ይዞታው የማን ነው?

30

ከ28 ዓመታት በፊት በወቅቱ አጠራር የሥጋ ሜዳ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር በአሁኑ ደግሞ የታጠቅ አሸዋ ሜዳ አካባቢ ነዋሪዎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄያቸውን ያነሳሉ። ጥያቄያቸውም በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ አግኝቶ ለዓመታት በሠላም ቢኖሩም ከአምስት ዓመታት በፊት ግን ያላሰቡትና ጥያቄያቸውን ዳግም መልሶ ወደ ችግር የሚቀይር አጋጣሚ እንደተፈጠረ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ዕውነታቸውን ለማስረዳት ያቀረቧቸው የሰነድ ማስረጃዎች እንዲሁም የሰው ምስክሮች ቢኖሩም በአገሪቱ የመጨረሻው የፍትሕ አካል የሆነው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የወሰነው ውሳኔ ሐዘንን የጫረባቸው ነዋሪዎቹ ኤጀርሳ ቀንጨራ ወይንም በአማርኛ ስያሜው ‹‹ያረጀ ወይራ›› በሚል የሚጠራው ዛፍ በወቅቱ ለይዞታው ምልክት ሆኖ ነበርና አፍ ቢኖረው ዕውነታውን በመሰከረ ሲሉ ይገልፃሉ።እኛም እነዚህ ነዋሪዎች የገጠማቸው ችግር ምንድን ነው? በሚል ከቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ከፍርድ ባለመብቶች ጋር እንዲሁም የሚመለከተውን አካል አነጋግረን ከሰነድ ማስረጃዎች ጋር በማቀናበር እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።

የቅሬታው መነሻ

አቶ ኢፋ መገርሳ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በቡራዩ ከተማ ገፈርሳ ኖኖ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ለ48 ዓመታት ኖረዋል።በአካባቢው ተወላጅ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ኢፋ፤ ከ28 ዓመታት በፊት ሕብረተሰቡ ዕምነቱን የሚያካሂድበትም ሆነ ሥርዓተ ቀብር የሚያስፈጽምበት ስፍራ ባለመኖሩ ምክንያት ብዙ የሐይማኖቱ ተከታዮች አምልኮ ለመፈጸም ርቀው ይጓዙ እንደነበር ያስታውሳሉ።ቀብር ሲጋጥማቸውም ሆነ ልጆቻቸውን ክርስትና ሲያስነሱ ቀራንዮ መድሐኔዓለም አልያም ጀሞ ሚካኤል በመሄድ ብዙ መንገዶችን ለማቋረጥ ይገደዱ ነበር።ይህንን ለማስቀረት ሲባልም የአካባቢው ሕብረተሰብ ተሰብስቦ በቦታው ላይ ቤተክርቲያን እንዲቋቋምለትና ዕምነቱን እንዲያካሂድ ጥያቄ ለሚመለከተው አካል ያቀርባል።

በወቅቱ የነበረው የቀበሌ አስተዳደር እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት የሕዝቡን ጥያቄ ተግባራዊ ለማድረግ ከማንኛውም ይዞታ ነፃ የሆነ ስፋቱ 55 ሺህ 811 ካሬ ሜትር ቦታ ተመልክቶ ለቤተክርስቲያኑ መትከያ ፈቃድ እንደተገኘም አቶ ኢፋ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ ያስረዳሉ።በዚህም 1983 ዓ.ም ጀምሮ ቤተክርስቲያኒቱ ለምዕመኑ አገልግሎት ስትሰጥ ትቆያለች።

በ2006 ዓ.ም ግን ድንገት ‹‹ድሮ የእኛ የነበረን ይዞታ ቤተክርስቲያኗ በኃይል ወሰደችብን›› በሚል ስድስት ሰዎች ክስ ይመሰርታሉ።ጉዳዩም ከሥር ፍርድ ቤት እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሲታይ ቆይቶ በአሁኑ ወቅት ለግለሰቦቹ ከቤተክርስቲያኒቷ ይዞታ ላይ ተከፍሎ እንዲተላለፍ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ቦታው ታጥሯል።

ጉዳዩ በጣም የሚያሳዝን ነው የሚሉት አቶ ኢፋ፣ በሺዎች የሚቆጠር በርካታ ምዕመናን ባሉበት ቦታ የስድስት ሰዎች ሚዛን ደፍቶ ይህን መሠል ውሳኔ መወሰኑ የአካባቢውን ሕብረተሰብ ቅር ማሰኘቱን ነው የሚናገሩት።ግለሰቦቹ ለፍርድ ቤት ማስረጃ ሲያቀርቡ ይዞታውን ያወረሷቸው ወይዘሮ ጫልቱ ነቢ እንደሆኑ የሚያሳይ በአማርኛ የተሞላ የተገበረበት ሰነድ አቅርበዋል።ይህንን መሠረት በማድረግም ከቤተክርስቲያኒቱ ይዞታ ላይ ተወስዶ ለግለሰቦች እንዲሰጥ የተወሰነው ውሳኔ ለበርካቶች ፍትሕን የነፈገና ሕዝቡ እንዲያለቅስ ያደረገ ነው ይላሉ።

ወይዘሮ ጫልቱ በአካባቢው የራሳቸው ይዞታ የነበራቸው ሲሆን፤ ቤተክርስቲያኒቱ ያረፈችበት ቦታ ግን ከእርሳቸውም ሆነ ከማንም ባለቤትነት ውጪና ነፃ ይዞታ እንደሆነ በወቅቱ የነበሩ አመራሮች አምነው መስጠታቸውንም ይገልፃሉ።አቶ ኢፋ፤ በልጅነታቸው ከብቶች ይጠብቁበት፣ ለቤተሰባቸውም ጭራሮ ለቅመው የሚገቡበት ብሎም ከብቶች ግጦሽ የሚያወጡበት ቦታ እንደነበር በመግለጽ፤ ይዞታው የግለሰቦች እንዳልነበር ይናገራሉ።የወይዘሮ ጫልቱ ይዞታ ከቤተክርስቲያኑ ራቅ ብሎ ያለ ሲሆን፤ ሸጠው እንደጨረሱትም ይጠቁማሉ።

በአብዛኛው በአካባቢው የሰፈረ ሰው ከእነርሱ ገዝቶ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ከ300 ያልበለጠ ሜትር ካሬ ይዞታ በልጆቻቸው ተይዟል ሲሉ ክርክር ሲደረግበት የቆየው ይዞታ የቤተክርስቲያኒቷ እንደሆነ ያስረዳሉ።ይዞታው እንደተባለው የግለሰቦቹ ከሆነስ ስለምን 28 ዓመታትን ዝምታ መርጠው ቆዩ? በማለት ይጠይቃሉ።በመሆኑም በየደረጃው ሕዝብን ወክሎ የተቀመጠ የመንግሥት አካል ጉዳዩን ሊያዳምጥና የተዛባውን ፍትሕ ሊያስተካክል ይገባል።ቅሬታ ሰሚ አካላትም የሕዝቡን ቅሬታ በአግባቡ እንዲያደምጡና የሰነድ ማስረጃዎችን በመመልከት ምላሽ እንዲሰጡ ይጠይቃሉ።

ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ አባት አቶ ደጀኔ ዱጉማ፣ የቅሬታ መነሻ የሆነውን ቦታ ከአመሠራረቱ ጀምሮ እንደሚያውቁትና ከመሥራቾች መካከል አንዱ እንደሆኑ ነው የሚናገሩት።በ1983 ዓ.ም በአካባቢው ቤተክርስቲያን ስላልነበረ ሕብረተሰቡ እንዲተከልለት ያቀረበውን ጥያቄ መስተዳድሩ ተቀብሎ ድጋፍ ማድረጉን ያስታውሳሉ።ለዚህም የሚሆን ቦታ እንዲሰጥ ከአካባቢው ሽማግሌዎች ጋር ተነጋግሮ በአሁኑ ወቅት ቤተክርስቲያኒቷ ያረፈችበት ቦታ ይፈቀዳል።

ቦታው ለቤተክርስቲያን ይሁን በሚል ሕዝቡ ተፈራሞም ነበር።ይዞታው ከተወሰነና ፈቃድ ካገኘ በኋላም ካርታና ፕላን እንዲነሳ ከተለያዩ አካላት ጋር ደብዳቤ በመፃፃፍ ታቦቱ እንዲተከል ጥያቄ ይቀርባል።በዚህም ጉዳዩ ለአዲስ አበባ ከተማ ልማት ቢሮ ቀርቦ ፕላን እንዲነሳ ይፈቀዳል።

ለቤተክርስቲያኒቱ የተፈቀደው አጠቃላይ ስፋቱ 55 ሺህ 811 ሜትር ካሬ ሳይት ፕላን እንዲነሳ ይደረጋል።ይህ ሲደረግ ቦታው ከማንኛውም ይዞታ ነፃ ተብሎ ነው።በወቅቱ በዚሁ ይዞታ ላይ የነበሩ ባሕር ዛፎች ላይ እየተቆረጠ ቀደም ሲል ከቀበሌ ማሕበሩ ለዘመቱ ወታደሮች ተሸጦ ይሰጥም ነበር።ከታጠቅ ጦር ሰፈር ለነበሩ 25 ሺህ የጦር ጉዳተኞች የቀብር ቦታ ይሆናል በሚል ቦታው ለቤተክርስቲያኗ ይሰጣል።ሆኖም ግን በወቅቱ ከተፈቀደው ቦታ መካከል ከመንገድ በታች የሚገኘው የዘላቂ ማረፊያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታና ፕላን ግን እንደሌለው አቶ ደጀኔ አያይዘው ይገልፃሉ።ይህንኑ መሠረት በማድረግ ቦታው ተከልሎ ታቦተ ጽላቱ ገብቶ ከሁለት አሰርት ዓመታት በላይ ምዕመናኑ ሲገለገልበት ቆይቷል።

ለበርካታ ዓመታት ቦታውን ቤተክርስቲያኑ ሲገለገልበት ማንም የጠየቀ አልነበረም የሚሉት አቶ ደጀኔ፤ በ2006 ዓ.ም ግን በምን መልኩ እንደሆነ ባልታወቀ መንገድ ግለሰቦች የ‹‹ይገባናል›› ጥያቄ በማንሳት ቦታው ክርክር ሲደረግበት ቆይቷል።በስተመጨረሻም በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት በተያዘው ዓመት ሐምሌ ወር ሱቆቹን በማፍረስ ለግለሰቦች ተሰጥቶ ታጥሯል።ቤተክርስቲያኒቱ ለ28 ዓመታት የተጠቀመችበትን መሬት መንጠቅም የሕዝብን ሞራል መንካት ብሎም የቤተክርስቲያንን ሕልውና መዳፈር እንደሆነ መገንዘብ ይገባል።በመሆኑም መንግሥት ጉዳዩ የሕብረተሰቡን ስሜት በእጅጉ የጎዳ መሆኑን በመመልከት ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ የሕዝብ እንባ ሊያብስ እንደሚገባ ይናገራሉ።

ሌላው ያነጋገርናቸው አቶ አረጋ ጅማ፤ በግንባር ቀደምነት ቤተክርስቲያኒቱን እንዳቋቋሙ የሚናገሩ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው።ሕዝቡ ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ አቋርጦ አስከሬን በትከሻው ተሸክሞ ቀብር ይፈጽም እንደነበር የሚናገሩት አቶ አረጋ፤ ችግሩም ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ በመሄዱ በአካባቢው ከማንም ይዞታ ነፃ የሆነ ቦታ ስላለ ቤተክርስቲያን ይቋቋምበት በማለት ሕዝቡ መጠየቁን ያስታውሳሉ።

ጉዳዩም በዝርዝር ለአዲስ አበባ አገረ ስብከት ይቀርባል።አገረ ስብከቱም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወይንም ማዘጋጃ ቤት ይመራዋል።ማዘጋጃ ቤቱም የከተማ ልማት ኮንስትራክሽንም ጉዳዩን እንዲያጣራ በደብዳቤ ይመራል።በዚህም ባለሞያ መሐንዲስ በቦታው በመገኘት ከተመለከተ በኋላ ነፃ ይዞታ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ሕጋዊ እንዲሆን ይደረጋል።

ለ28 ዓመታትም በዚህ መልኩ ቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት ስትሰጥ ቆይታለች።በአሁኑ ወቅት ይዞታው ላይ የ‹‹ይገባኛል›› ጥያቄ የሚያነሱት ግለሰቦች ከነበረው ችግር አንፃር መፍትሔ መሰጠቱ በፈጠረላቸው እርካታ በወቅቱ ይመርቁ እንደነበር አቶ አረጋ በመግለጽ፤ ከድካምና እንግልት እንደዳኑም ይናገሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።22 ለቤተክርስቲያኑ ለንዋየ ቅድሳት ተብሎ የሚታሰቡ ሱቆችም ይነሱ ተብሎ ማስጠንቀቂያ እንኳ ሳይሰጥ እንዲፈርሱ ተደርጓል።መረጃ እያለ ይህን መሠል ውሳኔ መወሰኑም ተገቢነት በመሆኑ የሚመለከተው አካል እንዲያየው ይጠይቃሉ።

ቤተክርስቲያኒቱ

የታጠቅ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ መላከብርሃን ገብረእየሱስም በቤተክርስቲያኑ የተመደቡት ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ቢሆንም በተመደቡ ማግስት ሁኔታው እንደተፈጠረና የቤተክርስቲያኑ ንብረት የሆኑ 22 ሱቆች እንዳልነበሩ መደረጋቸውን በሐዘን ይገልፃሉ።አጥሩ ፈራርሶ አገር የተወረረ እስኪመስል 200 የሚደርሱ ወታደሮች ተመድበው አስለቃሽ ጭስ በመጣል እንዲፈርስ ተደርጓል በማለት በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።ነባር የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚገልጹት፤ ቦታው የቤተክርስቲያኒቱ ይዞታ ሆኖ ቢቆይም በቅርብ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ቦታውን ‹‹የእኛ ነው›› በሚሉ ግለሰቦች ክስ መመስረቱንም ይናገራሉ።

