‹‹…በማሽን አከራይ፣ በድለላ የስራ ፈቃዶች ኮሌጅ ከፍተው የሚያስተምሩ አግኝተናል›› -ዶክተር አንዷለም አድማሴ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር

380

ዘንድሮ ከዚህ ኮሌጅ ገብቼ ዲግሪ አገኘሁ ማለት ከበድ ያለ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት 21 ዓመታት በብዛት የተስፋፉት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆችና የስልጠና ተቋማት ህግና ሥርዓትን አክብረው መስራት ከረሱ ቆየት በማለታቸው ነው:: ይህ መሰሉ በደል በህዝቡ ላይ ሲሰራ አገር ላይም ከፍተኛ የሆነ ኪሳራን ሲያስከትል የሚመለከተው አካል የት ነበር? ስንል ለከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ለዶክተር አንዷለም አድማሴ ጥያቄያችንን አቅርበን እርሳቸውም ይህን ብለዋል::

አዲስ ዘመን፦ የኤጀንሲው ተልዕኮና ግብ ምንድን ነው?

ዶክተር አንዷለም፦ መንግስት ኤጀንሲውን በአዋጅ ያቋቋመበት ዋና ምክንያት ከፍተኛ ትምህርትን በተመለከተ ጥራቱን እንዲከታተል ቁጥጥር እንዲያደርግ አግባብነቱን እንዲፈትሽ ሥርዓት ዘርግቶ እንዲከታተል ነው:: የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምንላቸው ደግሞ የግልና የመንግስት ተቋማትን ያጠቃልላል::

አዲስ ዘመን፦ ከዚህ ተልዕኮ አንጻር የነበረው አፈጻጸም እንዴት ይለካል?

ዶክተር አንዷለም፦ ተልዕኮ ከማስፈጸም አንጻር ተቋሙ ያለበት ደረጃ በተለይም ከመጣሁ በኋላ ያየሁት በጣም የሚያሳዝን ነው:: ብዙ ተቋማት በህገ ወጥ ስራ ላይ ተሰማርተዋል፣ ብዙ ወረቀቶች ያለአግባብ ታድለዋል የትምህርት ጥራቱም እዚህም እዚያም የተጨፈላለቀበት ሆኖ አግኝቼዋለሁ:: ተቋሙም ይህንን ህገ ወጥ አሰራር ተከታትሎ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድና ለማስወሰድ የማይችል ነበር::

አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ እንደዚህ አቅመ ቢስ እንዲሆን ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው?

ዶክተር አንዷለም፦ የሰው ሀይል እጥረትና የሀብት መጠን ውስንነት ሲሆን፤ ባለው አቅም ይህንን ግዙፍ ስራ ለመስራት የሚያስችለው አልነበረም፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ተቋሙና ዘርፉ ሳይናበቡ ቆይተዋል ማለት ይቻላል::

አዲስ ዘመን፦ ከዚህ አንጻር የእርስዎ የመጀመሪያ እርምጃ ምንድን ነበር?

ዶክተር አንዷለም፦ መጀመሪያ ያደረግነው ባለን ሀብት የሰው ሃይልና አደረጃጀት ምንድን ነው ልናደርግ የምንችለው? የሚለውን ማየት ነበር፤ የመንግስትንም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትንም ልንለውጥ እንችላለን ወይ? የሚለውን ነው ያየነው ከዚህ አንጻር ቅድሚያ ያደረግነው ወደ ተቋሙ ተጨማሪ የሰው ሀይል እንዲቀጠር ሲሆን፤ በዚህም 0 ዓመት የስራ ልምድ ያላቸው 40 ያህል ባለሙያዎች በልዩ ሁኔታ ተቀጥረዋል፤ ቀጥለንም ለእነዚህ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ላላቸው ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥተናል፡፡

ሌላው ደግሞ በአደረጃጀት ደረጃ መዋቅሩን ቀይረን ወደ ሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ እነሱም ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ነው::

ያሰለጠንናቸውን ባለሙያዎችም በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ያሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በመፈተሽ ፍቃድ እንዳላቸው፣ እውቅና እንደተሰጣቸው፣ ተማሪዎቹን በምን መልክ እንደሚያስተምሩ እንዲያጣሩ አድርገናል::

አዲስ ዘመን፦ በዚህ የፍተሻ ሂደት ምን ያህሉን ማዳረስ ተቻለ?

ዶክተር አንዷለም፦ በፍተሻ ሂደቱ 167 ካምፓሶች ተዳስሰዋል፡፡ 46 የሚጠጉ ውጤቶችም ተገኝተዋል፡፡ በዚህ መሰረት አንዳንዶቹ በአስመጪና ላኪ፣ በማሽን አከራይ፣ በድለላ ስራ፣ በጽህፈት መሳሪያ፣ በእንደራሴነት፣ በህክምና መሳሪያዎች አስመጪነትና በሌሎች የስራ ፍቃዶች ኮሌጅ ከፍተው የሚያስተምሩ ሆነው ነው ያገኘናቸው:: በአሁኑ ወቅት 18 ካምፓሶች እንዲዘጉ አድርገናል፡፡

ሌላው ተቋማቱ ለአንዱ ካምፓሳቸው በወሰዱት ፍቃድ የተለያዩ ቅርንጫፎች ከፍተው የሚያስተምሩበት ሁኔታ ነው የተገኘው::

አዲስ ዘመን፦ ተቋማቱ እውቅና ባልተሰጣቸው መስክና ካምፓስ ከማስተማር በተጨማሪ የትምህርት ሚኒስቴር መስፈርትን ያላሟሉ ተማሪዎችንም የሚመዘግቡበት አሰራር እንዳለም ይታያል ይህንንስ አላገኛችሁም?

