ቤት ነጥቆ፤ ምትክ ቤትም ነፍጎ – ፍትህ ወዴት ?

10

60ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚጠጉት አባት አቀርቅረው ሲራመዱ አንገታቸውን ሰበር ያስደረገ ችግር እንዳጋጠማቸው መገመት ይቻላል። ወዳለሁበት እየቀረቡኝ ሲመጡ ወረቀቶች የታጨቁበት ሰነድ ማስቀመጫ ላስቲክን በቀኝ እጃቸው ጠበቅ በማድረጋቸው አያያዛቸው ምን ያክል አስፈላጊ ነገር ቢሆን ነው በሚል ትኩረቴን ሳበው። አጠገቤ ደረሱና ገፃቸውን እንድመለከት ዕድል ሰጡኝ። ዓይናቸው ያቀረረው ዕንባ ከድክመት ይልቅ ያሳለፉትን መከራና ልባቸው የተሸከመውን እልህ አሻግሮ ያሳያል። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ምን ልረዳቸው እንደምችል ጥያቄ አቀረብኩላቸው።

ሥማቸው አቶ አለማየሁ ማሞ በቀለ እንደሚባል ካስተዋወቁኝ በኋላ አባታቸው ጫካ መንጥረው ባቀኑት መንደር የሠሩትን ቤት በግፍና በማን አለብኝነት እንደተነጠቁ ጠቆሙኝ። የኋሊት በትዝታ ተጉዘው በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ዘመን አማኑኤል መሳለሚያ አካባቢ ዓለም ጤና መንደር ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ፈረጃ ወንዝ ድልድይ አጠገብ ሠርተውት የነበረውንና ከደርግ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች አዋጅ 47/67 የተረፈ ቤታቸው የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተርም እንዳለው ያስታውሳሉ። ለሥራ ጉዳይ ይርጋ ጨፌ ደርሰው ሲመለሱ በአሁኑ አጠራሩ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት የሚገኘው የቤት ቁጥር 338 የሆነው የግል መኖሪያ ቤታቸው ለሌላ ግለሰብ ተሰጥቶ ይጠብቃቸዋል።

ለምን? ብለው የሚመለከተውን አካል ሲጠይቁም በቤቱ ምትክ ማካካሻ እንደጠየቁና ጥያቄያቸውም ተቀባይነት አግኝቶ በቀድሞ የካ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ 15 ቀበሌ 26 ውስጥ የሚገኘው የቤት ቁጥር 737 እንደተሰጣቸው ይገለጽላቸዋል። ነገር ግን እርሳቸው ለቤታቸው ምትክ ያልጠየቁ በመሆኑ ይህንን ለማሳወቅ ብዙ ርቀቶች ቢጓዙም ሊሳካላቸው አልቻለም። ይብስ ብሎ ባልጠየቁትና ባልወሰዱት ቤት ማካካሻ ምትክ ቤት እንደተሰጣቸው ይነገራቸዋል። ሁኔታው ግርታንና ብስጭት የፈጠረባቸው አቶ ማሞ የውስጣቸውን አምቀው በዚሁ ቀበሌ የሚያውቋቸው ሠዎች ጋር ተከራይተው እየኖሩ ስለቤታቸው የሚመለከተውን አካል መጠየቅ አማራጭ አድርገው ይወስዳሉ። ይሁን እንጂ ጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኝ ቤት እያላቸው ቤት አልባ ሆነው ከአራት ቤቶች በላይ በኪራይ ይንከራተታሉ።

‹‹አውቆ የተኛ…›› ይሆንና ጉዳዩን የተመለከቱ ቢሮዎች ሁሉ ተገቢውን ምላሽ ሳይሰጧቸው ይቀራሉ። ፍትሕን ፍለጋ እንዲሁ እንደባከኑም በ1995 ዓ.ም ያልተመለሱ ጥያቄዎቻውን እንደሸከፉ ያሸልባሉ። እርሳቸውን ተከትለው ሕጋዊ ወራሽነታቸውን በፍርድ ቤት ያረጋገጡት ልጃቸው አቶ አለማየሁ የተለያዩ ተቋማት በሮችን ደጅ እንደጠኑ ይናገራሉ። ለ30 ዓመታት በጋምቤላ፣ ደቡብ ክልልና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የቤተሠባቸውን ሕይወት ለማሻሻል ደፋ ቀና ሲሉ መኖራቸውን በመግለጽም፤ ይህም ጉዳዩን በቅርብ ሆነው እንዳይከታተሉ ወደኋላ እንደጎተታቸው ይናገራሉ። አለአግባብ ተወስዷል ስለሚሉት የአባታቸው ቤትም የሚያስረዱ ማስረጃዎችን በማውጣት ጉዳዩን በዝርዝር ያስረዱን ጀመር።

