ጥበባዊ ስራዎችን – ለአገር ሰላምና አንድነት

8

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በጽህፈት ቤታቸው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ጋብዘው ሙያዊ ስልጠና እና ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ጥበብ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው አስተዋጽዖ ላይ ከመምከራቸው ባሻገር አርቲስቶች በሙያቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ጉድፍ የማሳየት፤ ለእውነት፣ ለፍትህ ብሎም ለአንድነት ጠበቃ የመሆን ኃላፊነት እስከምን ድረስ እንደሆነም መወያየታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በወቅቱ ሰፊ ዳሰሳዎችን በማድረግ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ማካፈላቸው ለጥበብ ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን በእለቱ የተገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሰጥተዋል። ኪነ ጥበብ ዳግም በድፍረት ለማኅበረሰቡ እንድትቆም አድርገዋል ሲሉ የመድረኩ ተሳታፊዎችም መስክረዋል።

በመድረኩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ጥበብ ሰፊ ገለጻ ከማድረጋቸው በዘለለ፤ የጥበብ አላማ ምን እንደሆነ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለጥበብ ያለውን አስተሳሰብ በመጥቀስ ማብራሪያ መስጠታቸውን በጊዜው በምክክሩ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ገልፀው ነበር። በተለይ ጠቢብ ማን ነው? በሚለው ነጥብ ላይ የራሳቸውን ምልከታ ማንሳታቸው በብዙሃን ዘንድ አድናቆትን ማግኘት የቻለ ነበር።

ከአምስት መቶው በላይ የሚሆነው የኪነ ጥበብ ማኅበረሰብ፤ ለሃገሩ በጥበብ ረገድ ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋፅኦ በጉልህ ተነስቶ በሙያው አሻራውን እንዲያሳርፍ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መቅረቡ ዘርፉን ለማነቃቃት የነበረው አስተዋጽኦም ግዙፍ ድርሻ የሚወስድ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅርን፤ አንድነትን፤ ሠላምን ከመስበክ አንፃር፤ ሃገር ውስጥ እስከዛሬ መሰራት የነበረበትን ያህል አልተሰራም የሚል እምነት እንዳላቸውም በዚህ ውይይታቸው ላይ ማንሳታቸው የሚዘነጋ አይደለም።

በተለይም ሕዝብ ለሕዝብ ሃሳብን በማንሳት፤ በቅድሚያ በአገር ውስጥ ፍቅርን ሠላምን በኅብረተሰቡ ዘንድ ለማስረፅ፤ «ቱር» ወይም የጥበብ ዝውውር እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከውጭ አገራት ማለትም በኤርትራ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሌ፣ ሱዳን፣ እያሉ በየአገሩ የሚዞር ቡድን መኖር እንዳለበት ገልፀው ይህን እቅዳቸውን እውን ማድረግ ለሚችሉት የጥበብ ቤተሰቦች አደራ ሰጥተው በቤተ መንግስት በጉብኝት ስነ ስርዓት እና በምሳ ግብዣ ተመራርቀው ነበር የተለያዩት።

ከላይ በመነሻችን የጠቅላይ ሚኒስትሩን እናከአምስት መቶ በላይ የሚሆኑትን የጥበብ ቤተሰቦች ምክክር በድጋሚ ለማስታወስ የፈለግነው ያለ ምክንያት አልነበረም። መንግስትም ሆነ የጥበብ ባለሙያዎች የአገርን ራእይ እውን ለማድረግ በተናጠል ግን ለአንድ አላማ እንደሚሰሩ ይታወቃል። ከዚህ በዘለለ በጋራ የሚፈጥሩትን ጉልህ የሰላም እና የአንድነት ድርሻ ምን ያህል ትልቅ መሆኑም ከጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይሆንም።

