‹‹የአገረ ብሄር ግንባታ በአንድ ጀምበር ተጀምሮ የሚጠናቀቅ ሳይሆን እየጎለበተ የሚሄድ ነው›› – የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ

63

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰተው ግጭት ሳቢያ የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ ኢኮኖሚውም ተዳክሟል። ከምንም በላይ ደግሞ የእኔነት ስሜት ነግሶ ቆይቷል። በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ በ2007 እና 2008 ዓ.ም አካባቢ በየቦታው የተነሳው አመፅ አንድ መላ ካልተበጀለት ‹‹አገር ይፈርሳል፤ ህዝብም ይበተናል፤››የሚል ስጋት ያደረባቸው ጥቂት ሰዎች በተነሳሽነት ተሰባስበው በጉዳዩ ላይ ለመምከር ወደዱ።

እናም ከየትኛውም ክፉ ተግባር የራቁ እና ስራቸው ላይ ብቻ ያተኮሩ የተባሉት እነዚህ ሰዎች የአገር መፍረስ ጉዳይና የህዝብ መበተን ስላሰጋቸው ራሳቸውን ከተጠያቂነት ተርታ አሰልፈው መፍትሄ ማምጣት እንዳላባቸው አመኑ። ነገ ልጆቻቸው ራሳቸው ስለምን ዝምታን መረጣችሁ ብለው እንደሚጠይቋቸውም አሰቡ።

ስለዚህም የዚህች አገር አንዱና ዋናው ችግር ‹‹የአገረ ብሄር ግንባታ አለማካሄዳችን ነው››ብለው አንድ ፕሮጀክት ቀረፁ። ለዚህም የመንግስትን ፈቃድ ከማግኘት ጀምሮ ገንዘብ እስከ ማፈላለግ ባዘኑ። ተሳክቶላቸውም ከ2010 ዓ.ም አንስቶ የተለያዩ ሲምፖዚየሞችን ማካሄድ ቻሉ። የዚህን ፕሮጀክት ዋና ጉዳይ፣ አስፈላጊነትና ተቀባይነት በተመለከተ ፕሮጀክቱን ከቀረፁት መካከል አንዱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑን ሲሆኑ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘንላችሁ ቀርበናል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።

አዲስ ዘመን፡- የአገረ መንግስት ግንባታ (na­tion bulding) ሲባል ምን ማለት ነው?

ፕሮፌሰር ካሳሁን፡-በእኛም ሆነ በተለያዩ ማህበረሰቦች እንደታየው በአንድ የታሪክ ወቅት ላይ የተለያዩ ማህበረሰቦች ተሰባስበው አንድ አገር ይፈጥራሉ።መንግስት አቋቁመውም በመንግስት ህጎችና አሰራሮች ስር ይተዳደራሉ።ይህ የአገረ መንግስት ግንባታ ይባላል።እነዚህ የተለያዩ ማህበረሰቦች በተለያየ የታሪክ ወቅት በፍቅርም፣በጠብም ሆነ በጋብቻ ኢኮኖሚያዊ በሆነ ግንኙነትም ሆነ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ሄዶ በመስፈር እንዲሁም በመፈናቀል አንድ ላይ ይመጣሉ።እነዚህ በአንድ ከመጡ አገረ መንግስት ግንባታ ወይም የመንግስት ግንባታ ይካሄዳል።

ይህ ግን የአገረ ብሄር ግንባታ ሊባል አይችልም።ምክንያቱም ልዩነቶች ቢኖሩም በትክክል በሚያስተሳስራቸው በጋራ ማንነታቸው ዙሪያ ተሰባስበው የጋራ እሴቶች እና ማንነቶች አክብረውና ከፍ አድርገው ይዘው የሚገኙበት ደረጃ ነው።

