ዕድሜ፣ ጥበብና ክብር

19

አንዳንድ አጋጣሚዎች ታፍኖ የኖረ ስሜት ድንገት ገንፍሎ እንዲወጣ ምክንያት ይሆናሉ። ታምቆ የኖረው ስሜት ምናልባትም ፀፀት፣ ቁጭት፣ ትዝብት፣ ግርምት፣ ቅንዓት ወዘተ… የወለደው ሊሆን ይችላል። ፀፀት አንድን ድርጊት ባልፈጸምኩት ወይንም ባልሆነ ኖሮ አሰኝቶ የሚያብሰለስል “ወይ እኔ” የሚፈጥረው ስሜት ሲሆን፣ ቁጭት ደግሞ “ሳልፈጽመው ወይንም ሳላደርገው” አለፈ ብለን ትናንትን በማሰብ የሚያንዘረዝር የስሜት ወላፈን ነው።

ትዝብት ራስንም ሆነ ሌላውን በውስጥ ስብዕና ቋንቋ ወይንም ያለቋንቋ የምንገመግምበት የተፈጥሯዊ ስብዕናችን መገለጫ ሲሆን፤ ግርምት የመደነቅና የመገረም፣ ቅንዓት ደግሞ በክፉም ሆነ በመልካም መንፈሳዊ ስሜት እየተገፉ ምላሽ መስጠት ነው። “ሰይጣናዊው ቅንዓት” አይረባም። ለክፉም ይዳርጋል። “መልካሙ መንፈሳዊ ቅንዓት” ግን በጎ ነገር ለመጨበጥና ካሰቡት ለመድረስ ጥሩ አንደርዳሪ ስሜት ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ ከላይ ለዘረዘርኳቸው ስሜቶች የራሱ ድንጋጌ እንዳለው ይገባኛል። እኔ የስሜቶቹን ዓይነት የበየንኩት በራሴ መረዳት ልክ መሆኑ ልብ ይባልልኝ።

ለማንኛውም ከላይ የዘረዘርኳቸውን ድብልቅልቅ የስሜት ዓይነቶች ለመጠቃቀስ የሞከርኩት አንድ ሰሞንኛ የቴሌቪዥን ትርዒት ሰበብ ሆኖኝ ነው። ፕሮግራሙ በመላው ዓለም ተላልፎ ስለነበር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለም ዜጎች በተደጋጋሚ ተመልክተውት አድናቆታቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጡ ሰንብተዋል።

ፕሮግራሙ “Britain’s Got Talent” በመባል የሚታወቀውና በየዓመቱ የሚደረግ የእንግሊዙ የተሰጥኦ ማስመስከሪያ (በተለምዶ አይዶል) በመባል የሚታወቅ የቴሌቪዥን “Talent Show” ፕሮግራም ነው። ለ13ኛ ጊዜ ተከናውኖ የተጠናቀቀው የ2019 ዓ.ም ፕሮግራም አሸናፊው ተለይቶ ፍፃሜውን ያገኘው ባለፈው ሰኔ ወር ነበር። የማጠቃለያ ፕሮግራሙ ከተከናወነ በኋላ እንኳን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በመላው ዓለም ደጋግመው ተመልክተውታል። አሁንም ድረስ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተመለከቱት ይገኛል።

ዴቪድ ዊሊያምስ፣ አሌሻ ዲክሰን፣ አማንዳ ሆልደንና የታለንት ሾው “ፈጣሪ” የሚባለውና በችሎታውም ሆነ በዳኝነት ብቃቱ ዝናን የተጎናጸፈው “አንቀጥቅጡ” ሳይመን ኮዌል በመራጭነት መንበሩ ላይ ተሰይመዋል። ሩብ ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓወንድ ሽልማቱን በዳኞችና በሕዝብ ድምፅ በማሸነፍ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ተወዳዳሪዎች መካከል በአንደኝነት የተወጡት የ89 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ኮሊን ታከሪ የሽልማቱ አሸናፊ መሆናቸው በይፋ ሲገለጥ ዳኞቹ ከወንበራቸው ተነስተው ደስታቸውን የገለጡበት ስሜት በራሱ ብዙ የሚፃፍለት ነው።

