ካልተጠበቀው የአርሰናሎች እጅ መፈታት ጀርባ

9

ላለፉት ሁለት ወራት በእንግሊዝ ክፍት ሆኖ የቆየው የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት መቋጫቸውን አግኝቶ ከመዘጋቱ በፊት የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ለ2019/20 የውድድር አመት ተጠናክረው ለመምጣትና የሊጉን ዋንጫ ማንሳት እንዲቻላቸው ውጤታማ ያደርጉናል ብለው የሚያስቧቸውን ምርጥ ተጫዋቾች የግላቸው ለማድረግ ሲለፉ ሰንበተዋል።

ከወትሮው በተለየ ዘንድሮ በደራው የተጫዋቾች ዝውውር ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ፓውንድ በላይ ወጪ ሆኗል። ከዚህ ገንዘብ መካከልም በተለይ የሊጉ ዋነኛ ተፎካካሪዎቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰስ አድርገዋል። በአርሰን ቬንገር የአሰልጣኝነት ዘመን ተጫዋች ለማስፈረም የሚሰስተው አርሰናልም ዘንድሮ ባልተጠበቀና በርካቶችን ባስገረመ መልኩ እጁ ተፈትቷል።

የታክቲክ ቀማሪው የሰሜን ለንደኑ ክለብ አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሪም በዝውውር መስኮት ሞቅ ደመቅ ያለና ሚዛን የሚደፋ የዝውውር ተሳትፎ አድርገዋል። የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት የአርሰናል የክረምቱ በጀት 45 ሚሊየን ፓውንድ እንደሆነ ሁሉም ሚዲያዎች ያስታወቁ ሲሆን፣ይህም በርካቶችን ተስፋ ቢያስቆርጥም በኋላ የሆነው ግን መድፈኞቹን ያስደሰተ ሆኗል።

በዝውውር መስኮቱ ብራዚላዊው ወጣት ጋብሪኤል_መርቲኔሊ፣ዊሊያም_ሳሊባ፣ የማድሪድ ኮከብ ዳኒ_ሴባዮስ በውሰት፣ የሴልቲኩን የግራ ተከላካይ ኬይራን ቴርኔይን በ25 ሚሊየን ፓውንድ እንዲሁም የ32 ዓመቱን ብራዚላዊ የመሀል ተከላካይ ዴቪድ ሊውዝን ከቼልሲ በ8 ሚሊየን ፖውንድ አስፈርመዋል።

አርሰናሎችን ከሁሉም በላይ ያስደንቃቸው ግን ኮትዲቫራዊውን የሊል ኮከብ ኒኮላስ ፔፔን ወደ ኤመሬትስ ማምጣት መቻላቸው ነው።ለፔፔ የተፈታው እጃቸው ወጪ ያደረገው 72 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብም ተጫዋቹን በእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ ታሪክ አራተኛው ውዱ ተጫዋች አድርጎታል። ተጫዋቹ ከአፍሪካ ተጫዋች መካከልም በከፍተኛ ወጪ በመዘዋወር ክብረ ወሰኑን እንዲረከብ አስቻሎታል።

በእርግጥም በዘንድሮው የተጫዋቾች የዝውውር ገበያ ኡናይ ኤምሪ የሚፈልጉትን ያገኙ ይመስላሉ። መድፈኞቹ አስፈሪ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ይዘዋል። የመሃል ሜዳ ክፍሉም በድንቅ ብቃት በተካኑ ተጫዋቾች የተዋቀረ ነው። ምንም እንኳን ማንችስተር ሲቲ እና ሊቨርፑልን ከመሳሰሉ ክለቦች ጋር ሲነፃጸር ምርጥ ነው ባይባልም ከአምናው በተሻለ የተከላካይ ሥፍራ ተጫዋቾችንም አዋቅረዋል።

የዘንድሮው የውድድር አመት ለአርሰናሎች እጅግ አስደሳች እንዲሆን፣ ድንቅ ወጣት ተጫዋቾችን በማስፈረምና ሪከርድ መስበር እና ለእዚህም ከአርሰናሎች እጅ መፈታት ጀርባ ደግሞ አንድ ሰው አለ፤ የክለቡ የእግር ኳስ ጉዳዮች ሃላፊ ራውል ሳንለሂ።