በአገራችን እንደሚታወቀው ሺ ዓመታት ለዘለሉ ጊዜያት ማህበረሰቦች በተለያዩ ሁኔታዎች አንድ ላይ ተሰብስበው መንግስት ሲመሰርቱ ኖረዋል። ልዩነቶች እንዳሉ ሁሉ አንድ የሚያደርጉን ደግሞ በርካታ ነገሮች አሉ። በችግርም፣ በበሽታም፣ በማህበራዊ ኑሮም፣በኢኮኖሚ መስተጋብርም አንድ የሚያደርጉን እንደ እሴት የምንጠቀምባቸውን አጠናክረን ልዩነቶችን ደግሞ በየጊዜው በየደረጃው እንደሁኔታው እየፈታን ከሞላ ጎደል በሙሉ አንድ በሚያደርጉን ዓላማዎች፣እሴቶችና በወደፊት አቅጣጫዎች ዙሪያ ስንሰባሰብ የአገረ ብሄር ግንባታ ጀመርን ማለት ነው።

ይህም በአንድ ጀምበር ተጀምሮ የሚጠናቀቅ አይደለም።ለምሳሌ የአገረ ብሄር ግንባታን ከበርካታ ዓመታት በፊት የጀመሩ አገራት እስካሁንም ድረስ አላጠናቀቁትም።ስለሆነም ስራው እየጎለበተ የሚሄድ ነው ማለት ይቻላል።

በሀገራችንም እነዚህ ሁሉ ነገሮች እያሉ ልዩነቶች ላይ እያተኮርን አልፎ አልፎ በተለያዩ አካባቢዎች እንደምናየው ሁሉ እየሄድን ነው፤ ግን እንዲህ ስናደርግ ደግሞ አንድ የሚያደርጉንን የጋራ ማንነቶቻችንእና እሴቶቻችንን እየረሳን ነው የሄድነው። ስለዚህ እነሱን አጉልቶ የማውጣት፣ያልተግባባንባቸውንና የልዩነት ነጥቦች ናቸው የምንላቸውን ደግሞ በአግባቡ እየፈታን እየሄድን እንቀጥልበታለን።

አዲስ ዘመን፡- የእንግሊዝኛውን ‹‹nation bulding›› የሚለውን ሐረግ አንዳንዶች ‹‹አገረ ግንባታ›› በማለት ሲገልፁት፣ ሌሎች ደግሞ ‹‹የብሄረ መንግስት ግንባታ›› በሚል ይገልፁታል። ሁለቱ አገላለጾች በፅንሰ ሐሳቡ ላይ የሚያመጡ የይዘት ለውጥ አለ?

ፕሮፌሰር ካሳሁን፡-አማርኛ ዘርፈ ብዙ እና ወደፊት የተራመደ ቋንቋ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ‹‹nation bulding /ኔሽን ቢልዲንግ›› የሚለው የእንግሊዝኛ ሐረግ ብሄር የሚል ትርጉም አለው። ‹‹አገረ መንግስት›› የሚባለው ደግሞ ከብዙ ሺ ዓመታት በፊት ጀምሮ በአገራችን የቆየ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ለብዙ ሺ ዓመታት የነፃ አገርነት ታሪክ ያላት ናት።

ይሄኛውን የአገረ ብሄር ግንባታ የሚለውን ግን በሚገባ ጀምራ ወደተግባር አልሄደችም የሚል እሳቤ ነው ያለው። እርግጥ ነው በተለያየ ጊዜ ሙከራዎች ተደርገዋል። ለምሳሌ በንጉሱ ስርዓት ህዝቦች ተመሳሳይ ቋንቋ ቢናገሩም እንዲሁም ተመሳሳይ እምነት ቢኖራቸውም ልዩነቶች እየጠበቡና አንድነት እየሰፋ ይሄዳል የሚል ግምት ነበር። ነገር ግን በዚህ ረገድ የተደረጉና የተወሰዱ አንዳንድ እርምጃዎች የቅራኔ ምንጭ ነው የሆኑት። ለምሳሌ ስልጣን የያዙ ኃይሎችን ቋንቋ ሁሉም ቢናገሩ ‹‹ተገዶ ተጭኖበት ነው››የሚሉ ወገኖች በዚህ ረገድ ተቃውሞ እያሰሙ ናቸው።

