ሰይጣን በ›ስምንተኛው ጋጋታ

9

እንደ አዲስ ለህትመት በበቃው “ስምንተኛው ጋጋታ” ልብ ወለድ በባለሙያ እይታ። ሰይጣንን በአካል በልቦለድ ውስጥ መቅረፅ በ“ዘመናዊ” ስነጽሑፋችን አልተለመደም። በተለይ በ“መደበኛው ልቦለድ” ሰይጣንን ገፀባሕርይ አድርጐ መሳል እንግዳነት አለው። ነገር ግን አንዳንዶች ደፋር ተንታኞች የዓለም ሥነ-ጽሑፍ በተለይም ረጅም ልቦለድ ያለሰይጣን ወይም ያለእርኩስ መንፈስ የኖረበት ዘመን የለም እስከማለት ይደርሳሉ።

በዓለም ሥነ-ጽሑፍ ታላላቅ ተብለው ከሚጠቀሱት ደራሲዎች መሃል እንደነ ዳንቴ አሊጌሪ፣ ጆን ሚልተን፣ ክርስቶፈር ማርሎ፣ ዎልፍጋንግ ገተ፣ ሚኻይል ሌርሞንቶቭ፣ ሚኻይል ቡልጋኮቭ ፣ አሌክሳንደር ፑሽኪን፣ ሔንሪክ ኢብሰን፣ ማርክ ትዌይን፣ ጆርጅ በርናንድ ሾ፣… እና ሌሎች ቢያንስ ስማቸው እንግዳ የማይሆንብን እና ተተርጉመውም ያነበብናቸው ደራሲዎች ይጠቀሳሉ። ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በተረታዊ አጻጻፉ ከዓለም ብዙ የመጻሕፍት ቅጂ ሻጭ ደራሲዎች አንዱ የሆነው ፓውሎ ኮዬልሆም ሰይጣንን በቀጥታ በገፀ ባሕርይነት ካመጡት ደራሲዎች ዝርዝር ውስጥ ሊካተት ይችላል።

ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር በ‹ሰባተኛው መልአክ› ባካተታቸው ሁለት “ፋንታሲ” ሥራዎቹ ውስጥ ለዚህ ጽሑፍ በተመረጠው በ“ስምንተኛው ጋጋታ” እና በ“አጋፋሪ እንደሻው” ሰይጣንን ገፀ ባሕርይ አድርጐ ቀርጿል። ባለታሪክ፣ ባለሚና አድርጐ በድርሰቶቹ ውስጥ ተርኮታል። ጽሑፉ በሰይጣን አሳሳል ወይም በእንግዳነቱ ሳይሆን፤ ይኽ መንፈሳዊ ገፀ ባሕርይ ወደ ድርሰቱ በገባበት ሰበብ እና በተላለፈበት ጭብጥ ላይ ነው ያተኮረው።

መርማሪነት፣ የሰው ልጅ ባሕርይ ነው። መጠየቁ የማኅበራዊም የግላዊም ዕድገቱ መሠረት ነው። መጠየቁ የመሻሻሉ የመበልፀጉ መነሻ ነው። ካልጠየቀ በቃኝ ባይ ይሆናል፤ ካልጠየቀ ለውጥ አይሻም፤ ካልተለወጠ ዕድገትና ውድቀት የሚባሉ ሂደቶችን አያልፍም። ተፈጥሯችን ግን እንዲያ ሆኖ ለመኖር አይፈቅድልንም። እናም እንደሰውነታችን እንጠይቃለን። ስለምንጠይቅም ዛሬ፣ ትናንት እና ከትናንት ወዲያ አንድ አይደሉም።

እጓለ ገብረ ዮሐንስ የሰው ልጅ አካባቢውን አሜን ብሎ ተቀብሎ በኖረበት ዘመኑ፣ “የተፈጥሮ ችሎታውን ባለማወቅ… በዙሪያው የሚገኙት የሥነፍጥረት ጉልበቶች መጫወቻ ነበር፣” ይላሉ (የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ ገፅ 97)።

