ዘረኝነት በእግር ኳስ ማጥላቱን ቀጥሏል

12

በተወዳጅና አዝናኝነቱ ከዓለም ህዝብ ዘንድ መንገስ የቻለ ስፖርት ነው፤ እግር ኳስ። ድምበር አልባነቱም ህዝቦች ያለ ልዩነት እንዲቀራረቡና በአንድ ቋንቋ እንዲግባቡም አድርጓል። በርካታ ሃገራት መልካም ገጽታቸውን የገነቡበት አንደኛው መሳሪያ እንዲሁም ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ የንግድ አካልም ሆኗል።

ባለሃብቶችን በቀላሉ መሳብ የቻለው ስፖርቱ በርካታ ተጫወቾችንም ባህር አቋርጠው እንዲጫወቱ አስችሏቸዋል። ነገር ግን ስፖርቱ ሰለጠነ በተባለ ዘመንና ሃገራት ሳይቀር ጥላሸት ከሚቀባው ዘረኝነት እስከ አሁንም መላቀቅ አልቻለም። እንዲያውም በዚህ ወቅት በተለይ ይስተዋልባቸው ከነበሩ ሃገራትና ሊጎችም አልፎ በርካቶች ዘንድ እየተተገበረ መሆኑ ይነገራል።

በቃላት፣ በምልክት፣ በድምጽ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች የሚከናወነው ድርጊቱ በተጫዋቾች ላይ በሚያደርሰው የስነልቦና ጫና ምክንያት ከሚወዱት እግር ኳስ ሊያርቃቸው እንደሚችልም የስፖርቱ ከዋኞች በመጠቆም ላይ ይገኛሉ። የቅርቡን ለማስታወስ ያህልም፤ ባለፈው እሁድ በቅርቡ ኢንተርሚላንን የተቀላቀለው ሮሜሉ ሉካኩ የቅጣት ምት ማግኘቱን ተከትሎ ተመልካቾች የጦጣ ድምጽ ያሰሙ ነበር። ፓውል ፖግባ፣ ታሚ አብርሃም እና ኩርት ዙማም ይህ ዓይነቱ ጥቃት በቅርቡ የደረሰባቸው ተጫዋቾች ናቸው።

የእንግሊዝና የቦርሲያ ዶርትመንድ የክንፍ ተጫዋቹ ጃደን ሳንቾም በአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ላይ ተመሳሳይ ጥቃትን አስተናግዷል። ይህንን ተከትሎም ተጫዋቹ በሰጠው አስተያየት «ይህ ነገር መቆም አለበት፤ ምክንያቱም የትኛውም ተጫዋች ጥቃት እየደረሰበት እግር ኳስን መጫወት ስለማይፈልግ። የተጫዋቾችን በራስ መተማመን የሚያወርድ ከመሆኑም ባሻገር ለስፖርቱ ያላቸውንም

 ፍቅር ያሳጣል» ማለቱን ጎል ዶፐት ኮም አስነብቧል።

ተጫዋቹ በዚህም ሳያበቃ «ሁላችንም ደስተኛ መሆን አለብን ማድረግ ያለብንንም ለማድረግ የዘረኝነት ጥቃቱ ሊቆም ይገባል። ደጋፊዎች የሚናገሯቸውን ነገሮች መለየት ይገባቸዋል ምክንያቱም እኛም ሰው ነን። ሰዎች ታዋቂ በመሆናችን ይህ ዓይነቱ ነገር ሲከሰት በዝምታ እንደምናልፍ ያስባሉ። ነገር ግን ለምንድነው እግር ኳስ የምንጫወተው ብለን እንዳስብ ያደርገናል» ሲልም ስሜቱን አንጸባርቋል።

የቀድሞ የማንቺስተር ሲቲ እና የአሁኑ የጣሊያን ብሔራዊ ቡን አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ በበኩላቸው፤ «እንዲህ ያለው የዘረኝነት ጥቃት ያበቃ መስሎን ነበር፤ ነገር ግን አሁንም እንደ እንግሊዝ ሁሉ በጣሊያንም ይስተዋላል። ይህንን ስህተት የሚፈጽሙ ሰዎችም ማጥፋታቸውን በጊዜ ሂደት ይረዳሉ። እንደሚመስለኝ ከሆነም ተግባሩን የሚፈጽሙት ተመሳሳይ ሰዎች ይመስሉኛል» ሲሉ ገልጸዋል።

የኢንተር ሚላን ደጋፊዎች በበኩላቸው ጣሊያናዊያን ደጋፊዎች ዘረኞች አለመሆናቸውን ገልጸዋል። «በካግላሪ ደጋፊዎች ለተንጸባረቀው ዘረኝነት ማዘናችንን እንገልጻለን» ሲሉም ከአዲሱ ተጫዋቻቸው ጎን መቆማቸውን አሳይተዋል። በደጋፊዎቹ ይፋዊ የፌስ ቡክ ገጽ በሰፈረው ጽሑፍ ላይም ተጫዋቹን «መረዳት ያለብህ ጣሊያን እንደ ሰሜን አውሮፓ ሃገራት የተጋነነ የዘረኝነት ችግር የሌለ መሆኑን ነው። ተጫዋቾቻንን ለማበረታታት እንዲሁም ተቃራኒውን ቡድን ለማሸበርም የተለያዩ ድምጾችን እናሰማለን። በመሆኑም የእኛን እንደ ድጋፍ እንጂ እንደ ተቃውሞ አትረዳው» ማለታቸውንም ቢቢሲ በድረ ገጹ አስነብቧል።

የሰሞነኛው መነጋገሪያ የሆነው ካግላሪ ክለብም ክስተቱን «አሳፋሪ» በማለት የገለጸው ሲሆን፤ በአሳፋሪው ድርጊት የተሳተፉትን በመለየት እስከ እገዳ የሚደርስ ቅጣት እንደሚያስተላልፍባቸው አስታውቋል።

አዲስ ዘመን  ነሐሴ 30/2011

ብርሃን ፈይሳ