አንድ አይነት እምነት ደግሞ ህዝቡ ቢከተል የተሻለ መቀራረብን ይፈጥራል የሚል እሳቤ ነበር፤ ነገሩ ከመልካም ማሰብ የመጣ ነው፤ ይሁንና ውጤቱ ‹‹የእኛም የአባቶቻችንም ኃይማኖት ወደኋላ እንዲቀር፣ የሌላው ግን ወደፊት እንዲራመድ ተደርጓል። የእኛ ቋንቋና ባህል ወደኋላ ሲሄድ የሌሎቹ ደግሞ ወደፊት ተራምዷል›› የሚሉ አሁን የምንሰማቸውን ነገሮች አስከትሏል።

በደርግ ዘመን ደግሞ በመደብ ትግል፣በህዝቦች አንድነት፣በሶሻሊዝም ርዕዮት ህብረተሰቡ ቢደራጅ አገረ ብሄር መንግስት መገንባት ይቻላል የሚል እሳቤ ነበር። እሱም ደግሞ ያመጣውን ምስቅልቅል አስተውለናል። ዓላማው ከመልካም ነገር ቢነሳም፣ በኃይል ለመጫን የተደረጉ ሙከራዎች አሉ፤ እነዚህ ደግሞ አብዛኞቻችን እንደምናውቀው የእርስ በእርስ ጦርነትን ጨምሮ ግጭቶችና የመሳሰሉትን ችግሮች አስከትለዋል።

በኢህአዴግ ዘመንም ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ህዝቡ ራሱን በራሱ ቢያስተዳድር፣ በቋንቋው ቢማር፣ ቢሰራና ህጋዊነቱን ተቀብሎ ተግባራዊ እያደረገ ቢሄድ መሰባሰብ ይመጣል የሚል እሳቤ ተያዘ። አፈፃፀሙን ስንመለከት ደግሞ አንዳንዱ የይስሙላ ሆኖ እናገኛዋለን፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በህገ መንግስት፣ በመግለጫዎችና በሌሎች ነገሮች ላይ የተባሉ ነገሮች በትክክል ስራ ላይ ሳይውሉ ቀርተው የተስፋ ቆራጭነት ስሜት እንዲጎላ አድርገው ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት የቀውስ መነሻ ለመሆን በቅተዋል።

በዚህም የተነሳም የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ የኢኮኖሚ ቀውስ አጋጥሟል፤ ሌሎች በርካታ ችግሮችም አጋጥመዋል። መንግስትንም በማናጋት ጭምር የአገሪቱን መሪ እስከማስቀየር አስኬዷል።

አሁንም በስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ ነው፤ በለውጡ ኃይሎች የሚመራው ኢህአዴግም እነዚህኑ ሙከራዎች እያደረገ ነው። ኢትዮጵያዊነት ወደኋላ ቀርቶ ነበር፤ እንዲሁም ገሸሽ ተደርጎም ነበር በሚል ለማጉላትና ጎን ለጎን ወደፊት ማስኬድ ያስፈልጋል ተብሎ አንዳንድ ጅማሬዎች ይታያሉ። በእነዚህም ተስፋ የሚፈነጥቁ እርምጃዎችም ተወሰደዋል።

በአንፃሩ ደግሞ አሁንም እንዳለመታደል ሆኖ ጊዜያዊም ቢሆንም የተለያዩ ችግሮች ውስጥ የገባንበት ሁኔታ እናያለን። ስለዚህ የአገረ ብሄር ግንባታ እንዲሁም የአገረ መንግስት ግንባታም ቢሆን ሁለቱም አንዳች እንከን ሳያገኛቸው ከአንድ ደረጃ ወደ ቀጣዩ ደረጃ እየተሸጋገሩ የሚሄዱ ሳይሆን ሁልጊዜ በሂደት ላይ ናቸው። ግንባታው ወደፊት ይራመድና አንዳንድ ቀውሶች ሲያጋጥሙት ወደኋላ ይሄዳል፤ከዛ ወደፊት የሚሄድ ነውና የትውልዶች ቅብብሎሽ ይሆናል። ይህም የጎደለውን አሟልቶ፣ የተዛባውን አስተካክሎ በመጨረሻ ወደተፈለገው ግብ ለመድረስ ይረዳል።