ግለሰቦች፤ በፍርድ ቤት በማስወሰን ቦታውን ለመውሰድ ሲሞክሩ የምዕራብ ሸዋ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢጲፋንዮስ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘኣክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በመፃፋቸው፤ እርሳቸው ጉዳዩ በሕግ እንዲታይና ያለአግባብ የቤተክርስቲያን መሬት እየተወሰደ ነው በሚል ለሚመለከተው አካል መፃፋቸውን ይናገራሉ።

በዚህም መዝገቡ ከፌዴራል ፍርድ ቤት ወደ ኦሮሚያ ስር ፍርድ ቤት ተመልሶ ጉዳዩ እንዲታይ ተደርጎ እንደነበርም ያስታውሳሉ።ነገር ግን በስተመጨረሻ ለግለሰቦቹ ውሳኔ ተላልፏል።ይግባኝም አያስቀርብም ተብሎ ተከልክሏል።ይህም ያለአግባብ 28 ዓመት ሙሉ ቤተክርስቲያኒቱ ይዛ የቆየችው ቦታ እንዲወሰድባት አድርጓል።ድርጊቱ የተፈፀመው ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ነው።ያ ሁሉ ንብረት ሲወድምም አፍርሳችሁ አንሱ ያለ አልነበረም።

የቤተክርስቲያኑ ንብረት የሕዝብ በመሆኑ የአገር ንብረት ነው።ይሁን እንጂ ይህን ባለማጤን ያለአግባብ ንብረቶች ተወስደዋል ይላሉ።በቤተክርስቲያኑ 2 ሺህ 800 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ካቴድራል ሕንፃ ቢጀመርም የቤተልሔም መስሪያ እንኳ እንደሌለው ይገልፃሉ።በመሆኑም ችግሩ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ መፍትሔ ብለው የወሰዱት ጉዳዩን በሽምግልና መጠየቅ ነው።

በሽምግልው ቢያንስ ለቤተልሔም መሥሪያ እንኳ ቢገኝ በሚል ድርድር እየተደረገ እንደሆነ የሚናገሩት አስተዳዳሪው፤ ድርድሩ ገና እንደሆነ ይገልፃሉ።ምክንያቱ ደግሞ በመጨረሻ በሽምግልናው ቀጠሮ ግለሰቦቹ ሊገኙ አለመቻላቸው እንደሆነ ነው የሚናገሩት።ቦታው 28 ዓመት ቤተክርስቲያኒቱ ይዛ የቆየችው ይዞታ ሲሆን፤ በይርጋ እንኳ 10 ዓመት ካለፈ በኋላ የሚጠይቅን አካል ይርጋ ያግደዋል የሚል ሕግ አለና ይህንንም ጉዳይ መንግሥት ሊያየው ይገባል ይላሉ።

በጠራራ ፀሐይ የቤተክርስቲያን ንብረት በመወሰዱም ሕዝቡ በሁኔታው ጥሩ ስሜት ላይ ባለመሆኑ ቤተክርስቲያኒቱ እያረጋጋች ነው።ሕግና መንግሥት ያለበት አገር በመሆኑም የቤተክርስቲያኒቷንና የሕዝበ ክርስቲያኑን ግፍ መንግሥት እንዲመለከተው በማለት ይጠይቃሉ።

ሰነዶች

ቤተክርስቲያኒቷን አስመልክቶ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የተፃፉ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችና የፍርድ ሂደቶችን የሚያመላክቱ የመዝገብ ግልባጮችን መመልከት ችለናል።ከእነዚህ መካከል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ለአዲስ አበባ አስተዳደር አካባቢ ጽሕፈት ቤት ሰኔ 7 ቀን 1983 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር 999/229/83 የላከው ደብዳቤ ይገኝበታል።

በደብዳቤው በሥጋ ሜዳ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር የሚኖሩ ምዕመናን በቤት (በጢስ) 640 በላይ የሆኑና በአካባቢው ከ25 ሺህ በላይ የሚሆኑ የጦር ጉዳተኞች የቀበሌ ገበሬ ማሕበር ማስተናገጃ ተቋቁሞላቸው የሚገኙ ሲሆን፤ በአቅራቢያቸው ቤተክርስቲያን እንደሌላቸው ያስነብባል።በዚህም ሰው ሕይወቱ ሲያልፍ ሥርዓተ ቀብር ማከናወኛ፣ ልጅ ሲወልዱ ክርስትና ለማስነሳትና ትምህርተ ወንጌል ለማግኘት፣ የቤተክርስቲያንም ሆነ የዘመናዊ ትምህርት ቤት በአካባቢው ባለመኖሩ ዕድሜያቸው ከአራት እስከ ሰባት የሚደርሱ ልጆች ርቀው ሄደው ከዕውቀት ገበታ ለመቋደስ አቅማቸው ስለማይፈቅድ ብሎም በአባባቢው ቤተክርስቲያን ባለመኖሩ በወቅቱ የሚያጋጥመውንና በቀጣይም ሊያጋጥም የሚችለውን ችግር በመዘርዘር መጠየቁን ያትታል።

ለቤተክርስቲያኑ መትከያ ይሆን ዘንድም በሥጋ ሜዳ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ክልል ውስጥ ልዩ ስሙ ኤጀርሳ ቀንጨራ ወይንም በአማርኛ ስያሜው ያረጀ ወይራ የተባለው ቦታ ከማንም ይዞታ ነፃ የሆነ 50 ሺህ ሜትር ካሬ ወይንም አምስት ሔክታር ስለሚገኝ ለቤተክርስቲያን፣ ለትምህርት ቤት እንዲሁም ሌሎች ቤተክርስቲያኑን ተከትለው መንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ተቋሞችን ለማቋቋም የሚያስችልና በዙሪያውም ለመካነ መቃብር የሚሆን ሰፊ ቦታ ስላለ ይኸው ቦታ እንዲፈቀድላቸው የአካባቢው ተወካዮች ጥር 26 ቀን 1983 ዓ.ም መጠየቃቸውን በደብዳቤው ይነበባል።

ደብዳቤው እንደሚያሳየው ጉዳዩ ሰፊ ጥናት ተደርጎበታል።በቀረበው ጥናትም የምዕመና ጥያቄ ትክክለኛና የቤተክርስቲያኗ መተከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የተጠቀሰው ቦታ እንዲጠየቅና ቦታው ሲፈቀድ ቤተክርስቲያኒቷ እንድትተከል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መፍቀዳቸውን ያስነብባል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር አካባቢ ጽሕፈት ቤት በመዝገብ ቁጥር አአአስ1/62/150 በቀን 20/12/1983 ዓ.ም በአዲስ አበባ አስተዳደር አካባቢ ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የተፃፈው ደብዳቤ ሌላው የተመለከትነው ሰነድ ነው።ደብዳቤው የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ሰኔ 7 ቀን 1983 ዓ.ም በቁጥር 999/229/83 የቤተክርስቲያንና የመቃብር ቦታን በሚመለከት ጥያቄ መቅረቡን ያሳያል።

