“ሰላም ፍቅር አንድነትና ብሄራዊ ኩራት ከአዲስ አበባ እንዲጀምር እንፈልጋለን፡፡” ኢ/ር ታከለ ኡማ

31

ሰላም ፣ፍቅር ፣ አንድነትና ብሄራዊ ኩራት ከአዲስ አበባ እንዲጀምር እንፈልጋለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ ተናገሩ፡፡

ኢ/ር ታከለ ኡማ ይህንን ያሉት በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ ከተማ የስፖርቱን ዘርፍ ለማሳደግ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በተዘጋጀው የዕውቅና እና የምስጋና መድረክ ላይ በተገኙበት ወቅት ነው፡፡

እንደ ምክትል ከንቲባው ገለፃ አዲስ አበባ የሀገራችን ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን ብዙ መልካም ነገሮችን በመጀመር ለክልል ከተሞችም አርአያ መሆን አለባት፤ ለአብነትም የዛሬ አመት የተሰራውን የችግረኞች ቤት እድሳትና በጠቅላይሚኒስትሩ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የችግኝ ተከላ ጅማሮውን በአዲስ አበባ አድርጎ ወደ ክልልም መውረዱን በማውሳት አሁንም በከተማ አስተዳደሩ በመንግስት ትምህርት ቤቶች የተጀመሩት ስራዎች ወደክልልም ይወርዳሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

‘’የከተማውን ወጣት ማገልገል ግዴታችን ነው’’ ያሉት ምክትል ከንቲባው የወጣቱን ፍላጎት ለሟሟላት እንደሚሰሩ በመግለፅ ፤ ስፖርትም የልማቱ አንድ አካል ስለሆነ ወጣቶችን በስፖርት ለማሳደግና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው በከተማዋ የስፖርቱን ዘርፍ ለማሳደግ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የተዘጋጀላቸውን የምስጋናና የእውቅና የምስክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡ በእውቅና አሰጣጥ ስነስርአቱ ላይ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም በስፖርት ዘርፍ ዘገባ ላበረከተው አስተዋፅኦ የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል፡፡

በመድረኩ ላይ በቀጣይነት በከተማዋ የስፖርቱን ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ ሊሰሩ በሚገቡ ስራዎች ዙሪያ ከስፖርት ማህበረሰብ እና ጋዜጠኞች ጋር ምክክር ተደርጓል፤ የፌደራልና የመስተዳደሩ ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡

ኢንተርናሽናል ዳኞች ባምላክ ተሰማና ሊዲያ ታፈሰም በዕለቱ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

በዳግማዊት ግርማ