የህዝብ አገልጋይ ፓርቲና እጩ ለማቅረብ የሚያስችል ሕግ

24

 ሰሞኑን የጸደቀው የኢትዮጵያ የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 67/2011 በረቂቅ ላይ እያለ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ በቦርዱ ለመመዝገብ ከ10 ሺ በላይ ሰዎችን ማስፈረም አለበት የሚለው አንቀጽ ሲያወያይ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ አንዳንድ ወገኖች የተጠየቀው የደጋፊ ብዛት ይበዛል ሲሉ አንዳንዶች ደግሞ አይበዛም ሲሉ ተደምጧል፡፡ በወቅቱ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የተጠየቀው የደጋፊዎች ብዛት እንደማያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡ አንድ ሀገርን እመራለሁ ብሎ ራእይ ለሰነቀ ፓርቲ የ10 ሺ ሰዎች ፊርማ ማሰባሰብ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ነበር ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር የሰላም አደራዳሪ ቡድን ኃላፊ አቶ ጌታነህ ዘለቀ ‹‹ለምርጫ 10ሺ ደጋፊ አግኝቶ ለማምጣት ችግር የለብንም። ችግሩ በሀገሪቱ ያለ ተጨባጭ ሁኔታ ነው።›› ይላሉ፡ ፡ ችግሩን ለመፍታትም ከመንግሥት ጋር አብረው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር ደስተኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል። በየቦታው የሚሰሙ ሁከቶች ከተወገዱ ከሚጠበቀው በላይ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ይቻላል›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

ህዝባችን ጋር ሄደን በተረጋጋ መልኩ ማነጋገር ሃሳባችንን ማስረዳት የምንችልበት ሁኔታዎች ግን የለም የሚሉት አቶ ጌታነህ፣ ለእዚህም ከመንግሥት ጋር ሰላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት። ‹‹በየቦታው ያለው ነገር ወደ ወደ ተሻለ ሁኔታ ይመጣል የሚል ተስፋ አለን የባሰ አይመጣም ” ሲሉ ያስረዳሉ።

የከፋ አረንጓዴ ፓርቲ አቶ ወንድሙ ወዲኤሮ የአቶ ጌታነህን ሀሳብ በመጋራት “ ለእኛ ስጋት የሚሆነው ድጋፍ ለማሰባሰብ የመንገድ ተደራሽነት የትራንስፖርትና የበጀት ችግር ነው›› ሲሉ ያመለክታሉ፡፡ ከቦንጋ ከተማ ብቻ 4ሺ ድጋፍ ማሰባሰብ እንደሚችሉም ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከፋ ማለት ቦንጋ ከተማ ብቻ አይደለም። ፓርቲያችን የህዝብ ተቀባይነት ያለው ከዛም በላይ ቢጠየቅ ማድረግ የምንችልበት ሁኔታ አለን›› ሲሉ ተናግረው፣ የአካባቢው የመንገድ ችግር ብቻ እንዲፈታም ነው የጠየቁት፡፡ ይህ ችግር ካልተፈታ በየወረዳው ድምፅ የሚያሰባስቡ አካላትን የማሰማራቱ ስራ በጣም አሰልቺና አድካሚ እንደሚሆንም ያመለክታሉ።

አገር አቀፍ ፓርቲዎች የ10 ሺ ሰዎችን ፊርማ እንዲያሰባስቡ የሚጠበቁበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ፌዴራል ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ቅዳሜ በአምስተኛ ዙር አራተኛ ዓመት ሦስተኛ አስቸኳይ ስብሰባው የኢትዮጵያ የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 67/2011 ላይ በመወያየት በሙሉ ድምፅ ባጸደቀበት ወቅትም አነጋግሯል።

ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ የሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተሻሻሉትን የረቂቅ አዋጁን አንቀፆች በንባብ አሰምተዋል። የረቂቅ አዋጁ 149 አንቀፆች ቀርበው ጠንካራ ክርክር ተካሂዶባቸዋል።