ቦታው ከከተማ ክልል ውጪ በመሆኑ ለጥያቄያቸው በመስሪያቤቱ በኩል ምላሽ እንዲሰጥም ይጠይቃል።ተያይዞም ቤተክርስቲያኑን አስመልክቶ በተለያዩ ወቅቶች ተቋማት የተፃፃፉት የደብዳቤ ግልባጮች ከሰነዶች መካከል የሚገኙ ሲሆን፤ የፍርድ ሒደቶችን የሚያመላክቱ የመዝገብ ግልባጮችንም ተመልክተናል።

የፍርድ ሒደት

ጉዳዩን አስመልክቶ በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች የተወሰኑ የውሳኔ መዝገብ ግልባጮች በሰነዶች ውስጥ የተመለከትን ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል በሰ/መ/ቁጥር 141638 ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የነበረው መዝገብ አንዱ ነው።በዚህ መዝገብ ላይ አመልካች የታጠቅ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሲሆን፤ ተጠሪዎች ወይንም ተከሳሾች ደግሞ አቶ ጫላ ካሳን ጨምሮ ስድስት የቤተሰብ አባላት መሆናቸው ሰፍሯል።በመዝገብ ግልባጩ እንደተመላከተው ለክርክሩ መነሻ የሆነው የይዞታ ወሰን ጉዳይ የተጀመረው በወልመራ ወረዳ ፍርድ ቤት የቡራዩ ምድብ ችሎት ነው።

በወረዳው ፍርድ ቤት እነ አቶ ጫላ በቤተክርስቲያኑ ላይ ክስ አቅርበው እንደነበርም ያትታል።በዚህም ሟች ወይዘሮ ጫልቱ ነቢ በቡራዩ ከተማ ገፈርሣ ኖኖ ቀበሌ ውስጥ ሲኖሩ ቆይተው በ03/13/1999 ዓ.ም በሞት ከዚህ ዓለም የተለዩ ሲሆን፤ ወራሽነታቸውን አረጋግጠውና ውርስ ተጣርቶ በመዝገብ ቁጥር 60191 በቀን 06/11/2007 ዓ.ም በተጠቀሰው ቀበሌና በክሱ ላይ አዋሳኙ የተገለፀው 10 ቀርጥ ይዞታ ተረጋግጧል።

ሆኖም ቤተክርስቲያኑ በግምት 4 ሺህ ሜትር ካሬ የሚሆን መሬት በ25/07/2006 ዓ.ም በሽቦ ከማጠሩም በላይ ከአጥሩ ውጪ ያለውን እንዳይከፋፈሉ መከልከሉን በመግለጽ፤ አጥሩን በማፍረስ ይዞታቸው እንዲለቀቅላቸው መጠየቃቸውን ያትታል።ቤተክርስቲያኑም ይዞታውን ለ24 ዓመታት ስታስተዳድረው እንደነበርና ሟች በሕይወት እያሉ በመሬቱ ሳይጠቀሙ ከሳሾች ሊወርሱ ስለማይችሉ ክሱ ውድቅ ይደረግ በሚል ክርክር ማድረጓን ያሳያል።

የወልመራ ወረዳ ፍርድ ቤት የግራ ቀኑን ክርክርና ማስረጃ ሰምቶና መርምሮ ክርክር ያስነሳውን ቦታ ቤተክርስቲያኒቷ ይዛ ስለመቆየቷም ሆነ የተሰጣት መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላቀረበችም ማለቱን ሰነዱ ያመላክታል።በተቃራኒው ግለሰቦቹ ክርክር ያስነሳው ይዞታ የአውራሻቸው መሆኑንና በአውራሻቸው ሲገበርበት መቆየቱን ያረጋገጡ እንዲሁም ቤተክርስቲያኗ ለአምልኮ መሬት ጠይቃ የወሰደችው እንደሌለ የተረጋገጠ በመሆኑ፣ በዕምነት ሥም የግለሰብን መሬት እየገፉ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ በውርስ ያገኙት ስፋቱ 10 ቀርጥ መሬት ውስጥ አጥር በማጠር አራት ሺህ ሜትር ካሬ የያዘችውን፣ ያላትን ንብረት በማንሳት ለግለሰቦቹ በሕግ አግባብ እንድትለቅ በማለት ይወስናል።

በውሳኔው ቅር የተሰኘችው ቤተክርስቲያኗም በፊንፊኔ ዙሪ ለኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ታቀርባለች። ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ የወረዳውን ውሳኔ ያፀናዋል።በመቀጠልም ቤተክርስቲያኗ ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ብታቀርብም ተቀባይነት አላገኘም።

በሰ/መ/ቁጥር 141638 ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የነበረው የመዝገብ ግልባጭ እንደሚያመለክተው በየደረጃው የነበረውን የፍርድ ሒደት በማብራራት በወልመራ ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 61424 ግንቦት 19 ቀን 2008 ዓ.ም ተሰጥቶ፣ በፊንፊኔ ዙሪያ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 27202 ሚያዝያ 13 ቀን 2009 ዓ.ም በተሰጠ ውሳኔና በኦሮሚያ ክልል ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 263231 ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም በተሰጠ ትዕዛዝ የፀናውን ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348(1) መሠረት ይሽረዋል።በተጨማሪም ጉዳዩ ተጣርቶ ተገቢውን ይወስን ዘንድ ጉዳዩ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 343(1) መሠረት ለፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይመለስ በሚል ጉዳዩን ወደ ሥር ፍርድ ቤት ዳግም ይመልሰዋል።

ጉዳዩም በዚህ መሠረት ሲታይ ይቆይና ቀድሞ የተወሰነው ውሳኔ ይወሰናል።በኋላም ዳግም ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይደርሳል።በዚህም በቀን 5/11/2011 ዓ.ም አመልካች ቤተክርስቲያኒቷ ተጠሪዎች ደግሞ እነ አቶ ጫላ ሆነው ይቀርባሉ።በዚህ መዝገብ ግልባጭ እንደሚነበበው፤ ቤተክርስቲያኒቷ በቀን 04/11/2011 ዓ.ም የሰበር አቤቱታው ታይቶ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 27202 በቀን 14/10/2011 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ አፈፃፀሙ ታግዶ እንዲቆይ ትጠይቃለች።