ከአንደበታቸው

አቶ አለማየሁ፤ ወላጅ አባታቸው ቀድሞ ከፍተኛ ስድስት ቀበሌ 03 የነበረው በአሁኑ ወቅት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከንጉሱ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በግል ጥረታቸው በሠሩት መኖሪያ ቤታቸው ይኖሩ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። አባታቸው በነበረባቸው ቤተሰባዊ ችግር ምክንያት በግቢያቸው ያከራዩ የነበሩትን አንድ የግል መኖሪያና ሁለት ደጃፍ ቤቶችን በ1963 ዓ.ም ለግለሰብ በወለድ አገድ ውል ለተወሰነ ጊዜ ያስይዙታል። በዚህ መካከል በ1967 ዓ.ም ንጉሱን በተካው ስርዓት በወጣው የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች አዋጅ 47/67 መነሻነት ቀደም ሲል ይከራዩ የነበሩትን ቁጥር 339 እና 340 የሚል መለያ የተሰጣቸው ቤቶች በመንግስት ይወረሳሉ። በዚህም ለራሳቸው ይኖሩበት የነበረው ዋና ቤታቸው አድርገው የመረጡት 338 ግን መኖሪያቸው በመሆኑ በወቅቱ ከነበረው የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የባለቤትነት ሰነድ እንደተቀበሉበት ይገልፃሉ።

ሚኒስቴሩ በቤቱ ላይ የግል ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር ለአባታቸው ቢሰጥም እንኳ በቤቱ ገብተው መኖርም ሆነ መጠቀም እንዳይችሉ በወቅቱ የነበረው የቀበሌ አመራር ያለአግባብ ቤቱን በማከራየቱ ቤት አልባ ሆነው እንዲቆዩ ያርጋቸዋል። ይህንኑ ከአዋጅ ውጭ የተወሰደና እንዲከራይ የተደረገ ቤት እንዲመለስላቸው አቤቱታ ሲያቀርቡና ፍትሕን ሲጠይቁም ቆይተዋል። ‹‹ቤቱ ይመለስልኛል›› በሚል ተስፋም እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ የቦታና የቤት ግብር ሲገብሩበት የቆዩ ቢሆንም ቤቱን ማስመለስ ሳይችሉ እንዲሁ ፍትሕን እንደተጠሙ ለዘላለም ላይመለሱ አሸልበዋል በማለት በሐዘን ሁኔታውን ያስረዳሉ። የቀበሌው አስተዳደር በሠራው እኩይ ድርጊትም ባለመብቶች ፍትሕ ተዛብቶባቸው እንዲኖሩ ሲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች ተከራይ ሆነው ተጠቃሚነታቸው ሊረጋገጥላቸው ችሏል።

የተወረሰውና ከአዋጅ ውጭ ተወስዶ የሚከራየውን ቤት ቁጥር 338 መኖሪያ በተመለከተ ለወረዳ ስምንት አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም ቤት ማስተዳደር እንጂ መመለስ የሚያስችል ሥልጣን እንደሌለው ምላሹን እንደሰጣቸውም አቶ አለማየሁ ይናገራሉ። የክፍለ ከተማው የሕዝብ ቅሬታ ሰሚ ስለ ጉዳዩ በደብዳቤ ለቀረበለት ጥያቄ ቤት ቁጥር 338 ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ሕጋዊ ውል ለተሰጠው ግለሰብ እየተከራየ እንዳለ ጠቅሶ፤ ለሟች ግን የማካካሻ ቤት በየካ ክፍለ ከተማ የቤት ቁጥር 737 እንደተሰጠ ቅሬታ ሰሚው የወረዳውን ቤቶች አስተዳደር ምላሽ ገልፆ በደብዳቤ እንዳሳወቃቸው ያስታውሳሉ። ሆኖም ግን አባታቸው አቶ ማሞ በተጠቀሰው ቀበሌ የተጠቀሰው መኖሪያ ቤት ያልተሰጣቸውና ማካካሻም ጠይቀው የማያውቁ ሲሆን፤ በአሁኑ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ኖረው በመጨረሻም በሕመም ምክንያት የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ላይ ይኖሩበት በነበረ ቤት ቁጥር 432 ሕይወታቸው ማለፉን አቶ አለማየሁ ይናገራሉ።

