‹‹የሰው ዓይን፣ መጋኛ፣ ጥሩ ቀን፣ መጥፎ ቀን…››

18

የትውልድ ሐረጋቸው በደቡብ ኢጣሊያ የሆነው ዕውቅ ደራሲ ማሪዮ ፑሶ ‹‹ኑዛዜ›› በተሰኘው ድርሰታቸው ያሠፈሩት ሳይጠቀስ አይታለፍም። ፑሶ የተወለዱት በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ቢሆንም እናታቸው ከኢጣሊያዊቷ ቺቺሊያ የፈለሱ ናቸው። ይህን አንተርሰው ሲጽፉ ‹‹የአጓጉል እምነት ነገር እናቴን በብርቱ ያጠቃት ነበር። አንድ ዕለት ምሳችንን በልተን እጃችንን ስንታጠብ በእጄ የነበረውን ሳሙና እርሷም እንድትታጠብበት ሰጠኋት። እርሷ ግን አልተቀበለችም። አስቀምጠውና ከዚህ አነሳዋለሁ አለችኝ። ዘወትር ነገሯ ሁሉ ግራ ስለሚሆንብኝ ‹‹ለምን!›› ብዬ ጠየቅኋት። ሣሙና በእጅ መቀባበል ፍቅር ያጠነፍፋል አለችኝ። በዚህ ተደነቅሁ›› ሲሉ አስፍረውታል።

ዕውቁ የእንግሊዝ ደራሲ ጆን ቢንግሐም ደግሞ ‹‹ማሪዮን›› በተሰኘው ልብወለድ መጽሐፋቸው ‹‹…… ወላጆቹ እዚህ ቦታ እሄዳለሁ ሳይል ጠፍቶ የቀረባቸውን ልጅ ለአያሌ ዓመታት ጠበቁ። ተስፋቸውም ብሩኅ ይሆን ዘንድ ልጃቸው ይተኛበት የነበረውን ክፍል መብራቱ እንደበራ ይተውት ነበረ። መዝጊያውንም አይቆልፉም። ወለል አድርገው ከፍተው ይለቁት ነበረ። በጥንቱ የእንግሊዞች እምነት መሠረት የጠፋው ሰው ቤት ክፍት ሆኖ መብራቱም በርቶ ከቆየ ፋናው ይስበዋል፣ መዝጊያውም ይጠራዋል ተብሎ ይታመንበት ነበርና!›› ብለውታል።

ዛሬ ይህ ያፈጀ አስተሳሰብ በዘመናችን እንደ ከንቱ ነገር እየተቆጠረ በአስቂኝነቱ ብቻ ‹‹ነበር›› ተብሎ በሥልጡኖች ዘንድ ተረት ለመሆን ቢችልም ገና ጓዝ ጉዝጓዙን ጠቅልሎ ያልሄደበት፣ ኮተቱን ይዞ ያልጠፋበት ሥፍራ ሞልቷል። የባህል ዕድገቱ ጊዜው የሚጠይቀውን ደረጃ ባልያዘበትና ሥልጣኔም ተዳርሶ አመዛኙን ኅብረተሰብ አመለካከቱንና አስተሳሰቡን ባልለወጠበት ቦታ ሁሉ ይኸ ከንቱ ነገር ጎልቶ ይታያል።

‹‹…… እስቲ እንዲያው በዶፋው ሌማት ከፍቶ እንጀራ የሚቆጥር ሰው አለ! ጠዋት ማታ ያ መከረኛ ሌማት እየተከፈተ እንዴት ይበርክት ጉድ ነው እኮ…..›› አሉ እኝህ አረጋዊት በመገረም። ይህ ልብ ወለድ አይደለም። የዚህ ጹሑፍ አቅራቢ በጆሮው የሰማው ነበር። ዱቄት ሲሠፈርና እንጀራ ሲቆጠር በረከት አጥቶ ‹‹አሲዳም›› ይሆናል እየተባለ በሀገራችን ይታመናል። ነገሩን ሲመረምሩት ለእጅ ዐመለኛ፣ ለሌማት ቀበኛ ማለፊያ መሸፈኛ መሆኑ አያጠራጥርም። ይህን የሰማ ኋላ ቀር አባወራ ታዲያ በጭፍን እምነት ተሸንፎ፣ በአጉል አመለካከት ተቀስፎ ከዱቄት እስከ ሌማት ያለውን መኖ ለጓዳ በዝባዦች ይለቃል።