መዝገቡም፤ አንድ ጉዳይ ለሰበር ችሎት ሊቀርብ የሚችለው ቅሬታ የቀረበበት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተገኘበት እንደሆነ ብቻና ዕግድ ትዕዛዝ የሚሰጠው ተከራካሪ ወገኖች ባሉበት ነገሩ እስኪሰማ ድረስ መሆኑን በመግለጽ፤ የሕግ ስህተት ተፈጽሞባቸዋል የተባሉትን ውሳኔዎች አግባብ ካለው ሕግና በየፍርድ ቤቱ ከተደረጉት ክርክሮች ጋር በማገናዘብ እንደመረመረው ሰነዱ ያስነብባል።በዚህም በሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች መሠረታዊ የሕግ ስህተት ሠርቷል ለማለት ባለመቻሉ የቀረበውን የዕግድ ጥያቄ አልተቀበለውም በማለት መዝጋቱን መዝገቡ ያሳያል።

የፍርድ ባለመብቶች

በቀድሞ አጠራሩ ታጠቅ ሥጋ ሜዳ በአሁኑ ገፈርሣ ኖኖ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር በአሸዋ ሜዳ ታጠቅ ቅዱስ ገብርኤል ትውልድና ዕድገታቸው የሆነው አቶ ሲሣይ ዘውገ የፍርድ ባለመብት የሆነው ቤተሰብ ተወካይ ናቸው።የጉዳዩ መነሻ ቤተክርስቲያኒቷ በ2006 ዓ.ም በደቦ አጥር ለማሳጠር በተነሳችበት ወቅት ነው ሲሉም ያስታውሳሉ።በግፍ አራት ሺህ ሜትር ካሬ ይዞታ አጥራ ይዛባቸው እንደነበር ነው የሚያስረዱት።

እንደ አቶ ሲሣይ ገለፃ፤ ለቤተክርስቲያኒቷ መሠረት ከሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከልም አያታቸው ወይዘሮ ጫልቱ ነቢ አንዷ ናቸው።አያታቸው በ1999 ዓ.ም ማረፋቸውንና በ2006 ዓ.ም ድረስም ቦታውን ሲገብሩበት ብሎም ሲጠቀሙበት እንደነበር ይናገራሉ።ሱቆቹም እገዳ ወጥቶባቸው ክርክር በሚደረግበት ወቅት የተሠሩ ሱቆች ናቸው ይላሉ።ቤተሰቡ ውስጥ ብዙዎቹ አቅመ ደካሞች በመሆናቸው የሥነልቦና ጫና ደርሶባቸው የተነጠቀ መሬት እንደሆነም ነው የሚያስረዱት።

ቤተክርስቲያኒቱ ከይዞታዋ ውጪ የሆነውን የአያታቸውን ውርስ ቦታ በደቦ ስታጥርም ወደ ሕግ አቤት ለማለት ማቅናትን ምርጫቸው ያደርጋሉ።ዕውነታው አዲስ አበባ ቦታውን ያላስተዳደረው ቢሆንም በክርክሩ ግን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያስተዳድረው እንደነበርና የአየር ካርታ እንዳለ ቤተክርስቲያኒቱ ታቀርባለች።ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃዎችን በጥልቀት ይመረምራል።በዚህም አዲስ አበባ እንዳላስተዳደረውና በመረጃ ቋት ውስጥ እንደማይገኝም ከሚመለከታቸው ቢሮዎች ይፃፋል።

ፍርድ ቤቱ፤ ሕጋዊ ሰውነት ባለው መንግሥታዊ አካል የአየር ካርታ ከተሰጠ እንዲያጣራ፣ ቦታውን አዲስ አበባ ያስተዳድረው ከነበረም ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ የአገር ሽማግሌዎች በቃለ መሐላ እንዲያረጋግጡና ለአፈፃፀም እንዳያስቸግር በችካል ይለይ የሚል ትዕዛዝ መሰጠቱን አቶ ሲሣይ ይገልፃሉ።ይህ ሲፈፀምም ግራና ቀኝ በተገኙበት ችካል መቸከሉንና የአገር ሽማግሌዎች ስለ ጉዳዩ የሚያውቁትን በቃለ መሐላ የምስክርነት ቃላቸውን ይሰጣሉ።

ወይዘሮ ጫልቱ በሕይወት በነበሩበትም ሆነ በአሁኑ ወቅት ክርክር ይደረግበት የነበረው ይዞታ ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት ባይኖርም ገብስ ዘርተው አርሰው ሲጠቀሙበትና ባሕር ዛፍ ሸጠው ይገለገሉበት የነበረ ይዞታ እንደሆነ ይናገራሉ።በ2011 ዓ.ም ብቻ እንጂ ሲታረስ የነበረ ይዞታም ነው ይላሉ።በግቢው ውስጥ ያሉት ወይራዎች ሁሉ የሚገኙበት ይዞታ የራሳቸው እንደነበርና ወደውና ፈቅደው ለቤተክርስቲያኒቷ እንደሰጡም አክለው ያብራራሉ።

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በአሁኑ ወቅት ውሳኔ የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሲሣይ፤ በዕምነቱ ሥም እየተንቀሳቀሱ ግማሹ በንሰሃ አባት በመምጣት ጉዳዩን እንደሚያቀዘቅዙትና እንደሚስተካከል ይነግራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።አባቶችንና የአካባቢውን ሕብረተሰብ በማክበርም ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ይቆያሉ።የሚበሉትና የሚጠጡት የሌላቸው አቅመ ደካማ የቤተሰቡ አባላትም በቦታው መኖር እየቻሉ መብታቸው በግፍ በመነጠቁ ለረጅም ዓመታት ለእንግልት ተዳርገዋል።

በስተመጨረሻም ጉዳዩ እልባት አግኝቶ ፍትሕ ማግኘታቸው ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ይናገራሉ።ይሁን እንጂ አንዳንድ ግለሰቦች ዕምነቱን ተገን በማድረግ መንግሥትና ሕዝብን ለማጋጨት እየጣሩ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አቶ ሲሣይ ያስረዳሉ።

በኦሮሚያና በፌዴራል ማንኛውም ፍርድ ቤቶች ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ ቱሊ ባይሣ የቤተሰቡ ሕጋዊ ጠበቃ ሆነው ለረጅም ዓመታት ጉዳዩን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ይገልፃሉ።ለረጅም ዓመታት በነበረው የፍርድ ቤት ክርክር ከሳሽ ጫላ ካሳን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች ናቸው።ግለሰቦቹ የወይዘሮ ጫልቱ ወራሾች ሲሆኑ፤ አራት ልጆችና ሁለት የልጅ ልጆች መሆናቸውንም ይናገራሉ።

ቤተክርስቲያኑ ሲመሰረት ወይዘሮ ጫልቱ የዕምነቱ ተከታይ ስለነበሩ እርሳቸውን ጨምሮ ሦስት በመሆን 1980ዎቹ መጀመሪያ ቤተክርስቲያኑ እንደሚሰረት ያደርጋሉ።በወቅቱ በአካባቢው ቤተክርስቲያን ስላልነበር ሦስቱ ግለሰቦች ቦታ አዋጥተው ቤተክርስቲያኒቷን ያቋቁማሉ።ቤተክርስቲያኒቷ የራሷን ይዞታ አጥራ ይዛም ትቆያለች።ወይዘሮ ጫልቱ በወቅቱ ቦታ ሲሰጡ በአሁኑ ወቅት ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቦታ ግን ቆርሰው ማስቀረታቸውን ነው ጠበቃው የሚያስረዱት።

