ስልጠናው የተጀመረውን ለውጥ በቁርጠኝነት የሚያስቀጥሉ አመራሮችን መገንባት ያስቻለ እንደነበር ተገለፀ

6

አዲስ አበባ፦ በኦሮሚያ ክልል የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ የተሰጠው ስልጠና ብቁ አመራሮችን በማውጣት የተጀመረውን ለውጥ በቁርጠኝነት የሚያስቀጥሉ አመራሮችን መገንባት ያስቻለ እንደነበር የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሀላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፤ በክልሉ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለማቃለልና የተጀመረውን ለውጥ በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ይህንን በቁርጠኝነት ማስፈጸም የሚችል አመራር የመፍጠርና የመገንባት ጉዳይ ደግሞ ዋና ተግባር ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ስልጠናው የተሰጠው በሁለት ምክንያቶች ነው ያሉት ሀላፊው አንደኛው ለውጡ በሚፈልገው ፍጥነት ለመጓዝ ይቻል ዘንድ በእውቀት፣ በግንዛቤና በክህሎት የዳበረ አመራር ለማውጣት ሲሆን ሌላው ከለውጡ ወዲህ ከህብረተሰቡ የሚነሱና ለውጡ እኛ ጋር አልደረሰም የሚሉ ቅሬታዎችን በውል ለመመለስ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለውጡን በሚፈልገው ፍጥነት የሚያስኬድ አመራር መፍጠር የክልሉ ዋነኛ አጀንዳ ተደርጎ እየተሰራ በመሆኑ ከህዝቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን በታችኛው እርከን የሚገኙ 80 ሺህ አመራሮች በ20 ዙር ማሰልጠን መቻሉን የጠቆሙት አቶ አድማሱ ሰልጣኞቹም ከ19 ከተሞች፣ 323 ወረዳዎች፣ 7ሺ 266 ቀበሌዎች የተውጣጡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የስልጠናው ዋና አላማ ለውጡንና ባህርያቱን በውል ተረድቶ በዛ ደረጃ ብቁ የሆነ አመራር መፍጠር ነው ያሉት ሀላፊው በሚጓዝበት ፍጥነት አብሮ መጓዝ የሚችል ፣ የአመለካከትና የተግባር አንድነት ያለው፣ የሚናበብ ፣ የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን ተቀብሎ በሚፈለገው ፍጥነት ተግባር ላይ የሚያውል አመራር መገንባት የክልሉ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

በሌላም በኩል የአገሪቱን፣የክልሉን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በውል ተረድቶ ለመፈጸም በአቅምና በአመለካከት የተዘጋጀ አመራር ወቅቱ የሚጠይቀው አካሄድ በመሆኑ ስልጠናው አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡

በስልጠናው አማካይነትም አመራሩ ለውጥን ተቀብሎ እስከ ታች ማድረስና የህዝቡን ፍላጎት በውል መረዳት፤ በዛ ልክ ወቅቱ የሚጠይቀውን አመራር መስጠት ፣የህዝቡን የልማት ፍላጎት በውል ማሳካት፣ የአገልጋይነት ስሜት መፍጠርና በአመለካከትና በተግባር አንድ መሆን እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል፡፡

ለውጡን መሸከም የሚችል ጠንካራ መዋቅር መፍጠር ሌላው የስልጠናው ኣላማ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አድማሱ በዚህም በክልሉ የህግ የበላይነትንና ሰላም ማረጋገጥ፣በሁሉም መስክ የለማችና የበለጸገች ኦሮሚያን የመገንባት ሂደቱን በስኬት ለማጀብ ስልጠናው ጠቃሚ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ስልጠናው ከላይ እስከ ታች ያለውን የመንግስት መዋቀር በውል በማስገንዘብ በስኬት ተጠናቀቀ ነው ያሉት አቶ አድማሱ በቀጣይም በስልጠናው የተገኙ ውጤቶችን የማስቀጠልና አመራሩ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ገብቶ የህዝቡን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሰላም ችግሮችን ለመፍታት ወደስራ የሚገባበት ይሆናል ብለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ስራዎች የሚመዘኑት ባስገኙት ውጤት እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

አዲስ  ዘመን ነሃሴ 8/2011

እፀገነት አክሊሉ