ዶክተር አንዷለም፦ አዎ በትክክል አግኝተናል፤ የመግቢያ መስፈርቱን ያላሟሉ ተማሪዎችን ተቀብለው ያስተማሩ ያስመረቁም ብዙ ናቸው:: ለምሳሌ ከ 10ኛ ክፍል፣ ከ 10+1 ተቀብሎ በዲግሪ የሚያስተምር ተቋም አግኝተናል፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ መመረቅ ብቻ አይደለም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ገብተው ስራ ያገኙ አለፍ ሲልም እድገት የተሰጣቸው ናቸው:: ሁኔታውም በትንሽ ቁጥር በሚታይ አይደለም፤ ልክ መኪና አንድ እክል ሲያጋጥመው አምራች ተቋሙ ምርቶቹን እንደሚሰበስበው ሁሉ መሰብሰብ የሚገባን የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ብዙ ነው:: ከዚህ አንጻር ተቋማት በከፍተኛ ሁኔታ ህገ ወጥነት ላይ ተሰማርተው ነው ያገኘናቸው::

አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ጋር ተማሪውን የህገ ወጥነቱ ተዋናይ አድርገነዋል፤ ሆኖም ጠያቂ እንዲሆን በእናንተ በኩል የተሰራ ስራ ነበር?

ዶክተር አንዷለም፦ ተቋሙ የሚያዘው ማንኛውም ኮሌጅ የተሰጠውን የእውቅና ፍቃድ በሚታይ ቦታ ላይ መለጠፍ አለበት ብሎ ነው:: ይህንን የማየት ግዴታ ደግሞ የተማሪው ነው:: እዚህ ላይ ግን ትልቅ ችግር የሆነው በቃል ብቻ ተነጋግሮ የመተማመን ፤ ተቋማትም ደግሞ ግልጽ በሆነ ቦታ ላይ ፍቃዳቸውን አለመለጠፍ ነው::

እንኳን ሄዶ ለሚጠይቃቸው ቀርቶ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሌላቸውን ፍቃድ አለን ብለው የሚያስተዋውቁ ብዙ ናቸው:: ይባስ ብሎ ኤጀንሲው የሚሰጠውን የፍቃድ ደብዳቤ በፎቶ ሾፕ በመቀያየር ሀሰተኛ መረጃን ለተማሪዎች የሚያሳዩ አግኝተናል:: ይህ ሁኔታ ወደ ክልሎችም አድጎ ደቡብ ላይ የእኛን ፊርማ በተመሳሳይ መንገድ እየሰሩ ተማሪዎችን ሲመዘግቡ የነበሩ ተቋማትም ጉዳይ በህግ ተይዞ ነው የሚገኘው::

አዲስ ዘመን ፦ የህገ ወጥ ስራውን እንደ ማሳያ ደቡብ ክልልን አንስተዋልና በሌሎቹስ አካባቢዎች ምን መልክ አለው?

ዶክተር አንዷለም፦ ህገ ወጥነቱ በዚህ በዚህ ቦታ የሚባል አይደለም፤ በመላው አገሪቱ ነው እየተሰራ ያለው፤ ለምሳሌ ጋምቤላ ላይ 12 ኮሌጆች አሉ፤ እኛ ለአንዳቸውም እውቅና አልሰጠንም ፤ የሚገርመው ደግሞ የክልል አመራሮች በእነዚህ ኮሌጆች ተምረው ተመርቀው በየቦታው ስራ ላይ ናቸው:: ከዚህ በላይ ደግሞ በእነዚሁ ኮሌጆች ለመማር ከደቡብ ሱዳን ሳይቀር እየመጡ ነው::

የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስራ ከጀመሩ ካለፉት 21 ዓመታት ጀምሮ የተረጨውን ዲግሪ እንዴት እንሰብስበው የሚለው ነገር ማሰብ የግድ ነው:: አሁን ፍተሻ ላይ ነው ያለነው:: ፍተሻውም ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እያንዳንዱ ተቋም እስከዛሬ ያስመረቃቸውንና አሁን በመማር ላይ ያሉትን ተማሪዎች መረጃቸውን ያስገባል:: ከዛ በመቀጠል ኤጀንሲው እነዚህ ተቋማት ፍቃድ አላቸው፣ ተማሪዎቻቸውን በትምህርት ሚኒስቴር መስፈርት ነው የመዘገቡትና አስተምረው ያስመረቁት የሚለውን በደንብ ከፈተሸ በኋላ ትክክለኛውን መረጃ ወደ መረጃ ሳጥን ውስጥ እናስገባለን:: በዚህ አሰራር ደግሞ በርካታ ኮሌጆች አደጋ ላይ ይወድቃሉ::

አዲስ ዘመን ፦ ያለ አግባብ ተረጭተዋል የሚሏቸው የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዎች እያስከተሉ ያለው ቀውስ እንዴት ይገለጻል?

