“እርቅ ደም ያድርቅ”

9

ዓመታቱ እጅግም ሩቅ የሚሰኙ አይደሉም፡፡ሀገራችን በዘርፈ ብዙ የችግሮች አረንቋ የውጥር ተይዛ ሕዝባችን “ኤሎሄ!” እያለ የሚቃትትበትና ምድሪቱም ራሷ ግራ ተጋብታ በመስቀልያ መንገድ ላይ ቆማ የምታምጥበት ወቅት ነበር፡፡ ለነገሩ ዛሬም ቢሆን ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ማለት ያዳግታል፡፡ ያንን ወቅት ለማስታወስ ያህል መንግሥት፣ ሕዝብና ሀገር በየአካባቢው ይገነፍሉ በነበሩ የቁጣና የጥፋት ወጀቦች እየተናጡ አቅጣጫ የጠፋባት ጊዜ ነበር ብሎ ማጠቃለል ይቻላል፡፡

በዚሁ ግራ አጋቢ ወቅት የተወሰኑ የሀገሪቱ ምሁራን፣ አዛውንቶች፣ ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና የሀገር ሽማግሌዎች በተደጋጋሚ እየተሰባሰቡ በሀገራዊ ሰላምና እርቅ ጉዳይ ይመክሩ ነበር፡፡ “ሀገራዊ መከራችንን እንዴት እናቅልለው፣ ሰላምንስ እንዴት ማስፈን ይቻላል?” የሚለው መሪ ሃሳብ ስብስቡ የተጨነቀበት ዋና ጉዳይ ነበር::

ከፖለቲካ ወገንተኝነትና ከቡድንተኝነት ነፃ የሆኑት እነዚህ ቅንና ተቆርቋሪ የሀገር ፈርጥ ዜጎች ከምክክራቸው በኋላ የደረሱበትንና ለሀገሪቱ ወቅታዊ ህመም መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ምክረ ሃሳብ አደራጅተው የሥልጣን እርከናቸውና የፖለቲካ ጡንቻቸው የፈረጠመውን የጎምቱ ሹማምንት ቢሮዎች እያንኳኩ ለሀገር ይበጃል ያሉትን ምክረ ሃሳብ በቃልና በጽሑፍ ማቅረቡን ተጉበት:::

ሃሳቡ የቀረበላቸው መሪዎችና የፖለቲካው ልሂቃን ተመካክረው የሰጡት መልስ አንድና ተመሳሳይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚያስገርመውና ትዝብቱ እስከ ታሪክነት የሚዘልቀው መልስ በእጅጉ ስሜትን የሚያቆስልና ህሊናን የሚያደማ ነበር፡፡ መልሳቸው ቃል በቃል ይህ ነበር፤ “መንግሥትም ሆነ ፖለቲካችን ከማንም ጋር አልተጣላም፡፡ እርቅ የምትሉት ማንን ከማን ለማስታረቅ ፈልጋችሁ ነው? ይልቅ የሚሻለው ችግር ያለበትንና የተጣላውን አካል ፈልጋችሁ አስታርቁ:: እኛ በረጅም ዓመታት ተሞክሯችን ችግሮች ሲፈጠሩ እንዴት እንደምንፈታ እናውቅበታለን፡፡”

የመጨረሻው ትልቁ የመንግሥት ሹምም ቡድኑ ከቢሯቸው በተገኘበት ወቅት የሰጡት የማሳረጊያ መልስ እነሆ እንዲህ የሚል ነበር፤ “እኔና ጓደኞቼ የምትሉት ዓይነት ችግር ስለመኖሩ እርግጠኞች አይደለንም፡፡ ፖለቲካችን የራሱን ችግር በራሱ ይፈታል፡፡ ከማንም ጋር እርቅ አያደርግም፡፡

የሚሻለው ግን እናንተ የስልሳዎቹ ትውልዶች እርስ በእርሳችሁ ብትታረቁ ነው፡፡” ይህን መሰሉ ለታሪክ ትዝብት የበቃው ትዕይንት የተፈጸመው በዚሁ በእኛ ጀንበር ሲሆን፤ ምስክሮቹም በሕይወት ይገኛሉ፡፡ ከዚህን መሰሉ መልስ ማግስት የኮሜዲውና የትራጄዲው ድብብቆሽ በቀናት ውስጥ ያስከተለው ሀገራዊ ውጤት ምን እንደነበር አልዘረዝርም፡፡

