እኛና እግር ኳሳችን

15

ሰሞኑን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን /ካፍ/ የኢትዮጵያ ስታዲየሞች ላይ አሳለፈ የተባለው ውሳኔ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ መሰንበቱ በበኩሌ አስገርሞኛል፡፡ በአገራችን ስታዲየሞች የሚገነቡት መሪዎች ከሰፊው ህዝብ ጋር እንዲገናኙባቸው፣ የድጋፍ ሰልፎች እንዲደረጉባቸው ፣ ግንቦት 20 እና የብሔር ብሄረሰቦች ቀን እንዲከበርባቸው ታስቦ ስለሆነ የካፍን ዝቅተኛ መስፈርት ማሟላት አለመቻላቸው አያስደንቅም፡፡

የስታዲየሞቹ ግንባታ በእንጥልጥል የሚቀረው ህዝብ መሰብሰብ የሚያስችሉ ጣሪያ የሌላቸው አዳራሾች መሆን ደረጃ ሲደርሱ ነው፡፡ በከፊል ግንባታው ተጠናቀቀ የሚባል ስታዲየም እንኳን የሚመረቀው ፖለቲካዊ ይዘት ባለው ክብረ በዓል እንጂ በእግር ኳስና አትሌቲክስ ጨዋታዎች አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት የሚዘጋጀው ዲዛይንና ተጠናቀቀ የሚባለው ስታዲየም በአንድ ምጣድ እንደተጋገሩ ሙልሙል ዳቦዎች በቅርጽ አይገናኙም፡፡

በእነዚህ ሜዳዎች የሚደረገው ጨዋታ የሚታጀበው ኢህአዴግ “99 በመቶ” ፓርላማውን ከተቆጣጠረ በኋላ በደበዘዘው “የፖለቲካ ሙግት” እንጂ በጭብጨባና ማበረታቻ ዜማዎች አይደለም፡፡ የእግር ኳስ ሜዳዎች ከስፖርታዊ መንፈስ ርቀው የፖለቲካ መልዕክቶች ማንጸባረቂያ መድረክ ከሆኑ ከራርሟል፡፡

የደጋፊዎች መፈነካከት፣ የፌዴሬሽኑና የክለቦች እሰጥ አገባ የዕለት ተዕለት ልማድ ሆኗል፡፡ ዳኞችን እያሯሯጡ የሚደበድቡ ደጋፊዎችንና የአስልጣኞች ስታፍ አባላትን በተደጋጋሚ ተመልክተናል፡፡ በአገራችን በ1920ዎቹ እግር ኳስ ሲጀመር ይደረግ እንደነበረው ዳኞች ፈረስ ላይ ተቀምጠው እንዲዳኙ ቢደረግ ሽምጥ ጋልበው ከአባራሪያቸው ማምለጥ ስለሚችሉ ፌደሬሽኑ ቢያስብበት ሸጋ ነው፡፡

ለዘለቄታው እግር ኳሱ ነጻ እዲወጣ ግን የቦክስ ክለቦችን ማስፋፋት ፍቱን መፍትሄ ነው፡፡ እርግጥ ነው የቦክስ ፌዴሬሽን በመሰል አስተያየቶች ተቆጥቶ “መቀለጃ ሆንኩ ፤ ተደፈርኩ” ብሎ ማሳሰቢያ እስከመስጠት ደርሷል፡፡

እንደ እኔ ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ከመበሳጨት ይልቅ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የቦክስ ስፖርት እንዲስፋፋ ቢሯሯጥ አመርቂ ውጤት ያገኛል፡፡ ገላጋይ በሌለበት የሚፈነካከተው ደጋፊ ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ዳኛ ፊት ከተፋለመ በሰው አካልና ንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ይቀንሳል::

እግር ኳሱ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለገና ጨዋታ ፣ ፈረስ ጉግስና ገበጣ ጀርባውን የሰጠው ስፖርታችን ጎብጧል:: ከዚህ ቀደም በኦሎምፒክ ውድድር በውሃ ዋና ከአሳዎች ጋር እንዲዋኝ ዓሳነባሪ ልከን ዓለም ጉድ ብሎናል፡፡

የእጅ ኳስ ተጫዋቾች በውጭ አገር ከሚገኝ አቻ ቡድን ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ የግብዣ ወረቀት ሲመጣላቸው ሱፋቸውን ገጭ ያደረጉ አመራሮች ተሰብስበው ሄደው አገር ጎብኝተው ሲመለሱ ደግሞ ራሳችን ጉድ ብለናል፡፡

“በእንቅርት ላይ…” እንዲሉ ስፖርቱን ከወደቀበት ለማንሳት አይተኬ ሚና የሚጫወቱት የስፖርት ጋዜጠኞች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በሌላው ዓለም በሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ሆነ በጋዜጦች ላይ እግር ኳስን በመተንተን ሙያዊ አስተያየት የሚሰጡት በእግር ኳስ ህይወት ያለፉ ኮከቦች ናቸው፡፡ በእኛ አገር ግን የእግር ኳስ ተንታኝ ለመሆን በስታዲየም አጠገብ ማለፍ በቂ ነው፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በ1944 ዓ.ም. የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር /ፊፋ/ አባል ይሁን እንጂ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፊፋ የሚታውቀው በዓለም አቀፍ ውድድሮች ሳይሆን በአመራርነት ለመመረጥ በሚደረጉ እልህ አስጨራሽ ፉክክሮች ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ የሚያካሂደው ምርጫ የአገራችን ፖለቲከኞች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ለመሆን ከሚያደርጉት ፍልሚያ በላይ አዋዛጋቢ ስለሆነ ምርጫ ቦርድ ጣልቃ እንዲገባ የሚጠይቁ ወገኖች በዝተዋል፡፡

