ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ የእቅዱን 60 በመቶ ብቻ አሳክቷል

21

. በ2012 በአምስት የትምህርት አይነቶች ስልጠና ለመስጠት አቅዷል

አዲስ አበባ፡- ስኳር ኮርፖሬሽን በ2011 በጀት ዓመት ለማምረት በእቅድ ከያዘው 60 በመቶውን ብቻ ሲያሳካ በ2012 በአምስት የትምህርት አይነቶች ስልጠና ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለፀ።

በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ አራት ሚሊዮን 194ሺ 150 ኩንታል ስኳር ለማምረት ታቅዶ ሁለት ሚሊዮን 516 ሺ 350 ወይም የእቅዱን 60 በመቶ አሳክቷል።

“ያቀድነውን ያህል ምርትና ገቢ አላገኘንም” ያሉት ስራ አስፈፃሚው፤ ለምርትና ገቢ መቀነስ የሸንኮራ አገዳ በሚፈለገው ደረጃ አለመመረቱ፣ የቴክኒክ ችግር፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ የሚገቡ የፋብሪካ ግብዓቶች ፣ ኬሚካሎች፣ ማዳበሪያ፣ የጸረ ተባይ መድሃኒቶች፣ መለዋወጫዎችና ለግብዓቶች መግዣ የሚውል የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ጋሻው ማብራሪያ የአቃቂ ቤዚክ ሜታል ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ለስኳር ፋብሪካዎቹ ሮለርና ሌሎች መለዋወጫዎችን ለሶስቱም ፋብሪካዎች ባለማቅረቡ፤እንዲሁም የፋብሪካዎቹ ቁጥር ወደ ስምንት በማደጉ የመለዋወጫ አቅርቦት እጥረት ለምርት መቀነስ አስተዋጾ አድርጓል።

አቶ ጋሻው ከውጫዊ ችግር በተጨማሪም የተቋሙ የማስፈጸም አቅም ውስን መሆን፣ የነበሩት ፋብሪካዎች በአንድ ጊዜ ወደ ስምንት እንዲያድጉ በመደረጉ የሦስት ፋብሪካ ሰራተኞች ወደ ሌሎቹ መበተናቸው፤ በሚፈለገው ደረጃ ምርታማ የሆነ ፈፃሚ የሰው ሀይል እንዳይኖር ማድረጉን ገልፀዋል ።

አዳዲሶቹ ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታቸው ተጠናቅቆ የሸንኮራ አገዳ ምርት አለመድረስ፤ በአንዳንድ ስፍራዎች ምርቱ ደርሶ የፋብሪካዎች አለመጠናቀቅ ፣ የኤሌክትሪክ፣ የውሃና የአገልግሎት የግንባታ ስራዎች አለመከናወን ለምርት መቀነሱ ተጨማሪ ምክንያቶች እንደነበሩ አቶ ጋሻው ጠቁመዋል ።

ኮርፖሬሽኑ ምርታማ እንዳይሆን የፋይናንስና አስተዳደራዊ አሰራሮች ተግዳሮቶች እንደሆኑ በጥናት በመረጋገጡ በኢንዱስትሪዎች የፕሮጀክት አገልግሎት የአደረጃጃትና የአሰራር ጥናት ችግሩን ለመፍታት ስራ መጀመሩን አቶ ጋሻው ተናግረዋል።

አዲሱ አደረጃጀት ስራና ሰራተኛን የሚያገናኝ፣ ከዋና ስራ አስፈፃሚው በታች ያሉ ሀላፊዎችና ሰራተኞች እውቀትን፣ ክህሎትን፣ የስራ ዝግጁነትንና ልምድን መሰረት በማድረግ ምደባ እንደሚካሄድ፣ የተለያዩ ስያሜን ይዘው የነበሩ የሥራ ክፍሎችን በማጣመር ቀልጣፋና ውጤታማ ስራ ለማከናወን የሚያስችል አደረጃጀት መዘርጋቱን አቶ ጋሻው ገልፀዋል።

አቶ ጋሻው ኮርፖሬሽኑ ብቁ የሰው ሀይል ለማፍራት በ2011 በጀት ዓመት ከደረጃ አንድ እስከ አራት ስልጠና የሚሰጥ “የስኳር አካዳሚ” መከፈቱን፣ በ2012 ዓ.ም በእርሻና በፋብሪካ ሙያ በአምስት የትምህርት አይነቶች ስርዓተ ትምህርት በመቅረጽ ስልጠና ለመጀመር ፈቃድ መገኘቱን ተናግረዋል።

አቶ ጋሻው ከአምስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በሁለተኛ ዲግሪ በሰባት የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ስርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶ ስልጠና በመጀመሩ የመጀመሪያዎቹ 80 ሰልጣኞችም በዘንድሮው ክረምት ትምህርት እንደሚጀመሩ፣ በአምስት ዙር ከ600 እስከ 800 የኮርፖሬሽኑ ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚያገኙና ኮርፖሬሽኑ በዘርፉ ምርምር ለሚያደርጉ ሰራተኞቹ የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድልም እየሰጠ እንዳለ ተናግረዋል።

አጎናፍር ገዛኸኝ

አዲስ  ዘመን ነሃሴ 8/2011