ኢንተርፕራይዙ ከ275 ሚሊዮን ብር በላይ ሰበሰበ

36

አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2011 በጀት ዓመት 275 ሚሊዮን 583 ሺ 602 ብር መሰብሰቡን አስታወቀ።

የኢንተርፕራይዙ የማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ ወይዘሮ ዘሀራ መሀመድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት ተቋማቸው ስምንት ሚሊዮን 487 ሺ 743 የትራፊክ ፍሰትን በማስተናገድ 264 ሚሊዮን 307 ሺ134 ብር፣ ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ እንዲሁም ከሌሎች አግልግሎቶች 11 ሚሊዮን 276 ሺ 468 ብር ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

የመንገዱን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያም የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብሮችን መካሄዳቸውን እንዲሁም የ24 ሰዓት የመንገድ ላይ የትራፊክ ቁጥጥር እንደሚደረግ የተናገሩት ቡድን መሪዋ፤ በአገልግሎት እድሜ ማብቃትና በአደጋ ምክንያት በንብረቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመወያየት መንገዶችን በመሥራትና በመጠገን ምቾት እንዳይጓደል መደረጉን አብራርተዋል፡፡

እንደ ቡድን መሪዋ ገለጻ ኢንተርፕራይዙ የአገልግሎት አሰጣጡን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ ሄዷል ፤ በዚህም የመንገድ ላይ መብራት ማስፋፊያና ዝርጋታ፣ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያና የደንበኞች የጥሪ ማዕከል ግንባታ፣ እንዲሁም የስራ ቦታን ምቹ የማድረግ ተግባራት ታቅደው በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አምስት አመት ያስቆጠረው የአዲስ አበባ – አዳማ የፍጥነት መንገድ የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፤ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ከ31 ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎችን በማስተናግድ ከ965 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰብስቧል። ኢንተርፕራይዙ በ2011 በጀት ዓመትም የድሬዳዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድንም ስራ አስጀምሯል።

አዲስ  ዘመን ነሃሴ 8/2011

አጎናፍር ገዛኸኝ