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት የቤቶች አስተዳደር ቤቱ ከተወረሰ በኋላ እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ በማን ይተዳደር እንደነበርም መግለጽ እንዳልቻለ ይጠቁማሉ። ውል የተሰጠውም ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በመሆኑ በመካከል የነበሩት የ15 ዓመታት ክፍተቶች ሊጣሩና ሊመረመሩ የሚገባ እንደሆነ ነው የሚጠቁሙት። አባታቸው ለተወረሱ ቤቶቻቸው ወርሃዊ አበል ተፈቅዶ አበሉን ሲጠቀሙ የቆዩ መሆኑንም በማስታወስ፤ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ግን የአበሉን ጉዳይ ለማጥራት ባደረጉት ጥረት በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም በቂርቆስ ወረዳ ስምንት ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት በሚዘጋጀው የክፍያ ሰነድ(ፔይሮል) ላይ የአባታቸው ሥምና ይኖሩበት የነበረው 737 የቤት ቁጥር ተጠቅሶ በመገኘቱ ሕይወታቸው ካለፈ 15 ዓመታት በኋላ ሥማቸው በመክፈያ ሰነዱ ላይ እንዴት ሊሰፍር ቻለ የሚለው ጥያቄን እንዳጫረባቸው ያሳውቃሉ። ይህም አበሉን የሚጠቀም አካል ሊኖር ይችላል የሚል ጥርጣሬን ይፈጥርባቸዋል። ማካካሻ እንደተሰጠ በማስመሰል ተጠቃሚ የሆነ አካል ሊኖር ይችላል በሚል ከክፍለ ከተማዎቹ ቅሬታ ሰሚ ጽሕፈት ቤቶች እስከ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ድረስ ቢያቀኑም ለጥያቄያቸው ግን ተገቢውን ምላሽ የሚሰጣቸው ሊያገኙ አልቻሉም። በአሁኑ ወቅት ጥያቄውን የሚያቀርቡት አቶ አለማየሁ ለዓመታት የደረሰባቸውን እንግልት የሚመልስና የሚክስ ተግባር ባይኖርም ያፈሰሱትን እንባ ግን መንግስት ትክክለኛ ፍትሕን በመስጠት እንዲያብስላቸው ይጠይቃሉ።

በእጃቸው የሚገኙ ሰነዶች

ከኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር የከተማ ቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ቁጥር 6/18911 የሆነ ደብተር በእጃቸው ቤቱ የአባታቸው ስለመሆኑ ለማረጋገጫነት ከያዟቸው ሰነዶች መካከል ይገኛል። በደብተሩ ቤቱ በሸዋ ክፍለ አገር በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ስድስት ቀበሌ 03 እንደሚገኝና የቤት ቁጥሩ 338 መሆኑን ያመለክታል። ይዞታውም በምሪት በ1948 ዓ.ም እንዳገኙት ያመላክታል። በተመሳሳይ ቀበሌ ላይ ይገኙ የነበሩትን የቤት ቁጥር 339 እና 340 ማስረከባቸውንና ማስረጃዎቹ ተጣርተውም ደብተሩ ታኅሣስ 22 ቀን 1980 ዓ.ም መሰጠቱን ያሳያል።

ሚያዝያ 4 ቀን 1982 ዓ.ም የቀረጥ ቴምብር የተለጠፈበትና አቶ ማሞ ለቀበሌው የፃፉት ማመልከቻ ሌላኛው የተመለከትነው ሰነድ ነው። በማመልከቻቸው ላይ እንደሰፈረው የቤት ቁጥር 338 ለመኖሪያ በሚል እንደሠሩትና በቀበሌው የሚገኙ 339 እና 340 በትርፍ ቤት ለቀበሌው መመለሳቸውን አስፍሯል። ይሁን እንጂ ለመኖሪያ የመረጡት ቤት በሌላ ግለሰብ በመያዙ ቤታቸው ተለቆላቸው እንዲገቡበት 15 ዓመታትን ሙሉ ሲያመለክቱ መቆየታቸውንም ያስረዳል። ይሁን እንጂ ቤቱ ሊለቀቅላቸው ባለመቻሉ ለእንግልት መዳረጋቸውን ገልፀው፤ ለግለሰቡ ቤት ካልተገኘ ሲኖሩበት በነበረው ከፍተኛ 15 ቀበሌ 19 የቤት ቁጥር 432 ሊዛወር እንደሚችል በመግለጽ የግል ቤታቸው እንዲዛወርላቸው መጠየቃቸው ከማመልከታቸው ይታያል።