ስብሃት ገ/እግዚአብሔር፣ በ“ስምንተኛው ጋጋታ”፣ ጠያቂነት እንደነውር የሚያስወቅስበት እንደ ሃጥያት የሚያስወግዝበት እንደ ወንጀል የሚያስቀጣበትን፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አኗኗር ነቅፏል። በተለይ ሰይጣንን ገፀ ባሕርይ አድርጐ በተረከባቸው ገጾች ስብሃት ይኼን ሥርዓት ሲቃወም መርማሪነትን ሲያበረታታ እናገኘዋለን። ሰይጣንን ገፀ ባሕርይ አድርጐ ማምጣቱም ሁልጊዜም ከአንድ አቅጣጫ የሚፈስ “እውነት” ተቀባይ መሆናችን የዋህነት መሆኑን ለማመልከት ይመስላል።

በታሪኩ ውስጥ ሰይጣን በሦስት የተለያዩ ሁኔታዎች ያጋጥመናል። በያዙት ጭብጥ ተቀራራቢነት በተለይ ሁለቱን፣ ማለትም ሰይጣን ከኢየሱስ ጋር በሲኦል የተወዳጀበትንና ከዋና ገፀ ባሕርይ ከአቶ አልአዛር ጋር ያደረገውን የስልክ የሐሳብ ልውውጥ በማንሳት፤ ስብሃት መርማሪነትን በተረታዊ ድርሰቱ አማካይነት አበረታቷል ያስባለኝን ለማስረዳት እሞክራለሁ።

የሃይማኖት መጻሕፍት እንደሚያስተምሩት ሰይጣን ከእግዜር በታች ከሰው በላይ ሆኖ ምድርን በክፋቱ የሚገዛት፣ የዚህች ዓለም ገዢ ነው። ሰይጣን፣ ሳጥናኤል በትርጉሙም፣ “ሰግዶ አሰጋጅ” ተብሎ አስቀድሞ የተሰጠውን የመላዕክት አለቅነት በገዛ እጁ ያጣ፣ በአምላኩ ላይ አምጾ ክብሩን የተነጠቀ መንፈሳዊ ፍጡር ነው። የፈጣሪውን ዙፋን በመመኘቱና ፈጣሪውን በማስቆጣቱ ወደ ምድር ተጥሏል።

አዳምና ሄዋንን አስቶ ከእግዜር መንገድ አስወጥቶ ፀጋቸውን አስገፍፏል። ለሞትም መምጣት ዋነኛው ምክንያት ሆኗል። የኢዮብንም ትግስት ተፈታትኗል፤ የኢየሱስንም ያርባ ቀን ጾም፣ የ3 ዓመት ከ3 ወር ተልዕኮ ለማክሸፍ ሞክሯል። እናም ሰይጣን የእግዚአብሔር ተቃራኒ የሰው ልጆችም ጠላት እንደሆነ የሃይማኖት አባቶችና መጻሕፍት ይመሰክራሉ።

የስብሃት ድርሰት ግን ሰይጣንና ኢየሱስን ያወዳጃል። ሃይማኖታዊውን እውነት የምናይበት ሌላ መነጽር ያጠልቅልናል። ወይም እውነቱን ለማየት ከቆምንበት አቅጣጫ በተቃራኒው አቁሞ ያየነውን በሌላ ዐይን ያሳየናል “ኢየሱስ ፍቅር ነውና አዳምን ወዶት ሊያድነው የሞትን ወንዝ እንደተሻገረ ሁሉ፣ ሰይጣንንም ወዶት በስደት አገሩ በሲኦል ሊጠይቀው የዘላለምን ወንዝ ተሻገረ። ሰይጣንም በግዞት አገር ሊጐበኘው የመጣውን እንግዳ እደጀሰላም ድረስ ወጥቶ ተቀበለው፣ ይወርድ ዘንድ አህያውን ባለሻኛውን ያዘለት፣ ይገባ ዘንድ በሩን ከፈተለት…” (127-8)

በዚህ ክፍል ሰይጣን እንግዳው ኢየሱስን ጠላና ቆሎ አቅርቦ ከጨዋታ ጋር አስማምቶ ያስተናግደዋል። ኢየሱስ ሲኦል ድረስ የወረደው የሰይጣንን ወዳጅነት ፈልጐ አይደለም። ሰይጣንን “አታሎ” ነፍሳት ሊሰርቀው እንጂ።