ዶክተር አንዷለም፦ 10 ሺና 20 ሺ ወረቀት ቢሆን ምንም ችግር የለውም ሆኖም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ያለአግባብ መቁረጫ ነጥብን ሳያሟሉ የገቡ ገብተውም ተምረው የተመረቁ ናቸው:: የሚገርመው እኮ ተማሪዎች ዲግሪያቸው እንደማይሰራ የሚያውቁት አንዳንዶቹ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ አስበው በእኛ ተቋም ለማረጋገጥ ሲመጡ ነው:: እኛም ያለንን መረጃ አጣርተን ዲግሪው ህገ ወጥ እንደሆነና እንደማይሰራ እንነግራቸዋለን:: ቀጣሪ መስሪያ ቤቶችም ይህንን ስለማያውቁ በውስጣቸው በርካታ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ሰራተኞችን እያስተዳደሩ ነው:: ይህ እንደ አገር መፈታት ያለበት ችግር ቢሆንም እንዴት የሚለው ግን የመንግስትን ውሳኔ ይፈልጋል::

አዲስ ዘመን ፦ ሊወሰድ የታሰበው ርምጃ ጥሩ ቢሆንም ከጠፋው ጥፋት አንጻር በተለይም ወደ ኋላ ሄዶ እርምጃ መውሰዱ እንደ አገር የሚያስነሳው ሌላ ችግር የለም? ይህስ ታይቷል?

ዶክተር አንዷለም፦ እኛም ስጋት አለን :: እርምጃ ከተወሰደ ሁሉም ተቋማት አይተርፉም:: ከተረፉም በጣም ጥቂት ነው የሚሆኑት:: ተቋማቱን ዘግተን ብንወጣ አሁን ላይ እየተማረ ያለውን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪ ምን እናደርጋለን የሚለው ስጋት ነው፤ ሌላው ደግሞ ይህንን ዲግሪ ይዘው በየመንግስት ተቋማት ተቀጥረው ያሉትስ ምን ይሆናሉ? የሚለው ሌላው ነው:: በመሆኑም መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ መስጠት አለበት::

በ 2012 ዓ.ም አንድም ተቋም ወደ ህገ ወጥ አሰራር ይገባል ብዬ አላስብም ፤ ከገቡም በራሳቸው መቀለድ ነው:: እኛ የምናደርገው ተቋማቱን ሙሉ በሙሉ እንዘጋለን:: ሃላፊዎችና ባለሀብቶቹን ደግሞ በወንጀል እንዲጠየቁ እናደርጋለን:: መንግስት ለዚህም ቁርጠኝነቱን አሳይቷል::

ወንጀሉን ለማደራጀት የትኛው ተቋም በምን ያህል የሚለውን በአግባቡ የምንፈትሸው ይሆናል:: ከዚህ አንጻር የወደፊቱን የማስተካከል እድል አለ እስከ ዛሬ የተበተነውን ወረቀት ግን እንዴት እንሰብስበው የሚለው ከባድ ስራን የሚፈልግ ሆኗል ግን እንሰራዋለን፡፡

አዲስ ዘመን፦ አንድ ሰው የያዝከው ዲግሪ ህገ ወጥ ነው በዚህ ምክንያት ደግሞ ከስራህ ተሰናብተሀል ሲባል ምን ሊፈጠር እንደሚችል ታስቧል?

ዶክተር አንዷለም፦ ለምሳሌ አንድ ተቋም የመስሪያ ቤቱን ሰራተኛ ፋይል ወደኛ መረጃ ቋት አስገብቶ ትክክለኝነቱን ለማረጋገጥ ሲፈልግ ሰውየው በተቋሙ መረጃ ቋት የማይታወቅ ዲግሪውም ሀሰተኛ ሲሆን ሰራተኛውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሸኘት ነው ቀጣይ እርምጃው:: ዲግሪህ ሀሰተኛ ነው ተብሎ የተሸኘው ሰራተኛ ደግሞ በቀጥታ የሚሄደው ወደ አስተማረው ተቋም ነው ፤በዚህ አካሄድ ደግሞ አንድ ኮሌጅ በ20 ና 30 ሺ ሰው ሊከሰስ ነው:: ሁኔታው እንደ አገር የሚያስከትለው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ ካለመሆኑም በላይ ኮሌጁ ለዚህን ያህል ሰው የሚሰጠው ምላሽ ወይም ሌላ ነገር ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ በራሱ በጣም ከባድ ነው:: ሆኖም ሁኔታው ሲፈጠር ከማየት ሌላ አሁን ላይ ምንም አማራጭ የለም::

አዲስ ዘመን ፦ እስከ አሁን ስለ ግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ነው ያወራነው የመንግስቶቹስ ከችግሩ ነጻ ናቸው?

ዶክተር አንዷለም፦ ነጻ አይደሉም ፤ በዚህ ህገ ወጥ ተግባር ውስጥ ተዘፍቀው የሚገኙ ናቸው:: ለምሳሌ አዲስ አበባ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ከክልል የመጡ ዩኒቨርሲቲዎች የማታ እናስተምራለን ብለው ተማሪዎችን ይመዘግባሉ:: ያስተምራሉ:: ቤተ መጻህፍታችሁ ፣ ቤተ ሙከራዎቻችሁ፣ መምህራኑ የታሉ ሲባሉ መልስ የላቸውም:: በሌላ በኩል ደግሞ ከግል ኮሌጆች ጋር በጥምረት እናስተምራለን ብለው የቀን ተማሪ መዝግበው ሲያስተምሩ ይገኛሉ:: ሆኖም እነዚህ ተቋማት በዚህ መልኩ አስተምረው የሚሰጡት ዲግሪ በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የለውም:: ለህብረተሰቡም አሰራሩ ህጋዊ እንዳልሆነ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ተናግረናል:: እያንዳንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፕሬዚደንትም በዚህ ስራው ተጠያቂ ይሆናል::

እስከዛው ድረስም በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ አማካይነት ከ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በዚህ መልክ ማስተማር እንደማይችሉ ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል:: እስከ አሁን ያስተማሯቸውንና በማስተማር ላይ ያሉትን የተማሪዎች መረጃም በጽሁፍ በዝርዝር እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል:: ይህንን መሰረት አድርጎም መንግስት የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል::

አዲስ ዘመን ፦ ስለዚህ ህገ ወጥነቱ በግል ተቋማቱ ላይ ብቻ የቆመ አይደለማ?

