ሙያውን እናክብር ለሕዝብም እንስራ!

22

 ‹‹ይገርማል ዛሬ በዚህች አገር በጋዜጠኛነት ሙያና በፖለቲካ ውስጥ እጁን ያላስገባ ማግኘት አይቻልም፤ ግን ለምን?›› እያልኩ ለጥያቄዬ መልስ ለማግኘት በሃሳብ ስማስን የጋዜጠኛነት ሙያ ትልቅ አደጋ እንደተጋረጠበት የሚጠቁም አንድ ፅሁፍ ጉግል ላይ አነበብኩ፡-

‹‹በጋዜጠኛነትና በካድሬነት ፣ በጋዜጠኛነትና በአክቲቪስትነት፣ በጋዜጠኛነትና በመድረክ አስተዋዋቂነት፣ በጋዜጠኛነትና በማስታወቂያ ሰራተኛነት፣ በጋዜጠኛነትና በስብሰባ መሪነት፣ በጋዜጠኛነትና በማህበራዊ ሚዲያ ባለሟልነት፣ በጋዜጠኛነትና በጦማሪነት፣ በጋዜጠኛነትና በፌስቡክ ተጠቃሚነት ወዘተ… መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ አልታወቀም፡፡

‹‹አንዲት ነጠላ ዜማ የለቀቀ ሁሉ ከእነ ጥላሁን ገሠሠ እኩል “አርቲስት” የሚል መጠሪያ ሲሰጠው እንዳየነው ሁሉ፤ በፌስቡክ ሁለትና ሦስት መስመር አስተያየት ጽፎ የለጠፈ ሁሉ “አክቲቪስት” አንዳንድ ጊዜም “ጸሐፊ” አለፍ ሲልም “ጋዜጠኛ”፣ ተንታኝ፣ ጦማሪ፣… የሚል ካባ እስከመደረብ የደረሰበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው፡፡ በማህበራዊ ሚዲያው ከሩብ ገጽ ያልበለጡ አስተያየቶችን በመጻፍ የታወቁ ሰዎች “ጋዜጠኛ” ተብለው በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን እስከ መቀጠር ደርሰዋል ፡፡

‹‹ በብዙዎች ዘንድ አራተኛ አእማደ መንግስት እንደሆነ የሚነገርለት ጋዜጠኛነት ደረጃው ከህግ አውጪ፣ ከህግ አስፈጻሚና ከህግ ተርጓሚ ጋር ተመጣጣኝ በመሆኑ ደረጃው ብቻ ሳይሆን ኃላፊነቱም ከፍ ያለ ነው፡፡ እናም ጋዜጠኞች አለቃቸው የሆኑትን (አድማጭ፣ተመልካችና አንባቢ) ስለሚፈሩ የሙያውን መርህና ስነ ምግባር ጠብቀው በመስራት ራሳቸውንም ሙያቸውንም ያስከብራሉ … ››ይላል፡፡

ይህ እውነታ በሁሉም ዘንድ እንደ መርህ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂው ምህዳሩን አመቻችቶልኛል በማለት ብቻ ያልተጣራውን ወሬ ሁሉ ማሰራጨትና ህዝብን በተሳሳተ መረጃ ማደናገር ለህሊናም የሚከብድ ነው፡፡ ዛሬ በአገራችን መላው ሕዝባችንን ቀስፎ ከያዘው ድህነት እንዳይላቀቅ የተቆለፈ ሰንሰለት የሆነበትን የመልካም አስተዳደር ችግር ማጋለጫ መድረክ አድርገን ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ሚዲያዎች አንዳንዶች የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎትና ስሜት ሸሽገው በሚረጩዋቸው ትንታኔዎች ሊባክኑ አይገባም፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ተቋማቱም ሆኑ ጋዜጠኞች ወቅቱ የሚፈልገውን የሕብረተሰብ ንቃተ ሕሊናን በመመዘን የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ውድቀት ግድ የሌላቸውና የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱትን ማጋለጫ፣ በአስተዳደራዊ በደል የተጎዱትን ፍትሕ እንዲያገኙ ጉዳታቸውን ማመላከቻ፣ በተዛባ ፍርድ የፍትሕ ያለህ የሚሉትን ሚዛናዊ ፍርድ እንዲያገኙ ለማስቻል ለውጥን ከራስ መጀመር ወደተሻለ ዕድገት የሚያሸጋግር መሆኑን ማረጋገጥ የግድ ያስፈልጋል፡፡

እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሚያሳትማቸው ጋዜጦችና መፅሔት ላይ መሰረታዊ የቅርፅና የይዘት ለውጥ ለማድረግ ወስኖ ለተግባራዊነቱ በመትጋቱ በሙሉ ልብ መናገር የሚቻልበትን ለውጥ ማየት ተችሏል፡፡ በዚህም አንባቢዎቹ የሚረኩባቸውንና መርጠው ሊያነቡዋቸው የሚችሏቸውን ፅሁፎች በማቅረብ፣ሕዝብ ጉዳቱንና ብሶቱን ለሚመለከተው አካል የሚያደርስበትን፣ ማናቸውም አስተሳሰቦች የሚስተናገዱበትን መድረክ መፍጠር በመቻሉ የሚያበረታታ የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት ተችሏል፡፡

ጋዜጦቻችን የሕዝብ አንደበት መሆናቸውን ስለምናምን ባመቻቸነው መድረክ የተጠቀሙ መፍትሄ እያገኙ መሆናቸውን ስንገልፅ በኩራት ነው፡፡ በተለይም በየሳምንቱ ረቡዕ እየታተመች የምትሰራጨው ‹‹አዲስ ዘመን ረቡዕ›› ጋዜጣ በመልካም አስተዳደር ችግሮችና ተጓዳኝ በሆኑ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራን በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ሥራ በመስራት ለብዙዎች መፍትሄ አቅጣጫን እያመላከተች ትገኛለች፡፡ ይህንኑ በጎ ተግባሯንም አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡

በአገሪቱ የሚገኙ የግልም ሆኑ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን የሚያሰራጩት መረጃ ለሕዝብ ጥቅም እስካልሰጠ ድረስ በሕዝብ ተመራጭነታቸው እየቀነሰና እየከሰሙ መሄዳቸው የማይቀር ስለሚሆን ጠቃሚውን አማራጭ የመያዝ ፍላጎቱ የራሳቸው ቢሆንም እንኳ ፤ ከሕዝብ ጥቅም የላቀ ምንም ነገር እንደሌለ መገንዘብ ግን አማራጭ የለውም፡፡ በዚህ ረገድ ሙያውን አክብሮ ለሕዝብ መቆም በሕዝብ መመረጥን ስለሚያስከትል ጠቃሚውን መስመር መያዝ ይገባናል፡፡

አዲስ  ዘመን ነሃሴ 8/2011