አርአያነቱ የታየበት የ”በጎነት በሆስፒታል‘ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት

19

በጎ ፍቃደኝነት እውቀትን፣ ገንዘብንና ጉልበትን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ማበርከት ነው። አገልግሎቱም በሞራል እና በሌሎች የድጋፍ አይነቶችም ይገለጻል። አገልግሎቱ ፆታ፣ ዘር፣ ቀለም፣ ብሄር፣ ሃይማኖት፣ ፖለቲካና ሌሎች የግል አመለካከቶችን ሳይጨምር በግለሰቦች አልያም በቡድኖች ይሁንታ የሚደረግ መልካም ተግባር ሲሆን ፣ ከህሊና እርካታ ውጪ ገንዘብ አልያም የተለየ ጥቅም የሚገኝበት አይደለም።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በዓለም ዙሪያ በየአመቱ በርካቶችን የሚያሳትፍና በኢትዮጵያም አድማሱን በማስፋት እየጨመረ ነው። በዘንድሮው የክረምት ወቅትም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በአዲስ አበባ ከተማም በተለያዩ ዘርፎች የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች እየተሰጡ ሲሆን፣ በጤናው ዘርፍም በአስራ ሁለት የመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን በማሳተፍ ለአንድ ወር ያህል አገልግሎቱ ሲሰጥ ቆይቷል።

ሰሞኑንም ከአዲስ አበባ ከተማ የወጣቶችና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ፣ ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የተውጣጡ አካላት በጥቁር አንበሳ፣ ዘውዲቱና ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታሎች በመገኘት ወጣቶቹ እያከናወኗቸው ያሉ የበጎ ፍቃድ ስራዎች ተጎብኝተዋል።

በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት የኬሚካልና ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዋ ወጣት ሮዛ ሽተ በክረምት ወቅት እቤት ከመቀመጥ ለምን ህዝቡን አላገለግልም በሚል ስሜት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመሳተፍ ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣችው። ሮትራክ በተሰኘ ክለብ አማካኝነት በአገልግሎቱ የመሳተፍ እድል እንደገጠማት ትናገራለች። ህሙማንን መርዳትና መንከባከብ የሚያስደስትና የአእምሮ እርካታ የሚሰጥ ነው የምትለው ወጣት ሮዛ፣ ይህም በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ለመሳተፍ ይበልጥ እንደገፋፋትም ታስረዳለች።

በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የአንድ ወር ቆይታዋ ለህሙማን መንገድ የማሳየት፣ ካርድ የማውጣት፣ ራጅ የማስነሳት፣ህሙማንን የመንከባከብ፣ ላብራቶሪ ውስጥ ያሉ ስራዎችን የማገዝና ሌሎችንም ስራዎች አከናውናለች።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በገንዘብ ሊተመን የማይችል ትልቅ ደስታና ስጦታ የሚገኝበት ተግባር መሆኑን የምትገልፀው ወጣቷ፤ በሆስፒታሉ ቆይታዋ የአእምሮ እርካታ ብቻ ሳይሆን ትልቅ ትምህርት እንደቀሰመችበትም ትጠቁማለች። ትንሽ ሰጥቶ ብዙ የሚወሰድበት ስትልም ነው አገልግሎቱን የምትገልጸው። ሌሎች ወጣቶችም በዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መሳተፍ እንዳለባቸው መክራ፣ ሁሉም ሊሳተፍበት እንደሚገባም ትጠቁማለች።

በአድማስ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዓመት የዲግሪ ተማሪው ወጣት ሶፎኒያስ መርድ፣ ዩኒቨርሰቲው ባቋቋመው የወጣቶች የበጎ ፍቃድ ቡድን አማካኝነት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመሳተፍ ነው ከአንድ ወር በፊት ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል የመጣው።

በሆስፒታል ቆይታውም በፅኑ ታመው አልጋ የያዙና አቅመ ደካማ የሆኑ ህሙማንን ከሌሎች በጎ ፍቃደኞች ጋር በመሆን ተንከባክቧል። በተለይም መድሃኒት ለህሙማን የማምጣት፣ ክፍያ የመፈፀምና የህሙማኑን ንጽህና የመጠበቅ ስራዎችን ሰርቷል።