በምርጫው በሀገር አቀፍ ፓርቲነት ለመወዳደር የሚፈልጉ ፓርቲዎች የ10 ሺ ሰዎችን የድጋፍ ፊርማ ለማሰብሰብ እንቸገራለን የሚል አስተያየት እየሰነዘሩ ነው የሚል ሀሳብ ቀርቧል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፓርቲዎቹ አንደ ሀገር አቀፍ ፓርቲ የ10 ሺ ሰዎችን ፊርማ ማሰባሰብ አይከብድም፤ ብዙ ጥረት አድርገው መሰብሰብ ይችላሉ የሚሉ አስተያየቶችም ተሰጥተዋል፡ ፡ የምክር ቤቱ አባል አቶ መሐመድ ሐሰን 10 ሺ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ከአፍሪካ በህዝብ ብዛት 2ኛ ለሆነች ሀገር ትንሽ መሆኑንና የሚያሳስብ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው ያነጋገረው ጉዳይ ደግሞ ወንድና ሴት ተወዳዳሪዎች አንድ ቦታ ተወዳድረው እኩል ድምፅ ቢያገኙ ሴቷ እንድታልፍ ይደረጋል የሚለው አንቀጽ ነው፡፡ በዚህ ላይ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ወንድና ሴት አንድ አካባቢ ተወዳድረው ዕኩል ድምፅ ካገኙ ሴት እንድታልፍ ይደረጋል የሚለው አንቀጽ ሴቶችን የሚያበረታታ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 35 ለሴቶች የተለየ ድጋፍ ይደረግላቸዋል እንደሚልም ጠቅሰው ድንጋጌውም ከዚህ ጋር እንደማይጋጭ ነው የተናገሩት፡፡ “እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች የመከሰት ዕድላቸው 0.01በመቶ ነው ያሉት ምክትል አፈጉባኤዋ፣ ‹‹ከ160 በላይ ፓርቲዎች ቢኖሩም አንድም የፓርቲ ሴት አመራር አይታይም” በሚል አስተያየታቸውን ገልጸዋል። ይህ ሴቶችን የሚመለከት አንቀጽ ብዙ ማከራከሩን ተከትሎም በምክር ቤቱ አባላት ድምጽ ተሰጥቶበት ወንድ ሴት እኩል ቢያመጡ ሴቷ እንደምታልፍ የሚደንግገው አንቀጽ ውድቅ ተደርጓል፡፡

ምክር ቤቱ ያጸደቀውን የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የምክር ቤቱ አባል ዶክተር አድሃና ኃይሌ እንዳሉት፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ ለረጅም ጊዜ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ባለፈው ሃምሌ በረቂቅ አዋጁ ላይ የህዝብ መድረክ ሲካሄድ ተሳትፈው እንደነበር አስታውሰው፣ ውይይቱ ጥንቃቄ ተደርጎበት የተካሄደ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ በፊት እንደተወያዩበት ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የተዘጋጀው ሰነድ አልደረሰንም በማለታቸውም ሌላ ቀነ ቀጠሮ ተደርጎ ውይይት መደረጉን ይገልጻሉ። በወቅቱ የምክር ቤቱ አባላት ሀሳብ ለመስጠት ዕድል እንዳልነበራቸው አስታውሰው፣ ‹‹የራሳችንን ሃሳብ ለመስጠት ባለፈው አርብ ውይይት አድርገናል›› የሚሉት ዶክተር አድሃና፣ በውይይቱ ላይ ቦርዱ ሠፊ ማብራሪያ መስጠቱን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ውይይቶቹ በየደረጃው ሲካሄዱ የቆዩት ለአንድ ድርጅት ተብሎ አይደለም›› ያሉት የምክር ቤት አባሉ፣ ምርጫው በትክክል እንዲካሄድ ለማድረግ ታስቦ ነው ብለዋል።

‹‹ለሴቶች በምርጫ ላይ የተለየ ዕድል ለመስጠት አንቀፅ 35 ስለድጋፍ የሚለው ሴቶች ቀደም ሲል በነበረባቸው ጭቆና በአዎንታዊ አድልዎ የማፅደቅ ነገር ነው፤ አዎንታዊ አድልዎ ችግር የለውም ፤ በትምህርት ላይ ወይም ወደ ኃላፊነት ማምጣት ሊሆን ይችላል›› ያሉት ዶክተር አድሃና ፣ይሄ የምርጫ ጉዳይ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩበት መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

በመሆኑም በምርጫ ህጉ ወንድ እና ሴት እኩል ድምጽ ካገኙ ሴቷ እንድታልፍ ተደንግጎ የነበረው ረቂቅ አንቀጽ ቢያልፍ ኖሮ ተሸነፍክ የተባለ ፓርቲ ፍርድ ቤት ይከስ ነበር ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ሴቶች ከወንድ ጋር ተወዳድረው ዕኩል ድምፅ ካገኙ ያልፋሉ የተባለው በድምጽ ብልጫ ውድቅ መደረጉን ያመለክታሉ።

