አጼ ልብነ ድንግል ሲታሰቡ

19

አጼ ልብነ ድንግል ህይወታቸው ያለፈው ከዛሬ 579 ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት (ነሐሴ 30 ቀን 1532 ዓ.ም) ነበር። አጼ ልብነ ድንግል የአጼ ናኦድ ልጅ የአጼ በእደ ማርያም የልጅ ልጅ ናቸው። አጼ ዘርዓ ያቆብ ደግሞ ቅድመ አያታቸው ናቸው። አጼ ናኦድ 13 ዓመት ገዝተው በ1500 ዓ.ም. ሲሞቱ አጼ ልብነ ድንግል ገና የ12 ዓመት ታዳጊ ሆነው ነገሡ። ስመ መንግሥታቸውም ወናግ ሰገድ ተባለ።

ወናግ ማለት በውጋዴን ቋንቋ አንበሳ ማለት ነው። የግዕዙን ወይም የአማርኛውን ቋንቋ “አንበሳ” ሰገድነን ትተው በውጋዴን (ሱማሌ) ቋንቋ ወናግ ሰገድ የተባሉበት ምክንያት ምናልባት ያን ጊዜ በይፋትና በፈጠጋር ያለውን ግዛት የሚያውኩ ያዳልና የሱማሌ ተወላጆች ስለነበሩ እነርሱ በሚያውቁት ቋንቋ ተሰይሞ ለማስፈራራት ይሁን ወይም የነርሱ ገዢ ጭምር መሆናቸውን ለማስተዋወቅ አሊያም ከአባታቸው ከአጼ ናኦድ ስመ ነገስት (አንበሳ ሰገድ) በትርጉም ቢቀር በአጠራር እንዲለይ መሆኑ በትክክል አይታወቅም።

አጼ ልብነ ድንግል ራሳቸው ለፖርቱጋል ንጉስና ለሮማ ሊቀ ጳጳስ በጻፏቸው ደብዳቤዎች ላይ “ስሜ ልብነ (እጣን) ድንግል ትርጓሜው ድንግል ያበራችለት ማለት ነው። ይህም ስም የተሰጠኝ ቅድስት ጥምቀትን በተቀበልኩበት ቀን ነው። በነገስሁ ጊዜ ደግሞ ዳዊት ተባልሁ” ይሉ ስለነበር ከዳዊት በተጨማሪ ወናግ ሰገድ በመባል በሁለት ስመ መንግስት ይጠሩ ነበር።

ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ልብነ ድንግል እስከ አጼ ቴዎድሮስ” በተሰኘ መጽሐፋቸው አጼ ልብነ ድንግል በነገሱ ጊዜ ወጣት ስለነበሩ እናታቸው እቴጌ ናኦድ ሞገሳና የቅድመ አያታቸው የአጼ በእደ ማርያም ባለቤት እቴጌ እሌኒ በሞግዚትነት ያግዟቸው እንደ ነበር ጠቅሰዋል። በመጀመሪያ፣ የዓፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት የሰላምና የደስታ ቢሆንም የመጨረሻ ጊዜያቸው በግራኝ መነሳት ምክንያት የጦርነት፤ የሁከት፤ የመከራና የስደት ጊዜ ሆኖባቸዋል።

በወቅቱ ሞግዚት (እንደራሴ) የነበሩት ንግስት እሌኒና አጼ ልብነ ድንግል በዘመኑ ገናና ከነበረችው ፖርቱጋል ንጉስ ከነበረው አማኑኤልና ከእርሱ በኋላ ከነገሰው ዮሐንስ ጋር ደብዳቤ ይጻጻፉ ነበር። ከፖርቱጋል መንግሥት በቀጥታም ሆነ በእቴጌ እሌኒ በኩል የጀመሩት ወዳጅነት ለጊዜው ጠቡን አጣደፈው እንጂ ከወረራ ሊያድናቸው አልቻለም ነበር። በመጨረሻም ቢሆን ከአረብና ቱርክ መንግሥታት ድጋፍ እያገኘ መላ ኢትዮጵያን መቆጣጠር የቻለውን ግራኝን ለመውጋት ፖርቹጋሎች መጥተው የረዷቸው በተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ምክንያት ነው።

የአጼ ልብነ ድንግል ጦር በሽምብራ ኮሬ ጦርነት ቢሸነፍም ጨርሶ ሊወድቅ አልቻልም ነበር። በዚህ ጦርነት ብዙ መኳንንት ቢያልቁም ግራኝና ጦሩ አንዱን አውራጃ አስገበርኩ ፤ ሹሙን አሰለምኩ፤ ገደልኩ ማረኩ ቢሉም ሌላው ደግሞ ተነስቶ የጦር አለቃ እየገደለባቸው፤ ንጉሱንም ለመማረክ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ንጉሱ አጼ ልብነ ድንግል ከታማኝ አሽከሮቻቸው ጋር ሆነው በቤጌምድር እየተዋጉ ከቆዩ በኋላ ቤጌምድርን ለቀው ደብረ ዳሞ አጠገብ ወዳለው የማይደፈር ተራራ ሄደው ተቀመጡ። በደብረ ዳሞ ቆይታቸው ታመው ህመማቸው እየጠናባቸው ሄዶ በአርባ አምስት ዓመታቸው ህይወታቸው አለፈ። (ተክለፃዲቅ መኩሪያ ህልፈታቸው በሕዳር ወር መጀመሪያ ላይ ነው ይላሉ፡፡)

አጼ ልብነ ድንግል ከግራኝ ጋር ጦርነት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ህይወታቸው እስኪያልፍ ድረስ አሥራ አምስት ዓመት ሙሉ ልጆቻቸውና መኳንንቶቻቸው ሲሰደዱ ፤ ሲማረኩ ፤ ሲገደሉ ከአገር አገር እየዞሩ መንግሥታቸውን ሲከላከሉ ነው ያሳለፉት። የጦርነት ፣ የሞት ፣ የመንከራተት፣ የመራብና የመጠማት አደጋ ከጊዜው ርዝማኔ ጋር ተስፋ አስቆርጧቸው መንፈሳቸውን አላላውም። አስራ አምስት ዓመታት ከተድላ ከደስታ ከሞቀ ቤተ መንግሥት ተለይተው በዱርና በበረሃ እየተዘዋወሩ ከኃይለኛ ባለጋራ ጋር እስከመጨረሻው ለመከላከል መዋጋታቸው ቆራጥነታቸውን ያሳ ያል። አጼ ልብነ ድንግል ቢሞቱም በፖርቹጋሎች እገዛ በልጃቸው በአጼ ገላውዲዮስ ዘመን በተደረገ ጦርነት ግራኝ አሕመድ ሞቷል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 29/2011

የትናየት ፈሩ