በአካባቢው የሚገኙ በርካታ ነዋሪዎችም ከወይዘሮ ጫልቱ የገዙት ይዞታ ላይ እንደሚኖሩ ይናገራሉ።ክርክር ሲደረግ የነበረበትን ቦታም ወይዘሮ ጫልቱ መኖሪያ ቤት ስለነበራቸው ለባሕር ዛፍና ለእርሻ ይጠቀሙበት ነበር።ይህንንም ምስክሮች ፍርድ ቤት ቀርበው አስረድተዋል።

ከ28/7/2006 ዓ.ም ላይ ቤተክርስቲያኒቱ አጠቃላይ ስፋቱ ሁለት ሔክታር ከሆነው መሬት ላይ አራት ሺህ የሚሆነውን አጥራ መያዟ ለክርክሩ መነሻ እንደሆነ ነው የሚገልጹት።ሌላውን ደግሞ የቤተሰቡ አባላት እንዳይጠቀሙበት ሰበካ ጉባዔው በጉልበት ሰዎችን በማሰማራት ያስፈራሯቸዋል።በዚህ መነሻም ጉዳዩን በፍርድ ለመያዝ ይወሰናል።ፍርድ ቤት ሲቀርቡም ምላሻቸው የነበረው ቦታው የወይዘሮ ጫልቱ መሆኑንና በስጦታ እንደሰጡ በክርክሩ መቅረቡን ያስታውሳሉ።

በመቀጠልም የቡራዩ ከተማ ለይዞታው ካርታና ፕላን እንደሰጠና እንዲቀርብ ቢገልጹም በተደረገው የማጥራት ተግባር ግን በቦታው ላይ ካርታና ፕላን አለመሰጠቱ ከተማ መስተዳድሩ ምላሹን እንደሰጠ አቶ ቱሊ ይናገራሉ።በዚህም ቦታው በኮሚቴ እንዲጣራ ይወሰናል።የሚመለከታቸው አካላት ተውጣጥተው የተካተቱበት ኮሚቴም፣ ቦታው ከድሮ ጀምሮ የወይዘሮ ጫልቱ እንደሆነ፣ እርሳቸው ካረፉበት 1999 ዓ.ም እስከ 2006 ዓ.ም ቤተሰቦቻቸው ይጠቀሙበት እንደነበር፣ ከዚያ በኋላም ቤተክርስቲያኒቷ እንደያዘችውና በቦታው ላይ ምንም ዓይነት ማስረጃ እንደሌለ ለፍርድ ቤት ያቀርባል።

ጠበቃው፤ የወረዳ ፍርድ ቤት በ19/9/2008 ዓ.ም ቦታው የግለሰቦቹ በመሆኑ ቤተክርስቲያኒቷ ልትለቅ እንደሚገባ ውሳኔ ማሳረፉንም ያስታውሳሉ።ውሳኔውም እስከ ኦሮሚያ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ይፀናል።ይሁን እንጂ በውሳኔው ቅር የተሰኘችው ቤተክርስቲያኗ ለፌዴራል ሰበር የክስ ጭብጡን በመቀየር ቦታውን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ በ1983 ዓ.ም ካርታ ተሰጥቷል በማለት እንዳቀረበች ይናገራሉ።

ቦታው የወይዘሮ ጫልቱ ሳይሆን የመንግሥት ቦታ ነበር በማለትም ይከራከራሉ።የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎቱም በኦሮሚያ ልዩ ዞን ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተላለፉትን ውሳኔዎች በመሻር የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያጣራ ይመልሰዋል።

የቤተክርስቲያኒቷ ዋነኛ መከራከሪያ የነበረውም በ1983 ዓ.ም ከአዲስ አበባ መስተዳድር ካርታ ተሰጥቷል የሚል ነበር።ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የፍርድ ባለመብቶች የሆኑት ተከራካሪ ግለሰቦች ያቀረቡት ማስረጃ የአየር ካርታ እንደሆነ በመግለጽ ይከራከራሉ።አቶ ቱሊ አያይዘው፤ አየር ካርታ ባለቤትነትን ማረጋገጫ ሰነድ ሊሆን አይችልም ይላሉ።ከዚህ ባሻገር አካባቢው ገጠር ቦታ የነበረና 1983 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ ኦሮሚያ ስር አልነበረም። በችሎቶቹም ላይ አዲስ አበባ እዚህ ቦታ ድረስ የሚደርስ አስተዳደር እንዳልነበረው ክርክር ይደረጋል።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመጣመር በ1983 ቦታውን ማን ያስተዳድረው እንደነበር እንዲያጣራ ይወስናል።በስተመጨረሻም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕላን ኢንስቲትዩት ማስረጃዎችን በመመልከት አዲስ አበባ ቦታውን እንዳላስተዳደረ ለፍርድ ቤቱ ማስረጃ ይልካል።በመቀጠልም ከ1980ዎቹ እስከ 1990ዎቹ ዓ.ም ድረስ አካባቢውን ያስተዳድሩ የነበሩ ግለሰብ በሕይወት ያሉ በመሆኑ በአካል ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ቤተክርስቲያኒቷ መጠየቋን ጠበቃው ይናገራሉ።

አቶ ጫላ ሁንዴ የተባሉ ግለሰብ ቀርበውም ቦታው የወይዘሮ ጫልቱ ሳይሆን የሕዝብና የመንግሥት ነው በማለት መመስከራቸውን አቶ ቱሊ ያስታውሳሉ።ባዶ ቦታ ለቤተክርስቲያን መሰጠቱንም ይመሰክራሉ።አዲስ አበባ ግን ቦታው ላይ ደርሶ እንዳላስተዳደረ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት የምስክርነት ቃላቸው ይገልፃሉ።ፍርድ ቤቱም ቦታው የቤተክርስቲያኒቷ ሳይሆን ለግለሰቦቹ ነው የሚገባው በማለት ይወስናል።ውሳኔውም እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ ግለሰቦቹን የፍርድ ባለቤት እንደሆኑ ያረጋግጣል።ይሁን እንጂ ይህ ያልተዋጠላቸው ግለሰቦች ውሳኔውን ባለመቀበልም ወደተለያዩ አካላት ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።