እርቅ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው:: ካጠፉ ዝቅ ብሎም እንኳ ይቅርታ መጠየቅ መዋረድ ሳይሆን የስብዕና ልዕልና መገለጫ ነው፡፡ ይቅርታ የሚጠየቀው አንዱ በዳይ ሌላው ተበዳይ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የሰላማዊ አብሮነት ማቆራኛ ብቸኛ ምሥጢሩ እርሱ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ይቅርታ ለሰጪውም ሆነ ለተቀባዩ የስሜት ቁስል ፈውስ የሚሰጥ ፍቱን መድኃኒት ነው::

ጉዳቱ እንዳያመረቅዝና እያደር እንዳያገረሽ ብቻም ሳይሆን ጠባሳ ትቶ እንዳያልፍም ያግዛል፡፡ ይቅርታ መሰጣጣትና መቀባበል በግለሰብ፣ በቡድንም ሆነ በማኅበር ደረጃ እሴቱ ከፍ ያለ፤ ወጤቱም የሰመረ ጭምር ነው፡፡ “እርቅ ደም ያድርቅ እየተባለ” የሚመሰከርለትም ስለዚሁ ነው::

በርካታ የከበሩ ባህላዊ እሴት ያላትን ሀገር የሚያስተዳድሩት መሪዎቻችንና ልሂቃን ወደ ውስጣቸው ተመልከተው ለሀገራዊ ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን ባህላችንን እየመረመሩ መፍትሔ ቢፈልጉ ኖሮ የመከራችን ክብደት ከዕለት ወደ ዕለት እያጎበጠን ባልሄደ ነበር እያልኩ እቆዝማለሁ፡፡ እንደ አንድ ዜጋ፡፡

የይቅርታን ኃያልነት፣ ፈዋሽነትና “ደም አድርቅነት” ሳስብ ሁለት አብነቶች ቀድመው ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ፡፡አንደኛው የተፈጸመው በዚሁ በሀገሬ ምድር ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ባህር ማዶ የሚሻገርና በግሌም ብዙ የተማርኩበት ነው::

ከሀገሬ ልጀምር፡፡ ታሪኩ የተፈጸመው ከዓመታት በፊት በደቡቡ የሀገራችን ምድር በሃዲያ ውስጥ ነው:: የመረጃ ምንጬ ደግሞ በአካባቢው የልማት ሥራ በማከናወን የተመሠገነው የሥራ ባልደረባዬና ጓደኛዬ ነው፡፡ ይህ ሰው ዛሬም ስለ ታሪኩ እርግጠኛነት መስክር ቢባል ከተፍ ማለት ይችላል፡፡ በጽሑፍ የሰጠኝን ይህንን ታሪክ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተደረገ አንድ ጉባዔ ላይ ይሄው ጓደኛዬ ሲጠቅሰው ብዙዎቹ ታዳሚዎች በእንባ እንደተራጩ ነግሮኛል፡፡

በአጭሩ ታሪኩን ላስታውስ፡፡ ለረጅም ዓመታት በፍቅርና በመከባበር የኖሩ ሁለት የአካባቢው ጎረቤታማቾች አንድ ወቅት ላይ በመሃላቸው ያለመግባባት ተፈጥሮ ይቃቃራሉ፡፡ መቃቃራቸው ከአዋቂዎቹ አልፎ እስከ ታዳጊ ወጣቶች ድረስ ይዘልቃል:: የእኔ ጥቃት ይበልጣል እየተባባሉ የሚወቃቀሱትና ለክፉ የሚፈላለጉት ቤተሰቦች ብሶታቸውን በታዳጊ ልጆቻቸው ፊት ሲተርኩ ውጤቱ ሊከፋ እንደሚችል ያስተዋሉ አይመስሉም::

አንድ ዕለት ማቴዎስ የሚባው የአንደኛው ቤተሰብ ታዳጊ ወጣት ቤተሰቦቹ የተቀያየሙትን ቤተሰብ ልጅ ፊታሞ የምትባለውን ታዳጊ ወጣት ቂም እንዳረገዘ አባብሎ ለጨዋታ በሚል ሰበብ ወደ ወንዝ አብራው እንድትወርድ ያደርጋል:: ምስኪኗ ፊታሞም በልጅነት ዕድሜ ተታልላ ማቴዎስን ተከትላ ለተጋበዘችበት “ጨዋታ” አብራው ወደ ወንዝ ወረደች፡፡

