“የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው ጨረታ ማጭበርበር ፈጽሞብናል”ቅሬታ አቅራቢዎች

138

 “ጨረታው ተበልቷል”

የፌዴራል የመንግስት ግዥ ኤጀንሲ

 “ጨረታው ግልጽ ስለሆነ የጨረታ መመሪያና ማብራሪያ አልሰጥም”

 አየር መንገዱ

 “ጨረታውን ማሳገድ ይችላሉ”

 የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ

አዲስ አበባ፤- የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ ለሚያስገነባው ቁጥር ሁለት ተርሚናል ለተለያዩ የንግድ አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎች ያወጣውን ጨረታ ማጭበርበሩና ጨረታውን መሰረዙ አግባብ ያለመሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎች ገለጹ። አየር መንገዱ ‹‹ጨረታውን የሰረዝኩት በተቋሙ መመሪያና አሰራር መሰረት ነው፤ አሰራሬ ግልፅ ስለሆነም ስለጨረታው ማብራሪያም ሆነ የተቋሙን መመሪያ አልሰጥም›› ብሏል። የፌዴራል የመንግስት ግዥ ኤጀንሲ በበኩሉ “ጨረታው ተበልቷል ማለት ይቻላል›› ብሏል።

አየር መንገዱ ባወጣው ጨረታ የተሳተፉና የቴክኒክ መስፈርቱን ያሟሉ ስምንት ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ባቀረቡት አቤቱታ ‹‹ተቋሙ ከአገሪቱና ከዓለም አቀፍ ህግ የጨረታ ስርዓት ውጪ ያፈነገጠ አሰራርን ፈፅሞ ስላጭበረበረን ጉዳት አድርሶብናል›› ብለዋል።

እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ማብራሪያ የጨረታው የመዝጊያና የመክፈቻ ጊዜ በግልጽ መነገር ሲገባው በሚጠበቀው ሰዓት አልተካሄደም፤ ጨረታውን ለማሸነፍ 40 በመቶ ነጥብ የሚይዘውን ቴክኒካል መወደዳሪያ ነጥብ በጊዜው በጽሁፍ አላሳወቀም፤ 60 በመቶ ነጥብ የሚይዘውን የቀረበውን የገንዘብ መጠን መወዳደሪያ ያሳወቀው ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው።

‹‹አየር መንገዱ ጨረታውን ለመክፈት ተጫራቾችን ከጠራ በኋላ ‹ጨረታው ሲከፈት ታያላችሁ እንጂ ተጫራቾች ያቀረቡትን ዋጋ አልገልፅም› በማለቱ፤ ያቀረብነው ዋጋ ካልተገለጸ የእኛ መገኘት ለምን አስፈልገ? እንዲህ አይነት የጨረታ አካሄድ ሊኖር አይገባም ብለን በመቃወማችን ጨረታው ሳይከፈት ልንመለስ ችለናል›› ብለዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ‹‹አየር መንገዱ ጨረታውን በድጋሚ ለመክፈት ጠርቶን ‹ጨረታው ሲቀደድ ታያላችሁ እንጂ የመወዳደሪያ ዋጋውን አንነግራችሁም፤ በጽሁፍ እናሳውቃችኋለን› ብሎ አሰናብቶናል፤ በጽሁፍ ሳያሳውቅም ጨረታውን ሰርዞ ለሰባት ቀናት አየር ላይ የሚቆይ ማስታወቂያ አውጥቷል›› ይላሉ።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ አየር መንገዱ ግልጽ ጨረታ አውጥቶ ተጫራቾች ያቀረቡት ዋጋ እንዳይታይ መከልከል እንደማይችል፣ ጨረታውን መሰረዝ ከፈለገም የተጫራቾች የቴክኒክና ፋይናንሻል ሰነድ ከመታየቱ በፊት መሆን እንደሚገባው፤ ሰነዱ ከታየ በኋላ ጨረታውን መሰረዝና በሰባት ቀን ቆይታ የሚያበቃ ጨረታ ማውጣቱም ሕገወጥ መሆኑን ገልፀዋል።

‹‹የአየር መንገዱ ሀላፊዎች ጨረታውን ከፍተው የእኛ መረጃ እንዲታይ ማድረጋቸው በጥቅም ለተሳሰሯቸው ሰዎች ለመስጠት ሲሆን፤ የጥቅም ትስስር ያላቸው ሰዎች በቀድሞው ተርሚናል የሚሰሩ ናቸው፡፡ ጨረታውን ለመሰረዝ የሚያስችል ምክንያትም የላቸውም ›› ሲሉም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያስረዳሉ።

ስለጨረታው ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በፌዴራል መንግስት ግዥ ኤጀንሲ የመንግስት ግዥ አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ መቅደስ ብርሃኑ፤ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የግዥና የንብረት አስተዳደራቸውን የሚገዛ ህግና የሚከታተል ተቋም እንደሌላቸው በመግለፅ፤ አብዛኞቹ የልማት ደርጅቶች የኤጀንሲውን አዋጅ ቁጥር 649/2001 መነሻ በማድረግ የራሳቸውን መመሪያ በማዘጋጀት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ያስረዳሉ።

እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ የመንግስት ጨረታ መርህ ጨረታው ከመውጣቱ በፊት ሙሉ ዝግጅት መደረጉን ማረጋገጥ አለበት። ጨረታ ሲወጣ በጨረታው ሰነድ ላይ ግልጽና ዝርዝር መስፈርቶች መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ቅሬታም ሲፈጠር የመፍቻ ሰርዓት መዘርጋት፤ አሰራሩንና ውሳኔውን ለሚመለከታቸው አካላት ግልጽ ማድረግ ፤ የመንግስት ንብረት በጥንቃቄ መያዙንና ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ፤ ከዚህ ሲያፈነግጥም ተጠያቂነትን ማስከተል ያስፈልጋል።

ዳይሬክተሯ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ በቀረበው ቅሬታ መረጃዎች ዕውነት ከሆኑ የአየር መንገዱ የጨረታ አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ፤ ጨረታ ሲካሄድ የመክፈቻውና የመዝጊያው ጊዜ በግልጽ መቀመጥና በዚያ መሰረት መፈፀም እንዳለበት፤ እንዲሁም የጨረታ ርዝማኔም በተጫራቾቹ ጠያቂነትና በአጫራቹ ፍቃድ ሳይሆን በተቋሙ መመሪያ ሊፈፀም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ዳይሬክተሯ ‹‹አየር መንገዱ ጨረታውን ከከፈተ በኋላ የሁሉንም የጨረታ ሰንዶችን ተጫራቾች ባሉበት ማንበብ ነበረበት። የጨረታውን ሰነዶች ከፍቶ ካየ በኋላ ‹የተጫረቱበት የገንዘብ መጠን አይገለጽም› ማለት ተገቢ አይደለም።

ያልተነበበ የጨረታ ሰነድም ተቀባይነት የለውም። መስፈርቱን ያሟሉና ያላሟሉትም መገለጽ ነበረባቸው። ቃለ ጉባዔ ተይዞ ታዛቢዎቹና አጫራቾቹ መፈረም ይገባቸው ነበር። ሁለቱ ተደምሮ አሸናፊዎቹንና ተሸናፊዎቹንም መግለጽ ያስፈልግ ነበር›› ብለዋል።

ተቋሙ ጨረታውን መሰረዝ የሚችለው የቴክኒኩና የፋይናንሻል ሰነዶቹ ከመከፈታቸው በፊት እንደነበር ያስረዱት ዳይሬክተሯ ‹‹ከተከፈተ በኋላ ግን ሂደቱን ሰርዞ እንደገና ጨረታ ማውጣት ጨረታው ተበልቷል ማለት ነው›› ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋዜጠኛ የኢትዮጵየ አየር መንገድ ጨረታው የተሰረዘበትን ምክንያት እንዲያብራራ፣ የተቋሙን የጨረታ መመሪያና የጨረታ ሰነድ እንዲሰጠው የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጁን አቶ አስራት ጋሻውን ጠይቆ ፤ ‹‹የአየር መንገዱ የጨረታ መመሪያ ላንተ አያስፈልግህም፤ የምንነግርህን መረጃ ብቻ ነው መጠቀም ያለብህ፤ ይህ የድርጅቱ የውስጥ አሰራር ነው።

በአጠቃላይ ለሶስቱ ጥያቄዎችህ መልስ አልሰጥህም ባትለፋ ነው የሚሻልህ›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ‹‹ ከዚህ በላይ ላናግርህ አልችልም›› በማለትም ጆሮው ላይ ሰልክ ዘግተዋል።

የዝግጅት ክፍሉ የአየር መንገዱን ምላሽ አካትቶ ዜናውን ለማስነበብ ለቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጊዜያዊ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታነህ ጥያቄ አቅርቦ እርሳቸውም ጥያቄው በጽሁፍ እንዲቀርብና የህዝብ ግንኙነቱን አናግረው መረጃ ለማግኘት እንደሚሞክሩ፣ ማብራሪያም እንደሚሰጥ ቢገልፁም ለህትመት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም።

በፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ የፍትሀብሄር ፍትህ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ምስክር ታሪኩ ‹‹ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለፍርድ ቤት አቤቱታ በማቅረብ ጨረታውን ማሳገድ ይችላሉ ፤ በጠቅላይ አቃቢ ህግ ፍትሐብሄር ዳይሬክቶሬት ልደታ በሚገኘው ቢሮ መጥተው ስለቅሬታቸው መነጋገር እንችላለን።

መፍትሄ ለማግኘትም ከአየር መንግዱ ሀላፊዎች ጋር እንነጋገራለን። ተገቢ ያልሆነ አሰራር ተከትለው ከሆነና መስተካከል የሚችል ከሆነ እንዲፈታ እንሞክራለን። ትክክል ካልሆነም ለግለሰቦቹ አቅጣጫውን እናሳያቸዋለን›› ብለዋል።

አዲስ  ዘመን ነሃሴ 8/2011

አጎናፍር ገዛኸኝ