ውስጥን ማፅዳት ሚዛናዊ አስተሳሰብና ተግባር እንዲኖር ያደርጋል

23

አዲስ አበባ፡- ውስጥን ማፅዳት የተሻለ የሚዛናዊ አስተሳሰብና ተግባር ባለቤቶች እንደሚያደርግ ተጠቆመ፡፡ ውስጥን ማፅዳት የማንፈልገውን ነገር ከውስጣችን ማፅዳት ሲሆን ልቦናችን የሚቆሽሸው መሰረታችን እውቀት ላይ ያልተመሰረተ ሲሆን ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አሕመድ ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር በውስጥ ጽዳት ምንነት ፣ አስፈላጊነትና አተገባበር ዙሪያ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በርካታ ሃሳቦች ከተወያዮቹ ተነስተዋል፡፡ውስጥን ማፅዳት የተሻለ የሚዛናዊ አስተሳሰብና ተግባር ባለቤቶች እንደሚያደርግም በውይይቱ ተነግሯል፡፡

ሰፈራችንን እያፀዳን ውስጣችን ያለውን ነገርም ማጽዳት ያስፈልጋል በሚል ማህበረሰቦቻችን በየሰፈራቸው ቡናና ሻይ እያፈሉ አካባቢን ብቻ ሳይሆን ውስጥን ማፅዳትንም መገንዘብ እንዲችሉ የተዘጋጀ ፕሮግራም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ በውይይቱ መጀመሪያ ጠቁመዋል፡፡

እድር፣ እቁብ እና መስሪያ ቤቶችን የመሳሰሉ የማህበረሰብ ልቦናዎች በማህበረሰብ ውስጥ በደል እንዳይፈፀም የሚከላከሉ በመሆናቸው ለውስጥ ፅዳት  ብንጠቀምባቸው ውጤት ያስገኛሉም ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ህብረተሰብ እቁብ እንደሚገባ ነገር ግን ወደ ባንክ እንደማይሄድ በውይይቱ የተነሳ ሲሆን፣ ይህ የሚያመለክተው ደግሞ ማህበረሰቡ ከባንክ ይልቅ ጎረቤቱን እንደሚያምን ነው፡፡ ይህ መተማመን በማህበረሰብ ደረጃ ቢያድግ እጅግ ጠቃሚ እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡

ሰው ንፁህ ለመሆን ራሱን ብቻ ሳይሆን አካባቢውንም ማፅዳት አለበት ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች ውስጣችንን ስናፀዳ ታሪካችን ውስጥ ያሉና ይዘን እየሄድናቸው ያሉትን ፍርሀት፣ ጭንቀት፣ ሳይሰሩ ማግኘት፣ ውሸት፣ ክህደት፣ ፍትህ አልባነት፣ ባለሰባራ ሚዛንነትን መሰል ነገሮችን አብረን ማጽዳት አለብን ብለዋል፡፡

በውይይቱ የተበዳይን በደል ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት መዘርጋት እና ላለፉ ነገሮች ይቅር መባባል ያስፈልጋል፤ በፍቅርና በእውነት ላይ የተመሰረተ ወደ እርቅ መዳረሻ ይቅርታን በማስገባት ደፋር መሆን አዲሱ ባህላችን ሊሆን ይገባልም ተብሏል፡፡ “የግልፅነት መጉደል የሴረኝነት አስተሳሰብን ያመጣል” ያሉት ተወያዮቹ በተደጋጋሚ የምንሰማቸው ውሸቶችና መጥፎ ነገሮች ተዋህደውን ትክክል አለመሆናቸውን መገንዘብ እስኪሳነን ድረስ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ ጠቅሰዋል፡፡

በውይይቱ እንደተነገረው ለሁሉም ድርጊት መሰረቱ ሀሳብ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ያገኘውን ሁሉ የሚበላ ሰው ጤናማ እንደማይሆን ሁሉ የሰማውን ሁሉ የሚወስድ ሰውም አእምሮው የተበላሸ ይሆናል፡፡ ሀሳቡ የተመረዘ ሰው ራሱን ብቻ ሳይሆን አካባቢውንም ያጠፋል፡፡

ስሜት ከላያችን ላይ ወጥቶ ሳይጋልበን በፊት ድርጊቶቻችን ለእኛ፣ ለማህበረሰቡና ለሀገር ጠቀሜታቸው ምን ያህል ይሆናል? የሚለውን ማሰላሰል እና ማመዛዘን ተገቢ እንደሆነም ተነስቷል፡፡

ራሳችን ላይ እንዲደረግ የማንፈልገውን ነገር ሌሎች ላይ አለማድረግ፣ ትንፋሻችንን ማዳመጥ፣ ትውልዱን የአንድነት እና መፈቃቀር ስሜት እንዲይዝ አድርጎ መቅረፅ፣ ግልፅነትን ማስፈን፣ ህዝብ እንዲያወራ ማድረግ፣ ክፉ ሀሳብን አለመስማት፣ ሌሎችን ማገልገል እና ያለንን ማካፈል የመሳሰሉ መልካም ነገሮችን በማዳበር ውስጥን ማፅዳት እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል፡፡

አዲስ ዘመን ነሐሴ 19 / 2011 

 ድልነሳ ምንውየለት