ጥራጊ ከቤት ወደ ውጪ በማውጣት ፈንታ ከውጭ ወደ ቤት የሚጠረግበት ሁኔታም እንዲሁ ጥርስ የሚያስከድን አይደለም። የተደረደረው አረቄና ጣሪያ እየሰነጠቀ በመውጣት የሩቅ ሰው ሳይቀር የሚጣራው የቴፕ ትርትር ሳይበቃ የቤቱ ጥራጊ በተጨማሪ እየተሰበሰበ ይቀመጣል። እየተጠረገ ወደ ውጭ በማለት ፈንታ በረንዳ ያለው የሲጋራ ኩስታሪና የክብሪት ቁርጥራጭ ሳይቀር በመጥረጊያ እየተገፋ ወደ ቡና ቤቱ ይገባና እዚያ ከሚጠብቀው የጉድፍ ስብስብ ጋር ተደባልቆ ጥግ ይይዛል፣ ይከብራል። አንዳንዶች ደግሞ ጥራጊው የጀምበር ጥልቀትን ጠብቆ በጓሮ በር እንዲወጣ ያደርጋሉ። በፊት በር ግን ፈጽሞ አይቃጣም። ‹‹ገቢ ያሳጣል፣ ጠጪ ይገፋል›› ይባላል። ጥራጊ የሚያስከብር ባህል!!

አንዱ በጥራጊ ክምችት ገቢ ሲመኝ ሌላው ደግሞ እጁን በበላው ቁጥር የገዛውን ሎተሪ፣ የጣለውን ዕቁብ ያሰባል። ውስጥ እጁን ሲያሳክከው አልፎ ተርፎ በአራጣ ያበደረውን ብር የሚያልም ለዘመድ ስጦታ የሚጓጓ ሞልቷል። እንዲሁ ከሰማይ ወርዶ ዱብ የሚልለት የሳንቲም በረከት ያለ የሚመስለውም ሰው የተትረፈረፈ ነው። ሳይሠራ፣ ሳይጥር ፣ ሳይግር ማለት ነው።

ዕቁብ እንኳ ራሱ የጣለውና ባለዕጣ የሚሆንበት ነው። በአራጣ ያበደረውንም በውድም ሆነ በግድ ያገኛል። የሚገርመው የሎተሪው ምኞት ነው። ለዚያውስ ቢሆን በእርሱ እጅ ማሳከክና በገንዘቡ ኖት መሐከል ምን ዝምድና አለ?

ከቤቱ ወጥቶ ግራ እግሩን እንቅፋት ሲመታው ‹‹በቀኝ እውላለሁ›› ብሎ ደስ ብሎት ተስፋውንም እንደ በጋ ፀሐይ የበራ አድርጎ መንገዱን ይያያዘዋል። በአንጻሩ ደግሞ እንቅፋቱ የመታው የቀኝ እግሩን ከሆነ ወደ ቤቱ ይመለሳል። ሙግት የማይረታ፣ ችግር የማይፈታ መሆኑን ስለሚያምን ቀጠሮ ያስተላልፋል። ያውም በመልእክት እንጂ ራሱ ባነቀፈው እግር ተራምዶና ሄዶ አይደለም። የእግር ነገር ከተነሣ ውስጥ እግሩን ሲያሳክከው የስጋት ማዕበል የሚወርድበት የሀገራችን ሰው ጥቂት እንዳልሆነ ይነገራል። ውስጥ እግር ሲበላ መንገድ መሄድን ወይም መቃብር መርገጥን ያመለክታልና!! ‹‹መንገድ ወደ የት?›› ይህ ጥያቄ ደግሞ አሳሳቢ ነው። ሞትም በሩቅ መንገድነቱ ስለሚታሰብ የእግር ማሳከኩን ጉዳይ እንደዋዛ አያልፉትም።

ጅብ ሰባት ጊዜ ሲጮህ ሰው ይሞታል ተብሎ ይፈራል። ትልቅ ዛፍ ሲወድቅ ትልቅ ሰው ይሞታል ተብሎ ይሰጋል። ጉልበተኛ ነፋስ በሚነፍስበት ወቅት ቆርቆሮ መነቃቀሉ፣ ጎጆ መመንገሉ ብቻ አይደለም የሚታሰበው። ይበልጡንም በሠፈር የታወቀ፣ በሀገር የታወቀ ሰው እንደሚሞት ይታመናል። ቁራ እዋ! እዋ! እያለ ጩኸትን በጣሪያ ላይ ሲያስተጋባ ባለቤቱ ይሞታል ተብሎ ብርቱ ስጋት ላይ ይወድቃል።