ሰይጣንና ኢየሱስ በሰዎች ነፍሳት ላይ የየራሳቸው ፍላጐቶች አሏቸው። ሁለቱም እነዚያን ነፍሳት ይፈልጓቸዋል። የስብሃት ኢየሱስም ከሰይጣን የተወዳጀ የመሰለው በሰይጣን ግዛት (ሲኦል) ከታሸጉት ነፍሳት ወደራሱ ግዛት በዘዴ ለመውሰድ ብሎ መሆኑን እናያለን።

“ሳቀ ኢየሱስ ከት ብሎ ሳቀ፣ ሲኦል ግድግዳው ተሰነጠቀ፣ ነብሳት ነቁ በስንጥቁ፣ በሺ በእልፍ እየወጡ አመለጡ። ሰይጣን ይህን አልጠረጠረ፣ ‘ንገረኝ አብሬህ ልሳቅ፣’ አለ።” (129)

የስብሃት ኢየሱስ፣ “ወንድሜ ሳጥናኤል ሆይ፣” እያለ ሰይጣንን እያባበለ የሰይጣን ንብረት (ዜጐች) የሆኑትን ነፍሳት ዘርፎታል። ስብሃት ግን እዚህ ጋር ቆም ብለን፤ የኖረውን ትረካ ገልበጥ አድርገን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ማታለል የሰይጣን ተግባር ሆኖ ሳለ፣ በዚህ ትረካ ውስጥ ግን አታሎ መዝረፍ የኢየሱስ ሆኗል። በርግጥ ሰይጣን ሲያታልል ሞትን ለሰው ልጆች አመጣ፤ ኢየሱስ ሲያታልል ነፍሳት ዘላለማዊ የደስታ ኑሮ እንዲኖሩ ያደርጋል።

ኢየሱስና ሰይጣን በተወዳጁበት በዚሁ ክፍል የተነሳን ሌላ ሁኔታም እናንሳ “ውድ ወንድሜ ሳጥናኤል ሆይ፣ እስቲ የምድርን ነገር አንሳና ስለ ሰው ልጆች አጫውተኝ። መሬት ስጋ አብቅላ አድጐ ሲያብብ፣ ያበበው ጠውልጐ ሲረግፍ፣ በሌላ አበባ ሲተካ የሚነግር ወሬ ጨዋታ አምጣ። እገሌ እንዲህ ሆነ እንዲህ ደረሰበት የሚል ጨዋታ። ተረት ብጤ ጨዋታ…” (129) ኢየሱስ ለሰይጣን የ“እንደምን ላስተናግድህ” ጥያቄ ስለምድር የሚያወራ ተረት ብጤ ጨዋታ እንዲያጫውተው ጠይቆታል። ሰይጣን ደግሞ እንደ እንግዳ ተቀባይነቱ የእንግዳውን ጥያቄ ተቀብሎ የእንግዳውን ሐሳብ ለመሙላት ካዲሳባ ተረት ይዞ መጥቷል።

…ከዚያማ ሰይጣን ተረቱን ጀመራታ.. የመኖር የመሞት ጨዋታ፣ ኩኩሉ አይነጋም ጨዋታ፣ አየሁሽ ለየሁሽ ጨዋታ፣ እንቁልልጭ ሙልልጭ ጨዋታ፣እንቆቅልሽ ቆቅ ታንቆልሽ ጨዋታ። አቶ አልአዛር… ቤታቸው በራፍ ሊደርሱ ጥቂት እርምጃ ሲቀራቸው እንቅፋት መታቸውና ወደቁ። ተነሱ፣ ሰውነታቸውን ደባበሱ፣ ልብሳቸውን አራገፉና ወደ ቤታቸው በር ራመድ ራመድ…ኧ..? ቤታቸው ከስፍራው የለም።

ኧ..? (130) አቶ አልአዛር የድርሰቱ ዋና ባለታሪክ ናቸው። አቶ አልአዛር አንድ ጊዜ የውሽማቸውን ቤት በሌላ ጊዜ የራሳቸውን ቤት ከስፍራው አጥተዋል። ይኼ የሰውየው አንጻራዊ እውናዊ ገጠመኝ በሰይጣንና በኢየሱስ ጨዋታ እንደተረት ተቆጥሯል። ተረቱ ኑሮን ተረት ያደርጋል። ሰውንም ጭምር። የሰው ልጅ ተረት ተራኪ ነኝ ይበል እንጂ ራሱም ተረት ነው ይላል። በኑሮና በተረት መሃል ፈጥረነው የቆየነው ድንበር ሙሉ በሙሉ ይጣስና ሁለቱ አንድ ይሆናሉ።