ነሐሴ 23 ቀን 1987 ዓ.ም በክልል 14 ዞን አንድ ለወረዳ ስድስት መስተዳደር ጽሕፈት ቤት የአቶ ማሞ ባለቤት ወይዘሮ ደብሪቱ አሳምነው ቤቱ እንዲመለስላቸው ያስገቡት አቤቱታ ከሰነዶቹ መካከል አግኝተነዋል። በባለቤታቸው አቶ ማሞ ሥም የተመዘገበ በወረዳ ስድስት ቀበሌ 03 ክልል ውስጥ የቤት ቁጥር 339 እና 340 የሆኑትን በትርፍ ቤትነት በወጣው አዋጅ መሠረት ማስረከባቸውን ያቀርባሉ። ከዚህ ውጪም 338 የቤት ቁጥር ለራሳቸው የመኖሪያ ቤትነት መምረጣቸውን ያሳያል። የግል ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ያገኙበት ይኸኛው ቤት ላይ ግን በግል ቀበሌው ሠው አስገብቶ ስለነበር እንዲለቀቅላቸው በየጊዜው ቢያመለክቱም ሰሚ አካል አልተገኘም። በዚህም ቤት እያላቸው ቤት አልባ ሆነው መውደቃቸውን በመግለጽ፤ ‹‹አንድ ሠው ለመብቱ ማስረጃ እያለው በመብቱ ግን ተጠቃሚ ካልሆነ የተሰጠው ማስረጃ ወይንም በጠቅላላው ማስረጃ ዋጋው ምን ላይ ነው?›› ሲሉ መሞገታቸውም ከማመልከቻቸው ይነበባል።

አቶ አለማየሁ፤ በ 02/13/2010 ዓ.ም ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ችግራቸውን ዘርዝረው መፍትሔ እንዲሰጣቸው የጠየቁበት፣ በ2011 ዓ.ም በዘጠነኛው ወር ላይ ለከንቲባው ጽሕፈት ቤት ላቀረቡት ቅሬታ ተገቢው ምላሽ ባለማግኘታው በፋክስ የላኩት ቅሬታ እንዳለ የሚያመላክትና በርካታ ቤቱን የተመለከቱ ሰነዶች በእጃቸው እንደሚገኙም ለመመልከት ችለናል። በተመሳሳይ በቤት ቁጥር 338 የቦታ ግብር መክፈላቸውን የሚያሳዩ ደረሰኝ ግልባጮችን ተመልክተናል። በሰነዶቹም ሌሎቹ ቤቶች ኪራይ ቀመስ በሚል በአዋጅ ሲወረሱባቸው 338 የቤት ቁጥር ግን ለግል መኖሪያቸው መርጠውት ማረጋገጫ ደብተር ካገኙበት ከ18/6/1980 ዓ.ም እስከ 8/12/1992 ዓ.ም ድረስ የቦታ ግብር መክፈላቸው ይታያል።

በቀን 25/12/2009 ዓ.ም የየካ ምድብ ችሎት አቶ አለማየሁ የአቶ ማሞ በቀለን ልጅነትና ወራሽነት እንዳፀደቀው ሰነዶች ያሳያሉ። በተያያዘ በጉዳዩ ላይ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በመዝገብ ቁጥር አ/ከ/ክ/ከ/ወ/8/ቤ/አስ/ጽ/ቤት572/10 በቀን 18/07/2010 ዓ.ም ለክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ለሕዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽሕፈት ቤት የሰጠው ምላሽ ይገኛል። የአቶ አለማየሁን አቤቱታ መነሻ በማድረግ የክፍለ ከተማው የሕዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽሕፈት ቤት በቁጥር አ/ከ/ክ/ከ/የህ/ቅ/አ/ማ/ጽ/ቤት/532/10 እና በ 21/06/10 በተፃፈ ደብዳቤ የቤት ቁጥር 338 በምን አግባብ ወደ መንግስት እንደዞረ፣ የተወረሰ ከሆነ ደግሞ በቅጽ 003 መኖር አለመኖሩን፣ ከመቼ ጀምሮ መንግስት እንደያዘው በአጠቃላይ ቤቱ ወደ መንግስት የገባበት ምክንያት የሚያስረዱ ማስረጃዎችን በማጣራት ከማብራሪያ ጋር እንዲልኩ መጠየቃቸውን አስፍሯል።

ወረዳውም ቤቱ በቀድሞ ከፍተኛ 15/ቀ/26/3/1619/79 እና በቀን 3/11/79 በአዲስ አበባ አጠቃላይ የከተማ ነዋሪዎች ማሕበር ከፍተኛ 15 ቀበሌ 26 ጽሕፈት ቤት በፃፉት ደብዳቤ አቶ ማሞ በ06/01/03 ታጠቅ ቀበሌ ውስጥ ቀድሞ ከሰሯቸው ቤቶች ውስጥ 338 የተመዘገበውን ቤት የመኖሪያ ቤት ማረጋገጥ በቅጽ 004 ሞልተው መምረጣቸውን ገልፀው፤ በማካካሻነት በቀበሌው የሚገኘውን የቤት ቁጥር 737 በግል ቤት ውስጥ እንደገቡና ግለሰቡ በዚህ የግል መኖሪያ ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ የተፃፈ ደብዳቤ በማስረጃነት ያለ መሆኑ፣ ሌላ ግለሠብ ደግሞ በቤት ቁጥር 338 ውስጥ በየወሩ 12 ብር ከ50 ሣንቲም በመክፈል ከ1996 ዓ.ም የተዋዋሉት የቤት ኪራይ ውል በማስረጃነት ያለ መሆኑ ቤቱ በመንግስት ቤትነት እየተዳደረ መሆኑን ማሳያ እንደሚሆን ጠቅሶ መፃፉ ይታያል፤ ቅጽ 003 በተመለከተ ግን ከማህደራቸው ላይ ማግኘት እንዳልቻለ