ቀደም ሲል የጥፋቱን ሤራ ያቀናበረው ማቴዎስ ጊዜ ሳያባክን የፊታሞን እጅና እግር አስሮ ወደ ወንዝ ውስጥ በመወርወር ሕይወቷን በመቅጠፍ የወላጆቹን ጉዳት በድርጊቱ እንደካሰ በመቁጠር ጨዋ መስሎ መኖር ይጀምራል፡፡ ከአካባቢው የተሰወረችው ፊታሞም ለወራት ያህል ፍለጋ ከተደረገ በኋላ በድኗ ወንዝ ውስጥ ተጥሎ ይገኛል፡፡

የአካባቢው ሽማግሌዎች ጉዳዩን በጥልቀትና በጥበብ ከመረመሩ በኋላ ድርጊቱ በማን፣ እንዴትና ለምን እንደተፈጸም ይደርሱበታል፡፡ ድርጊቱን የፈጸመው ታዳጊው ማቴዎስም ቀርቦ ሲጠየቅ የወላጆቹን በደል ለመበቀል ያን የመሰለ ጭካኔ በልጅ አቅሙ መፈጸሙን ያምናል:: ሁኔታው ግልጥልጥ ብሎ ይፋ ከሆነ በኋላ በአካባቢው ባህል መሠረት የሚፈጸመው ሥርዓት ተከናውኖ በማጠቃለያው ላይ የሟች ፊታሞ ወላጅ አባት ገዳዩን ማቴዎስን አንድ ሌሊት ልክ እንደ ልጃቸው ራቁቱን አቅፈውት እንዲያድሩ ተወሰነ፡፡

ለፊታሞ አባት ውሳኔው የመረረ ቢሆንም አደረጉት:: ማቴዎስን ልክ እንደ በኸር ብርቅዬ ልጅ በብብታቸው ውስጥ አቅፈው አሳደሩት:: የፈሰሰው የንፁኋ ብላቴና ደምም በዚህን መሰሉ እርቅ ተደምድሞ በአካባቢው ባህል መሠረት “እርቅ ደም ያድርቅ” ተብሎ ተዘመረ:: እኒህን መሰል ታሪኮች በየባህሉ ቢፈለጉ ሺህ በሺህ እንደሚገኙ መገመት አይከብድም፡፡ ልብ ያለው ልብ ካለ፡፡

ሌላኛው ገጠመኜ ይሄው ጸሐፊ ከሁለት ዓሠርት ዓመታት በፊት በቦታው ተገኝቶ ተሳታፊ የነበረበት ክስተት ነው፡፡ ጸሐፊው በ50ኛው የአሜሪካ ክፍለ ግዛት የተገኘው ከ23 ሀገራት ከተጋበዙ መሰል የሙያ ባለቤቶች ጋር የአጭር ጊዜ ሙያዊ ስልጠና ለመውሰድ ነበር፡፡

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተፋፋመበት (እ.ኤ.አ ከ1939 – 1945) ወቅት የዋሑ የሐዋይ ግዛት ሕዝብ ሀገር ሰላም ብሎ የዕለት ኑሮውን በሚከውንበት በዲሴምበር 7 ቀን 1941 ዓ.ም ቁጥራቸው ከ350 በላይ የሆኑ የጃፓን ቦንብ ጣይ አውሮፕላኖች እየተፈራረቁ አረራቸውን በማዝነብ “ዕንቁዋ” “Pearl Harbor” በመባል የምትታወቀውን የደሴቷን አካባቢና የአሜሪካኖቹን ዝነኛ የባህር ኃይል የጦር ቤዝ በእቶን እሳት በማጋየት ፍጡራንን እንዳልነበር በማድረግ ወደ ዶግ አመድነት መለወጣቸው በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

ይህ ጥቃት ያንገበገባቸው አሜሪካኖችም አድብተውና አስልተው እ.አ.አ. በኦገስት 1945 ዓ.ም ለሁለት ቀናት እሳት ለብሰውና ጎርሰው በታላላቆቹ ሂሮሺማና ናጋሳኪ ሁለት የጃፓን ከተሞች ላይ “Fat Man and Little Boy” የሚል ስያሜ የተሰጣቸውን የአቶሚክ ቦንቦች በማዝነብ ከሁለቱም ከተሞች ሲሶ ያህል ንፁሃንን በመፍጀት እጃቸውን ቂም ባሳደፈው ደም አጨማለቁ፡፡ ከዚያ አስከፊ ቁጣ የተረፉትና ከዚያ ወዲህ እየተወለዱት ያሉት የደሴቶቹ ዜጎች ሳይቀሩ ዛሬም ድረስ መዘዙ ለአካለ ስንኩልነት እያዳረጋቸው ይገኛል፡፡