የውሻ ጩኸት ከቀዬ ጥበቃ፣ ከጎበዝ ማንቂያነት፣ ከዘበኛ ቀስቃሽነትና አጋዥነት አልፎ የሞት ‹‹ሲግናል›› ሊሆን የበቃበት እምነትም አለ። ርቦትም ይሁን፣ ጠምቶት አሞትም ይሁን ከፍቶት ውሻ በተሰባበረ ድምፅ ሲጮህ ‹‹አለቀሰ›› ይባላል። እንዲህ ሲሆን በሰፈሩ ሰው ይሞታል እየተባለ ሰሚው ይሰጋል። የታመመ ማ ሰብ ይጀምራል።

ጠዋት ጠዋት ጥርስ መቦረሽ ለጤንነት የሚያበ ረክተው ድርሻ ሰፊ እንደሆነና በዚያው ልክም ማታ ማታ ወደ መኝታ ከማለት በፊት ቦርሾ ማጽዳት ተገቢ እንደሆነ ሐኪሞች አበክረው ቢመክሩም የአጓጉል እምነት ተሸናፊው ግን ማታ ጥርስ የተፋቀ እንደሆነ ‹‹የቅርብ ዘመድ ይሞታል›› ይላል።

እነዚህን ከፍ ሲል የተጠቃቀሱትን ‹‹የሞት ሲግናሎች›› በጥልቀት ስንፈትሽ አንዳንድ ጥያቄዎች ይከሰታሉ። ውስጥ እግር ባሳከከ ቁጥር መቃብር የሚረገጥ ቢሆን መሬቱስ ይበቃ ነበርን? የጅብ ጩኸት በሰባት ሰባት ጊዜ እየተቀመረ ቢሰላና ‹‹ስንት ጊዜ ሰባት›› እንደደረሰ ሒሳብ ቢደረግ በየቀኑ የሟች ብዛትም ስንት እንደደረሰ ሒሣብ ቢደረግ በየቀኑ የሟች ብዛት እንዲህ ተቆጥሮ ይደረስበት ይሯልን? ዘወትር በሚነፍሰው ጉልበተኛ ነፍስ ልክ ኃይል ሰው ዕውቅ ሰው ቢሞት ኖሮ አንድስ ታላቅ ሰው በዚህች በሠፈርንባት ምድር ሕልውናውን ሊያስመሰክር ይበቃ ነበርን? ውሾች በጮሁ (ባለቀሱ) ጊዜ ሁሉ በቀበሌው ሰው የሚያልቅ ቢሆን ኖሮ ለወሬ ነጋሪ እንኳ የሚተርፍ ይገኛልን? በምሽት ጥርስ በተፋቀበት ወቅት ሁሉ የቅርብ ዘመድ ቢሞት ኖሮ ወንድምና እህት ያለው ፍጡር ይገኝ ነበርን? ለጥያቄዎቹ ዝርዝር መልስ ከመፈለግ ይልቅ ‹‹አጉል እምነት›› ብሎ መቋጠሩ የሚበቃ ይመስለኛል።

ባዶ እንስራ ያዘለች ውሃ ቀጂ ያገኘችውን ሰው ሁሉ መንገዱን ዘግታ ታቋርጣለች። መንገዱ የቀና ይሆንለት ዘንድ በመመኘት ነው። ሙሉ የተሸከመችው ግን ለተንኮል ካላሰበች በቀር ታሳልፈዋለች። መንገደኛም ባለ ሙሉ እንስራ ሲያጋጥመው ገና ከሩቅ ይቆማል። ባዶ ያዘለችዋን ግን ተሸቀዳድሞ ያቋርጥና ‹‹ቀናኝ›› ብሎ ይፈነድቃል። ምክንያቱም ባዶ እየሞላ የሚሄድ ነው። ሙሉው ግን እየጎደለ ይሄዳልና አይወደድም። የሚገርመው ግን አንዳንዱ ጣሳ እንደ መነኩሴ ቆብ ተደፍቶ እንሥራውን አቀስሶ ሲዋብ ከመታየት በቀር የእንስራውን ባዶነት ወይም ሙሉነት አይገልጥም። ነገር ግን ለክፉም ሆነ ለበጎ ባለ እንስራዋ እና መንገደኛው ስለሚተዛዘኑበት ጉዳዩ በመተማመን የሚጨረስ ነው።

