“ማህበራዊ ፍትህ ከሰፈነ የብሔር ጥያቄ በሂደት ይከስማል” ዶክተር ኮንቴ ሙሳ የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር

263

አዲስ አበባ፦ በመላው አገሪቱ ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን ከተቻለ የብሔር ጥያቄ በሂደት እየከሰመ የሚሄድ መሆኑን የአፋር ህዝብ ፓርቲ አስታወቀ::

የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ኮንቴ ሙሳ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት የብሔር ጥያቄን ማክሰም የሚቻለው በመላው አገሪቱ ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን ሲቻል ብቻ ነው::

እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ የብሔር ጥያቄው መነሻው የፍትህ እጦት፣ በቋንቋ አለመጻፍ፣ አካባቢን አለማስተዳደር ሲሆኑ፤እነዚህ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ማህበራዊ ፍትህን ለማምጣት ዝግጁ የሆነ አስተዳደር ሲኖር ነው፡፡

የሰው ልጅ የብሄርን ካርድ ይዞ የሚንቀሳቀስበት ምንም ምክንያት የለውም ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ይህንን አጀንዳ ይዘው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞች በአብዛኛው ህዝብ መሸነፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ የብሔር ጥያቄ በማህበራዊ ፍትህ ከተመለሰ አክራሪነቱ ከስሞ ብሔራዊነት ወደሚለው አስተሳሰብ መሄድ ይቻላል ብለዋል፡፡

ሊቀ መንበሩ ማህበራዊ ፍትህ ማስፈን የሚቻለው እያንዳንዱ ዜጋ ደህንነት እንዲሰማው በማድረግና ሰው በሰውነቱ እንጂ በብሔሩ መለካት እንደሌለበት መተማመን ላይ ከተደረሰ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም አፋር ያለው አማራ በብሔሩ ሳይሆን በሰውነቱ ከተከበረና እርሱም ምቾት የሚሰማው ከሆነ ያን ግዜ ማህበራዊ ፍትህ ማስፈን ይቻላል ብለዋል፡፡

አዲስ  ዘመን ነሃሴ 8/2011

እፀገነት አክሊሉ