ወደ ስልጠናችን ልመለስና ታሪኩን ላያይዝ፡፡ አሰልጣኞቻችን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ የየዘርፉ ታላላቅ ምሁራን ነበሩ፡፡ በአጋጣሚ ያንን ሥልጠና በተባባሪነት ሲያግዙ የነበሩት በሀገራችን ታሪክ የደመቀ መልካም ምስክርነት ያተረፉት ጄኔራል ታዬ ጥላሁን ነበሩ:: ጄኔራል ታዬ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አንስቶ እስከ ዘመነ ደርግ ድረስ የአየር ኃይል አዛዥ፣ የመከላከያ ሚኒስትር፣ የሀገር አስተዳደር ሚኒስትር፣ የባህር ኃይል አዛዥ በመሆን ያገለገሉ ብርቱ መኮንን ነበሩ:: በቅርቡ ግለ ታሪካቸውን ለአንባቢያን ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ከአሰልጣኞቻችን መካከል በተለየ ሁኔታ በዓለም ላይ ዝናቸው የናኘው ጃፓናዊው ፕሮፌሰር አሬጋ አንዱ ነበሩ:: ሥልጠናው ከመጀመሩ በፊት የሐዋያኑን ባህል ለማስተዋወቅ አንድ የባህል ቡድን ወደ መድረኩ ወጣ:: የባህላዊውን ትርዒት የሚመሩት ደግሞ በእድሜ የገፉ አዛውንት አባት ነበሩ፡፡

እኒህ አረጋዊ አባት ከትርዒት አቅራቢዎቹ ጋር መድረኩን እንደያዙ ስለዝግጅታቸው ገለፃ በመስጠት ጀምረው በመሃሉ ስለ ራሳቸው መመስከር ቀጠሉ:: “እኔ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካ የባህር ኃይል አባል በመሆን ጃፓኖች ያደረሱብንን አሰቃቂ የግፍ ገፈት ቀምሻለሁ፡፡ እንደምትመለከቱት ግማሽ አካሌ ሽባ የሆነው የቦንቡ ፍንጣሪዎች ከሰውነቴ ውስጥ ሊወጡ ስላልቻሉ በዚሁ ምክንያት የካንሰር ሕመምተኛ በመሆን ለዓመታት እየተሰቃየሁ እገኛለሁ::

እስከዛሬም በሕይወት ለመቆየት የቻልኩት በፈጣሪ ልዩ ርዳታ የተነሳ ነው፡፡ ሐኪሞቼ እንዳረጋገጡልኝ በዚሁ በካንሰሩ ምክንያት በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ከዚህ ዓለም በክብር እንደምሰናበት ስለተገለፀልኝ ተዘጋጅቼ የዘላለማዊ እረፍት ቀኔን እየተጠባበቅሁ ነው:: የዚያን አሰቃቂ የጃፓን ወረራ 55ኛ ዓመት በዓል ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ስለምናከብር እስከዚያ ብደርስ ዕድለኛ ነኝ፡፡ እንኳን ወደ ውቢቱ ሐዋይ በደህና መጣችሁ፡፡ በባህላችን መሠረት ባልደረቦቼ ለእያንዳንዳችሁ የአበባ ጉንጉን በአንገታችሁ ላይ ያጠልቁላችኋል፡፡” የአዛውንቱ መረጋጋት፣ ለዛና ሞገስ ዛሬም ድረስ ከትዝታዬ አልጠፋም፡፡

እኒህ ታላቅ የሐዋይ አባት ልክ ንግግራቸውን ሲጨርሱ ተጋባዡ ጃፓናዊ ፕሮፌሰር ከመቅፅበት ከወንበራቸው ተስፈንጥረው መድረኩ ላይ በመውጣት በአዛውንቱና በትርዒት አቅራቢዎቹ እግር ሥር ተደፍተው እየተንሰቀሰቁ “ጃፓን በድላችኋለችና ይቅር በሉን፡፡ ሀገሬ ክፉ ጥፋት ስላደረሰችባችሁ ይቅር በሉን! ማሩን::

ስላፈሰስነው የንፁሃን ሐዋያን ደም ይቅርታ አትንፈጉን:: ” በማለት በእንባቸው እየታጠቡ በመማጠናቸው በብዙ ገላጋዮች ብርታት ወደ ወንበራቸው ሊመለሱ ነው ብለን ስንጠብቅ በእያንዳንዳችን እግር ሥር እየወደቁ “እናንተም የየሀገሩ ተወካዮች ማሩን!” በማለት መማጠኑን ገፉበት:: “ሐዋያኑንስ ይሁን እኛ ደግሞ ምን ቤት ነን” ብለን ስንደናገጥ ግራ መጋባታችን ስለገባቸው ይመስላል ከልብ በሆነ መቃተትና እንባ እንዲህ በማለት ነው ይቅርታ እንድናደርግላቸው የተማጠኑት::