ዶክተር አንዷለም፦ የመንግስት የግል የምንለው ነገር የለም ሁሉም ተዘፍቀውበታል:: ተቋማቱ ከዚህ አድራጎታቸው መውጣት አለባቸው ብለን እየሰራን ነው::

አዲስ ዘመን፦ በዚህ ደረጃ ለተስፋፋው ህገ ወጥ አሰራር ግን በዋናነት ተጠያቂው ማነው?

ዶክተር አንዷለም፦ ለዚህ ሁኔታ መፈጠር የበርካቶች እጅ አለበት፤ አንዱና ዋናው ግን ባለሀብቱ ነው፡፡ ይህ ማለት ባለሀብቱ ያለአግባብ ሀብት ለመሰብሰብ፣ ብዙ ተማሪዎችን ለመያዝ ሲል ህገ ወጥ አካሄድን መርጧል፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርትን ለመከታተል የሚያበቃ ውጤት ያልያዘን ተማሪ ይመዘግባል ፤ ተማሪውም ስለመመዘገቡ ብቻ ይደሰታል ወላጆችም ልጃቸው ስለተመዘገበ ብቻ ገንዘባቸውን ይከፍላሉ፡፡ ይህ ትልቁ ችግር ነው፡፡

አንድ ተቋም ፍቃድ ወስዶ ወደ ስራ ሲገባ ሥርዓቱን ማክበር መቻል ይኖርበታል ሥርዓቱን ያለማክበር ለህግ ተገዢ አለመሆን ወይንም ደግሞ ያለአግባብ ለመክበር መሞከር በሰው ልጆች ጊዜ ጉልበትና ሀብት እንዲሁም በአገር ላይ መቀለድ ነው፤ የሚያደርሰው ተጽዕኖም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ኤጀንሲው ይህን ህገወጥነት ለምን ማስቆም አቃተው?

ዶክተር አንዷለም ፦ ለዚህ ሁሉ ህገ ወጥነት መነሾ ኤጀንሲው በአግባቡ ሃላፊነቱን አለመወጣቱ፤ ሥርዓት ማስከበር አለመቻሉና የቁጥጥርና ክትትል ስራው ደካማ መሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ውጪ የዚህ ተቋም አደረጃጀት በክልል ላይ አለመኖሩ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል፤ ይህም ቢሆን ግን ተማሪው ራሱ ህጋዊ ከሆነ መጀመሪያ ስለሚማርበት ተቋም ፍቃድ፣ እስከመቼ እንደሚቆይ በየትኛው ካምፓሱና በምን የትምህርት ዓይነት ለማስተማር እንደተፈቀደለት ማረጋገጥ ያስፈልገፈው ነበር፡፡

ተቆጣጣሪው አካል በአግባቡ አለመቆጣጠሩ ባለሀብቶቹ ወደዚህ ስራ ሲሰማሩ ህግና ሥርዓትን አክብረው አለመስራታቸው ተማሪው ደግሞ ጠይቆ ከህገ ወጦች እራሱን አለመቆጠቡ አስተዋጽኦ አድርገዋል ብዬ እወስዳለሁ፡፡

ተጠያቂው ብዙ ቢሆንም ከኤጀንሲው ይጀምራል፤ ኤጀንሲው በትክክል ስራውን ስላለመስራቱ ይህ ሁሉ ችግር ሲፈጠር የት እንደነበር ይጠየቃል:: በሁለተኛ ደረጃ በቦታው ተመድበው ይሰሩ የነበሩ ሃላፊዎች እንዲሁም የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚደንቶች ተጠያቂ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል የሚመለከታቸው በርካታ የመንግስት አደረጃጀቶች ተጠያቂነት ውስጥ መግባት አለባቸው:: እዚህ ላይ የተጠያቂነት መጠኑ ማነስና መብዛት ነው እንጂ

 አብዛኞቻችን መጠየቅ መቻል አለብን:: ካልሆነ ግን የደሃ ልጆችን ህይወት አምስትና ስድስት ዓመት እየቀነስን ፣ ህይወታቸውን እያበላሸን እንቀጥላለን ማለት ነው::

አሁን ላይ አገሪቱ ከምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ህብረተሰቡ ልጆቹን ከራሱ አርቆ ማስተማር አይፈልግም ፤ ለዚህ ደግሞ አንድ የእርሻ በሬውን ወይም ሌላ ንብረቱን ሸጦ ነው የሚያስተምረው፤ ግን አራት ዓመት ሙሉ ለፍቶ ተምሮ ዲግሪህ አይሰራም የውሸት ነው ማለት ከህይወቱ ላይ አራትና አምስት ዓመት መንጠቅ ነው::

ዛሬ ላይ ነርሶቻችን ማደንዘዣ ወጋን ብለው ማድረቂያ የሚወጉት፣ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ድንጋይ የሚወረውሩት፣ የሚናድ ህንጻና ድልድይ የሚሰሩ ወጣቶችን የምናወጣው በዚህ ህገ ወጥ በሆነ አካሄድ ባስተማርነው ትምህርት ምክንያት ነው:: እንደዚህ ሰፋ አድርገን ካየነው ደግሞ ባለሀብቱ፣ መምህሩ፣ መዝጋቢው (ሪጅስትራሩ) ተጠያቂዎች ናቸው::

የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ዜጋው እራሱ ይጠይቃል፤ ሲቪል ሰርቪሱም ትንሽ ቆይቶ የወሰድከውን ደመወዝ መልስ ማለቱ አይቀርም፤ ከዚህ ከዚህ አንጻር ችግሩ እጅግ ሰፊና ከባድ ነው::

አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚደንቶች በምን አግባብ ነው ተጠያቂ የሚሆኑት ?