በአካባቢ ንጽሕና ጉድለት ሳቢያ የሚራባውን የዐይጥ መንጋ ፅዳት ባለመጠበቅ ምክንያት የሚመጣ መሆኑ እምብዛም አይታመንም። አይጥ ሲከሰት የቀበኛን መበራከት ያበሥራል።

ጉንዳን በፊት በበር ከገባ ‹‹ጥቁር እንግዳ›› ተብሎ ተከብሮ በማለፊያ ዘመድነት ይስተናገዳል። በጓሮ ከመጣ ግን የምቀኛን፣ የደበኛን ማሴር ይጠቁማል። አንዳንዶቹ ደግሞ ጉንዳን ሲበዛ ‹‹ጦር መጣ›› ብለው ያስባሉ፣ ይጨነቃሉ። ይሁንና ‹‹ጥቁር እንግዳ›› ተብሎም ተስተናግዶ የምቀኛን ተንኮል ጠቁሞ ወይም የጦር መምጣትን አመልክቶ ያው ዞሮ ዞሮ መቆንጠጡን አይተውም።

ሰው የውስጥ ከንፈሩን ሲነክስ ‹‹ዘመድ አነሣኝ›› ይላል። ምላሱን የነከሰ ደግሞ ‹‹ባዕድ አነሣኝ›› የሚሉም ‹‹እገሌ በደግ አያነሣኝምና እርሱ ይሆናል›› የሚሉም ታይተዋል። ጥርሳቸው ሙዳ ሥጋውን ጥሎ ዒላማ በሳተ ቁጥር በደኀና እቤቱ የተቀመጠውን፣ አንሥቷቸው እንኳ የማያውቀውን ጨዋ የሚያብጠለጥሉ ሞልተዋል።

ዓይን ሲርገበገብ ገሚሱ የናፈቀውን ዘመድ ለማየት ያለው ጉጉት የበዛ ይሆናል። ከፊሉ ደግሞ እንባ እንደሚፈሰው ይተነብያል። ዓይን በሚርገበገበው ልክ ዘመድ የሚታይ ቢሆን ኖሮ ግን ዓመታቱ ሁሉ የዘመድ አዝመድ መጠያየቂያ ከመሆን አልፈው ለሌላ ተግባር የሚውሉበት ሁኔታ አይፈጠርም ነበር።

አቦል ቡና ላይ የሚደርስ ሰው ሲቀዳ ከተፍ የሚል ‹‹ የልብ ወዳጅ›› ተብሎ ይመረቃል፣ ይከበራል፣ ይበልጥ ይወደዳል። ሁለተኛ ላይ ከቸች ያለ ግን ተንኮል የሚያስብ፣ ነገር የሚተበትብ፣ ‹‹ያልታወቀ ጠላት›› ተብሎ ከልብ ይጠላል፣ ይረገማል፣ የሻጉራም መታየት ይጀምራል። እንግዲህ ይህ የጀበና ዳኝነት ደጉን ሰው ለክፉ ሰጠ፣ ክፉውን በደግ ለወጠ፣ ሁሉን ያለአግባብ ለተገመደለ ፍርድ አጋለጠ ማለት ነው።

ነገርን ነገር ይቀሰቅሰዋልና የጠላት ወሬ ከተነሣ ዘንድ ውሻ የጌታውን ጠላት የማወቅ ጉልበት ‹‹አለው›› የሚሉም አልታጡም። በእርግጥ ውሻ የበላበትን የማይረሳ፣ ጌታውን የማይከዳ ነው። ይህ አሌ አይባልም። ይሁንና እንግዳ ሲመጣ ጠረኑን ባለማወቁ አይቶትም ባለማወቁ ወይም አንዳንዴ ሲላመደው ባለመሻቱ (በለመደውም ላይ) ይጮሀል። ይህ ግን እንግዳው ሰው በልቡ ያሰበውን ዐውቆ ነው ማለት አይደለም። እስከ አሁን ድረስ ውሾች ከሥነ ልቦና ‹‹ተመራማሪነትም›› አልፈው ‹‹ልብ ዐወቅ ነቢይ›› የሆኑበት ዘመን ያለ አይመስለኝም። በአሳዛኝ መልኩ ግን በሀገራችን ባለው የጭፍን እምነት መሠረት ‹‹ውሻ የጌታውን ጠላት ያውቃል›› በሚል አስተሳሰብ ውሻ ዘወትር የሚጮህበትን ሰው በትዝብት ማኀደራቸው አኑረው በተንኮለኝነትና በደንበኝነት ይመዘግቡታል። ሰውየውንም በጥንቃቄ ይመለከቱታል።

