ልጓም ያጣው የስደተኞች የባህር ላይ እንግልትና ህልፈት

17

በዓለም ላይ ሰዎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፣ ለትምህርት፣ ለጉብኝት፣ ለንግድ ለመሳሰሉ ምክንያቶች በህጋዊ መንገድ ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር ይዘዋወራሉ። በአንጻሩ፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በአገር ውስጥ በሚፈጠር የእርስ በእርስ ጦርነት ሳቢያ ከሚደርስባቸው አደጋ ራሳቸውን ለማዳን፤ በሙስና በተዘፈቁ እና ሰብአዊ መብትን በሚጥሱ መንግስታት የተማረሩ፤ እንዲሁም እራሳቸውን ከድህነት ቀንበር ለማላቀቅ በማለም በህገወጥ መንገድ የሚሰደዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዓለማችን ሕዝቦች በስደት የግፍ ጽዋ እየተጎነጩ ይገኛሉ።

በተለይ ደግሞ አፍሪካውያን በአገራቸው ተዋርደውና ተንቀው የበይ ተመልካች ከሆኑበት የአገዛዝ ስርዓት እና በገዢዎቻቸው ከሚደርስባቸው በደል ተላቅቀው ለነገ የተሻለ ኑሮ በማለም፤ በህገወጥ መንገድ የቀይ ባህርንና የሜድትራኒያንን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ይሰደዳሉ።

በዚህም በአፋኝ መንግስታት ጭቆና መንስኤም ይሁን የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከሀገር ሀገር የሚደረገው አሰቃቂው ጉዞ የአባባይና ጨካኝ ደላሎች እኩይ ተግባር ተጨምሮበት ህገወጡ የሰዎች ዝውውር ሰብአዊ መብት የሚረገጥበት፣ የሰው ልጅ ክብር የሚዋረድበትና ግለሰቦች ያለፍላጎታቸው የሚደፈሩበት ነው።

በተጨማሪም፤ ለበርካታ ቀናት የሚላስ የሚቀመስ፤ እንዲሁም ህክምና እና መጠለያ ጭምር አጥተው ሲንገላቱ የቆዩ ስደተኞች፤ በህገወጥ አዘዋዋሪ ወንበዴዎች ተጨማሪ የገንዘብ ክፍያ እየተጠየቁ በአደባባይ በግፍ የሚገደሉበት፤ ከነሕይወታቸው ወደ ባህር ውስጥ የሚወረወሩበት፤ በርካቶች በባርነት እና በጉልበት ብዝበዛ የሚማቅቁበት፤ አምራች ወጣት ዜጎች ሳይቀሩ የባህር እና የበረሃ ሲሳይ ሆነው የትም ወድቀው የሚቀሩበት ነው። በአንጻሩ፤ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ የሆኑ ግፈኞች እና ወንጀለኞች የገቢ ምንጫቸው አድርገው የተንደላቀቀ ኑሮ የመሰረቱበት ነው።

በዚህ አሰቃቂ ጉዞም ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ 20 ሺህ ስደተኞች የጣሊያንን ድንበር ተሻግረው አውሮፓውያኑን ሲቀላቀሉ፤ 20 ሺህ የሚገመቱት ደግሞ በጉዞው ወቅት ሕይወታቸውን እንዳጡ መረጃዎች ያመለክታሉ:: በእንዲህ አይነቱ እንግልት ውስጥም ሆነው ተስፋ ሰንቀው በአጋጣሚም ይሁን በእድል የባህር እና የበረሃ ጉዞ የቀናቸው ስደተኞች የሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ሰለባ የሚሆኑበት አጋጣሚው ሰፊ ነው። ከዚህም ባሻገር፤ በሄዱበት አገር ባይተዋር ሆነው ከአገር እንዲወጡ ሲጎተጎቱና የአሰቡትን የህልም እንጀራ ጋግረው ሳይበሉት በመጠለያ ካምፖችና በእስር ቤት ሕይወታቸውን ሲገፉ ይታያል።

በአሮጌ እና አስተማማኝ ባልሆኑ መርከቦችና ጀልባዎች ለቁጥር የሚታክቱ ስደተኞችን ጭኖ በባህር ላይ የሚደረግ ጉዞ እጅግ አደገኛና አያሌ የሰው ሕይወትን የቀጠፈ ሲሆን፤ ብዙውን ጊዜ በጉዞውም የመርከቦች የቴክኒክ ብልሽት እና የባህር ላይ ወንበዴዎች ድንገተኛ ጥቃት ስለሚያጋጥም በየዕለቱ ብዙ ተጓዦች ሕይወታቸውን ያጣሉ። በአጠቃላይ፤ የሕይወት አድን ሠራተኞችን ጨምሮ ወንጀልን እና የባህር ላይ ውንብድናን የሚቆጣጠሩ ፖሊሶች ቁጥር አናሳ መሆኑ የባህር ላይ ጉዞውን ይበልጥ የከፋ ያደርገዋል።