ዶክተር አንዷለም፦ ለምሳሌ አንድ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ከአንድ የግል ኮሌጅ ጋር በጥምረት ትምህርት እሰጣለሁ ሲል ኮሌጁን የመረጠበት መስፈርት ወይም አካሄድ ሊታወቅ ይገባል፤ በምን አግባብ መረጥከው ተብሎ ሲጠየቅም መልስ መስጠት መቻል አለበት:: አሁን ባለው አሰራር ግን ተማሪዎች ይመዘገባሉ የሂሳብ ቁጥር (አካውንት) ይከፈታል እዛ ውስጥ የሚገባውን ገንዘብ ፕሬዚደንቶቹ ይከፋፈላሉ:: ስለዚህ ያ ፕሬዚደንትም ሆነ የግል ኮሌጁ ባለቤት ተጠያቂዎች ናቸው::

ሌላው አንድ መምህር ከክልል ዩኒቨርሲቲ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ለሶስት እና ከዛ በላይ ሳምንት ሲያስተምር ይቆያል፤ ደመወዝ የሚበላበትንና የተመደበበትን ስራ ማነው የሚሰራለት፤ ይህ የሚያሳየው ለግል ጥቅም ሲባል እዛ የመንግስት ስራን ይበድላል የደሃ ልጆችንም ሜዳ ላይ ይበትናል ማለት ነው፤ ከዚህ አንጻርም ይህ መምህር ያለበት ፕሬዚደንትም ተጠያቂ ነው::

አዲስ ዘመን፦ መንግስት ግን የችግሩን ግዝፈት ተገንዝቦታል ብለው ያስባሉ? ከሆነስ እርምጃ ለመውሰድ ምን ያህል ዝግጁ ነው?

ዶክተር አንዷለም ፦ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከስር ያሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረስ ቁርጠኝነት ባይኖረው ኖሮ እኛም ወደዚህ አይነት አካሄድ ልንገባ አንችልም ነበር:: ነገ እነዚህ ወጣቶች ናቸው ተመርቀው ወጥተው የሚመራውን ህዝብ የሚያገለግሉት:: ስለዚህ መንግስት አካሄዱ እንዲስተካከልና ሥርዓት እንዲይዝ ይፈልጋል፡፡

ለምሳሌ እኔ ወደተቋሙ ከመጣሁና አደረጃጀቱ ከተቀየረ በኋላ ያስጠናነው ጥናት የሚያሳየው ውጤት በጣም አስደንጋጭ ነው:: ይህንን ውጤትም በቀጥታ ለሚኒስትሯ ለፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ነው ያቀረብነው፤ እርሳቸውም ወደሚመለከተው የመንግስት አካል አስገብተዋል፤ ከዛም ምን እና እንዴት አይነት እርምጃ ይወሰድ የሚለውን በሂደት ከፋፍለን አስቀምጠነዋል::

የመጀመሪያው ስራ ከላይ እንደተገለጸው የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች እንዲያውቁት ተደርጓል፤ ከዛ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በመጥራት ምን አይነት ወንጀል እየተሰራና በአገር ላይ ከፍተኛ ጥፋት እየደረሰ እንደሆነ በማስረዳት ምክር ቤቱ ያለውን ስልጣን ተጠቅሞ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀናል፡፡

ሌላው ሁሉንም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለሀብቶች፣ ሃላፊዎችና መገናኛ ብዙሃንን በመጥራት ያገኘነውን ውጤት እንዲያውቁት አድርገናል:: እነሱም እውነት ይህንን እየሰራን ከሆነማ ትውልድ እየገደልን ነው እርምጃ ይወሰድ አሉ:: እኛም “ጎሽ” ብለን ወጣን :: ከዛ ግን እከሌ ይህንን አድርገሃል እያልን በስም ስንሰጣቸው መጮህ ጀመሩ::

ከዚህ ሂደት በኋላ ነው እንግዲህ መንግስትም የጀመራችሁትን ቀጥሉ ብሎ ያዘዘው:: እኛም በአጭር ጊዜ ውስጥ 18 ካምፓሶችን ዘጋን:: መንግስት ተቋሙን በማደራጀት በኩል የሰው ሃይል እንጨምር ስንለው በመፍቀድ፣ ርምጃም ልንወስድ ነው ባልን ጊዜ ምንም ዓይነት ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ወደ ኋላ ሳይጎትቱን እርምጃ እንድንወስድ ድጋፍ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ አግዞናል:: ይህም ቢሆን ግን ስራውን ጀመርነው እንጂ አልጨረስነውም ወደ ክልል ገና አልወጣንም፡፡

አዲስ ዘመን፦ እነዚህ በብልሹ አሰራራቸው የተለዩ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግብረ መልሳቸው ምን ነበር?