አገልግሎቱ ከልብ በመነጨና በፍላጎት ላይ በመመስረት ለሰዎች አስፈላጊውን ሁሉ እርዳታና ድጋፍ በነጻ ማድረግን እንደሚጠይቅ ወጣት ሶፎኒያስ ይገልጻል። እነ ወጣት ሶፎኒያስን በአገልግሎቱ ወቅት የተለያዩ ችግሮች ገጥመዋቸዋል። ከእነዚህም መካከል አንዱ በአንዳንድ ታማሚዎች በኩል በጎ ፍቃደኞችን እንደ ትንሽ ልጅ በመቁጠር አገልግሎታቸውን ለመቀበል ዝግጁ አለመሆን ነው። ሁሉም የአገልግሎቱ ጥቅም ገብቶት ተባባሪ ቢሆን መልካም መሆኑን ተናግሮ፣ በበጎ ፈቃደኞች በኩልም የተረጂዎችን ስሜት መረዳት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል። በጎ ፍቃደኝነት ከፍተኛ የአእምሮ እርካታን እንደሚሰጥ እና ሌሎች ወጣቶችም በአገልግሎቱ መሳተፍ እንዳለባቸውም ይመክራል።

ወጣት አዶናይ አለማየሁ በብራይት ፊውቸር አካዳሚ የ9ኛ ክፍል ተማሪና የአካዳሚው ስካውት ማህበር አባል ነው። ወገኑን በአቅሙ ለመርዳትና ክፍተት ያለበትንም ቦታ ለመሙላት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ወደ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ነው ከአንድ ወር በፊት የመጣው። አገልግሎቱን ለመስጠት ያነሳሳው ዋናው ምክንያትም ሆስፒታሉ በአብዛኛው እናቶች የሚወልዱበት በመሆኑና አቅሙ በፈቀደ ሁሉ ለእናቶች ድጋፍ ለማድረግ ካለው ፍላጎት የተነሳ መሆኑንም ይጠቁማል።

ለወጣት አዶናይ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሃሳብ ወይም በአቅም ለሌሎች ብሩህ መንገድ ማሳየት ነው። እርሱና ጓደኞቹ በመሆን የተለያዩ መጽሃፎችን ለሆስፒታሉ ለማበርከት አስበዋል። ለንባብ የተዘጋጀውን ስፍራ ከወዲሁ እያፀዱና ቀለምም እየቀቡ መሆናቸውን ይናገራል።

‹‹የሆስፒታሉን ካርድ ክፍል እንደ አዲስ አደራጅተናል፤ ሌሎች ስራዎችንም አከናውነናል›› የሚለው ወጣት አዶናይ፣ በሆስፒታሉ የተለያዩ አትክልቶችን እርሱና ጓደኞቹ ለመትከል ሃሳብ እንዳላቸውም ይጠቁማል። በበጎ ፍቃድ አገልግሎት መሳተፍ የሚፈልጉ ወጣቶች በየትኛውም አጋጣሚና ቦታ ሙከራ ማድረግ እንደሚችሉና ለዚህም ከእነርሱ የሚጠበቀው ፍላጎት ብቻ መሆኑንም ያመለክታል። ሌሎች ወጣቶችን አገልግሎቱን እንዲቀላቀሉ ለማነሳሳትም በቴሌግራም አማካኝነት የጋንዲ መታሰቢያ በጎ ፍቃደኞች ቡድን በማቋቋም መልእክት እያስተላለፉ መሆናቸውንም ይናገራል።

የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ታሪኩ ደሬሳ በሆስፒታሉ እየተሰጠ ያለው የክረምት ወቅት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በበጎ የሚታይና በአርያነትም የሚጠቀስ ነው ይላሉ። በጎ ፍቃደኛ ወጣቶቹም ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ ወዲህ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ይናገራሉ።

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በጎ ፍቃደኞቹ ወደ ሆስፒታሉ የመጡት በቀይ መስቀልና በአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፍቃደኞች ማህበር አማካኝነት ነው። 70 የሚሆኑ በጎ ፍቃደኞች ተሰማርተው አገልግሎት እየሰጡ ናቸው።

