዝ!

ኢትዮ ቴሌኮም ከሞባይል ስርቆት ጭምር እታደጋችኋለሁ ብሎ አንድ ሰሞን ሞባይሉን ሁሉ መዘገበ። ሞባይል የተሰረቁ ሲሄዱ የረባም መልስ ሳያገኙ ተመለሱ። አንድ ጓደኛችን ሞባይል ተሰርቆ አቅራቢያው የሚገኝ ኢትዮቴሌኮም ሄዶ ያመለክታል፤እኛም ሲመለስ እንዴት ሆንክ ብለን መጠየቅ። አንዱ ሰራተኛ ‹‹ፍሬንድ ብትሸበልል ይሻልሃል›› ብሎ በስልት እንዳሰናበተው የነገረን ትዝ አለኝ። ያ ህግ አንድም ቀን የተሰረቀ ሞባይል ሳያስገኝ በለውጡ ተሻረ መሰለኝ።

ለነገሩ ከፖሊስ በላይ የሚያስጥል ከየት ይመጣል። ችግሩ ሄዶ ሄዶ ፖሊሱንም ሊበላ ስለሚችል ለህልውናው ብሎ መፍትሄ ካላመጣ በስተቀር ሌብነቱ አይን ያወጣ መሆኑን ቀጥሏል። ፖሊስ ሆይ ህዝቡን ከእነዚህ ቀማኞች ካላስጣልክ አንተም ከመበላት አትድንም። የምንሰማውም ይህንኑ ነው፤ ተጀማምረሃል፤ቢያንስ ራስህን አንድን! ለእኛ ደግሞ እግዚር ያውቅልናል!!!

አዲስ ዘመን ነሀሴ 7/2011

 ዘካርያስ