የአሜሪካና ቻይና የንግድ ጦርነት ለአለም ኢኮኖሚ ስጋት ፈጥሯል

15

የአለም ኢኮኖሚ ወደ ሬሴሽን ( ስራ መጥፋት ) እንዲያመራ ያደረገው ዋነኛው ምክንያት በሁለቱ ኃያላን ሀገራት መካከል በመካሄድ ላይ ያለው የንግድ ጦርነት ነው። ሕንድ ወደሬሴሽን አልተቃረበችም።እጅግ ከፍተኛ የስራ መቀዛቀዝ መከሰቱን እየመሰከረች ነው። ከሙምባይ የሚወጡት መረጃዎች የሚያመለክቱት አለም አቀፍ ደረጃ ያለው ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ የመዳከም ምልክት እያሳየ መሆኑን ነው። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ቀጣዩ በአለም ደረጃ የስራ መጥፋት ይከሰታል። ሞርጋን ስቴንሊ የሚለው የሚታመን ከሆነ ከአሁን ጀምሮ ባሉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ክስተቱ እውን ይሆናል።

ቻይናና አሜሪካ ከ2018 (እኤአ) ጀምሮ አንዱ በሌላው ላይ ታሪፍ በመጨመርና ሌሎች እርምጃዎችን በመውሰድ በንግድ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። የሆንግኮንጉ የኢኮኖሚ ፕሮፌሰር ላውረንስ ጄ ላው ዋነኛው ምክንያት አለምን በኢኮኖሚና በቴክኒዮሎጂ የበላይነት ለመቆጣጠር (ለመምራት) በአሜሪካና በቻይና መካከል እያደገ የመጣው ጦርነት ነው ሲሉ ይልጻሉ። እያደገና እየተስፋፋ የመጣው ሕዝበኝነት፤ የመነጠል ንቅናቄ፤ ብሔርተኝነትና የፕሮቴክሽኒዝም ንቅናቄ በየትኛውም የአለም ክፍል አሜሪካንን ጨምሮ በስፋት የመታየቱ ነጸብራቅ ነው ይላሉ።

የንግድ ግጭቶቹ አካባቢዎች የኃላ ታሪክ አላቸው። የንግድ ጦርነቱ የብዙ አካባቢዎችን ያካትታል። የትራምፕ አስተዳደር ታሪፍ የጣለባቸውን አንዳንድ ክፍሎች ምክንያታዊነት አስመልክቶ ፒተር ናቫሮ የሁዋይት ሀውስ የንግድና የማኒፋክቸሪነግ ፖሊሲ ዳይሬክተር የአስተዳደሩን አቋም ገልጾአል።የተወሰዱት እርምጃዎች ግልጽ በሆነ ሁኔታ የመከላከል እርምጃዎች ናቸው ብሏል። አሜሪካኖች በባሕርማዶ ያፈሰሱት የተከማቸው በትሪሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በየአመቱ ጉድለት የሚያሳይ ሲሆን ሌሎች ሀገራት አሜሪካ ኢንቨስት ማድረግን በመቃወም የአሜሪካንን ንብረት ለመግዛት እየተጠቀሙበት ነው። እያደረግን እንዳለው ካደረግን እነዚህ ትሪሊዮን ዶላሮች በውጭ ዜጎች እጅ ስለሆኑ ይሄንን ገንዘብ አሜሪካንን ለመግዛት ሊጠቀሙበት ይችላሉ ብሏል። ከሰባት ወራት ምርምራ በኋላ የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ሮበርት ላይቲዘር አሜሪካ የጣለችው ታሪፍ መሰረት ያደረገው በአሜሪካ ግምት በምሁራን አእምሮአዊ ንብረት ላይ የደረሰውን የኢኮኖሚ ጉዳት ዘረፋና ሌብነት መሰረት ያደረገና የውጭ ካምፓኒዎች ኢንቨስትመንትንና ሌሎችንም እንዲያረጋግጡ ቴክኒዮሎጂም ትራንስፈር እንዲያደርጉ በማሰብ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው የአለመግባባቱ መነሻ ቻይና በአሜሪካ ላይ የምታካሂደውን ስለላ የተመለከተ ነው። የአሜሪካ ባለስልጣናት፤ የንግድ ሰዎች፤ አካዳሚኮችና ድርጅቶች ቻይና በስለላ አገልግሎቷ በኩል የአሜሪካን አእምሮአዊ ንብረትና ወታደራዊ ቴክኒዮሎጂ ትሰርቃለች ወይንም ፖሊሲዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የአሜሪካ ፓተንት ያላቸው በቻይና ገበያ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ከቻይና ካምፓኒዎች ጋር በጋራ ቬንቸር እንዲሰሩ ታስገድዳለች የሚል ክስ ያቀርባሉ። ይህም የቻይና ካምፓኒዎች ከሌሎች በተሻለ ለቴክኒዮሎጂዎች ሰፊ እድል እንዲያገኙ ያደርጋል፡ የቀድሞው የብሔራዊ ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ኬይት ቢ. አሌክሳንደር የቻይናን ኢንዱስትሪያዊ ስለላ በታሪክ ውስጥ ትልቁ የሀብት ዝውውር ሲሉ ይጠሩታል።