ራውል ሳንለሂ፡ ከእግር ካስ ስራ ጋር የተዋወቀው እአአ በ2003 ነው። የገበያ ማኔጅመንት ስራውን አሃዱ ያለው ደግሞ በስፔኑ ሃያል ክለብ ባርሴሎና ሲሆን ፣ከአምስት አመታት በኋላም የኑካም የእግር ኳስ ዳይሬክተር ለመሆን ችሏል።

ሳንለሂ በባርሴሎና ቤት የ10 አመታት ቆይታውም እአአ በ2013 ኔይማር ጁኒየርን ከብራዚሉ ሳንቶስ፣ ሉዊስ ሱዋሬዝን ከሊቨርፑል፣ ሴስክ ፋብሪጋዝን ከአርሰናል እንዲሁም በርካታ ታላላቅ ተጫዋቾችን ለካታላኑ ክለብ አበርክቷል። እነዚህን ተጫዋቾች የሰበሰበው የካታላኑ ክለብ ሶስት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ መሆን ችሏል።

ሰውየው በስፔን ቆይታው ያስመዘገበው ስኬቶችም ከማንም ቀደመው የታዩት ደግሞ በአርሰናል ነበር። ጥሩ ተጫዋቾችን በጥሩ ዋጋ የማግኘት ብቃት ያለው ራውል ሳንለሂ፣አርሰናልን የተቀላቀለው በ2018 ላይ የክለቡ የእግር ኳስ ጉዳዮች መሪ በመሆን ነው። መድፈኖች በወቅቱ ለለውጥ የሚንደረደሩበትና የክለቡ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢቫን ጋዚዲዝም ከወራት በኋላ ወደ ኤሲ ሚላን ማቅናታቸው ራውል የክለቡ የእግር ኳስ ጉዳዮች ሃላፊ እንዲሆን አስችሎታል።

በእርግጥ ሳንለሂ በአርሰናል አዲሱን የስራ ሃላፊነት ከተረከበ በኋላ ነገሮች ጥሩ አልነበሩም። በተለይ የክለቡ በፋይናንስ አቅሙ መንገዳገዱ፣ የራምሴ በነፃ መልቀቅና አስተዳደሩም ክፉኛ አሰልችቶታል።ይሁንና የንግዱ ሰው በዘንድሮው የዝውውር መስኮት ያሳየው ብልጠትና የቢዝነስ ብቃቱን ሁሉን አስረስቶታል።

ምንም እንኳን አርሰናል ለሁለት አመታት ከታላቁ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ መራቁን ተከትሎ በደረሰበት የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት በተገደበ በጀት ለመንቀሳቀስ ቢገደድም፣ በራውል ተፅእኖ ተጠቃሚ ተጫዋቾች ወደ ክለቡ መጥተዋል።፡ ስድስት ተጫዋቾች ወደ መድፈኛው ሲቀላቅሉ የፔፔ ዝውውር የክለቡን ሪከርድ ሰብሯል።

የ50 አመቱ ሰው እነዚህን የመሳሰሉ ዝውውሮች ሲፈፀም፣ የተጋነነ ወጪ አለማውጣቱና የክለቡን ወጪና ገቢ በማመጣጠን 91 ሚሊየን ፓወንድ ብቻ ነው ወጪ ያደረገው። አልክስ ኢዎቢ፣ሎረን ኮሲዬልኑ፣ ጃንኪነሰን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን በመሸጥ 60 ሚሊየን ፓውንድ ገቢ በማስገኘቱም የበርካቶችን አድናቆት አትርፏል።

የመድፈኖቹ ደጋፊዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ የዘንድሮውን የውድድር አመት በጭንቀት እንዳያሳልፉ ምርጥ ተጫዋቾችን ወደ ኤመርትስ በማምጣት እፎይታን ሰጥተዋልና ከሁሉም ቀድመው ራውል ሳንለሂ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 7/2011

 ታምራት ተስፋዬ