ጠበቃው፤ በ2006 ዓ.ም ቤተክርስቲያኒቷ ያለአግባብ ቦታውን ስትይዝ ምንም ዓይነት ግንባታ እንዳይካሄድ እግድ ቢወጣም ሱቆቹን ግን የተለያዩ ሰዎችን በመጥራት ያስገነቡትና ከቤተክርስቲያኒቷ ጋር ውል እንዲገባ ሲያደርጉ መቆየታቸውን በመግለጽ፤ በአሁኑ ወቅት ይህንን አስመልክቶ የሚቀርቡ ቅሬታዎች መነሻቸው ትክክል አለመሆኑን ይገልፃሉ።ለአብነትም በቦታው ላይ ክምር አጣና ባለቤት የሆነው ግለሰብ ለረጅም ዓመታት ለቤተክርስቲያኒቷ ኪራይ ሲከፍል እንደነበር ያስታውሳሉ።

ውሉን አፍርሶ ከግለሰቦቹ ጋር ውል እንዲያስር ቢጠየቅም በክርክሩ ካላሸነፉ በቀር ከቤተክርስቲያኒቷ ጋር የገባውን ውል ሊያፈርስ እንደማይችል በመግለጽ፤ ኪራዩን መክፈሉን እንደቀጠለ ጠበቃው ይናገራሉ።በዚህም ይህንንም ቤተክርስቲያኒቷን ለመጠየቅ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ነው የሚያስረዱት።

በ5/11/2011 ዓ.ም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩ እልባት እንዳገኘ የሚጠቁሙት ጠበቃው፣ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ላይ ክርክሩ እየተደረገ የቤተክርስቲያኗ ክርክር ቀጥታ ስላልነበርና አሰልቺ በመሆኑ አንድ ፋይል ላይ ብቻ ለ27 ጊዜ ለአንድ ዓመት ከሁለት ወር መመላለሳቸው ይናገራሉ።በዚህ መካከል ከእነ አቶ ጫላ ምስክር መካከል አንዱ በጉዳዩ ዕርቅ እንዲወርድና በሽምግልና እንዲያልቅ ይጠይቃል።

ይህንንም በወቅቱ ተቀብለው በድርድር እንዲልቅ ፍላጎታቸውን ያሳያሉ።ሆኖም ግን ሽምግልናውን በመምረጥ ቢሄዱም ‹‹እንደሚሸነፉ አውቀው እየለመኑ ነው›› በሚል ቤተክርስቲያኒቷን ወግነው የሚከራከሩ ግለሰቦች በማስነገራቸው ሽምግልናውን በመተው በድጋሚ ወደ ክርክር ይገባሉ።በዚህም አራት የፍርድ ቤት ቀጠሮዎች አምልጠው ከሦስት ወራት በኋላ ዳግም ወደ ክርክር ይገቡና የፍርድ ባለ መብቶች ሆነው በተያዘው ዓመት ከተላለፈው የመጨረሻ ውሳኔ በኋላ ቤተክርስቲያኒቷ ዳግም ወደ ሽምግልና እንደመጣች ይናገራሉ።

ቤተልሔም የሚሠራበት ቦታ ማጣቷን ቤተክርስቲያኒቷ በመግለጧ ሁሉም ሕይወታቸው ሲያልፍ የዘላቂ ማረፊያ ስፍራቸው በዚያው በመሆኑ ምንም እንኳ በፍርዱ ክርክር ሲደረግ የነበረበት ይዞታ ቢፈረድላቸውም በሽምግልና ይታይ የሚለውን ሐሳብ የፍርድ ባለመብቶች ይቀበላሉ።በዚህም ቤተክርስቲያኒቱ የሁሉም ሰው መገልገያ በመሆኗ በክርክር ካሸነፉበትና ረትተው ከታጠረው ሁለት ሔክታር መሬት ላይ 3 ሺህ 600 ካሬ ለቤተክርስቲያኗ ይሰጥ በሚል ቤተሰቡ ቢወስንም ‹‹ትንሽ ናት፤ ዓይናችን አልሞላችም›› በሚል እንደተዉት ይናገራሉ።

ይህንንም የቤተሰቡ አባላት ለሠላም ሲሉ ተቀብለው ከቤተክርስቲያኒቷ እንዲሁም ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር ላለመጋጨት በድጋሚ ለመነጋገር ቢወስኑም ቤተክርስቲያኒቱ ግን በዚህ ሽምግልና በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ ቦታዎች ቅሬታዋን እያስገባች ነው።

የፍርድ ባለመብት የሆኑት የቤተሰቡ አባላት ቤተክርስቲያኒቱን ወክለው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ክርክራቸውን ሲጨርሱ ሽምግልናው ሊደረግ ይችላል እንጂ እንደማይሆን ከውሳኔ ደርሰዋል።አንዲት ስንዝር መሬት የቤተክርስቲያን አይደለም የግለሰብ እንዲወሰድ አንፈቅድም የሚሉት አቶ ቱሊ፤ ድርጊቱን እየፈፀሙ የሚገኙት ግለሰቦች እንጂ ቤተክርስቲያኗ አይደለችም ይላሉ።ቤተልሔም መሥሪያ ከሆነ አስፋልት ድረስ ቦታ ለምን አስፈለገ? ሲሉም ይጠይቃሉ።አያይዘውም ቦታው ከመንገድ ዳር በመሆኑ ለንግድ ነው የሚፈለገው በማለት ይጠቁማሉ።

በአሁኑ ወቅት በወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 57745 ላይ በ14 ግለሰቦች ላይ ቤተክርስቲያኒቱ ክስ መክፈቷን የሚናገሩት ጠበቃው፤ የክሱም ጭብጥ ግለሰቦቹ የቤተክርስቲያኒቱ ሠራተኞች የነበሩ መሆኑን በመጥቀስ ቦታውን ጎጆ ቀልሰው እንዲኖሩበት ተሰጥቷቸው እንደነበርና እንዲያስረክቡ የሚል ነው።በክሱ ውስጥ ካሉት ደግሞ አራቱ ሰዎች በክርክሩ እልባት በተሰጠው ቦታ ላይ የሚገኙ ናቸው።

ቤተክርስቲያኒቷ በተረታችበት ይዞታ ላይ በእነዚህ ግለሰቦች ላይ ክስ መክፈት ለምን አስፈለጋት? የሚል ጥያቄን የሚያጭር ነው የሚሉት ጠበቃው፤ ጉዳዩ በሚታይበት በወረዳ ፍርድ ቤት በመቅረብ በክርክሩ ላይ ጣልቃ ለመግባት መጠየቃቸውን ይናገራሉ።ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ አይመለከታችሁም እንዳላቸው ይገልፃሉ።ለዚህም ይግባኝ ጠይቀው እየተከታተሉ ይገኛሉ።

‹‹የቤተክርስቲያኒቷ ተንኮል ከፍተኛ በመሆኑ ፍርድ በተሰጠበትና ለግለሰቦች በተወሰነ ይዞታ ላይ ሌሎች ግለሰቦችን ከስሶ ክርክር መቀጠል ማለት ምን ማለት ነው?›› በማለትም ይጠይቃሉ።አራቱ ግለሰቦች ሱቆቹ ሲፈርሱ በራሳቸው ጊዜ ቤቱን አንስተው የለቀቁ ናቸው።ነገር ግን ችግሩን የሚፈጥሩ ግለሰቦች ቤተክርስቲያኒቱን ተገን በማድረግ የመሬት መቀራመትን የሚያካሂዱ ግለሰቦች በመሆናቸው የሚመለከተው አካል ሊያውቀው ይገባል ይላሉ።

ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁት

አቶ ጫላ ሁንዴ ነዋሪነታቸው በገፈርሳ ኖኖ ቀበሌ ነው።ቀደም ሲል 1984 ዓ.ም የኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣን እንደያዘ በቀበሌው አስተዳዳሪነት መሥራታቸውንና በአካባቢው ከ60 ዓመታት በላይ እንደኖሩ ይናገራሉ።በወቅቱ የአካባቢው ሕብረተሰብ ቤተክርስቲያን ባለመኖሩ ዕምነቱን የሚያካሂድበት ስፍራ ስላልነበር በ1983 ዓ.ም ጀምሮ ጥያቄው ተቀባይነት ማግኘት ችሏል።

በተሰጠው ፈቃድም አካባቢው በሙሉ ተቃኝቶ ወደሚመለከተው አካል በ1984 ዓ.ም ደብዳቤ መፃፋቸውንና ሳይት ፕላን እንደተነሳ ያስታውሳሉ።ታቦቱም በ1984 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ይገባል።1996 ዓ.ም ደግሞ ከአምቦ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ሲሠራ የጉቶ ካሳ ለቤተክርስቲያኑ እንደተከፈለም ይገልፃሉ።

በሥራ ላይ በቆዩባቸው ከ1984 ዓ.ም እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ ቦታው ዙሪያው በቤተክርስቲያኑ ስር ነበር የሚሉት አቶ ጫላ፤ ሱቆች ተሠርተው ሙሉ በሙሉ ቤተክርስቲያኑ ሲጠቀምበት የነበረ ይዞታም እንደነበር ያብራራሉ።ደመራ ሲደመርም ሆነ ጥምቀተ ባሕሩ የሚያርፈው በዚሁ ቦታ ላይ የነበረ ሲሆን፤ የታቦት ማረፊያ እንደሆነም ይናገራሉ።በአሁኑ ወቅት ግን በምን ምክንያት እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ ሱቆቹ ፈርሰው በግለሰብ እጅ ገብቶ አጥር ታጥሯል።በፍርድ ቤት የተሰጠው ምስክርነትም ውድቅ ተደርጎ የሚያሳዝን ውሳኔ በመወሰኑ መንግሥት ሊያውቀውና መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል ባይ ናቸው።

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ቡራዩ ከተማ መስተዳድር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ባለሞያ አቶ ብርሃኑ በየነ፤ የአካባቢው ተወላጅና አስተዳዳሪም እንደነበሩ ይናገራሉ።መሬቱ ቤተክርስትያኒቱ ስትቋቋም ጀምሮ በቤተክርስቲያኒቷ ስር እንደነበር ይገልፃሉ።በስፍራው ከፊል ባህር ዛፍ የነበረ ሲሆን፤ ይህንን በመሸጥ ስትጠቀም የነበረችው ቤተክርስቲያኒቷ ናት።ባለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት መሬቱ በቤተክርስቲያኒቷ ስር የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ግለሰቦች ባነሱት የባለቤትነት ጥያቄ ተፈርዶላቸዋል።

በጂአይኤስ ላይም የቤተክርስቲያኒቷ አመራሮች ዞረው አስመዝግበዋል።በወቅቱም ቅሬታ ሲነሳ አልነበረም።ይህ ማስረጃም የሚያመላክተው ይዞታው የቤተክርስቲያኑ እንደሆነ ነው ይላሉ።በወቅቱ ይዞታውን ቤተክርስቲያኑ ሲያስለካም የቀረበ ቅሬታ አልነበረም።የቤተክርስቲያኑ ሰበካ ጉባዔ ተወካዮች ያስለኩት ግለሰቦቹ በአሁኑ ወቅት ያጠሩት መሬት ጨምሮ ነበር።በዚህም አጠቃላይ ስፋቱ የተለካው 54 ሺህ ሜትር ካሬ አካባቢ ነበር ይገልፃሉ።

የሚመለከተው አካል

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ቡራዩ ከተማ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡን ምላሽ፤ ቤተክርስቲያኒቱ ካሉት ስድስት ቀበሌዎች መካከል በገፈርሣ ኖኖ ቀበሌ ትገኛለች።በአካባቢው ላይ የታጠቅ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በማስተር ፕላኑ መሠረት እንዳለ ይታወቃል።ይሁን እንጂ በቢሮው በኩል ይዞታው ተከልሎ የተሰጠ መረጃ የለም።ድንበሩም አይታወቅም ይላሉ።እንደ ቤተ ዕምነት ግን ቦታው ይታወቃል።በመሆኑም በቀጣይ ማሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላት ካርታና ፕላን መውሰድ እንደሚቻልም ያመላክታሉ።

በኦሮሚያ የመሬት ቆጠራና ምዝገባ (ኢንቨንተሪ) ተጀምሮ ነበር።በዚህም ከኦሮሚያ በተወሰደው የበረራ ፎቶ ለከተማውና ለፕላኑ የሚያስፈልገውን ይጠቀማሉ።ነገር ግን ለቢሮ የሚሆን መረጃ ቢያዝም ሕጋዊ ተደርጎ ለግለሰቦችና ለድርጅቶች የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ግን አልደረሰም።በ2006 የበረራ ፎቶ ወይም የጂአይኤስ መረጃዎች ተይዘዋል የሚሉት አቶ አለማየሁ፤ ጂአይኤስ ላይ የቤተክርስቲያኑ ምስልና አካባቢው ይታያል።ነገር ግን በቤተክርስቲያኑ ሥም አልተመዘገበም።በወቅቱ የመሬት መረጃ ሲቆጠር ቦታው የገብርኤል ቤተክርስቲያን ነው ተብሎ እንዳልተመዘገበም ይገልፃሉ።

ቤተክርስቲያኑ ቅሬታ ካለውም ጽሕፈት ቤቱ ድረስ በግንባር በመቅረብ ቢያናግሩ ለችግሮች መፍቻ መፍትሔ እንደሚፈለግ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ያረጋግጣሉ።ለቀጣይም መፍትሔ እንዲሆን መረጃዎችን በማምጣት በከተማው መመዘኛ መሠረት ለዕምነት ቦታ የሚሰጠውን ቦታ ቢወስዱ የተሻለ እንደሆነም ያመላክታሉ።

ምክትል ሥራ አስኪያጁ ይዞታውን አስመልክቶ በጽሕፈት ቤቱ የሚገኘው T-1806 ማሕደር እንዲወጣ ቢያስደርጉም በማቀፊያው ውስጥ ግን ሙሉ ሰነዱ ፍርድ ቤት ሄዶ እንዳልተመለሰ ከሚያሳየው ወረቀት በስተቀር ምንም ሰነድ አልተገኘም።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 / 2011

ፍዮሪ ተወልደ