ዶክተር አንዷለም፦ ወደ ክልል ገና ሳንሄድ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ብቻ 24 የሚጠጉ ችግር ያለባቸውን ኮሌጆች አግኝተናል እሱንም ይፋ አድርገናል:: በዚህ አካሄድ ደግሞ አብዛኞቹ ደስተኞች ነበሩ:: እስከ ዛሬም ስለለቀቃችሁን ነው እንጂ ሥርዓት እንይዛለን ወደሚልም መጥተዋል:: “የዛሬን ማሩን እንጂ ከዚህ በኋላ በህገ ወጥ መንገድ አንቀጥልም” ያሉም አሉ:: ግን መማር አለመማር የእኛ ስልጣን ባለመሆኑ ወንጀሉን ወደሚመለከተው አካል ይዘን እንሄዳለን ያ አካል ምን ሊወስን ይችላል የሚለውን በቀጣይ የምናየው ይሆናል::

እዚህ ላይ የስራ መንገዱ አንድ አይነት ባለመሆኑ ሥርዓት እናከብራለን ብለው የተጎዱም ነበሩና እነሱ እርምጃውን በጣም በደስታ ነው የተቀበሉት፡፡

አዲስ ዘመን ፦ በተለይም ኤጀንሲው ውስጥ የነበሩ የስራ ሃላፊዎችና በተዋዕረድ ያሉ ሁሉ ተጠያቂ መሆን የለባቸውምን?

ዶክተር አንዷለም፦ ችግሩን ወደዚህ ተቋም ብቻ ልንጠቀልለው አንችልም:: ኤጀንሲው ከፍተኛ የሆነ የአቅም ማነስ ነበረበት፡፡ አደረጃጀቱ የቀጨጨና በመላው አገሪቱ መድረስ የማይችል ነው፡፡ እኔ ወደዚህ ተቋም ስመጣ ይህንን ሁሉ ስራ የሚሰሩ 12 ሰራተኞችን ከሦስት መኪና ጋር ነው ያገኘሁት፤ በርግጥ አደረጃጀቱ በዚህ መልኩ እንዲቀጭጭ ያደረገው አካል የመጀመሪያውን ተጠያቂነት መውሰድ አለበት:: እዚህ ቦታ ላይ የተቀመጠው ሃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ በመሆኑ፡፡

ሌላው ተቋሙ ከፍተኛ የሆነ የሀብት እጥረት ነበረበት ፤ ይህ ችግር ስላለበት ግን ስራ አለመስራት ሳይሆን የነበረበት እንዲሟላለት የራሱን ጥረት ማድረግ፤ በዚህ የማይፈታ ከሆነ ደግሞ ከፍ ወዳለ አካል ማመልከት ይገባው ነበር ግን አልሆነም::

ሌላው ኤጀንሲው ችግሮቹን በሙሉ ብቻውን መውሰድ አለበት ብዬም አላምንም ፤ እንዲያውም ትልቁን ሀላፊነት መውሰድ ያለባቸው እራሳቸው የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን ፦ እነሱ ህገ ወጥ ሲሆኑ በቸልታ በማየቱ ብቻ ተጠያቂ አይሆንምን?

ዶክተር አንዷለም፦ ምክር ቤቱ በአዋጅ አቋቁሞ ያደራጀው ተቋም ስራውን ዘንግቶ ከተኛ በጣም አስቸጋሪ ነው:: ኤጀንሲው አካሄዳቸው አግባብ አለመሆኑን ማሳወቅ ነበረበት:: ይህንን ማድረግ ሲያቅተው ደግሞ ለመንግስት ተቸግሬያለሁ ብሎ እርዳታ ያስፈልገኛል ማለት ይገባው ነበር ግን አልሆነም::

አዲስ ዘመን ፦ አሁንስ ለቁጥጥርና ክትትል ስራው ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል?

ዶክተር አንዷለም፦ አሁን ለስራ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን አሟልተናል መኪኖችን በኪራይ እንጠቀማለን ፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ ከ 15 ቡድን በላይ በአንድ ጊዜ በተለያዩ አቅጣጫዎች መላክ ችለናል፤ በሙሉ እምነት መናገር የምችለው ኤጀንሲው አሁን ላይ በትክክል ስራውን ማከናወን የሚችልበት አቅም ላይ ነው ያለው፡፡

የምንቆጣጠራቸው ተቋማት እኮ በብዛትም፣ በብልጠትም፣ በመሽሎክሎክም ከኤጀንሲው በብዙ እጥፍ በልጠው ሄደዋል፤ ይሄንን የመገልበጥ ስራ ነው እየሰራን ያለነው:: ከዚህ አንጻር የእኛንም ድርሻ ወስደን በሚቀጥለው ጊዜ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ ተቋማት ይህንን መሰል ጨዋታ የሚጫወቱበት እድል አይኖርም:: ስርዓት ዘርግተናል አንዲት ስህተት ካገኘን በፍጥነት ተቋሙን እንዘጋለን፤ ባለሀብቱንም በወንጀል እንጠይቃለን፡፡

አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው በከፍተኛ ሁኔታ ስሙ ከሙስና ጋር ይነሳል፤ የቁጥጥር ባለሙያዎች በጥቅም ይያዛሉ ይባላልና ምን ይላሉ?

ዶክተር አንዷለም፦ አዎ የምንታማበት ሙስና ነው ፤ ምክንያቱም ትልቅ ቢዝነስ ያለበት ቦታ ስለሆነ:: እኔ ዛሬ ለአንድ ተቋም እውቅና ብከለክል አንድ አመት ሙሉ የቤት ኪራይ፣ የሰራተኛ ደመወዝና ሌሎች ወጪዎችን ያለምንም ገቢ ያወጣል፤ ስለዚህ በአቋራጭ ሰጥቶ ማምለጥን ይመርጣል፤ ሆኖም አሁን የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓታችንን ሁሉም ተቋማት በቀላሉ እንዲያውቁት አድርገናል:: በሌላ በኩልም አንድ ሪፖርት መቼ ተጀምሮ መቼ ይጠናቀቃል የሚለውን በጊዜ ገድበን አስቀምጠናል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ድርድር እንዳይኖር ለማድረግ ነው፡፡