 ገልፆ በፃፈው ደብዳቤ ያስረዳል።

የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽሕፈት ቤት በቁጥር አ/ከ/ክ/ከ/የሕ/ቅ/አ/ማ/ጽ/ቤት/657/10 በ4 ሚያዝያ 2010 ዓ.ም ለአቶ አለማየሁ ላቀረቡት ቅሬታ ምላሽ የሰጠበት ደብዳቤ ይገኛል። በዚህም የቤት ቁጥር 338 ምትክ በማካካሻነት በየካ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ከፍተኛ 15 ቀበሌ 26 የቤት ቁጥር 737 የወሰዱ ስለመሆኑ ወረዳው የገለፀ መሆኑን በመጠቀስ፤ ከተሰጠው ምላሽ የተለየ በተቋሙ ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ ማሳወቃቸው በደብዳቤው ይታያል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ በቁጥር አአ/ቤ/አስ/ኤ/4/13/11 በ06/07/2011 ዓ.ም ለአቶ አለማየሁ ምላሽ የሰጠበት ሰነድ ለመመልከት ችለናል። በዚህም በወረዳው በቀድሞ ቀበሌ ሦስት ዓለም ጤና መንደር የቤት ቁጥር 338 አለአግባብ በመወሰዱ እንዲመለስላቸው በ06/07/2011 ዓ.ም መጠየቃቸውን ያስረዳል። ሆኖም ግን ‹‹የቤት ይመለስልኝ›› ጥያቄውን ኤጀንሲው የማይመልሰው ሲሆን፤ የተሰጠው ሥልጣን የመንግስት ወይንም የቀበሌ ቤቶችን የማስተዳደር እንጂ የመመለስ አለመሆኑ እንደተገለፀላቸው ደብዳቤው ያሳያል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽሕፈት ቤት በቁጥር አአ/ከፅ/84/7.7/17 በ14/08/2011 ዓ.ም ለአቶ አለማየሁ ምላሽ መስጠቱን የሚያሳይ ሰነድ ነው። በደብዳቤው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለአንድ ቀንም ቢሆን የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ያስተዳድረው የነበረ መሆኑ ማረጋገጫ የቀረበበት ቤት በመንግስት ይዞታነት የሚቀጥል ይሆናል የሚል መመሪያ በመኖሩ ከወረዳው የመንግስት ቤት ለመሆኑ የተፃፈ መረጃ በመኖሩና ከቤቶች አስተዳደር ቢሮ የተፃፈላቸው መልስ በመመሪያው መሠረት በመሆኑ ቅሬታው አግባብነት ስለሌለው ማስተናገድ እንደማይችል ማሳወቁ ይነበባል።

ማካካሻ ሰጪው

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ዋና የሥራ ሒደት ቡድን መሪ አቶ ጡሀዬ ሀሰን፤ የቤት ቁጥር 338 አስመልክቶ የሚገኘውን ማህደር በማገላበጥ ምላሽ ሰጥተውናል። በዚህም በማህደሩ ውስጥ በ1996 ዓ.ም የተቀመጠ ሰነድ እንደሚያሳየው የቀበሌ ቤት እንደሆነ ነው። በአዋጅ 47/67 የተወረሱ ቤቶች የግል የነበሩበት ሁኔታ ቢኖርም ሲወረሱ ግማሹ የግል የተወሰነው ደግሞ የመንግስት ይሆናል በማለትም በወቅቱ የነበረውን አሠራር ያብራራሉ። በዚህም በተመሳሳይ የቤት ቁጥር የግልና የመንግስት ቤቶች ሊገኙ እንደሚችሉም ነው የሚጠቁሙት። በዋናነት ግን አስተዳደሩ የሚያየው ሕጋዊ ውል አለው? ወይንስ የለውም? የሚለውን ነው። በዚህም መሠረት ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ከመንግስት ጋር የኪራይ ውል ገብቶ ሲጠቀሙበት የቆዩ ግለሰብ እንዳሉ ነው።