ይህ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ምክክር በአንድ ወቅት ተዘምሮለት የሚያበቃ እንዳልሆነ መገንዘብ ብዙ ማሰላሰል የሚጠይቅም አይደለም። ይልቁንም አስገራሚ የሚሆነው ለብዙ አስርት ዓመታት ተራርቀው የቆዩት የጥበብ ባለሙያዎች እና መንግስት ከተሞሸሩ ዓመት ሳይሞላቸው ትስስራቸው የሚቀዘቅዝ እና ፋይዳ የማይኖረው ከሆነ ነው። መንግስት ቃል በገባው ልክ የጥበብ ዘርፉን መደገፍ ካልቻለ እንዲሁም የጥበብ ቤተሰቡ የአገር አንድነት፣ ሰላም እና ብልፅግና የፊት ተሰላፊ አምባሳደር ሚናው ላይ ከተዳከመ ‹‹ለምን›› የሚል ጥያቄ እና ግርምትን ማጫሩ አይቀሬ ነው።

እኛም ከወራት በፊት የተደገሰውን የአብረን እንስራ ምክክር መነሻ በማድረግ አንድ ሰበዝ ለመምዘዝ እና ጥልቅ ባይሆንም በጥቂቱ የታሪካዊ ጉዞ ጅማሮውን ከእንጭጩ ለመገምገም ወደናል። ለማሳያ ይሆን ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን አደራ እንደ መነሻ አድርጎ ከዚህ አንፃር የተደረጉ የዘርፉ ጥረቶችን በወፍ በረር ቅኝት አደረግን።

የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኪነ ጥበብ ቤተሰቡ ጋር ከተመካከሩበት እና አደራ ከሰጡበት ጉዳይ መካከል ‹‹የሰላምን ጥቅም የሚያጎሉ አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎችን በመላው አገሪቷ ለመስራት ጥረት አድርጉ›› የሚለው ይገኝበታል። ይህን መነሻ በማድረግም የኪነ ጥበብ ቤተሰቡ በከፍተኛ ሞራል እና መነቃቃት የተለያዩ ዝግጅቶችንና የኪነ ጥበብ ውጤቶችን ለመስራት እንቅስቃሴ ሲያደርግና በተግባርም አንዳንድ ሁነቶችን ሲያዘጋጅ ተመልክተናል።

መልካም አላማን አንግበው ከተፀነሱ ሃሳቦች መካከል በግዙፍነቱ ብሎም መላው አገሪቷን ለማካለል በማቀዱ የሚጠቀሰው የገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ኮንሰርትም ከውጥኖቹ መካከል በቀዳሚነት የሚነሳ ነው። በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ዝግጅት 500 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ ከተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም ከመታሰቡ በዘለለ አንድነት እና ሰላምን የሚያጎሉ የኪነ ጥበብ ስራዎች እንደሚቀርቡበት ውጥን ተይዞለታል። ለመሆኑ ይህ ግዙፍ ሃሳብ በታሰበለት ጊዜና የዝግጅት ልክ መሬት ላይ በቶሎ

 ለማውረድ ያልተቻለበት ምክንያት ምን ይሆን?

ዳዊት ይፍሩ የሙዚቃ ደራሲ፣ አቀናባሪ፣ ፒያኒስት፣ ጊታሪስት እንዲሁም ቫዮሊኒስት ነው። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማህበራትን በፕሬዚዳንትነት ይመራል። በዚህ በጎ ዓላማን በያዘ የሙዚቃ ኮንሰርት ዝግጅት ላይ በአስተባባሪነት ተሳታፊ ነው። ሃሳቡ ከመነሻው ሲፀነስ ዋና ሚና ነበረው። ሃሳቡን መሬት ላይ ለማውረድ ሰፋ ያለ ጊዜ የወሰደበትን ምክንያት እና እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረገው ቆይታ አብራርቷል።

እንደአርቲስት ዳዊት ሃሳብ በቀዳሚነት አገሪቷ ላይ የሚፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ችግር የማረጋጋት ስራ መስራት የጥበብ ባለሙያው ቀዳሚ ተግባር ነው። ከዚህ አንፃር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ስፍራቸው ከመመለስ እና ከማቋቋም አኳያ የድርሻቸውን ለማበርከት መዘጋጀታቸውንም ይናገራል። በሙያቸውም ህዝብ ለህዝብ የማቀራረብ ሃላፊነትን ለመውሰድ እንደተዘጋጁም ይገልፃል።