ዶ/ር አድሃና ‹‹የጸደቀው አዋጅ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በጣም ጥሩ ነው፤ ሁሉም ይሄን አዋጅ በሚገባ ተገንዝቦ በአዋጁ መሠረት ዝግጅት አርጎ ከተንቀሳቀሰ ምርጫው ግሩም ፣ውጤቱም ጥሩ ይሆናል። ማንም ያሸንፍ ማን ህዝብ የመረጠው ተመራጭ ይሆናል ማለት ነው። ብዙ የተስተካከሉ ነገሮች አሉበት እና በጣም ጥሩ ነው የሚል ዕምነት አለኝ።” ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ሌላ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ አዲስ አንተነህ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የ2012 ምርጫን አስመልክቶ አጠቃላይ ህጉን በተመለከተ የተደረገው ውይይት እና የጸደቀው አዋጅ ምርጫው ፍትሐዊ ከማድረግ ትክክለኛ የህዝብ አገልጋይ ሊሆን የሚችል ድርጅት እንዲመጣና በዛ ልክም እጩዎችን ለማቅረብ የሚያስችል ሕግ ነው።

ቀደም ሲልም ባለፉት ቀናትም በእያንዳንዱ የህጉ አንቀጽ ላይ ሠፊ ውይይት እንደተደረገበት ጠቅሰው፣ በጸደቀበት እለትም በበለጠ ቀሩ በተባሉ ጉዳዮች ላይ ሠፊ ውይይት አድርገን መሻሻል የሚገባቸውን አንቀጾችም በዛው ልክ ተሻሽለው እንዲጸድቅ መደረጉን ተናግረዋል። ‹‹አዋጁ ሁሉንም አካል ወይም ድርጅት ሊያስደስት አይችልም፤ ህዝብን ማዕከል አድርገን ስናየው መሠረታዊው ጉዳይ ለሕጉ ተገዢ ሆነን እንድንሄድ የሚያስችሉ ጉዳዮች ናቸው። ይላሉ።

እያንዳንዱ ተፎካካሪ ድርጅት ከራሱ ፍላጎት አኳያ እንዲሻሻሉ የሚፈልጋቸው የራሱ አንቀጾች ይኖራሉ ያሉት ወይዘሮ አዲስ፣ በዋነኛነት ግን ሀገሪቱንና ህዝቡን የሚጠቅሙ አንቀጾች መጽደቃቸውን ይናገራሉ፡፡ ሀገር የሚመራ ፓርቲ ከ110 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ፍላጎት ማሟላት የሚችል ወደ ልማት የሚወስድ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፣ እሱን ታሳቢ ያደረገ ኃላፊነት እንደሚወስድ አድርጎ የምርጫ ተፎካካሪ መሆን እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ አዋጁ ጥሩ ምርጫ አካሂዶ የሚያገኘውን ቦታ በተገቢው መንገድ እንዲጠቀም መጠቀም እንደሚያስችልም ይናገራሉ።

እንደ ወይዘሮ አዲስ ገለጻ፤ ምርጫ የአንድ ወገን ተግባር ብቻ አይደለም፤ መንግሥት መወዳደሪያውን ያመቻቻል ፤ ህጉን ከማውጣት ጀምሮ ነፃ መሆኑን ያሳውቃል። ከዚህ ውጪ ለመወዳደር የሚመጣው ፓርቲ ራሱን አሟልቶ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ማንኛውም አካል ለሕግ ተገዢ መሆን የሕግ የበላይነትን ማክበር እና ያን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራት ይኖርበታል፤ ህዝቡም ጥሩ ዕጩዎች እንዲቀርቡ ያለው አስተዋጽዖ ሠፊ ነው።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ዕጩዎችን የሚያቀርቡት ከህዝቡ ውስጥ ነው። ህዝቡም ዕጩዎችን ሲመርጥ ይጠቅሙኛል የሚላቸውንና በስነ ምግባር ለቀጣይ አምስት ዓመታት ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ ዕጩዎች እንዲመርጡ ማድረግ ይኖርበታል፤ ይሄ ለማንም የሚሰጥ አይደለም። የፖለቲካ ፓርቲው ዕጩ ካቀረበ ህዝቡ በደንብ መገመገም መቻል አለበት፡፡ የሚጠቀመው ራሱ መራጩ ነው።

በምርጫው ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ መኖር እንዳለበት ጠቅሰው፣ ማንኛውም ተፎካካሪ ድርጅት ሀገርንና ህዝብን ታሳቢ ያደረገ ዕጩ እንዲያቀርብ፣ ኅብረተሰቡም ብዙ ተሳትፎና ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያለው የዕጩ ዝግጅት እንዲደረግ ግፊት ማድረግ አለበት። ሲሉ ወይዘሮ አዲስ ያገልፃሉ። ለእዚህ ደግሞ አዋጁ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው ያስገነዘቡት፡፡

አዲስ ዘመን ነሀሴ 21/2011

 ኃይለማርያም ወንድሙ