እንደሚታወቀው፤ ሕገ ወጥ የሰዎች ደላሎች ስደተኞችን ወደ አውሮፓ በህገ ወጥ መንገድ ለማስኮብለል ሲፈልጉ፤ አጠቃላይ የስደት ጉዞው አልጋ በአልጋ እንደሆነ አስመስለው ያታልላሉ። በተጨባጭ ሲታይ ግን እነዚያ ደላላዎች፤ የሰው ልጅ ልክ እንደ እንስሳ መንጋ በማይረባ መኪናና ጀልባ አጭቀው የሰው ሕይወት እንደ ቅጠል ያረግፋሉ። በዚህም እአአ በ2019 ብቻ ወደ 900 የሚጠጉ ህገ ወጥ ስደተኞች በሜዲትራንያን ባህር ሰጥመው መሞታቸው የዚህ አረመኔያዊና እኩይ ተግባር ውጤት ነው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በዚህ አሰቃቂ ጉዞ ሕይወታቸውን ካጡ አፍሪካውያን ስደተኞች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ሊቢያን እንደመሸጋገሪያ ተጠቅመው በሜድትራኒያን ባህር ለመሻገር ሲሞክሩ የነበሩት ናቸው። ሊቢያም የቀድሞ መሪዋ ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ በ2003 ዓ.ም ለ42 ዓመታት ከቆዩበት ዙፋናቸው በሕዝባዊ ዓመፅ ተወግደው ከተገደሉ ማግስት ጀምሮ ታጣቂ ቡድኖች እንደቅርጫ ስጋ የተከፋፈሏት ሲሆን፤ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህም በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቃ ትገኛለች፡፡

ሊቢያ በሁለት ጦር ሰባቂ ኃይሎች መካከል በሚደረገው ፍልሚያ ዜጎቿ የከፋ ሰብዐዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ የተጋረጠባቸው ሲሆን፤ አገሪቱም የወንበዴ መፈንጫ በመሆን የተለያዩ ወንጀሎች ተበራክተውባት ትገኛለች። በተለይ ይቺን አገር እንደ ድልድይ በመጠቀም የሜዲትራኒያንን ባሕር አቋርጠው ምዕራባውያኑን ለመቀላቀል እንደዋነኛ መሸጋገሪያ እየተጠቀሙ የሚገኙት አፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እያሻቀበ የመጣ ሲሆን፤ በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ብቻ ከአርባ የሚበልጡ ስደተኞች በሊቢያ ባህር ዳርቻ እንደሰመጡ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) በድረ ገጹ አስታውቋል።

የዩኤንኤችሲአር ቃል አቀባይ ቻርሊ ያክስሌይ እንደገለጹት፤ ስደተኞቹን አሳፍራ የነበረችው ጀልባ ሰምጣ አርባ ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ 60 የሚሆኑትን ማዳን ተችሏል። እነዚህ ከሞት የተረፉ ስደተኞችም ከትሪፖሊ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው የባህር ዳርቻ ከተማ አል ኮምስ ከትመዋል። የአገሪቷ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ከአካባቢው ዓሣ አጥማጆች ጋር በመተባበር እነዚህን ስደተኞች ከተጋረጠባቸው የሞት አደጋ መታደግ መቻላቸውን ተናግረዋል።

የደረሰውን አስከፊ አደጋ ተከትሎ በማዕከላዊ ሜዲትራንያን የዩኤንኤችሲአር ልዩ መልዕክተኛ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አይቀሬ አደጋዎች ናቸው የሚለው አስተሳሰብ ሊወገድ ይገባል። በባህር ሕይወታቸውን እየቀጠፉ ያሉትን ማዳን ብቻ ሳይሆን ከመጀመሪያውም ሕይወታቸውን እንዲህ ያለ አደጋ ላይ ጥለው የሚያሰድዳቸው ጉዳይ ምንድን ነው? የሚለውን መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል ብለዋል።

የዩኤንኤችሲአር ቡድንም ከአደጋው ለተረፉት የህክምናና የሰብአዊ ርዳታዎችን በመለገስ ላይ መሆናቸውን ድርጅቱ በድረገጹ ያስታወቀ ሲሆን፤ በያዝነው ዓመትም በሜዲትራንያን ባህር ስደተኞችን አሳፍራ የነበረች ጀልባ ሰምጣ አሰቃቂ የሚባል አደጋ ደርሶ 150 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡም ተገልጿል።

አሁን የደረሰውን አደጋ ጨምሮ ከጥር ወር ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ አውሮፓ ለመድረስ በሚል ተስፋ የሜዲትራንያን ባህር ሲያቋርጡ 900 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል። ይህ አሰቃቂ የባህር ላይ ጉዞ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን ተከትሎም ዩኤንኤችሲአር የተባበረ እርዳታ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት በመስጠት ለአውሮፓ ህብረት ሀገራትም የነፍስ አድን መርከቦች እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል።

ድርጅቱ ከዚህም በተጨማሪ፤ በባህርም ላይ ሆነ በአየር ላይ ጉዞ በሚከሰት አደጋ ላይ ለነፍስ አድን ስራ የተሰማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ የተጣለው ህጋዊ ገደብ ሊነሳ ይገባል ብሏል። እንዲሁም፤ በወደብ አካባቢ የሚገኙ ሀገራት በፈቃደኝነት ላይ የሚስሩ የነፍስ አድን ሰራተኞችን ማበረታታት እንጂ መከልከል እንደማይገባቸው ድርጅቱ በድረገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ፤ ስደተኞችን ከሊቢያ አውጥቶ ወደተሻለ ስፍራ በመውሰድ የተደላደለ ሕይወት እንዲኖሩ መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

የዩኤንኤችሲአር ምክትል ኮሚሽነር ኬሊ ክሌመንትስ ከሰሞኑ በሊቢያ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ በአካል ተገኝተው የተመለከቱ ሲሆን፤ በእስር ላይ ያሉ ስደተኞችም ሊለቀቁ ይገባል ብለዋል። ምክትል ኮሚሽነሯ አክለውም፤ አራት ሺህ 800 የሚሆኑ ስደተኞችን ለማስለቅ ከሊቢያ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 24/2011

 ሶሎሞን በየነ