ህይወት እየቀጠፈ ያለው አመጋገብ

25

 ምግብ ለሰው ልጅ ጤና እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው።የሰው ልጅ ህልውናም የተመሰረተው በምግብ ላይ ነው ማለት ይቻላል።ይህን ህልውናውን ለመጠበቅ ደግሞ የሰው ልጅ ምግቦችን ከእንስሳት አልያም ከእጽዋት አዘጋጅቶ ይመገባል።በአሁኑ ወቅት ደግሞ በምግቦች ውስጥ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በማስገባትና በፋብሪካዎች ውስጥ በማቀነባበር ለምግብነት እስከማዋል ተደርሷል።

የሰዎች የጤና ሁኔታና አማካይ የመኖር እድሜ አሁን አሁን በሚመገቧቸው የምግብ አይነትና ጥራት እንደሚወሰን በተለያዩ ግዜያት የተሰሩ ጥናቶች ያመለክታሉ።በተለይም ተፈጥሯዊ ምግቦችን የሚመገቡ ሰዎች ጤናማና ረጅም የመኖር እድሜ እንደሚኖራቸውና ከዚህ በተቃራኒ ግን በፋብሪካ የተቀነባበሩና ተፈጥሯዊ ይዘታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ምግቦችን የሚመገቡ ሰዎች በቀላሉ ለተለያዩ በሽታዎች እንደሚጋለጡና የመኖር እድሜያቸውም በእጅጉ እንደሚያጥር ያረጋግጣሉ።

ቢቢሲ ምግብን በተመለከተ በጤና ገፁ ላንሴንት ሜዲካል ጆርናል ይፋ ያደረገውን አንድ ጥናት ዋቢ በማድረግ ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ መሰረት ሰዎች የሚመገቧቸው ምግቦች በየዓመቱ 11 ሚሊዮን ያህሉን በአጭሩ እያስቀሩ ናቸው ሲል ገልጿል።

እንደጥናቱ ከሆነ ሰዎች በየቀኑ የሚመገቧቸው ምግቦች ሲጋራ ከማጨስ በበለጠ ገዳይ እንደሆኑና በዓለም ዙሪያ ከሚከሰቱ አምስት ሞቶች መካከል አንዱ የሚከሰተው ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ ነው።በተለይም በዳቦ፣ ሶይ፣ ሶስና በተቀነባበረ ስጋ ውስጥ የሚገኘው ጨው የሰዎችን ከፍተኛ የመኖር እድሜ በማሳጠር ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ይላል።

ተመራማሪዎች ጥናቱ ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን ቅጥ ያጣ የሰውነት ውፍረት ሳይሆን ዝቅተኛ ጥራት ያላቸው ምግቦች በተለይ በልብ ላይ ምንያህል ጉዳት እያደረሱ እንደሆኑና ለካንሰር ህመም ዋነኛ መንስኤ እየሆኑ እንደመጡ ያሳያል ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የበሽታዎች ጫና ጥናት በሁሉም ሀገራት በሰዎች አሟሟት ዙሪያ ትክክለኛ ግምገማ የሚያካሂድ ሲሆን በቅርቡ ባካሄደው ግምገማም አመጋገብ በአብዛኛው ህይወትን የሚያሳጥር ስለመሆኑ ለማረጋገጥ የአገራትን የአመጋገብ ልማድ ከግምት ውስጥ አስገብቷል።ይንንም መነሻ በማድረግ አደገኛ የሚባሉ ምግቦች በውስጣቸው የሚይዟቸውን ንጥረ ነገሮች ከሚያስከትሏቸው የሞት መጠን ጋር ዘርዝሯል።

ከፍተኛ የጨው መጠን ያለባቸውና ከተፈተገ ስንዴ የሚዘጋጁ ምግቦች ለ3 ሚሊዮን ሰዎች ሞት ምክንያት መሆናቸውን የጠቆመ ሲሆን ፤ አነስተኛ የፍራፍሬ ይዘት ያላቸው ምግቦች ደግሞ 2 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች ሞት መንስኤ መሆናቸውን ጠቅሷል።ዝቅተኛ የለውዝ፣ ጥራጥሬ፣ አትክልትና ከባህር ምግቦች ውስጥ የሚገኙ ኦሜጋ 3 እና የፋይበር መጠን ያላቸው ምግቦችም ሌሎቹ ዋነኛዎቹ ገዳዮች መሆኑን አመልክቷል።

በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የጤና መለኪያዎችና ምዘና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ክርስቶፈር መሪ ምግብ በዓለም ዙሪያ ጤናን የሚመራ ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን በጥናቱ ለማረጋገጥ ተችሏል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡

ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ ከሚከሰቱ 11 ሚሊዮን ሞቶች መካከል 10 ሚሊዮን የሚሆኑት በልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች ምክንያት ሲሆን በምግቦች ውስጥ የሚገኘው የጨው መጠን ከፍተኛ መሆን በነዚህ በሽታዎች ለሚከሰተው ሞት ማሻቀብ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ እንዳበረከተ በጥናቱ ተመላክቷል።ከፍተኛ የጨው መጠን ደግሞ የደም ግፊትን በመጨመር ለድንገተኛ የልብ ህመምና ወደ አእምሮ የሚሄድ ደም መቋረጥ /stroke/ እንደሚያጋልጥ ተጠቁሟል።

ጨው በልብና በደም ቧንቧ ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ ያለው በመሆኑ ልብ ሥራዋን በአግባቡ እንዳታከናውን አለያም ከናካቴው ሥራዋን እንድታቆም እንደሚያደርጋትም ጥናቱ ያሳየ ሲሆን፣ ሆኖም ግን ካልተፈተገ ስንዴ የሚዘጋጁ ምግቦች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች ተቃራኒ ተፅእኖ አላቸው።የልብና የደም ቧንቧዎችን የሚጠብቁና ለልብ ችግር የማጋለጥ እድላቸውም ዝቅተኛ መሆኑን ጥናቱ ገልጿል።ካንሰርና የስኳር በሽታዎችም ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ቀሪ የበሽታ አይነቶችን እንደሚይዙም በጥናቱ ተጠቁሟል።

ትክክለኛ የአመጋገብ ሥርዓትን በመከተል ረገድ ፍፁም የሆነ ሀገር እንደሌለ ያረጋገጠው ይኸው ጥናት፤ አብዛኛዎቹ ሀገራት የተወሰነውን ጤናማ አመጋገብ ሥርዓት ብቻ መርጠው እንደሚከተሉና ይህም ዓለም ምን ያህል ከጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት እያፈነገጠ እንደመጣ አሳይቷል።በዓለም ዙሪያ ከምግብ ሰንሰለት ውስጥ ከጠፉ ጤናማ ምግቦች መካከል ለውዝና ጥራጥሬ መሆናቸውንም ጠቅሷል።

የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ኒታ ፎሮሂ በለውዝና ጥራጥሬ የምግብ አይነቶች ላይ በሰዎች ዘንድ ያለው አመለካከት ምግቦቹ አነስተኛ ጉልበት እንደሚሰጡ ቢሆንም ከዚህ በተቃራኒ ግን ምግቦቹ የተሟላና ትክክለኛ የቅባት መጠን የያዙ መሆናቸውና ኃይል እንደሚሰጡም ያስረዳሉ።የዋጋቸው ነገር እንዳለ ሆኖ አብዛኛው ሰው ምግቦቹን እንደ መደበኛ የምግብ ዓይነቶች እንደማይቆጥራቸውም ይናገራሉ።

በቅባትና በስኳር መካከል የነበረው ክርክርና ቀይና በፋብሪካ የተቀነባበሩ የስጋ ውጤቶች ከካንሰር ጋር ባላቸው ዝምድና ዙሪያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ትኩረትን የሳቡ ጉዳዮች ቢሆኑም በሰውነት ጤና ላይ ያላቸው ጉዳት ካለተፈተገ ስንዴ የሚዘጋጁ ምግቦችን ፣ ፍራፍሬዎችን ፣ ለውዝ ፣ ጥራጥሬና አትክልቶችን ካለመመገብ ከሚመጣ የጤና ጉዳት እንደማይበልጥ ፕሮፌሰር መሪ ይገልፃሉ።

የጥናቱ ተመራማሪዎቹ በአሁኑ ወቅት መወራት ያለበት ጉዳይ በምግቦች ውስጥ ስለሚገኙ ስኳርና የስብ ንጥረ ነገሮች ሳይሆን ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት እንዴት መከተልና መበረታታት እንደሚገባ ነው ያሉ ሲሆን፣ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአማካይ የመኖር እድሜ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መምጣቱን ገልፀዋል።

ፕሮፌሰር መሪ በአሁኑ ወቅት ዋነኛው የትኩረት ጉዳይ በምግቡ ውስጥ ያለው የስብና የስኳር መጠን እንዳልሆነ አስጠንቅቀው፤ በትክክል ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ጥያቄ በልብ ድካም ምክንያት የምንሞተው በሃምሳዎቹ የእድሜ አካባቢ ነው? ወይስ ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የካንሰር ህመም ሊይዘኝ የሚችለው በአርባዎቹ አድሜ ነው? ሲሉ ይናገራሉ።