“ጃፓን በኢኮኖሚዋ ታብያለች:: በቴክኖሎጂ ዕውቀቷ ኮርታለች፡፡በሥልጣኔያችን ምክንያት ዓለምን ንቀናል፡፡ ስለዚህ ሀብት ቢኖረንም ደስታ ከዜጎቻችን ርቆ ፈገግታ አልባ እስከመባል ደርሰናል:: የጃፓን ሕዝብ ደስታ ርቆታል:: ስለዚህ የትዕቢታችንን ፍሬ እያዘመርን ስለሆነ እናንት የ23 ሀገራት ተወካዮች ሕዝባችሁንና ሀገራችሁን ወክላችሁ ይቅር በሉን፡፡ ከፈጣሪ ጋርም አስታርቁን …፡፡”

የጠቀስኳቸውን ታሪኮች ልብ ብለን ብናስተውል ብዙ ትምህርት የሚሰጡን ይመስለኛል፡፡ ይቅር መባባል የራቃት የዛሬይቱ ሀገሬ መንታ መንታ እያነባች የእርቅ ያለህ እያለች የምትጮህ ይመስለኛል:: በግጭት፣ በመፈናቀልና ከክልሌ ውጣ በሚል የእብሪት ግፍ የስንቱ ወገናችን ደም ደመ ከልብ ሆኖ እንደቀረ ቤቱ ይቁጠረው::

ከዩኒቨርሲቲ ግቢዎቻችን ሳይቀር በከንቱ ሕይወታቸው የተቀጠፈውን የልጆቻችንን በድን እየተቀበልን መቅበራችን የዕለት ክስተት ሆኗል:: “በዚህን አካባቢ በተከሰተ ችግር ይህንን ያህል ሰው ሞተ” የሚለው ዜና የተዘወተረና የቀለለ ወሬ እስከሚሆንብን የታወርን ይመስለኛል፡፡

“ችግሩን ጥቂት ቡድኖችና ግለሰቦች የፈጠሩት እንጂ የሕዝብ ለሕዝብ ጣጣ አይደለም እያሉ መንግሥታችንና ፖለቲከኞቻችን ሲሸነግሉንና ሲያቄሉን አሜን ብለን የተቀበልን ይመስለኛል:: ጥቂት ግለሰቦችም ሆኑ “አንዳንድ ጥቅመኛ ግለሰቦች” የሚዘሩት የእንክርዳድ ዘር ዞሮ ዞሮ ሕዝብን ከሕዝብ ከማጋጨት መች አዳነን፡፡ ስለዚህ ምኑ ላይ ነው “ሕዝብ ለሕዝብ” ከደሙ ንፁህ የሚሆነው::

የሚፈናቀለው ሕዝብ፣ የሚሞተው ሕዝብ ከሆነ ልዩነቱ ምኑ ላይ ነው፡፡ የምንሞተውም የምንገዳደለውም እኛው እርስ በእርስ አይደለምን፡፡ ልዩነቱ ወይ አልገባኝም ወይ አልገባቸውም:: መንበረ ሥልጣኑን የተቆናጠጡት መሪዎቻችን “ብሔራዊ እርቅ አውጀው” ደም የተቃባው ቢታረቅ፣ የተገፋፋው ቢቀራረብ፣ የጎሪጥ የሚተያየው ቢተቃቀፍ ምን ክፋት አለው::

ዛሬም እንደ ትናንቱ ፖለቲከኞቻችንና መሪዎቻችን ልባቸውንና ጆሯቸውን “ለብሔራዊ እርቅ” ባይደፍኑ እያልኩ እንደ ዜጋ ደግ ደጉን አመኛለሁ:: በግሌ ታማ አልጋ ላይ የዋለችው ሀገሬ ልትፈወስ የምትችለው “ብሔራዊ እርቅ” በምድሪቱ ላይ ሲታወጅ ብቻ እንደሆነ አምናለሁ:: ያለበለዚያ ነገራችን ሁሉ “አለባብስው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንዳይሆንብን እሰጋለሁ:: የሰላም ሚኒስቴር፣ የሰላም ኮሚሽን “እርቅ ደም ማድረቁን” ፈጥናችሁ አረጋግጡ:: ሰላም ይሁን!

አዲስ ዘመን ነሃሴ 8/2011

(በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)