እኒህ አዛውንት ያሸነፉት በተለያዩ ዘውጎች የቀረቡ ምርጦችን ድል በመንሳት ነበር። ለምሳሌ፤ አንዳንድ ተወዳዳሪዎች በተስረቅራቂ ድምጻቸው ሙዚቃቸውን እያርከፈከፉ መድረኩን በማድመቅ ብዙዎችን አስፈንጥዘው ነበር። አንዳንዶች ደግሞ “አስማት” እያልን በምንጠራው ትርዒት ተመልካቾቻውን አፍዝዘዋል። አንዳንዶች አጥንት ያልተፈጠረባቸው እስኪመስል ድረስ ያሳዩት የዳንስ ጥበብና እንቅስቃሴ አስደማሚ የነበረ ሲሆን፤ አንዳንድ ተወዳዳሪዎችም በኮሜዲ ችሎታቸው በሳቅ አፍነክንከዋል።

እድሜ ጠገቡ አረጋዊ ተወዳድረው አሸናፊነታቸውን ያወጁት እነዚህን መሰል የመድረክ ከዋክብትና ፈርጥ ደምቀው የጥበባቸውን ብርሃን በማንፀባረቅ ነበር። የአብሪ ከዋክብቱ ብዛትና ችሎታ ለዳኞችም ሆነ ለድምፅ ሰጪዎች አዳጋች ቢሆንም የኮሊን ታከሪ የብርሃን አቅም ግን ሁሉንም በልጦ ለመድመቅ አልተቸገረም።

ቀለም፣ ዕድሜ፣ ችሎታ ዕወቀትና ዘር ልዩነት ባልተደረገበትና ከአስር ዓመት በታች ከሆኑ ሕጻናት ጀምሮ ለዘጠና አንድ ፈሪ እስከሆኑ ተወዳዳሪዎች ድረስ በተሳተፉበት በዚህ አስደናቂ ውድድር ካሸነፉት አዛውንት ምን ትምህርት መቅሰም ይቻላል? በዚህ ጽሑፍ የምዳስሳቸው ርዕሰ ነገሮች የሚያተኩሩት ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይሆናል።

ወደ አዛውንቱ ኮሊን ታከሪ የኋላ ታሪክ ጥቂት ተንደርድሬ አንዳንድ ጉዳዮችን ላስታውስ። አዛውንቱ ድምጻዊ የእንግሊዝ የጦር ሠራዊት አባል የነበሩና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከስድስት ዓመታት በኋላ በተባበሩት መንግሥታት ዕዝ ሥር ተዋቅሮ ወደ ኮርያ ልሣነ ምድር የዘመተው ጦር አባል ነበሩ። አሁን በሀገራቸው ተከብረው የሚኖሩ ጡረተኛ።

ስለ ኮሪያ ጦርነት ጥቂት ላስታውስ። የታሪክ ሰነዶች ለእማኝነት ካቆዩልን ሰነዶች መረዳት እንደሚቻለው የኮሪያ ልሣነ ምድር ጦርነት እንዲካሄድ ሰበብ የሆነው በሁለት የአይዲዮሎጂ ጎራ የተሠለፉ ሁለት ተጻራሪ ኃያላን ሀገራት ያቀናበሩት የትራዤዲ ውጤት ነው። ሁለቱ ኃያላን መንግሥታት ሶቪዬት ኅብረትና አሜሪካ አንድ ግንባር በመፍጠር ወራሪውን የጃፓን ሠራዊት ከኮሪያ ምድር ጠራርገው ካባረሩ በኋላ ምስኪኗን ኮሪያ እንደ ድፎ ዳቦ ለሁለት በመግመስና በመቀራመት የግላቸውን አሻንጉሊት መንግሥታት አቋቋሙ።

