አጼው የመጀመሪያውን የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎውን በድል አወራረደ

5

በ2011ዱ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ጨዋታ ሐዋሳ ከተማን በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መድረክን የተቀላቀለው ፋሲል ከነማ ውድድሩን በድል ጀመረ።

በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ በሜዳው በባህር ዳር አለም አቀፍ ስታዲየም መቶ ሺ በሚገመት ደጋፊው ፊት የታንዛኒያውን አዛም እግር ካስ ክለብ ያስተናገደው ፋሲል፣ ጨዋታውን አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ነው ማሸነፍ የቻለው።

በህብረ ቀለማት በደመቁ ደጋፊዎች፤ ከአራቱም ማዕዘን ጎልተው በሚሰሙ የድጋፍ ድምጾችና ማራኪ ጭፈራዎች በሚያስደንቅ መልኩ ታጅቦ በተካሄደው ጨዋታ የፋሲል ከነማን ብቸኛ የማሸነፊያ ግብ በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ማጠናቀቂያ ላይ ያስቆጠረው በዛብህ መለዮ ነው።

በዛብህ አጼዎቹን ከመቀላቀሉ ከአመት በፊት በወላይታ ዲቻ ቆይታው በተመሳሳይ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መድረክ ላይ ክለቡ በሃዋሳ አለም አቀፍ ስታዲም የግብፁን ዛማሊክ 2ለ1 ሲያሸንፍ ግብ ማስቆጠሩ አይዘነጋም።

ውጤቱን ተከትሎም ፋሲል ከነማ በሜዳው 3 ነጥብ በመያዝ በቀጣይ ከ 12 ዓመታት በፊት የተመሰረተው እና በ2018/19 የውድድር ዓመት 3ኛ ደረጃ ይዞ ካጠናቀቀው ከአዛም የእግር ኳስ ክለብ ጋር የመልስ ጨዋታ የሚደርግ ይሆናል። የሁለቱ ከለቦች የመልስ ጨዋታም ከ15 ቀናት በኋላ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ከተማ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

አጼው የመጀመሪያ የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎውን በድል የጀመረበት ጨዋታም ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር የተለያየበት ሆኗል። የመጨረሻ ጨዋታቸውን በድል በመወጣት ከክለቡ ጋር የተለያዩት አስልጣኝ ውበቱ፣ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት፣ በውጤቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል። ፍላጎታቸው ባይሆንን በግል ጉዳይ ከክለቡ ጋር በይፋ መለያየታቸውን ጠቅሰው፣በቀጣይ ከለቡን የሚረከብ አሰልጣኝ የክለቡን ውጤት እንዲያስቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በጨዋታው የኢትዮጵያ እግር ካስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጂራ፣የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጥኝ ኢንስተራክተር አብረሃም መብራቱ፣ የባህር ዳርና ጎንደር ከተማ ከንቲባዎችን ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ታድመውበታል። ከተማዋና ታላቁ ስታዲየም ዳግም የሐገር ኩራት መሆናቸውን አስመስክረውበታል።

ይሁንና በመስተንግዶ ረገድ በዕለቱ በነበረው ያልተቀናጀ የቲኬት አቆራረጥ ችግር ከገባው ደጋፊ አንፃር የተገኘው ገቢ አነስተኛ መሆኑ እንደሚያስቆጭም ተጠቁሟል።

በተመሳሳይ በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ያቀናው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑ መቐለ 70 እንደርታ በካኖ ስፖርት 2 ለ 1 በሆነ ጠባብ ውጤት ተሸንፏል። በአፍሪካ የውድድር መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉት መቐለ 70 እንደርታዎች እስከ 80ኛው ደቂቃ 2 ለ 0 ተመርተው ከቆዩ በኋላ አማኑኤል ገብረሚካኤል ወሳኟን 1 ግብ በጨዋታው ማጠናቀቂያ ላይ አስቆጥሯል።

መቐለ 70 እንደርታዎች ከሜዳቸው ውጪ አንድ ግብ ማስቆራቸው ወደ ቀጣይ ዙር የማለፉ እድላቸው ከፍ ያደርገዋል። በዚህ መሰረት መቐለ 70 እንደርታዎች ከ15 ቀናት በኋላ በሜዳቸው የሚያደርጉትን ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርባቸው 1 ለ 0 ማሸነፍ ከቻሉ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ይችላሉ።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 7/2011

 ታምራት ተስፋዬ