እኛ የአገረ ብሄር ፕሮጀክት ግንባታ ይዘን ወደፊት መንቀሳቀስ ጀምረናል፤የሚቀሩን ነገሮች ደግሞ አሉ። ይህም ጅማሬያችን በህይወት ዘመናችን ተጠናቆና ተሟልቶ እናየዋለን በሚል ሳይሆን ቢዘገይም መጀመሩ መልካም ነው በሚል ነው፤ ምክንያቱም አገር፣ ህዝብና ትውልድም ይቀጥላሉና፤ እናም በተከታታይ ያሉ ትውልዶች እያሻሻሉና መስመር እያስያዙ ይሄዳሉ በሚል ነው። ግንባታው ከእኛ በኋላ የሚመጡ በርካታ ትውልዶችንም ትጋት ይጠይቃል።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ አስቀድመው እንደጠቀሱት በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀውም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግጭቱም መፈናቀሉም እንዲሁም ፖለቲካዊ ቀውሱ ተባብሶ ነበር። ለዚህ ምክንያቱ ኢትዮጵያዊነት ተዘንግቶ በብሄር ብሄረሰቦች ላይ ብቻ በመሰራቱ ነው የሚሉ አካላት አሉና በእርስዎ እምነት ምክንያቱ ምንድን ነው? መፍትሄውስ?

ፕሮፌሰር ካሳሁን፡- አንዳንድ ወገኖች በብሄረሰብ መብት ላይ ብቻ በትኩረት መሰራቱ በራሱ አሉታዊ ነው፤ችግር ያመጣል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ አሁንም ቢሆን ለብሄረሰቦች መብት እውቅና ሰጥቶ ይህን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ነገሮች አሟልቶ መሄዱ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ይላሉ።በእኔ እይታ ሁለቱም አተያይ የሚጋጭ አይመስለኝም።

በትክክል ስራ ላይ ከዋለ የኢትዮጵያዊነትም ሆነ የብሄረሰቦች መብት ግንባታ ጎን ለጎን ሊካሄድ ይችላል ብዬ አምናለሁ። ችግሩ የመጣው መልካም ነገሮችን በፖሊሲና በህግ ደረጃ እንዲሁም በህገ መንግስትና በመፈክር ደረጃ እያስተጋባን አፈፃፀማችን የተለየ መሆኑ ላይ ነው። ለምሳሌ ከወታደራዊ አስተዳደር መወገድ በኋላ እስካሁን የነበሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች ይፈታሉ በሚል ሁላችንም ተስፋ ሰንቀን ነበር።

በ66ቱም አብዮት ጊዜ እንዲህ አይነት ተስፋ ነበር፤ ምክንያቱም ሰፋ ያለ የህብረተሰብ ክፍል የተሳተፈበት ህዝባዊ ንቅናቄ ነበር የተፈጠረው።ወደ ተግባር ሲመጣ ከታለመውና ተስፋ ከተጣለበት እንዲሁም ከተደነገገው ተቃራኒ የሆኑ አድራጎቶች በወቅቱ መፈፀማቸው ግን ይታወቃል።

በእርግጥ በኢህአዴግ ዘመን ባለፉት 27 ዓመታት የተከናወኑ ተግባሮች ሙሉ ለሙሉ አሉታዊ ናቸው የሚል እሳቤ የለኝም። በርካታ ጥሩ የሚባሉ እና አሁንም ልንቀጥልባቸው የሚገቡ ስራዎች አሉ ብዬ አስባለሁ። በደርግም ጊዜ በርካታ መልካም ስራዎች ተሞክረዋል። ስራ ላይም ውለዋል። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ይዘን ወደፊት እንቀጥላለን። በመሆኑም በብሄረሰብና በአገራዊ ማንነት ዙሪያ ራሱን የቻለ ምንም የማይለወጥ ተቃርኖ አለ ብዬ አላስብም።ሁለቱም ጎን ለጎን መሄድ ይችላሉና።