የሜዲትራንያን ሀገራት በተለይም ፈረንሳይ፣ ስፔንና እስራኤል ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር በተያያዘ በዓለም ዝቅተኛውን የሞት መጠን ያላቸው መሆኑ በጥናቱ የተጠቆመ ሲሆን፤ በደቡብ ምስራቅ፣ ደቡብና መካከለኛው እስያ የሚገኙ ሀገራት ከዚህ በተቃራኒ የሚገኙ መሆናቸው ተረጋግጧል።በዚህም መሰረት እስራኤል በዓመት ውስጥ ከ100 ሺ 89 በመሆን ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ዝቅተኛ የሞት መጠን ያላት አገር ስትሆን ኡዝቤክስታን ከ100 ሺ ሰዎች ውስጥ 892 በመሆን ከፍተኛውን ደረጃ ይዛለች።

በሌላ በኩል ደግሞ ጃፓንና ቻይና ከጨው አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ያላቸውን ግንኙነት እየለወጡ የመጡበትን አመላካች ሁኔታዎች በጥናቱ ተገልጿል።በተለይም ቻይና ከአተርና ከሌሎች ጨዋማ ምግቦች ጋር ከፍተኛ የጨው መጠንን የምትጠቀም በመሆኑ ጨው የአገሪቱ ቁልፍ የምግብ አካል እየሆነ መምጣቱ ተጠቁሟል።ይሁንና የተቀነባበሩ ምግቦች ፍላጎት እያደገ መምጣት በምግቦቹ ውስጥ ተጨማሪ ጨው እንዲኖር አስገድዷል።ይህም በማንኛውም ሀገራት በጨው ምክንያት ከፍተኛ የሞት መጠን እንዲኖር አስተዋፅኦ ማድረጉን ጥናቱ አመላክቷል።

በዚህ ረገድ የጃፓን እጅግ አስገራሚ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር መሪ፤ ልክ እንደ ቻይናውያን ሁሉ ከሰላሳና ዓርባ ዓመታት በፊት ከፍተኛ የጨው ተጠቃሚዎች ነበሩ።አሁንም ጨው ቁጥር አንድ ችግራቸው ቢሆንም በሚያስደንቅ ሁኔታ ፍጆታቸውን እየቀነሱ መጥተዋል።በበርካታ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉና የልብ በሽታን ሊከላከሉ የሚችሉ አትክልትና ፍራፍሬዎች መሰል ይዘት ያላቸው ምግቦችም በብዛት አሏቸው፡፡

በጥናቱ እንግሊዝ ከፈረንሳይ፣ ዴንማርክና ቤልጂየም ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ ትልቁ ችግራቸው ያልተፈተገ ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች እንደ ልብ አለመጠቀም መሆኑ ታውቋል።በዚህም ምክንያት በእንግሊዝ 14 በመቶ የሚከሰተው ሞት ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ሲሆን ይህም ከ100 ሺ ሰዎች ውስጥ 127 እንደማለት መሆኑ ተገልጿል።

‹‹ምንም አይነት መስፈርት ቢቀመጥ የምግብ ጥራት በዋናነት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው›› ሲሉ ፕሮፌሰር መሪ ያሰምራሉ።ሰዎች ያልተፈተጉ የእህል ምግቦችን፣ ፍራፍሬዎችን፣ ለውዝ፣ ጥራጥሬና አትክልቶችን የሚመገቡ ከሆነና በምግብ ውስጥ የሚጠቀሙትን የጨው መጠን መቀነስ የሚችሉ ከሆነ ጤናማ ህይወት መኖር እንደሚችሉም ይጠቁማሉ።ይሁንና ፕሮፌሰሩ ትልቁ ጉዳይ ገንዘብ ነው ይላሉ፡፡

እንደ እርሳቸው አባባል ከሆነ ደሃ በሚባሉ ሀገራት በቀን ውስጥ አምስት ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን መጠቀም እስከ 52 በመቶ የሚጠጋውን የቤተሰብ ገቢ ሊወስድ ይችላል።

ፕሮፌሰር ፎሮሂ በበኩላቸው በአመጋገብ ሥርዓት ዙሪያ ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤና ሃብት ካለው ጤናማ ምርጫዎችን ሊያደርግ ይችላል።ይሁንና የሚተላለፍለት መልእክት አንድ ገዝቶ አንድ በነፃ እንዲያገኝ ከሆነ ጤናማ ስለማይሆንና ለጤና አስፈላጊ የሆኑ ምግቦችን በራሱ እንዲገዛ ስለማያስችለው መልእክቱ ላይሰራ ይችላል።ለዚህም ህብረተሰቡ ጤናማ የሆኑና ቀላል አማራጮች ያስፈልጉታል፡፡

ሁለቱም ተመራማሪዎች የምግብ ይዘት ከሆኑት ስብ፣ ስኳርና ጨው በበለጠ ሰዎች በትክክል ሊመገቧቸው በሚገቡ ምግቦች ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ ይስማማሉ።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 14/2011

 አስናቀ ፀጋዬ