ኮሚኒስቷ ሶቪዬት ኅብረት የሰሜኑን ክፍል “የኮሪያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ” የሚል የፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ካባ በመደረብ መንበረ ሥልጣኑን ለኮሚኒስት ፓርቲው መሪ ለፕሬዚዳንት ኪም ኤል ሱንግ አስረከበች። የደቡቡን ክፍል ደግሞ ሌላኛዋ ባለ ጡንቻ ሀገር አሜሪካ “የኮሪያ ሪፐብሊክ” የሚል ምዕራባዊ ርዕዮት ቀብታ ሲያንግ ማን ሪህን ፕሬዚዳንት አድርጋ በትረ ሥልጣን አስጨበጠች። ይሄው የረቀቀ የፖለቲካ ጨዋታ ሰበብ ሆኖ አንድ ሕዝብ ለሁለት ተገምሶ በሁለት ርዕዮተ ዓለም ታዛ ሥር እንዲተዳደር በመደረጉ ወንድማማቾቹ ኮሪያውያን እንደ ባዕድ የጎሪጥ ከመተያየት አልፈው በሰይፍ ተሞሻለቁ። ወንድም ወንድሙን እየጣለ ፎከረ። አቅራራ። በሁለት ጎራ የተከፈሉና ከአንድ ማህጸን የተወለዱ ልጆች ወዲያና ወዲህ ሆነው እየተታኮሱ ተጋደሉ።

የማታ ማታ በሶቪዬት ኅብረት የሚደገፈው አፍለኛው ኮሚኒስታዊው የሰሜኑ መንግሥት ድል በድል እየተቀዳጀ የደቡቡን ወንድም ሕዝብ በመውረር ዋና ከተማዋን ሴዑልን እስከ መቆጣጠር በመድረስ የሸናፊነት ሰንደቁን አውለበለበ። አቅሙ ተሽመድምዶ እጅ የሰጠው የደቡብ ኮሪያው መንግሥት በ1943 ዓ.ም የድረሱልኝ ጥሪ ኡኡታውን ለዓለም ማሕበረሰብ አደረሰ።

ይህ መራራ የወረራ ጥቃት ጩኸት የራሷን ታሪክ ያስታወሳት ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት የእንተባበር ጥያቄ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ከሰላም አስከባሪ ጦሩ ጋር ተሰልፋ ደቡብ ኮሪያን እንደምትታደግ ለመንግሥታቱና ለወዳጇ አሜሪካ ፈጣን ምላሽ ሰጠች።

በዚሁ መሠረትም ከ1943 – 1945 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ውስጥ 3518 ያህል መኮንኖችን፣ የበታች ሹሞችንና ወታደሮችን የተካተቱበት ሦስት የቃኘው ሻለቃ ጦር በሦስት ዙር እንዲዘምት ተደርጓል። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአንደኛው ሻለቃን ጦር በጃን ሜዳ ተገኝተው በሸኙበት በሚያዝያ 4 ቀን 1943 ዓ.ም ለምን ሀገራቸው በጦርነት ውስጥ እንድትካፈል እንደፈለጉ የገለጹት እንዲህ በማለት ነበር።

“በእኛ ላይ የደረሰውን አንዘነጋም። ማንኛውም ሕዝብ ነፃነት በሚወዱ ሕዝቦች አክብሮትና እርዳታ መተማመን ይገባዋል ብለን ስለምናምን አሁንም ነፃነትን ለማክበርና ለማስከበር ረጂም ጎዳና ትጓዛላችሁ። ከብዙ ሺህ ዓመታት ጀምሮ ለኢትዮጵያ ነፃነት የተጋደሉት የጀግኖች አባቶቻችን መንፈስ ይከተላችኋል። በጦር ሜዳ ክንዳችሁን ያፀናል። ልባችሁንም ያበረታል። ”

ኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆቿን ወደ ኮሪያ ያዘመተችው፤ “እልም አለ ባቡሩ፤ ወጣት ይዞ በሙሉ” በሚለው የካሣ ተሰማ የስንብት ጥዑመ ዜማ አጅባ ሲሆን፤ ከምድረ እንግሊዝ ወደ ኮሪያ የተንቀሳቀሰው መሰል የታላቋ ብሪታኒያ የሰላም አስከባሪ ጦርም ልክ እንደ ካሣ ተሰማ (ምንም እንኳ ዜማውና ግጥሙ ተመሳሳይ ባይሆንም) ጦሩን በተስረቅራቂ ድምፁ እያነቃቃ አብሮ የዘመተው ታሪኩን በዝርዝር የገለጽነው በ“Britain’s Got Talent” ውድድር የ2019 ዓ.ም አሸናፊና የያኔው የቀድሞ ወታደርና የ89 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋው ኮሊን ታካሪ ነበር።

ያ አፍለኛ ወጣት ዘማች ወታደር ኮሊን ታካሪ ምናልባትም ከኢትዮጵያ ጀግኖች ጋር በኮሪያ ልሣነ ምድር የጦር አውድማ ምሽግ ውስጥ የየሀገራቸውን ዜማ እያንጎራጎሩ ሳይደናነቁ አይቀሩ ይሆናል። ጉዳዩን ከፍ እናድርገው ከተባለም የኢትዮጵያው ጦር በሀገሩ ፉከራና ቀረርቶ እየታጀበ የጦር ሜዳውን ቀውጢ አድርጎ ድል በድል ሲያዘምር ወጣቱ ታካሪም በሀገሩ የፉከራና የቀረርቶ ዓይነት እንግሊዛዊያን የጦር ጓዶቹን እያበረታታ ለድል ሳያበቁ አልቀረም።

የዛሬው አዛውንት ኮሊን ታካሪ ዛሬም ያ የወጣትነት ስሜቱ (አንተ እያልኩ በመጻፌ ይቅርታ እጠይቃለሁ) ሳይበርድና ተስረቅራቂ ድምጹ እንደ ዕድሜው ሳያረጅ ዓለምን በሚያስደንቅ ተሰጥኦው የዕድሜ እኩዮቹንና የጦር ሜዳ ጓዶቹን በኳየር መልክ አደራጅቶ እርሱ ከፊት እየመራ ተፈጥሮ የለገሰችውን ጥበብ በመጠቀም ዓለምን ከዳር እስከ ዳር አስጨብጭቦ ጉድ አሰኝቷል። በታላቅ የክብር ማማ ላይም ራሱን ከፍ አድርጓል። ኮሊን ታካሪ ከሽልማቱ ጎን ለጎን ልዩ ዝግጅቱን የእንግሊዝ ንግሥትና የንጉሣውያን ቤተሰቦችና የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚገኙበት ማቅረቡም በራሱ ከግምትም በላይ ከፍ ያለ ዝና የሚያጎናጽፈው ነው።

የሀገሩ ሕዝብና መንግሥት ብቻም ሳይሆን በሕይወት የሚገኙት የተለያዩ ሀገራት የጦር ሜዳ ጓዶቹም ጭምር የደስታ መልዕክታቸውን አዥጎድጉደውለታል። የሀገሬ ሰው “የማታ እንጀራ ይስጥህ” እንደሚለው መሆኑ ነው።

ወደራሳችን ጉዳይ ተመልሰን ውስጣችንን እንፈትሽ። የእኔው ሀገር የኮሪያ ዘማች ጀግኖችስ በምን ደረጃ ላይ ናቸው? እንኳን በአደባባይ ተወዳድረው በተፈጥሮ ስጦታቸው ሊጨበጨብላቸው ቀርቶ ኑሯቸው ራሱ ምን ይመስላል። የዕለት ጉርሳቸውና የዓመት ቀለባቸውን የሚያገኙት ሳይሳቀቁ ነውን? የረባ መጠለያስ አላቸው ይሆን? የጤንነታቸው ሁኔታና ቤተሰባቸውስ ምን ይመስላል? ኮሊን ታካሪ ኢትዮጵያን የመጎብኘት ዕድል ቢያገኝና ከቀድሞ ኢትዮጵያውያን ጓዶቹ ጋር መገናኘት ቢችል ኖሮ ምን ይሰማው ይሆን? የግሌ መልሴ እንጃ የሚል ነው።