የቲያትር፣ የፊልም፣ የሰአሊያን እንዲሁም ደራሲያን ማህበራት ሃላፊዎች ተሰባስበው በባህል ሚኒስቴር አስተናባሪነት ይህን ታላቅ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በተለይ የዚህ ፕሮግራም ዋና ዓላማ ዘር፣ ቀለም እንዲሁም ማንነትን ሳይወስን ሙዚቃ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያስተሳስር መሆኑን በማስገንዘብ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተፈጠረ ያለውን ትኩሳት የማቀዝቀዝ ሚናን ለመጫወት አልመዋል። ኢትዮጵያውያንን የሚያስተሳስር ስለ ሰላም እና አንድነት የሚሰብክ አንድ መሪ መዝሙር የማውጣት እቅድም እንዳላቸው ተናግሯል።

አንጋፋ፣ ታዋቂ እና ወጣት ድምፃውያንን በማሰባሰብ የሶስቱንም ዘመን እንዲወክሉ እና ስራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ የማድረግ ስራ ለማከናወን ማሰባቸውን የሚያነሳው ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ ሆኖም ግን ሃሳቡን ስኬታማ ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ ላይ እንቅፋት እየገጠማቸው እንደሆነ ይናገራል።

በተለይ የሰላም፣ የአንድነት እና የፍቅርን አርማ አንግቦ በሁሉም ክልሎች ላይ ሊደረግ የታሰበው የሙዚቃ ኮንሰርት ጊዜውን ጠብቆ እንዳይካሄድ እዚህም እዚያም የሚከሰተው አለመረጋጋት፣ ችግር እና ውጥረት እንቅፋት እየሆነባቸው እንደመጣ ከመግለፅ አልተቆጠበም።

‹‹አሁን በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ያለው ስሜት የእኔነት ስሜ ትና አመ ለካከት ነው ›› የሚለው ዳዊት ይፍሩ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ባቀዱት ልክ እና ጊዜ ዝግጅታቸውን ለማሳካት እክል እየፈጠረባቸው እንደሆነ ያነሳል። ከዚህ ባሻገር ግን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ቴሌቶን በማዘጋጀት ገንዘብ ለመሰብሰብ እንዳሰቡ ገልጿል። በተጨማሪ መላው የአዲስ አበባ ህብረተሰብን የሚያሳትፍ የሙዚቃ ዝግጅት በሚሊኒየም አዳራሽ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ገልጿል። በዚህም የሙዚቃ እና የጥበብ ስራዎች ህዝብ ለህዝብ ያለውን ግንኙነት የሚያሳይ ዝግጅት ለማቅረብ ማሰባቸውንም ነው የሚናገረው።

የጥበብ ቤተሰቡ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ጉልህ ድርሻ ታሳቢ አድርጎ ሰላም እና አንድነት እንዲሁም ፍቅር በአገሪቷ ላይ እንዲሰፍን የድርሻውን ለመጫወት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። በምሳሌነት ያነሳነው የሙዚቃ ኮንሰርት እና የገቢ ማሰባሰቢያ የጥበብ ስራዎች ዝግጅት የሚያሳየው ይህንኑ ነው።

ሆኖም ግን የጥበብ ቤተሰቡ ሙያውን ለዚህ መሰል በጎ ተግባር ለማዋል በሚተጋበት ወቅት ስራዎቹን በተገቢው መሬት ላይ ማውረድ እንዳይችል የሚያሰናክሉ እክሎች መብዛታቸው ውጤቱን ግንጥል ጌጥ አድርጎታል። ለዚህም ነው የዝግጅቱ አስተባባሪ የሆነው ዳዊት ይፍሩ ይህን ችግር ለማለፍ እውቀት ያለው በእውቀቱ፤ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ተባብሮ ሰላም እና አንድነትን የሚያመጡ የጥበብ ስራዎች ላይ መሳተፍ አለበት ሲል ጥሪውን የሚያስተላልፈው።

 አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/ 2011

 ዳግም ከበደ