በሁለቱ ግዙፍ የአለም ኢኮኖሚዎች አሜሪካና ቻይና ላይ የተፈጠረው የንግድ ውጥረት ነው የአለምን ኢኮኖሚ ወደስራ መጥፋት የመራው። የማስጠንቀቂያ ደወሎች ከሌሎችም እውነተኛ ጠቋሚዎች ታይተዋል። የቦንድ ሽያጭ መታጠፍ በ2008 አስቀድሞ የታየውን አጠቃላይ አለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ቀውስ ይመስላል። ሞርጋን ስቴንሊ ንግዱ በአሜሪካ በኩል ዳግም የሚጦዝ ከሆነና ከቻይና በሚገቡት ሸቀጦች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ ከጨመረች አለም አቀፉ ኢኮኖሚ በሶስት አራተኛ ሬሴሽን ውስጥ መግባቱን እንመለከታለን ብሏል።

የሕንድ ኢኮኖሚ ለሬሴሽን (ለስራ መጥፋት ) ቅርብ አይደለም። ከፍተኛ የሆነ መቀዛቀዝ መኖሩን ግን እየመሰከረ ነው። አንዳንድ ክፍሎች የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪውን የመሰሉ በአደገኛ ሁኔታ ወደሬሴሽን እየቀረቡ ነው። የሕንድ ኢኮኖሚ ለሶስት ቀጥተኛ ሩብ አመታት ያቆለቆለ ሲሆን የእድገት ጠቃሚዎቹም ከፍ አላሉም። ሁለቱም የኢንዱስትሪ ምርቶችና ዋነኛ የመሰረተ ልማት ክፍሎች መቀነሳቸው ታይቷል። (ዲክላየን) አድርገዋል።

ግዙፍ የሆነ የስራ መጥፋት አደጋ በእንግሊዝና በሌሎች የአውሮፓ ኢኮኖሚዎች ላይ ተጋርጧል። ብሬክሲት ያዘለው በፖለቲካው መስክ እርግጠኛ አለመሆን ሁለተኛ ሩብ ኢኮኖሚውን ኮንትራት ውስጥ በመክተቱ የሆነ የስራ ማጣት ስጋቶችን ደቅኗል። በአለም አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚው በመቀዛቀዙ ምክንያት ግሎባል ማእከላዊ ባንክ ወደ እርምጃ ገብቷል። ሕንድ እንደ መለያ የተቀመጠውን የፖሊሲ ተመን ባልተለመደ ሁኔታ በ35 መሰረታዊ ነጥቦች ቆርጣለች። ኒውዚላንድ በ50 ታይላንድ በ25። በሕንድ የሬሴሽኑ ሁኔታ ግዙፍ ባይሆንም መንግስትና ፖሊሲ አውጪዎች ሊከሰት ይችላል የሚሉትን ሁኔታ አልዘነጉም። አጥራቸውን ማጠባበቅና ማጠናከር ገና አልጀመሩም።

