ቴሌቪዥን ጣቢያው ደመወዝ እንደከለከላቸው ሠራተኞች ገለፁ

80

አዲስ አበባ፡- አፍሪ ኸልዝ የቴሌቪዥን ጣቢያ መብታቸውን በመጠየቃቸው ደመወዝ እንደከለከላቸው የተቋሙ ሠራተኞች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡

በአፍሪ ኸልዝ የቴሌቪዥን ጣቢያ የካሜራ ክፍል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ በየነ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጸው፤ እርሱን ጨምሮ ሰባትየሥራ ባልደረቦቹ ደመወዝ ሳይከፈላቸው ሁለት ወራት ከሰባት ቀን አሳልፈዋል፡፡ ከዓመት በላይ በድርጅቱ በቆየባቸው ጊዜያትም ደመወዝ በወቅቱ ተከፍሏቸው እንደማያውቅ ጠቅሶ፤ የሰኔ ወር ደመወዝ ሳይከፍላቸው የሐምሌ ወር መውሰጃ ጊዜ በመድረሱ ሠራተኞችን ለከፍተኛ ቅሬታ መዳረጋቸውን፣ ሁኔታው ግራ ያጋባቸው ሠራተኞችም ልመና በተሞላበት ሁኔታ ተደጋጋሚ ቅሬታ ቢያቀርቡም ደመወዛቸው ሊከፈላቸው እንዳልቻለ አስረድቷል፡፡

ከዚህ ቀደምም መሰል ችግሮች ሲያጋጥሙ ፊርማ እያሰባሰቡ ይጠይቁ እንደነበርና መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ የተባረሩ ሠራኞች እንደነበሩ አቶ ሀብታሙ አስታውሶ፤ ተቋሙ ሥራውን በጀመረበት አካባቢ በነበሩ መዘግየቶች ዋና ሥራ አስኪያጇ ገንዘብ አጥሯቸው በመዘግየቱ ይቅርታ ይጠይቋቸው የነበር ቢሆንም በሰኔ ወር ላይ በተፈጠረው መዘግየት ቤተሠብ አስተዳዳሪ እንደሆኑና ችግር ላይ እንደወደቁ ለተቋሙ ቢያሳውቁም ምንም ምላሽ ሊያገኙ እንዳልቻሉ፣ ከሠራተኞች መካከል ከቤት አከራዮቻቸው ቤት እንዲለቁ የተነገራቸው እንዳሉም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠቁመዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጇ ቅሬታዎች ሲበረቱና ጉዳዩ ለሕዝብ ጆሮ ሲደርስ የሰኔ ወርን ከሐምሌ ወር ጋር አንድ ላይ ለመክፈል ከገንዘብ ከፋይ ጋር በመቀመጥ ቅሬታውን ለመገናኛ ብዙሃን ለማድረስ የሄደና ያልሄደውን በመለየት ላልሄዱት ሲከፍሉ፤ መገናኛ ብዙሃን ዘንድ መሄዳቸውን ያመኑ ሰባት ሠራተኞች ከደመወዛቸው የአምስት ቀናት ተቆርጦ እንደሚሰጣቸው እንደገለፁላቸው አስረድተዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሁኔታው ንዴት ፈጥሮባቸው ደመወዛቸውን ላለመቀበል ወስነው ከሄዱ በኋላ ካለባቸው ችግር አንፃር የአምስት ቀናቱ ተቆርጦ እንዲሰጣቸው ዳግም ቢጠይቁም ልዩ ልዩ ምክንያቶችን በመደርደር የሁለት ወራት ደመወዝ ሳይከፈላቸው ሰባት ቀናት እንዳለፋቸው ገልጸው፤ አሁንም ሥራቸውን እየሠሩ እንዳሉ፣ ቤተሠቦቻቸውም ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡

በአፍሪ ኸልዝ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ሞገስ ናደው፤ የደመወዝ መዘግየት አጋጥሞ እንደነበር አምነው መዘግየቱ እንደ ማንኛውም በአገሪቱ እንዳሉ ድርጅቶች ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ሠራተኞቹ ቅሬታቸውን በማቅረባቸው በተቻለ አቅም ክፍያው እንዲፈፀም ተደርጓል፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ሁሉም ሠራተኛ ላይ ቅሬታ እንዳለ አስመስለው የሚያቀርቡት ትክክል አይደለም በማለት አስተባብለዋል፡፡

አቶ ሞገስ ፤ የዘገየው የሰኔ ወር ደመወዝ ሲሆን፤ ከሐምሌ ወር ጋር እንዲከፈል ተደርጓል፡፡ ተቋሙ ተሯሩጦ ክፍያውን በ30 ቀናት ውስጥ ከከፈለ ይህን ያክል አደጋ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ 377/96 መሠረት ደመወዝ የሚከፈለው ለተሠራ ሥራ ብቻ እንደሆነ አንቀጽ 54 ንዑስ ቁጥር 1 ይደነግጋል፡፡ ዘግይቷል፤ መዘግየቱ ግን ድርጅቱ ባጋጠመው የገንዘብ ችግር ምክንያት ነው፡፡ ሥም ለማጥፋት ካልተፈለገ በስተቀር አንድ ወር ደመወዝ በመዘግየቱ በዚህ ደረጃ መቅረቡ ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡

ተቋሙ ከ50 በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፤ ደመወዝ በመዘግየቱ ምክንያት ሰባቱ ሠራተኞች የሥራ ገበታቸው ላይ አልተገኙም፡፡ የቅርብ የሥራ ክፍል ኃላፊም ለአምስት ተከታታይ የሥራ ቀናት እንዳልተገኙ አቅርቧል፡፡ ማሕደራቸው ሲታይም የጎላ ችግር ስላልነበረባቸውና ደመወዝ ዘግይቶ ስለተሰጣቸው ምንም እንኳ ጥፋታቸው የሥራ ውል እስከማቋረጥ የሚያደርስ ቢሆንም ለአምስት ቀናት በመቅረታቸው ያልሠሩበት ሊከፈላቸው ስለማይገባ ተመላሽ ይደረግ በሚል መወሰኑን ጠበቃው አስረድተው፤ መፍትሄ የሚሆነውም ሥራቸውን አክብረው በመገኘት ቅሬታ ሲያቀርቡ ተቋሙ ችግሩን ተመልክቶ ተገቢው ውሳኔ ለማስተላለፍ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ጠበቃ፣ የሕግ አማካሪና መምህር አቶ ዳኛቸው መኮንን ሲያብራሩ፤ አሠሪው በወቅቱ ደመወዝ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ከደመወዝ ጋር የተያያዙ ነገር ግን እንደ ደመወዝ የማይቆጠሩ ሌሎች ክፍያዎችም በውላቸው መሠረት አብረው መከፈል ይኖርባቸዋል፡፡ ሠራተኛው በቀን የሚያገኘው አማካኝ ደመወዝ በውል ስምምነቱ መሠረት የተወሰነ ሆኖ በአገሪቱ መነሻ ወለል አልተቀመጠም፡፡

በቀጣሪና በተቀጣሪ ስምምነት መሠረት በቀን የሚከፈለው አማካኝ ደመወዝ በሣምንት አልያም በወር ተሰልቶ በወቅቱ ሊከፈል ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የውሎ፣ የትርፍ ሰዓት፣ የበረሃና የመጓጓዣ ክፍያዎችና ሌሎች እንደየ መሥሪያ ቤቱ የሚከፈሉ ሁሉ በደመወዝ መክፈያ ቀን ሊከፈሉ ይገባል፡፡

በስምምነታቸው መሠረት መከፈል በሚገባው ቀን ክፍያ ካልተፈፀመ አሠሪው ግዴታውን አልተወጣም ማለት ነው፡፡ አሠሪው ግዴታውን ሳይወጣ ሲቀርም በሕግ ተገድዶ ደመወዛቸውንና ወጪያቸውንም አስልቶ በክርክሩ ሒደት ደመወዝ መከፈል ከቆመበት እስከሚወሰንበት ድረስ ያለው ጊዜ ወለድ ታስቦ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡

የሥራ ውሉ ሳይቋረጥ ከሆነ ደመወዝ እንዲከፍልና በዚህ ምክንያት የተጉላሉበት ነገር ካለ ተካክሶ እንዲከፈል ይደረጋል፡፡ ከዕዳዎች ሁሉ በቅድሚያ መከፈል ያለበት የሠራተኛ ደመወዝ መሆን እንደሚጠበቅበትም አቶ ዳኛቸው አሳውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ ኣብርሃ እንደሚናገሩት፤ በአገሪቱ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲቋቋሙ ብሮድካስቱ ጥልቅ ክትትል ያደርጋል፡፡ ክትትሉም ድጋፍን መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ መገናኛ ብዙሃኑ ሲቋቋሙ ማሟላት ያለባቸው አስፈላጊ ግብዓቶች ይታያሉ፡፡

በሒደትም መጀመሪያ ባስገቡት የፕሮጀክት ጥናት መሠረት ስለማንቀሳቀሳቸው ቁጥጥርና ክትትል ይደረጋል፡፡ ወደ ተግባር ከገቡ በኋላም ያሏቸውን መርሃ ግብሮች የሚያሻሽሉ ከሆነ በየጊዜው ይፈተሻል፡፡

የኤዲቶሪያል ለውጥ ካደረጉም ለባለሥልጣኑ ያሳውቃሉ፡፡ በዚህ መሠረትም ክትትል ይደረጋል፡፡ ነገር ግን መገናኛ ብዙሃኑ ከሰራተኞቻቸው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት አስመልክቶ ለባለሥልጣኑ የቀረበ ቅሬታ የለም፡፡ ተቋማቱ በየራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ የመምራት መብታቸው የተጠበቀ በመሆኑ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ የማየት ሥልጣን የለውም፡፡

አዲስ  ዘመን ነሃሴ 8/2011

ፍዮሪ ተወልደ