ሀገሬ ልታፍርበት፣ ሕዝባችን አንገት ሊደፋበት፣ መንግሥትም ንስሃ ሊገባበት ከሚገቡ ብሔራዊ ውርደቶቻችን መካከል የጀግኖቻችን አያያዝ ጉዳይ አንዱ ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝም። ለሀገር ነፃነትና ክብር የደምና የሕይወት ዋጋ የከፈሉ ጀግኖቻችን ዛሬ አስታዋሽ አጥተው እንባቸውን ወደ ፈጣሪ ሲረጩ ደጋግሜ ተመልክቻለሁ። በፉከራና በቀረርቶ ባህላዊ እሴታችን እየተንበሸበሽን ጀግኖቻችንን ግን ዘንግተናል።

ይህንን ጽሑፍ የጻፍኩት መደበኛ ቢሮዬ ከሚገኝበት መሃል አራት ኪሎ ከሚገኘው የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አራተኛ ፎቅ ላይ ሆኜ ነው። ከፎቁ አናት ላይ ሆኜ ቁልቁል ወደታች ስመለከት በእብሪት ተሞልቶ የወረረንን የፋሽስት ጦር ያብረከረኩ ጀግኖች ጉልበታቸው ርዶ አልባሳታቸው ተበጫጭቆ፣ ወግ ያለው መጫሚያ እንኳ አጥተው ምርኩዛቸውን ተደግፈው ሲቆዝሙ በነጋ በጠባ አስተውላለሁ። በቂ ልብስ፣ የዕለት እንጀራ፣ ወግ ያለው መጠለያ ለእነርሱ ብርቅ ነው። የታደጓት ሀገር ረስታቸዋለች። ማሕበሩ የሚሰጣቸውን ወርሃዊ ዳረጎት ሊቀበሉ ደጅ ሲጠኑ መመልከት እንደምን ልብን እንደሚሰብር አይቶ መመስከር ይቻላል።

ፋሽስት ኢጣሊያ ድል የተመታበት 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል ሲከበር መርሐ ግብሩን ለማስተባበር ዕድል አግኝቼ ስለነበር ብዙ ጀግና እናትና አባት አርበኞችን ለማነጋገር ችያለሁ። የሁሉም ብሶት ተመሳሳይ ነበር። “ሀገርም ሕዝብም ረሳን” የሚል ስሞታ። “ውለታችን እንደሚገባ አልታወሰም” የሚል እሮሮ። “ጀግንነታችን እንኳ የሚታወሰው በዓመት ሦስት ቀናት የካቲት 12 ፣ 23 እና ሚያዝያ 27 ብቻ ነው” የሚል ወቀሳ።

የኮሪያ ዘማቾችም ሆኑ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ማኅበር አባላት ሕይወት ምንም ልዩነት የለውም። ሁለቱም ትውልዶች በጉስቁልና ውስጥ እንደወደቁ ማረጋገጥ አይከብድም። የ“Brtitain’s Got Talent 2019” አሸናፊው የኮሪያ ዘማች የኮሊን ታካሪ ጉዳይ እስከዚህ አጨዋውቶ አጓጉዞናል። ተፈጥሮ በሰጠችው ጥበብ፣ የዕድሜ ጉዳይ ሳይገድበው ክብር የተጎናጸፈውን የእንግሊዙን ጀግና ያህል እንኳ ባይሆን ለጀግኖቻችን ቀሪ ዕድሜ ሀገርና መንግሥት አንዳች ቁምነገር ፈጽሞ እንዲታደጋቸው በፀፀት፣ በቁጭት፣ በትዝብት፣ በግርምት፣ በቅንዓት ድብልቅልቅ ስሜት ውስጥ ራሴን ዘፍቄ በዜግነቴ “ጀግኖቻችንን እንታደግ” የሚል ጥሪ በእንጉርጉሮ አጅቤ በማቅረብ ሃሳቤን አጠቃልላለሁ።

«ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣

የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ።» ሰላም ይሁን!!!

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 15/2011

በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