አቶ ማሞ በቤት ቁጥር 338 ላይ የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር ያላቸው መሆኑን በአዲስ አበባ አጠቃላይ የከተማ ነዋሪዎች ማሕበር ምክር ቤት ለቀበሌ 03 ገልፆ በመፃፍ፤ ለመንግስት ግብር መክፈል የሚያስችላቸው መረጃ ለሚፈለገው ክፍል እንዲፃፍላቸው የጠየቀበትን ደብዳቤ በመመልከት የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር ለግል እንጂ ለቀበሌ ቤት እንደማይሰጥ አቶ ጡሀዬ ይገልፃሉ።

አቶ ጡሀዬ፤ በማህደሩ ካሉት ሰነዶች መካከል ግለሰቡ ትርፍ ቤት እንደነበራቸውና በወቅቱ የነበረው አስተዳደር ቤቱን በአዋጅ 47/67 እንደወረሰውም ማስረጃዎችን በመመልከት ይናገራሉ። አቶ ማሞ በወረዳው የሚገኘውን 338 ቤት ምትክ ደግሞ በማካካሻነት በአሁኑ ወቅት የሚኖሩበትን 737 ቤት ቁጥር የግል ቤት እንደተሰጣቸው መረጃዎች ያመላክታሉ ሲሉ ሰነዶቹን በማገላበጥ ይገልፃሉ። ስለዚህም አባታቸው ቤቱን በማካካሻነት የወሰዱ በመሆናቸው በወረዳው የሚገኘውን የቤት ቁጥር 338 በመባል የሚታወቀው ቤት ላይ የመብት ጥያቄ ማንሳት አይችሉም። የዚህ ቤት ጉዳይም እንባ ጠባቂ እንዲሁም የተለያዩ የሕዝብ ቅሬታ ሰሚ አካላት ጋ ደርሶ ወረዳው ምላሽ መስጠቱንም ነው የሚናገሩት።

በአዋጅ 47/67 ኪራይ ቀመስ ቦታዎችን መንግስት ይወርስ እንደነበር የሚታወቅ ቢሆንም የቤት ቁጥር 338 ግን አዋጁን ያወጣው ወታደራዊው የደርግ መንግስት ተገርስሶ የኢህአዴግ መንግስት አዋጁን በአዋጅ ከሻረ በኋላ መሆኑን በመግለጽ፤ ይህ ሊሆን የቻለበትና እንዴት ወደ መንግስት ሊዞር ቻለ? በሚል ለአቶ ጡሀዬ ጥያቄ አቀረብንላቸው። እርሳቸውም ‹‹ይህንን በወቅቱ የነበረው አስተዳደር በምን መልኩ እንደሠራ አይታወቅም። ይህ ለእኔም ግልጽ አይደለም›› ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተውናል።

አቶ ጡሀዬ፤ በማህደሩ የተገኙት ሰነዶች የቤት ቁጥር 338 የመንግስት ሆነው ሌላ ግለሰብ ውል እንደተዋዋሉባቸው የሚያሳይ እንጂ በምን አግባብ ከግል ወደ መንግስት እንደዞረ የሚሳይ ማስረጃ የለም ይላሉ። ከዛ ቀደም ብሎ ደግሞ የግል ነበር የሚያሰኙ ማስረጃዎችም በማህደሩ ይገኛሉ። አንድ ሠው የግልም የመንግስትም ሁለት ቤት ሊይዝ ስለማይችል አንዱን ማስረከብ ይጠበቅበታል። ግለሰቡ 737 የቤት ቁጥር በማካካሻነት በመውሰዳቸውም 338 የቤት ቁጥርን መንግስት ተረክቦ 737 የቤት ቁጥር ተሰጥቷቸዋል።

በወረዳው በተገኘው የቀድሞ ማህደር ላይ 1996 ዓ.ም ድረስ ቤቱን የተመለከቱ ማስረጃዎች የታሰሩ ሲሆን፤ ከዛ በኋላ ግን መረጃዎችን በዘመናዊ መንገድ በተደራጀ ሁኔታ ስለሚገኙ በኮምፒውተር ላይ በመመልከት፤ በአሁኑ ወቅት እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ከመንግስት ላይ 338 ቤትን የተከራዩት ግለሠብ የኪራይ ውላቸውን ማደሳቸውን በመመልከት አቶ ጡሀዬ አሳውቀውናል።

ማህደሩ ምን ያሳያል?