እርግጥ እንዳልሽው የአገራዊ ማንነት ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጠው በመፈክር ደረጃ ሲቀነቀን የነበረው የጋራ ማንነታችን ጉዳይ ሳይሆን የልዩነታችን ጉዳይ ሆኖ ቆየ። ይህን ተከትሎም ባለፉት ጥቂት ዓመታት አብዛኛው እንዲያውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማለት እችላለሁ በሂደቱ የመሳተፍ ነገር ችላ እየተባለ መጣ፤ የህግ የበላይነት እየተናቀ ህዝቡ በተለይ በወጣቱ ክፍል ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የገባበት ሁኔታ እንደተከሰተ እናውቃለን።

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የሚዘጋጀው ‹‹የአዲስ ወግ›› መድረክ በብሄረ መንግስት ግንባታ ዙሪያ በድሬዳዋ መካሄዱ ይታወሳል።ይህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ምን ያህል አስፈላጊነው ብለው ያመናሉ? ደግሞም እናንተ ከቀረፃችሁት ፕሮጀክት ጋር ሲተያይስ ልዩነት ይኖረው ይሆን?

ፕሮፌሰር ካሳሁን፡- በመጀመሪያ ደረጃ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ በጣም ያስፈልጋል።እንዲህም ሲባል ሙሉ ለሙሉ እሱ ብቻ ነው ለማለት ሳይሆን አንዱና ዋና የሆነውን የአገረ ብሄር ግንባታን ከልብ አምነን በጥብቅ በመከተል ስራ ላይ ብናውል እንጠቀማለን። ለምሳሌ በሰንደቅ ዓላማ ላይ እንኳ ብናይ ስምምነት የለንም። የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙርን ልብ ብሎ ላዳመጠ በመዝሙሩ ውስጥ ያሉ ስንኞች በእኔ እይታ በጣም ጥሩ ናቸው። ነገር ግን ተስማምተን ስላላደረግነው የተጫነብን መስሎ ስለሚሰማን ነው። ለምሳሌ የሚጠቅመው ቢሆንም ጣፋጭ ነገርን ለህፃን በግድ ጉረስ ሲሉት ያለቅሳል፤ ይወራጫል።

ህገ መንግስት ላይ ሲመጣም ስምምነት የለንም። ይህ ለምን ሆነ ?መላው ህዝብ፣ሁላችንም በእያንዳንዱ አንቀፅ ላይ ተነጋግረን ይሁንታችንን ሰጥተን አሊያም ደግሞ አብዛኛው የሚያስማማውን ጉዳይ ይዘን ከዚያም የእኔ ህገ መንግስት ነው፣ የእኔ ሰንደቅ ዓላማ ነው እንዲሁም የእኔ ብሄራዊ መዝሙር ነው እንድንል የሚያስችል ሁኔታ ስላልፈጠርን እንጂ እነዚህ ነገሮች በራሳቸው መጥፎ ሆነው አይደለም።

አብዛኛው ችግራችን ደግሞ ያለፈውን መልካም ነገር ማስታወስ አንፈልግም። ክፉውን ብቻ በመውሰድና በማጋነን ነው የምናስታጋባው። ለምሳሌ በሁሉም በመንግስት መሪዎች ሳይቀር ስለደርግ አዎንታዊ ገጽታ ሲናገር አይሰማም። እርግጥ ነው ከአቅም በላይ በሆነም አሊያም በሌላ ምክንያት መጥፎ ተግባራት ተፈፅመዋል።

ያንኑ መጥፎ ጎኑን ብቻ ነው የምናጎላው። ደርግ ቀይ ሽብርን ብቻ ለማካሄድ የተደራጀ መንግስት አድርገን የምንስልበት ሁኔታ አለ። በእርግጥ በየቤታችን የደረሰብን ነገር ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ሁሉንም ነገር ደምስሶ ከዜሮ ከመጀመር ይልቅ በሚዛናዊነት መልካሙን ነገርም በመውሰድ የጎደለውን እየሞላን ብንሄድ ይመረጣል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አማካይነት የተካሄደው ውይይትም እኛ ከምንለው ጋር የሚጣረስ አይደለም። ነገር ግን ዋናው ነገር ዞሮ ዞሮ ፈታኙና ወሳኙ ጉዳይ ተግባር ነው። መልካም ነገሮችማ ያልተነገሩበት ጊዜ የለም። በደርግም ጊዜ ይሁን ላለፉት 27 ዓመታት ስልጣን ላይ ባለው ኢህአዴግ ጊዜ እየተነገሩ ናቸው። ዋናው ነገር ግን ተግባራዊ የማድረጉ ጉዳይ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያዊነትና ብሄረሰቦች ግንባታ ላይ ቢሰራ የሚጣረስ ነገር አይኖረውም ብለዋል፤በርካታ ወገኖች ግን ኢትዮጵያዊነት ላይ ብዙ መሰራት አለበት ሲሉ ይናገራሉ። በምን አይነት መልኩ ቢሰራ ነው በአገር ደረጃ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት የሚቻለው?