በሌላ በኩል የተጀመረው የንግድ ጦርነት አለምን ወደ ሬሴሽን ይገፋታል ሲል ሮይተርስ ድረ ገጽ ዘግቧል። የማርክ ጆንስን ሪፖርት ጆሴፊን ማሰንና ዊሊያም ማክሊን ተመልክተውታል። ከለንደን የሮይተርስ ዘጋቢ እንደገለጸው የአሜሪካና የቻይና የንግድ ንግግር በመክሸፉ በቻይና ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ (ታሪፍ ) ተጭኗል። ይህም የአለምን ኢኮኖሚ ወደ ሬሴሽን ( ስራ ማጣትና መቀዛቀዝ) ገፍቶታል። የሞርጋን ስቴንሊ ተንታኝ እንደገለጸው የፌዴራል ሪዘርቭ የሰጠው ውሳኔ የአሜሪካንን አመታዊ የወለድ ትርፍ ዜሮ አስገብቶታል። ግዜያዊ የሆነው አለም አቀፍ የንግድ ውጥረት በአጠቃላይ ያለብዙ ጉዳት አይሎ የሚታይ ቢሆንም በስተመጨረሻ ከባድ የሆነ ችግር ማስከተሉ አይቀርም። አንድ የባንክ ተንታኝ የንግድ ንግግሩ ከቆመ ምንም አይነት ስምምነት አይኖርም፤ ከቻይና በሚገቡት የ300 ቢሊዮን ዶላር ሸቀጦች ላይ አሜሪካ 25 በመቶ ቀረጥ ከጣለች አጠቃላይ የአለም ኢኮኖሚ ወደ ሬሴሽን ውስጥ ሲገባ እናያለን ብሏል።

የፌዴራል ሪዘርቭ ሁሉንም ተመን የቆረጠው በ2020 ዜሮ ደረጃ እንዲደርስ ነው። ፈጣን የፖሊሲ ምላሽ አለመኖር፤ የተለመደው የፖሊሲ ስርጭት ዝግመት ማለት የሚሰጠው ትርጉም እየጠበቀ የመጣውን የፋይናንስ ሁኔታና ሙሉ በሙሉ እየጎነ ያለውን የአለም ሬሴሽን መቀልበስ አንችልም ማለት ነው።

ግሎባል ሬሴሽን (በአለም ኢኮኖሚ ላይ የስራ መጥፋትና መቀዛቀዝ) የሚገለጸው እድገቱ በአለም ደረጃ በአመት ከ2.5 በመቶ ደረጃ በታች ሲሆን ነው። በአማካይ አሜሪካ ከቻይና ከምታስገባው 200 ቢሊዮን ዶላር ሸቀጥ የ25 ፐርሰንት ታሪፍ ጭማሪው ከ3 እስከ 4 ወር በቦታው ላይ ይቆያል። የአለም እድገት በ50 መሰረታዊ ነጥቦች ላይ በአመት 2.5 ፐርሰንት ይሆናል። የተፈጠረው የንግድ ውጥረት የሚያስከትለውን ውጤትና ተጽእኖ በብዙ መልኩ ትኩረት አልሰጡትም ሲል የሞርጋን ስቴንሌ ተንታኝ ኢንቨስተሮችን አስጠንቅቋል።

በመጀመሪያ ደረጃ የተፈጠረው የንግድ ውጥረት በአሜሪካ ኮርፖሬት ክፍሎች በጥልቀት ይስፋፋል። ቻይና ደግሞ ታሪፍ አልባ ገደቦችን የግዢ ውስንነትን በተግባር ልታውል ትችላለች።የአለም እድገት መቀነሱን ተከትሎ በአለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱት ስራዎች ከድርጅቶች የሚገኘው ትርፍ ሊመታ ይችላል። ካምፓኒዎች በታሪፍ መጨመር የተነሳ ለተጠቃሚዎች ሙሉ በሙሉ መድረስ አይችሉም።

በተዘዋዋሪ ያለው ተጽእኖ ደግሞ መስመሩን የተከተለ አይደለም። የፋይናንስ ሁኔታው በጣም በመጥበቁ፤ የፖሊሲ ሁኔታዎች እርግጠኛ አለመሆን ድርጅቶች ያላቸውን በራስ መተማመን ስለሚመታው ይህም ገንዘባቸውን እንዳያንቀሳቅሱ ካፒታል ወጪያቸውንም እንዲያቆሙ ያደርጋል።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 9/2011

 ወንድወሰን መኮንን