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት አስተዳደር ግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ክትትልና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት የሚገኘው ማህደር ውስጥ ቤቱን አስመልክቶ በተለያዩ ወቅቶች የተሰነዱ ማስረጃዎች እንደሚገኙ ለመመልከት ችለናል። ከእነዚህም መካከል በ3/11/79 ዓ.ም በቁጥር ከ15/ቀ26/3/1619/79 በአዲስ አበባ አጠቃላይ የከተማ ነዋሪዎች ማሕበር የከፍተኛ 15 ቀበሌ 26 ጽሕፈት ቤት ለከፍተኛ 06 ቀበሌ 03 ከነማ ጽሕፈት ቤት የላከው ደብዳቤ ይገኝበታል።

በደብዳቤው መስከረም 21 ቀን 1969 ዓ.ም በቁጥር 484/15/3ታጠ/69 በፃፋት ደብዳቤ መሠረት አቶ ማሞ በ06/01/03 ታጠቅ ቀበሌ ውስጥ ቀድሞ ካሠሯቸው ቤቶች ውስጥ በ338 ቤት ቁጥር ውስጥ የተመዘገበውን የመኖሪያ ቤት ማረጋገጫ በቅጽ 004 ሞልተው መምረጣቸውን ገልፀው በማካካሻነት በቀበሌው በሚገኘው የቤት ቁጥር 737 በግል ቤት ውስጥ ሊገቡ መቻላቸውን ያሳያል።

በቁጥር ከ6/5/አሰበ/2/5/03/80 በቀን 9/6/1980 ዓ.ም ምክር ቤቱ ለቀበሌ 03 ጽሕፈት ቤት የላከው ደብዳቤ ይገኛል። አቶ ማሞ ለቤት ቁጥር 338 ግብር መገበር እንዲችሉ የቀበሌውን ጽሕፈት ቤት ማስረጃ እንዲሰጣቸው የካቲት 3 ቀን 1980 በተፃፈ ማመልከቻ ጠይቀው ሊተባበራቸው አለመቻሉን ያስነብባል። ቤቱ የአቶ ማሞ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ከከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር የተሰጣቸው የባለቤትነት ደብተር በእጃቸው ስለሚገኝ የመንግስት ግብር መክፈል የሚያስችላቸው መረጃ ለሚፈለጉት ክፍል እንዲፃፍላቸው ምክር ቤቱ ለቀበሌው አሳውቋል ።

በቁጥር ከ6/ቀ03/081/80 በቀን 7/03/80 የቀበሌ 03 ጽሕፈት ቤት ለከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር በፃፈው ደብዳቤ 338 ባለቤት የሆኑት አቶ ማሞ ቤቱን መምረጣቸውንና የቤት ቁጥር 339 እና 340 የተመዘገቡትን ቤቶች አስረክበው አበል የሚበሉበት መሆኑን ከሒሳብ ሹም ማረጋገጣቸውን ያሳያል። ግንቦት 27 ቀን 1980 ዓ.ም በቁጥር ከ6/8/አሰበ/2/5/03/80 ምክር ቤቱ ለቀበሌ 03 በላከው ደብዳቤ ደግሞ የቤት ቁጥር 338 የባለቤትነት ደብተር ያወጡበት በመሆኑ ቤቱ እንዲለቀቅላቸው ሚያዝያ 19 ቀን 1980 ዓ.ም በማመልከቻ መጠየቃቸውን ጠቅሶ፤ በመመሪያው መሠረት አንድ ቤታቸው እንዲለቀቅላቸው ይደረግ ማለቱ ይታያል። በ1996 ዓ.ም ሌላ ግለሰብ ቤቱን ከመንግስት በኪራይ የተዋዋሉበት ሰነድም ልንመለከት ችለናል።

አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት በቀድሞ ከፍተኛ ስድስት ቀበሌ 03 በቀበሌው ይገኝ የነበረው የአቶ ማሞ የግል መኖሪያ የሆነው 338 የቤት ቁጥር ምትክ ማካካሻ ተስጥቷቸዋል ወዳለው የካ ክፍለ ከተማ አመራን። የክፍለ ከተማው ቤቶች ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ቤቱ የሚገኝበት የቀድሞ ከፍተኛ 15 ቀበሌ 26 በአሁኑ ወቅት ወደ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር እንደተሸጋገረ ገልፆልናል። እኛም የክፍለ ከተማውን ምላሽ በመያዝ ወደ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት አስተዳደር ቤቶች ጽሕፈት ቤት አቀናን።

ጽሕፈት ቤቱ ቤቱን በዘመናዊ መንገድ በኮምፒውተር ላይ ባስቀመጣቸው መረጃዎች መካከል ቢፈልግልንም ሊገኝ ግን አልቻለም። ለዚህም ደግሞ ቤቱ የግል ከሆነ በጽሕፈት ቤቱ ሊገኝ እንደማይችልና ቦታው ድረስ ወርዶ ማየት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሞናል። ይህንን ምላሽ መሠረት በማድረግም የወረዳው ምክትል ሕዝብ ግንኙነትና ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ረቢራ ኢጃራ ቤቱን ለመፈለግ ቦታው ድረስ ወርደዋል። ቤቱን ካገኘነው በኋላም በአሁኑ ወቅት በቤቱ የሚኖረው ማን ነው? እንዴትስ አገኙት? የመንግስት ነው ወይንስ የግል የሚሉ ጥያቄዎችን ይዘን የቤቱን ባለቤት አነጋግረናል።

737 የማን ነው?