በደህናው ጊዜ ለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ከልምምድ በኋላ ስሙኒ ይከፈላቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ ዛሬ ግን እግር ኳሳችን ከነበረበት ዞር ሳይል ለአንድ ተጨዋች ዝውውር በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ወጪ ይደረጋል፡፡

አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በአንድ ወቅት አቶ ገዳሙ አብርሃ ከተባሉ ጸሐፊ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በጣሊያን ወረራ ወቅት እንደእርሳቸው እግር ኳስን ይጫወቱ የነበሩ ተጫዋቾች ስለ ግብ ጠባቂነት የነበራቸውን መረዳት ሲገልጹ ፣ “አስመራ ኳስ ይጫወት የነበረው ተስፋዬ አክሎግ አዲስ አበባ መጥቶ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መማር ሲጀምር ግብ ጠባቂ ተወርውሮ መሬት በመውደቅ ኳስ መያዝ እንደሚችል አሳየን፡፡

ከዚያ በፊት የምናውቀው ኳሱ ፊት ለፊት ቀጥታ ከመጣ በእጅ እንደሚያዝ ፤ በጎን ከሄደ ግን እግርን ዘርግቶ መመለስ እንጂ መውደቅና በእጅ መያዝ ጨርሶ እንደማይቻል ነበር።” ይላሉ፡፡

ታዲያ እንዲህ ያለው የግብ ጠባቂ ሚና በቅጡ የታወቀው ከብዙ ጥረት በኋላ ነው:: በዘመኑ የነበሩት እግር ኳስ ተጫዋቾች ግብ ጠባቂ መሬት ላይ ወድቆ በእጁ ኳስ ሲይዝ ፣ እንዴት ተደርጎ በማለት አምባጓሮ ይፈጥሩ ነበር ፤ በአየር የመጣ ኳስን እንደ ጭልፊት ተወርውሮ መያዝማ ጨርሶ የማይታሰብ ነው፡፡

ሲተዋወቅ ጀምሮ ፈተና የገጠመው ግብ ጠባቂነት አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ ሁነኛ ክህሎት ያለው ተጫዋች እንዳላገኘ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያውያን በረኞች የኮንሰንትሬሽን ችግር ስላለባቸው ከተጨዋቾች የሚለጋ ኳስንና ከተመልካቾች የሚወረወርን ድንጋይ እኩል መጠበቅ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ብዙዎቹ ክለቦች ከምዕራብ አፍሪካ አገራት በውድ ዋጋ ግብ ጠባቂ ያስመጣሉ፡፡

ስፖርት ኮሚሽን ይፋ ባደረገው ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተወዳዳሪ ከሆኑ ክለቦች 84 በመቶ ያህሉ የሚተዳደሩት በመንግስት ተቋማት ነው፡፡ ስምንት በመቶ የሚሆኑት በግል ባለቤትነት ሲተዳደሩ 13 በመቶ የሚደርሱት ህዝባዊ አስተዳደር አላቸው:: የተቀሩት አራት በመቶ ክለቦች ደግሞ በግልና በህዝብ የሚደገፉ ናቸው፡፡ በመንግስት ተቋማት ስር ያሉ ክለቦች በግለሰቦች ባለቤት ከሚተዳደሩትና ህዝባዊ መሰረት ካላቸው ክለቦች ዓመታዊ በጀት ከእጥፍ በላይ የሚበልጥ 50 ሚሊዮን ብር ይበጅታሉ፡፡

ክለቦች የራሳቸው መጫወቻ ሜዳ ቢኖራቸው የተሻለ ገቢ አግኝተው ከመንግስት ጥገኝነት መላቀቅ ይችላሉ የሚል አስተያየት ሲሰጥ እሰማለሁ:: አይደለም አነስተኛ የገንዘብ አቅም ያላቸው ክለቦቻችን የሳር ክዳን በለበሰች ጎጆ የመጀመሪያ ጽህፈት ቤቱን የከፈተው አንጋፋው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንኳን እስካሁን ድረስ በስሙ የተመዘገበ ስታዲየም የሌለው ምስኪን ነው፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም የተገነባው ፌደሬሽኑ ባቀረበው ጥያቄ ቢሆንም፤ የተመዘገበው በፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ስም ነው፡ ፡ ፌዴሬሽኑ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የሚያካሂደው በውሰት በሚጠቀማቸው ስታዲየሞች ነው፡፡

እግር ኳሳችን ያለበትን ደረጃና መንግስት ለእግር ኳስ ቡድኖች በየዓመቱ የሚመድበውን ከ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ካነጻጸርን ፣ ለአንድ ተጫዋች 350 ሺ ብር ወርሃዊ ደሞዝ መክፈል ቅብጠት ነው፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የአንድ ተጫዋች ደመወዝ ጣሪያ 50 ሺ ብር እንዲሆን መወሰኑ የሀብት ብክነትን ከመከላከል ባለፈ ተመጣጣኝ አቅም ያላቸው የእግር ኳስ ቡድኖች እንዲኖሩ ያደርጋል።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 8/2011

የትናየት ፈሩ