ተረቱ የሚያሳስበን ትልቅ ጥያቄ አለ። የልእለ ሰብአውያን እና የሰዎች ግንኙነት። ሰይጣንና እግዚአብሔር ልዕለ ተፈጥሯዊ ኃይላት መሆናቸው ተነግሮናል፤ እነዚህ ከሰው በላይ የሆኑ ፍጥረታት በዚህኛውም ሆነ በሌላ በማናውቀው ምድር ተገዢዎች አሏቸው። በገዢና ተገዢ መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ እንደሆነ ይሰበካል። ለምሳሌ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት መሠረት፣ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው የግንኙነት ማሰሪያ ገመድ ፍቅር ነው፤ እግዚአብሔር ሰውን ይወዳል። ስለወደደም፣ አንድያ ልጁን ለሞት አሳልፎ እስከመስጠት ደርሷል።

የስብሃት ሰይጣንና ኢየሱስ ግን ያን ግንኙነት አልተቀበሉትም። በሰዎችና በነሱ መካከል ያለው ግንኙነት በደራሲና በሚስለው ገፀ ባሕርይ መካከል እንዳለው ግንኙነት ነው። አማልክት ደራሲዎች፣ ሰዎች እና ሌሎች የምድር ነዋሪዎች ደግሞ የድርሰቶቻቸው አላባዊያን የሆኑበት። የምድራውያን ኑሮ ደግሞ ለስብሃት ኢየሱስ እና ለስብሃት ሰይጣን “ተረት ብጤ ጨዋታ” ነው።

በአቶ አልአዛርና በሰይጣን መካከል በተደረገ የስልክ የሐሳብ ልውውጥም ይኼ የደራሲው የ“ጠይቁ!” ግፊት ተጠናክሮ ይቀጥላል። በዚህ ምልልስ ሰይጣን ሰው ነበርኩ ይላል፤ ሰውም ሰይጣን ነው ይላል። በክፋትና ደግነት፣ በሰናያትና እኩያት፣ በመኖርና አለመኖር መካከል አለ ያልነውን ልዩነት አጥፍቶ ሁሉንም አንድ ያደርጋቸዋል። ያዋሕዳቸዋል። አባ ሽንኩርት የተባሉ (ምናልባት የሲኦል ደብተራ) ፍጡርን ጠቅሶ በገጽ 134 እንዲህ ይላል

“ምን ሰውነት ቢያምር የሚፈርስ ነውና ምን ትልቅ ቢሆኑ ሰው ትቢያ ነውና ምን ምስኪን ቢሆኑ ሰው ሕያው ነውና ምን ክፋት ቢጠሉ ሰው ሰይጣን ነውና”

አስቀድሞ እንዳልነው የምድር እና የአማልክቱ ግንኙነት የድርሰት አላባውያን እና የደራሲያንን ግንኙነት ከመሰለ፣ የምድራውያኑ ዕጣ ፈንታ በደራሲያኑ አስቀድሞ ይታወቃል ማለት ነው።

የስብሃት ሰይጣን በዚህ ምልልስ በሃይማኖት አካባቢ በተደጋጋሚ የሚነገሩና የሚታመኑባቸውን ታሪኮች ለውጦ ተርኳል። ለምሳሌ ሰይጣን፣ ሳጥናኤል፣ በሚባል ስሙ መልአክ – ሊቀመላእክት እንደነበረ ይታመናል። የስብሃት ሰይጣን ግን ይኼን ክዶ ሰይጣን ሰው ነበር እንጂ መልአክ አልነበረም ይላል።..ምን ክፋት ቢጠሉ ሰው ሰይጣን ነውና…. ሰይጣንም ሰው ነውን?.. አሉት አቶ አልአዛር.. እንደ አስተያየትዎ ጌታዬ፣ እንደ አስተሳሰብዎ። አባ ሽንኩርት እንደሚነግሩን ከሆነ ሰይጣን እጣን ቢሸተው ..እሰይ እጣን.. ቢል፣ ሰይጣን አሉት፤ ሰይጣን ሆኖ ቀረ።