ለምሳሌ ከዚህ ቀደም የነበረው ትልቁ ችግር ሪፖርት ይያዛል የመደራደሪያ እቅም ይኖራል ወደ ሙስና ውስጥ ይገባል:: አሁን ባለሙያው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ካልመጣ ተጠያቂ ነው:: በሌላ በኩል ይህ አይነቱ የሙስና አዝማሚያ የተቃጣበት ተቋምም ጥቆማ ቢያደርግ በእኛ በኩል የተዘጋጀ ማበረታቻም አለ:: በተጨማሪም ባለሙያዎቹ ተከታታይነት ያለው ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው ሃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ፤ ባለሀብቱም የግል ጥቅሙን ብቻ በማስቀደሙ የተጎዱ ዜጎችስ ካሳ አያስፈልጋቸውም ይላሉ?

ዶክተር አንዷለም፦ እንደዚህ ብዬ መናገር ባልችልም ዜጎች ናቸው ጉዳት ደርሶባቸዋል ጉዳቱ ደግሞ በራሳቸው ጥፋት ይሁን በተቋማት ማታለል ወይም በእኛ ቁጥጥር ማነስ ብቻ ዜጎች የሞራል ድቀት ደርሶባቸዋል፤ በቤተሰቦቻቸው፣ በልጆቻቸውና በስራ ባልደረቦቻቸው ፊት ሊዋረዱ ነው፤ ከዚህ አንጻር ምንም ቢመጣ ሊካሱ አይችሉም፡፡

መንግስት አንድ ፕሮፖዛል ይዞ ይቀርባል ብዬ ግን አስባለሁ ፤ ምክንያቱም እነዚህን ግለሰቦች ምን እናድርጋቸው? ፈተና ይሰጣቸው? እንደገና ይማሩ? ማነው ወጪውን የሚሸፍነው? ጊዜያቸውስ እንዴት ነው የሚካካሰው? የሚሉ ጥያቄዎች ስላሉ እነዚህን ወደፊት በሂደት ከመንግሰት ጋር የምንነጋገርባቸው ነው የሚሆኑት፡፡

ሆኖም የትምህርት ተቋማቱ በህገ ወጥ መንገድ ባስተማሩት እያንዳንዱ ተማሪ በወንጀልም በፍትሀብሔርም ይጠየቃሉ፤ የሞራል ካሳም የሚጠይቅ ካለ የሚክሱት ራሳቸው ይሆናሉ:: ምክንያቱም የዘረፉትም የሰረቁትም ራሳቸው በመሆናቸው፡፡

በቀጣይ በስም፣ በቁጥር፣ በተቋም፣ እንለያቸዋለን ከዛ በኋላ መወሰን ወደሚችል አካል ይዘን እንሄዳለን:: የኤጀንሲው ድርሻ የሚሆነው ስራህን ሰርተሀል አልሰራህም፤ በጎን ተደራድረሃል አልተደራደርክም ነው እርሱም ይታያል::

አዲስ ዘመን፦ ይህ አይነቱ ሁኔታ ወደፊትስ አይከሰትም ማለት ይቻላል?

ዶክተር አንዷለም፦ አብዛኞቹ ባለሀብቶች ያልገባቸው ልብስ እያጠበች፣ እንጨት እየለቀመች፣ በቆሎ እየጠበሰች ልጇን ለማስተማር የምትለፋ እናትን ገንዘብ እየሰበሰቡ ለልጆቻቸው እያበሉ እንዳሉ ነው፤ ለወደፊቱ መፍትሔ መፈለግ እንዳለበት እናምናለን:: ከ 2012 ዓ.ም ጀምሮም ጠንክረን እንሰራለን:: በዚህ ተግባር መቀጠል የሚፈልጉትን አካላት እየቀጣን ብቻ ሳይሆን እያጠፋንም ነው የምንሄደው:: ግን ደግሞ የ 21 ዓመት ታሪክ እንዴት እናስተካክላለን የሚለውን ነው እያየን ያለነው፡፡

አዲስ ዘመን ፦ በዚህ ችግር ውስጥ የገቡና ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው የተያዙ ተቋማት መረጃ መቼ ይወጣል?

ዶክተር አንዷለም፦ መረጃው መውጣት የነበረበት ከዛሬ ሁለትና ሦስት ወር በፊት ነበር:: ሆኖም ምላሹ በጣም ከባድና አገር የሚያተራምስ በመሆኑ ተቋማቱ ሊፈርሱ ስለሚችሉ ሁኔታው ደግሞ ወደ ክልል ሲሄድ በጣም አደገኛ ስለሚሆን መውጫ መንገዱን ከመንግስት ጋር እንምከርበት በሚል ነው ያዘገየነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ ከዚህ አንጻር ቀጣዩ 2012 የትምህርት ዘመን ምን ይመስላል ማለት እንችላለን?