ሆስፒታሎች ሰው ተቸግሮ የሚመጣባቸውና በርካታ አገልግሎቶችም የሚሰጡባቸው ቦታዎች መሆናቸውን የሚናገሩት ዶክተር ታሪኩ፣ ከዚህ አኳያ ተጠቃሚዎችን ሙሉ በሙሉ ማርካት እንደማይቻል ይናገራሉ። በጎ ፍቃደኞቹ ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ ወዲህ በድንገተኛ እንዲሁም በካርድ ክፍል፣ ህመምተኞች በሚተኙባቸው ክፍሎችና በላብራቶሪ አካባቢዎች ላይ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። የህክምና ሙያ እየተማሩ ያሉ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችም ሆስፒታሉ ድጋፍ በሚያስፈልገው ቦታ ላይ ሁሉ በመገኘት እየረዱ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ይገልፃሉ።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በጎ ፍቃደኞቹ በሆስፒታሉ ውስጥ የጥገና፣ ፅዳትና ግቢ የማስዋብ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ። የባዮ ሜዲካል ተማሪዎችም ከሆስፒታሉ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የህክምና እቃዎችን የመጠገንና የማስተካከል ስራዎች አከናውነዋል። በዚህም የሆስፒታሉ ሰራተኞችም ሆኑ ተገልጋዮች ደስተኛ ሆነዋል። በጎ ፈቃደኞቹም በራሳቸው ውስጣዊ እርካታ እየተሰማቸው ይገኛል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶቹ ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ በሆስፒታሉ የሚሰጡ ሁሉንም አገልግሎቶች እንዲያውቁ ተደርጓል። በሆስፒታሉ ቆይታቸው በምን አይነት አገልግሎቶች ላይ እንደሚሳተፉና በተሳትፏቸው ጊዜ ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውና መረጃ ሲፈልጉ ማንን ማነጋገር እንዳለባቸው ገለፃ ተደርጎላቸዋል ። በተጨማሪም በሆስፒታሉ አስተባባሪ ቡድን ተቋቁሞ የበጎ ፍቃድ ስራውን እያገዘ ይገኛል። አሻሚ በሆነ የህክምና እወቀት ላይም በተመሳሳይ የማስተማር ስራ ተሰርቷል።

‹‹የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ መበረታታት ያለበትና በክረምት ወቅት ብቻ ሳይሆን በበጋ ወቅትም ተጠናከሮ መቀጠል የሚኖርበት ነው›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህም በየደረጃው ለህብረተሰቡና ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ። ህብረተሰቡም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በእጅጉ እንደሚያስፈልግ መረዳት እንደሚኖርበት ጠቅሰው፣ ግንዛቤው ከመጣ በኋላ ደግሞ ሂደቱን የሚያደራጅና የሚመራ አካል መኖር ይገባዋል ይላሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ የወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይለሰመአት መርሃጥበብ እንደሚሉት፤ ቢሮው ለአንድ ወር በ12 የመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ ሲያካሂድ የቆየውን የክረምት ወቅት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አፈፃፀምን ከጤና ሚኒስቴርና ከከተማው ጤና ቢሮ ሃላፊዎች ጋር በመሆን ተመልክቷል። በዚህም ቢሮው በተለይ በጥቁር አንበሳ፣ ዘውዲቱና ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታሎች ወጣቶች እያደረጉ ያሉትን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አርያነት ያለው መሆኑን አረጋግጧል።

በተለይም በወጣቶቹና በታማሚዎቹ በኩል ያለው ግንኙነት እጅግ ጠንካራ እንደነበረ የሚጠቅሱት ሃላፊው፣ ህሙማንም ለበጎ ፍቃደኞቹ አክብሮታቸውንና አድናቆታቸውን የገለፁበት እንደሆንም ለማየት መቻሉን አስታውቀዋል። ለወደፊትም በተለያዩ የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች ውስጥ በበጎ ፍቃድ ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ልምድ መገኘቱን ይጠቁማሉ ።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶቹ እንደየሆስፒታሎቹ ባህሪያት ይለያያል የሚሉት ሃላፊው፣ ሆስፒታሎቹ እንዲሰራላቸው በሚፈልጉት ስራ መሰረት ወጣቶቹ ህሙማንን የመንከባከብ፣ ካርድ ክፍሎችን ዳግም የማደራጀት፣ ህንፃዎችን ቀለም የመቀባትና ሌሎችን አገልግሎቶችንም ሰጥተዋል ሲሉ ያብራራሉ። ተመሳሳይ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም በአሁኑ ወቅት የተሰጡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን በመቀመር በስፋት በሌሎችም የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች ለአብነትም በትምህርት ቤቶች እንዲሰጡ ጥረት እንደሚደረግም ያመለክታሉ።

በዘንድሮው የክረምት ወቅት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በተለያዩ ዘርፎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ 1 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ዜጎች የተሳተፉበት ሲሆን፣ መርሃ ግብሩ መስከረም 17 ቀን 2011 ዓ.ም መጠናቀቁንም ለማወቅ ተችሏል። ሌሎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ሳይቋረጡ ዓመቱን ሙሉ እንደሚከናወኑ ከአዲስ አበባ ከተማ የወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስባበሪያ ቢሮ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 21/2011

 አስናቀ ፀጋዬ