ፕሮፌሰር ካሳሁን፡- አንደኛ የህብረተሰባችን ተሳትፎ ያስፈልጋል። መልካም የሆኑ የጋራ ነገሮቻችን ላይ መወያየትና ነቅሶ ማውጣት ግድ ይላል። ሁላችንም የምንኮራባቸው የአባቶታቻችን ስራዎች አሉ። እነሱን ነቅሶ ማውጣት ይጠቅማል። አሉታዊ ነገሮችን ደግሞ ተገንዝቦ እነሱን እንዴት እናስወግዳቸው በሚለው ላይም መስራት ያስፈልጋል።

በተለይ ደግሞ በወጣቱ ላይ መስራት ይገባል። ወጣቱ ክፍል ከሀገሪቱ ህዝብ አብዛኛውን ቁጥር ይይዛል፤የአገሪቱን እጣ ፈንታም የሚወስነው እርሱ ነው ተብሎ ይታመናል። ይህን ወጣት በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ በደንብ ማሳመን ያስፈልጋል።

አንዳንዶች ይህ ህገ መንግስት ተቀዶ የቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ መግባት አለበት ሲሉ ይደመጣሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ እንዳለ መቀጠል አለበት ይላሉ። ኢትዮጵያ ህገ መንግስት ያስፈልጋታል። ትክክለኛ የሆነና ሁሉንም ወይም ደግሞ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የእኔ ናቸው ብሎ ሊቀበላቸው የሚችላቸው አንቀፆችን የያዘ ህግ መንግስት ያስፈልጋል።

በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት በህግ ደረጃ በርካታ ጥሩ ጎኖች አሉት። ስለሰብዓዊ መብትም ሆነ ስለ ህዝብ ሉዓላዊነት ብዙ ቁምነገሮችን ያካተተ ነው። ችግሩ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ እነዚህንና መሰሎቹን ወደተግባር መመንዘር አለመቻል ላይ ነው።አንዳንድ የማያስፈልጉ አንቀፆች ደግሞ ሊኖሩ ይችላሉና እነዚህም ላይ በስፋት ህብረተሰቡ፣ የኃይማኖት ተቋማትም ሆኑ የግሉ ዘርፍ፣ እድሮችና ሌሎችም ሁሉ በተወካዮቻቸው አማካይነት አንጥረው አውጥተው ይህን ጉዳይ በድጋሚ እንወያይበት በማለት ብሄራዊ መግባባት መድረስ ይኖርባቸዋል።

ሌላው ፖለቲካዊ መግባባት በማን መካሄድ አለበት የሚለው ነው። አንዳንዶቹ በሊሂቃን፣ በፓርቲዎች፣ በመንግስትና በተፎካካሪዎች እንዲደረግ ይፈልጋሉ፤ ይህ አይደለም። ወደፊት እንዴት እንሂድ፤ ችግራችንን እንዴት እናስወግድ በማለት አንድ ሁለት ሶስት ብለን ነቅሰን አውጥተን ከላይ እስከታች ተወያይተን፣ ተከራክረን መስመር ማስያዝ ያስፈልገናል። እንዲህ ስል 110 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ይሰበሰባል ማለት አይደለም፤ ነገር ግን በሚያምኗቸው ተወካዮቻቸው አማካይነት መምክር ይችላሉ።

ስለዚህ ይህን የአገረ ብሄር ግንባታ ፕሮጀክት ስናካሂድ በተቻለ መጠን በጣም በስሱ የኃይማኖት ተቋማት፣ የፌዴራልና የክልል የፍትህ ማህበራት፣የሴቶች ማህበራት፣ የወጣቶች ማህበራት፣የግሉ ዘርፍና የመሳሰሉት እንዲሳተፉበት አድርጌያለሁ፤ ይቺ ግን ትንሽ ነገር ናት።

አዲስ ዘመን፡- ፕሮጀክቱ አሁን ምን አይነት ሂደት ላይ ደርሷል?