ዶክተር አንዷለም፦ 2012 ዓ.ም የመንግስቱም የግሉም ሥርዓትን በተከለተለ መንገድ ይመራል የሚል እምነት አለኝ:: በዚህ መንገድ ውስጥ አልገባም የሚል ደግሞ አፋጣኝ እርምጃ ይወሰድበታል:: ይህንን ደግሞ ሁሉም በግልጽ እንዲያውቀው ሆኗል:: በአጠቃላይ 2012 ዓ.ም ህግና ሥርዓትን ያከበሩ ተቋማት ብቻ የሚቀጥሉበት፤ የመንግስት ተቋማትም ቢሆኑ ህግና ሥርዓትን አንከተልም ካሉ ፕሮግራሞቹን ከመዝጋት ጀምሮ ፕሬዚደንቶቹን በህግ ተጠያቂ እስከማድረግ የሚሄድ እርምጃ የሚወሰድበት ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የእኛ ክትትልና ድጋፍ ይጠነክራል፤ ከአይጥና ድመት ስራ ተላቀን ወደ ስትራቴጂካዊ መንገድ እንገባለን በዚህ ደግሞ የትምህርት ጥራትን እንዴት እናስጠብቅ? አግባብነቱንስ እንዴት እንፈትሽ ወደሚለው ስራ እንሄዳለን፡፡

በቀጣዩ ዓመት በህብረተሰቡ ውስጥ በመግባት በየጓዳው መሄድ አለብን ብለን የህዝብ ግንኙነት ዘርፋችንን በከፍተኛ ሁኔታ የማጠናከር ስራ ሰርተናል፤ በተለይም ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ዝግጁ የሆኑ ተማሪዎችን ለመድረስ ጥረት ከማድረግም በላይ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ላይ የሚያነቋቸውን አካላት እናሰማራለን:: በተከታታይም በህትመትና በኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙሃን ህዝቡ ዘንድ እንደርሳለን የሚል እምነትም አለኝ::

ሌላው የቀጣይ ዓመት ስራ እያንዳንዱ ተቋም በዓመቱ ሊያስተምር የመዘገባቸውን ተማሪዎች መረጃ ወደኛ የመረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) በአንድ ወር ውስጥ ያስገባል፤ ሲያስመርቅም ሴኔቱ ባጸደቀ ማግስት ወደ መረጃ ቋቱ መረጃውን እንዲያስገባ ይገደዳል:: እኛ ደግሞ ይህንን መረጃ ሙሉ በሙሉ ለቀጣሪ መስሪያ ቤቶች ክፍት እናደርጋለን:: የትኛውም ተቋም መረጃ ቋቱን ሳያይ ሰራተኛ አይቀጥርም ማለት ነው::

አዲስ ዘመን፦ በቀጣዩ ዓመት ኤጀንሲው ጥርስ ያወጣል ማለት ይቻላል?

ዶክተር አንዷለም፦ ይህንን ማለት የምትችሉት እናንተ ናችሁ፤ እኔ ልል የምችለው ጥሩ ነው ግን አሁንም በውጤት መለካት አለበት ነው:: ከችግሩ ሙሉ በሙሉ መላቀቅ ስንችል ያን ጊዜ ጥርስ አውጥተናል፣ ጎብዘናል፣ ጠንክረናል የሚለውን ደረጃ ልሰጠው እችላለሁ:: አሁን ግን ገና ምኑንም አልነካነውም::

ግን ጥርስ ላልሽው ነገር አዎ አሁን ረዘም ረዘም ያለ ዱላ ይዘናል፤ ከዚህ በኋላ ወደኋላ እንመለስ ብንል እንኳን የማንችልበት ሁኔታ ነው ያለው፤ ስለዚህ ወደፊት ገፍቶ ከማስተካከል ሌላ ምንም መውጪያ የሌለው ከመሆኑም ባላይ ወይ ይጠፋል ወይንም ይሰራል፤ ሌላ ምንም ምርጫ የለውም፡፡

ህብረተሰቡ እየጮኸ ነው ፤ቀጣሪ መስሪያ ቤቶች በሙሉ የሰራተኞቻቸውን የትምህርት ማስረጃ አረጋግጡልን እያሉ ይገኛሉ፤ ስለዚህ አሁን ያለው ሁኔታ ለተቋሙ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው:: ይህንን መስራት ካልቻልን ከህዝብና መንግስት ጋር እንጋጫለን ::

አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ ራሱን በዚህ ደረጃ አይቶ ለስራ ከተነሳሳ የድጋፍ ጉዳይስ ማን ምን ማድረግ አለበት?

ዶክተር አንዷለም ፦ እኔ የፈለኩትን ብናገር ከተለያየ አካል ድጋፍ ከሌለ አንድ ኢንች መራመድ አልችልም:: በመሆኑም የእኛ ትልቁ ድጋፍ ሊሆን የሚገባው መገናኛ ብዙሃኑ ህብረተሰቡን በማንቃትና በማትረፍ የሚያሳየው ነው፤ ሌላው የአደረጃጀት ለውጥ ጠይቀናል በመንግስት በኩል አፋጣኝ መልስ ሊያገኝ ይገባል፤ የመንግስት መዋቅሮች ደጋፊ መሆን አለባቸው፤ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው ላይ ምንም ወንጀል እንዳይሰራ ያሉትን አደረጃጀቶች መጠቀምና መቆጣጠር አለበት:: የፍትህ አካላት፣ ደንብ አስከባሪዎች፣ የክፍለ ከተማና የቀበሌ አመራሮች ከጎናችን ሊቆሙ ይገባል:: ህብረተሰቡም በአካባቢው የሚሰራን ወንጀል ማጋለጥ አለበት:: የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ራሳቸውን ከችግሩ በማራቅ ሌሎችን በመከታተልና በመቆጣጠሩ በኩል ሊደግፉን ይገባል:: በዚህ ደረጃ መቀናጀት ከተቻለ ስራው ቀለል ከማለቱም በላይ ኤጀንሲው ወደ ጥራትና አዳዲስ ሃሳቦችን ወደማምጣት ይገባል::

አዲስ ዘመን፦ በጣም አመሰግናለሁ::

ዶክተር አንዷለም፦ እኔም አመሰግናለሁ::

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 15/2011

እፀገነት አክሊሉ