ወይዘሮ ማርታ አለማየሁ፤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በወረዳ ስምንት በቀድሞ አጠራር ከፍተኛ 15 ቀበሌ 26 የቤት ቁጥር 737 ውስጥ ነዋሪ ናቸው። ቤቱ የግላቸው እንደሆነና በሕይወት ከሌሉት ከእናታቸው ወይዘሮ መዓዛ ታመኑ እንዲሁም አባታቸው አቶ አለማየሁ አሻግሬ በውርስ ያገኙት ሲሆን፤ ይዞታውን ለረጅም ዓመታት እንደኖሩበትና ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዳለ በማውጣት ያሳዩን ጀመር።

ከቤቱ ባለቤት የተገኘ ሰነድ

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የውዝፍ ሥራዎችና ይዞታ አስተዳደር አገልግሎት የሽግግር ጊዜ መስተንግዶ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በቁጥር ቂ/ክ/ከ/17/15/8825/04 በቀን 27/11/04 ዓ.ም ለወረዳ ስምንት ገቢ አወሳሰንና አሰባሰብ ክፍል የፃፈው ደብዳቤ ወይዘሮ ማርታ ካሳዩን ሰነዶች መካከል አንዱ ነው። በዚህም በወረዳው የሚገኘውን የቤት ቁጥር 737 ከእነ ወይዘሮ መዓዛ ታመነ ለማግኘታቸው በ18/10/2004ዓ.ም በፃፉት ማመልከቻና ከአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቁጥር የቂ/ት/መቁ2629/03 በ17/05/2003 ዓ.ም እንደተረጋገጠ ያሳያል። በመሆኑም በካርታ ቁጥር cks 17/15/4566/01 በሥማቸው እንደተዛወረ ያሳያል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደርና የግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን ተነፃፃሪ የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ ሴሪ ቁጥሩ 020282 በሆነው ሰነድ ላይ የወይዘሮ መዓዛ ታመኑና የተጋሪ ሥም ደግሞ አቶ አለማየሁ አሻግሬን ሥም አስፍሯል። በዚህ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ላይም ቦታው በውርስ በ1963 ዓ.ም እንደተሰጠ ያመለክታል።

ማጠቃለያ

ቅሬታ የተነሳበት የቤት ቁጥር 338 የሚገኝበት ወረዳ በመሄድ ማረጋገጥ እንደቻልነው፤ ቤቱ በአንድ ወቅት የግል መኖሪያ ቤት እንደነበር ነው። ነገር ግን በማህደሩ ላይም ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳይኖር እንዴት እንደሆነ ባልታወቀ መንገድ ወደ መንግስት ዞሯል። ከግል ወደ መንግስት እንዲዞር የተደረገውም የደርግ ወታደራዊ መንግስት ካወጀው የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች አዋጅ 47/67 በኋላ መሆኑም እንዴት ሊሆን ቻለ? የሚል ጥያቄን የሚያጭር ነው። በሌላ በኩል በምትክ ማካካሻነት ተሰጥቷቸዋል የተባለው በቀድሞ የካ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ 15 ቀበሌ 26 የሚገኘው የቤት ቁጥር 737 እንደተባለው ለአቶ ማሞ ወይንም ለቅሬታ አቅራቢው አቶ አለማየሁ አባት በምትክ ማካካሻነት የተሰጠ ሳይሆን ሌሎች ግለሰቦች በ1963 ዓ.ም በውርስ ያገኙት እንደሆነ በአካል ወርደን መመልከት ችለናል። ይህ ከሆነ ታዲያ በምትክ ተሰጥቷል የተባለው ቤት የታለ?

ማረሚያ

ነሐሴ 8 ቀን 2011 ዓ.ም በፍረዱኝ አምድ ላይ ይዞታው የማን ነው? በሚል ርዕስ የታጠቅ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ከግለሰቦች ጋር የነበራትን የይዞታ ክርክር የተመለከተ ዘገባ መስራታችን ይታወሳል፡፡ በዘገባው ላይ ቤተክርስቲያኒቷ አለአግባብ ከሕጋዊ ይዞታዋ ላይ ለግለሰቦች ተቆርሶ እንደተሰጠባት የምትገልጸውን ቅሬታ ያስነሳውን ቦታ ምስል ከቤተክርስቲያኒቱ ምስል ጋር ተደራርቦ /በሞንታጅ/ መሠራቱ መረጃ ያዛባል ሲሉ የፍርድ ባለመብቶች ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ በመሆኑም ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እየጠየቅን ከላይ እንደሚታየው ታርሟል፡፡

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ነሀሴ 22/2011

ፍዮሪ ተወልደ