ፕሮፌሰር ካሳሁን፡- በመጀመሪያ ሲምፖዚየም ከተለያዩ አገራት ባገኘናቸው ልምዶች ላይ ተነጋግረናል። ሁለተኛው ሲምፖዚየም ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ የአገረ ብሄር ግንባታ ለማካሄድ ያሉ እድሎችና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው በሚል ጉዳይ ላይ ተነጋግረናል። በወቅቱ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመም ነበሩ። ያንን ቋጭተነው ለመንግስት በሚቀርቡ መንገዶች ማለትም ለፖሊሲም ሆነ ለምክረ ሐሳብ ግብዓቶች ናቸው ብለን በሰላም ሚኒስቴር በኩል ለመንግስት እንዲቀርብ አድርገናል።

ሌላው ደግሞ በፕሮጀክቱ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በአሜሪካ እና በአውሮፓ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ተወያይተናል። በቀጣይ ደግሞ በክልሎች ይህንኑ ጉዳይ ማካሄድ አለብን ብለን አስበናል። በክልል የምናገኘውን ምክረ ሐሳብ ደግሞ በተመሳሳይ ለመንግስት እናቀርባለን። መንግስት እነዚህን ሁሉ ሰብስቦ ከተኛበት መጮህ እንጀምራን። እየሰራ አለመሆኑንም እንናገራለን።

እየሰራባቸው ስለመሆኑ ግን ምልክቶች አሉ። ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በተለያየ ጊዜ ተገናኝተናል። ይህን ሐሳብ ከመጀመሪያው አንስቶ እየደገፉት ስለመሆናቸው መረዳት ችለናል።የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆኑ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ሀሳቡን እንደሚደግፉት አረጋግጠናል።

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ባለድርሻ አካሉም ሆነ ህዝቡ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ይላሉ? ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለዎት?

ፕሮፌሰር ካሳሁን፡-መልዕክቴ የሚሆነው ልማት ለማካሄድ፣ ህብረተሰቡ የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር ለማድረግ፣ የጋራ እሴቶቻችንን አጠንክረን ወደፊት ለመሄድ፣ ልዩነቶቻችንን ለመፍታት፣ የአገራችንን ዋና ዋና ችግሮች ለመፍታት በመጀመሪያ በአገራችን ውስጥ ሰላም ሊኖር ይገባል። በመሆኑም ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ተቀዳሚው ጉዳይ ነው።

በጋራ ለመነጋገርም ሆነ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሰላም የግድ ይላል። እኔና አንቺ አሁን ለመነጋገር የቻልነው አንፃራዊ ሰላም በመኖሩ ነው።ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ እየተባለ የሚጮኸው አገር ከሌለ ምን ላይ ተቆሞ ይጮሃል? ልማት ልማት ሲባልም ልማት አየር ላይ አይሰራም።

ስለዚህም እነዚህን እውን ለማድረግ በቅድሚያ ሰላም ያስፈልጋል። ምን አይነት ሰላም የተባለ እንደሆነ ፍትሃዊ ሰላም ነው የሚሆነው መልሱ። አንዳንዴ የአንዳንዱ ሰላም ለአንዳንዱ ሲኦል ሊሆን ይችላል።ስለዚህ ሰላም ምንድን ነው? እንዴትስ እናምጣው? እንዴትስ ፍትሃዊ እናድርገው? ከሰላሙስ ሁሉም ተጠቃሚ መሆን ይችላል ወይ በሚለው ላይ በሰፊው በመነጋገር መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

ፕሮፌሰር ካሳሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ።  

አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2011

 አስቴር ኤልያስ