እንጂ ሰው ነበር። እሰይ እጣን… (134) በሌላም በኩል በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሚከበሩትና ታቦት ከተቀረፀላቸው፣ ደብር ከቆመላቸው ሰማዕታት አንዱ ስለሆነው ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚነገረውን ታሪክ፤ የተጻፈውን ገድሉን በሌላ ለውጦ ሰይጣን ተርኮታል። በቤተ ክርስቲያን አንፃር ይኽ ታሪክ ሲተረክ የደራጐን ክፋት የጊዮርጊስ ቅድስናና ኃያልነት ጐልቶ ይንፀባረቃል። የስብሃት ሰይጣን ግን ያንን ይሽረዋል። ደራጐን ለጊዮርጊስ የተሸነፈችለት ለፈረሱ ስትል እንጂ በአንድ ትንፋሽ ልታጠፋው ትችል እንደነበር ይተርካል። እንግዲህ ተራኪው ሰይጣን በመሆኑም ይሆናል የታሪኩ አካሔድም፣ ጭብጥም የተለወጠው። እዚህም በሰይጣኑ አማካይነት ስብሃት ጠያቂነታችንን ያበረታታል።

‹ስምንተኛው ጋጋታ› ሃይማኖትን ለመፈተሽ፣ ወይም የቆዩ እምነቶችን ለመፈታተን የተጻፈ ድርሰት አይደለም። ወይም በተቃራኒው እነዚህኑ ሃይማኖቶች እና እምነቶች ለማጽናት የተጻፈም አይመስልም። ይልቁንም ዳኛቸው ወርቁ “እፎይ ብላለች- በርጋታ፣ በዝግታ፣ ታምማለች፤ በተገማሸረ መስክ ውስጥ እንደሚብሰከሰክ ውሃ … ” ያለላትን የልማድ ሕይወት፣ “ሰይጣን” ባለው ጠጠሩ ለማደፍረስ መሞከሩ እና እኛም እውነትን አጥልለን እንድንጠጣ መገፋፋቱ ነው።

ስብሃት እንድንመረምር ሲያበረታታን፣ “አሰናካይ፣ የሐሰት አባት” እየተባለ ለሚጠራው ሰይጣን ሰናያት ባሕርያት አልሰጠውም፣ አምነን እንከተለውም ዘንድ አልገፋፋንም፤ ይልቅ ሰይጣን ቦታ ብንቆም፣ ናቡከደነፆር ዙፋን ላይ ብንቀመጥ፣ ይሁዳን ብንሆን፣ ሂትለር ቦታ ብንቆም፣ … ታሪክን፣ እውነትን በምን መልኩ ነበር የምንረዳው እንድንል አበረታቶናል።

በዓለም ታሪክ ጠያቂነት ሲነወር ሲወገዝና ሲወነጀል ኖሯል። ለማወቅ የሚደረግ ጥረት ሲያስቀጣ ኖሯል። ፈላስፎች ተመርዘዋል፤ ተፈጥሮን መርማሪዎች ተሰቅለዋል፤ የሥነ-መለኮት ፈታሾች ተወግዘዋል – ታርደዋል፤ … ከነባር ዕውቀት፣ ከነባር እምነት፣ ከነባር ባህል እና ከነባር ልማድ ያፈነገጡ ሰዎች በመንግሥታት እና በሃይማኖት/በእምነት ስም የሰው ልጅ ሊያስባቸው የቻላቸውን ማሰቃያዎች እና የግፍ ግድያዎች ሁሉ ተቀብለዋል። ሃይማኖት፣ ባህል እና ጨቋኝ መንግሥት የመጠየቅ፣ የመመርመር ጠላት ሆነው ኖረዋል።

ስብሃት ሰውን እና ኑሮውን ተረት፣ ሰይጣንን ደግሞ ተራኪ አድርጎ ሲያመጣ፣ ሰውንም ዓለምንም የምንረዳበትን ዐይነ ልቡናችንን የማስፋት ዓላማ ይዞ ይመስለኛል። የፊት የፊቱን አትዩ፣ መርምሩ ሊለን ይመስለኛል። “ሁሉን መርምሩ መልካሙንም ያዙ፣” የተባለውንም ያስታውሷል።

 አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/ 2011

 አብርሃም ተወልደ