የውሻ ታሪክ ከተጠቀሰ ዘንድ ‹‹የእብድ ውሻ ወሬ ጤናማ ውሻ ፊት አይወራም›› የሚባልም ነገር አለ። አእምሮው ተቃውሶ በዳነ ሰው ፊት ስለሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ በሽታ አይነገርም። ይህ ርግጥ ነው። አብዶ የዳነ ሰው በመንፈስ ጭንቀት በመዋጥ ‹‹ ያን ጊዜ፣ ያመመኝ ጊዜ ያስቀየምኩት ሰው ይኖር ይሆን ምንስ አድርጌ ይሆን?›› እያለ በሐሳብ እንዳይባክንና ተመልሶ ወደ ነበረበት ሁኔታ እንዳይመለስ ወይም ሌላ ሕመም እንዳያገኘው በመስጋት ነው። ለዚያውም ቢሆን ለጊዜው ነው እንጂ እስከዚህ የሚያሳስብ ሆኖ አይደለም።

በመሠረቱ ውሾች ሰው የሚናገረውን ሰምተው የማሰብና የማሰላሰል ችሎታ እንዳለው ‹‹ሰብዓዊ ፍጡር›› በእዝነ ልቡና አሳድረው፣ በዓይነ ኀሊና ቃኝተው ነገር የማበጠር፣ የማዝከር ጉልበት የላቸውም። ጥቃቅን ትእዛዝ ተቀብለው በተግባር ከመተርጎም በቀር ‹‹ትናንት እንዲህ ተብሏል›› ብለው እንደ ሰው እያውጠነጠኑ የሚያጤኑም አይደሉም። ታዲያ እነርሱ ፊት ስለ ሌሎች ውሾች እብደት ቢወራ ምን ጉዳት አለው? እንግዲህ ይህን ሰምተው ያብዳሉ ሊባል ነውን? ይህ ቢሆንማ ኖሮ ሌላም ብዙ ነገር የሚሰሙት አለ ማለት ይሆናል። ‹‹ርኩሳን›› ናቸው። ከዘበኝነታቸው ሌላ ሁሉ ይጸየፋቸዋል። ይሰድባቸዋል። ከእነርሱም አልፈው በልክስክስነት፣ በአዳፋነት፣ በጎዳፋነት፣ በእበላ ባይነት ለተሰለፈ ሰብዓዊ ባሕርይ ሁሉ ያንን ‹‹ውሻ›› የተባለውን ስማቸውን አውርሰዋል። በግልጽነት ለሰው አውሰዋል። ኀሊና ቢኖራቸውና ሰምተው እርምጃ የሚወስዱ ወይም የሚያብዱ ቢሆን እንዲህ መጠላታቸውን ተረድተው ገና ድሮ ሁሉም ይታመሙ ነበር። የእብድ ዘመዳቸውን ወሬ እስኪሰሙም አይጠብቁም ነበር። ይህን ሁሉ አጉል እምነት ነው ከማለት ሌላ ምንም አንጨምርም።

ጽሑፉን በአጭር መግታትና እልባት ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ እንዲያው ዓበይት የሚባሉትንና ዘወትርም የሚታዩትንና የሚደመጡት ተጠቃቀሱ እንጂ በሰፊው አትቶ ማሳመር፣ በጥራዝ ማወፈር የሚቻል ይሆን ነበር።

‹‹በጨረቃ መሽናት ጨብጥ መሸመት›› ከተሰኘው አንሥቶ ‹‹በፀሐይ ላይ ተቀምጦ መብላት መጠጣት በምች መመታት›› የሚለውን ይዞ ‹‹ከአራስ ቤት ፈጥኖ መውጣት የሕይወት ጥፋት›› የተሰኘውን አስከትሎና ‹‹የሰው ዓይን፣ መጋኛ፣ ጥሩ ቀን፣ መጥፎ ዕለት ወዘተ……›› የሚለውን አግተልትሎ የጭፍን አማኝነትን፣ የአጉል አመለካከትን፣ ኋላ ቀርነትን የሚነግር ነው።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 11/2011

አሸናፊ ዘደቡብ