ሁለንተናዊ ብልፅግና ለተሻለች ኢትዮጵያ

25

አዲሱን ዓመት በመደመር እሳቤ ለመቀበል 13ኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ ደርሰናል። የዘንድሮ የጳጉሜን ወር ስድስቱ ቀናት ‘ጳጉሜን በመደመር’ ተብለው በተለያየ አርዕስት መልእክቶች የሚተላለፉባቸው ሆነው ተቀርጸዋል። ዛሬ ጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም ‘የብልፅግና ቀን’ ተብሎ ተሰይሟል።

የተፈጥሮ፣ ሰብአዊና ባህላዊ እሴቶች ባለፀጋ የሆነችውን ኢትየጵያን በመደመር ለማበልፀግ ህዝቦቿ ዝግጁ እንዲሆኑ ታስቦ እለቱ ብልፅግናን በሚያወሱ ውይይቶችና የሀሳብ ልውውጦች ሲካሄድበት ይውላል።

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት አዘጋጅነት ሁለንተናዊ ብልፅግናን በተመለከተ የሃይማኖት ሰባኪያን፣ የህክምና፣ የስነልቦና እና በማህበራዊ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ የአለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮችና ሌሎችም ባለሙያዎች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱን ተከታትለን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ብልፅግና በተለያዩ ባለሙያዎች አንደበት

ብልፅግና በተለያዩ መንገዶች የሚተረጎም እና ፈርጀ ብዙ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን፤ ተወያዮቹ እንደራሳቸው እይታ ትርጉም ለመስጠት ሞክረዋል። አንዳንዶቹ ብልፅግና ጥበብ፣ እውቀትና ፀጋ ነው ብለዋል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ በግለሰብ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብ እና በሀገር ደረጃ ሊገለፁ የሚችሉ ስለመሆናቸውም ያነሳሉ። ጥበብ፣ እውቀትና ፀጋን በመጠቀም ራስን፣ ቤተሰብን፣ ማህበረሰብና ሀገርን ማበልፀግ እንደሚቻልም ያስረዳሉ። ከኢኮኖሚና ልማት በላይ የሆነው ብልፅግና በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መልኩ ሊገለፅ እንደሚችል ያነሱም አሉ። በሀብት መበልፀግ፣ በቤተሰብና ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት እና በፖለቲካው መስክ ለሀገር የሚጠቅም ስራን በመስራት መበልፀግን እነዚሁ ግለሰቦች ዋቢ አድርገው ሀሳባቸውን ገልፀዋል።

ብልፅግና ለራስ ከማሰብ በዘለለ በአካባቢ ላሉ እህት ወንድሞች ማሰብና የጋራ ጥቅምን የማስቀደም አስተሳሰብ ውጤት እንደሆነ ያነሱት ተወያዮቹ፤ አገር ልትበለፅግ የምትችለው ተያይዞ ማደግ ሲቻል ብቻ ነው ይላሉ። ሌላውን በመጣል ራስን ብቻ ማሻገር ለውጥ አለማምጣት ብቻም ሳይሆን ወደ ብልፅግና ማምራት እንዳይቻል የሚያደርግ እንቅፋት እንደሆነም ገልፀዋል።

ብልፅግና የአገር ህልውና ማረጋገጫ ነው። አገር ስትበለፅግ ዜጎቿ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትና ከበሬታን ያገኛሉ። ልጆቿ በስደት ከመንገላታት ይልቅ በአገራቸው ሰርተው በመልፀግን ምርጫቸው ያደርጋሉ። የአገር ኢኮኖሚ በፅኑ መሰረት ላይ ስለሚገነባ ዜጎች የድህነት ስጋት ውስጥ አይገቡም፤ በዚህም የመኖር ህልውናቸው የተረጋገጠ ይሆናል።

ህይወትን ማሳመርና ጤናማ ማህበረሰብን መፍጠር የብልፅግና መገለጫ ሊሆን ይችላል ያሉት ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ የበለፀገ ህዝብ ህይወቱን እያመዛዘነ የሚመራ በመሆኑ አገርን ተጠቃሚ ያደርጋል። ብልፅግና ያለን ማካፈል፣ በጎነት፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ህብረት፣ ነጻነት፣ መረጋጋትና የደህንነት ስሜትን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው።

ብሔራዊ ትርክትና ሁለንተናዊ ብልፅግና

በአገር ደረጃ ሁሉንም የሚያግባባ እና የሚያስማማ ብሔራዊ ትርክት ሊኖር ይገባል። ትርክቱ አገር ወደ ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ በመደገፍ መንገዱን የተመቻቸ እንደሚያደርግ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል። ብሔራዊ ትርክት የሌለው ህዝብ አንድነቱ የተረጋገጠ ስለማይሆንና ለጋራ ራዕይ በአንድነት መንቀሳቀስ ስለሚቸግረው በዚህ በኩል ሰፊ ስራ በመስራት አገር እንድትበለፅግ ማድረግ ያስፈልጋል።

አንድ ብሔራዊ ትርክት ያለው ህዝብ በአንድ ልብና መንፈስ ወደ እድገት እና ብልፅግና የሚያደርገው ግስጋሴ የተቃና ሲሆን፤ አሁን በአገሪቱ የሚስተዋለው ግን ከዚህ በተለየ መልኩ አንድ ብሔራዊ ትርክት ሳይሆን ሁሉም በየድርሻው የራሱን ትርክት የሚያንፀባርቅበት ነው። ይህ ደግሞ ለመከፋፈል በር ከፋች ሲሆን እየታየም ነው።

ነጻነት ከብልፅግና ጋር ያለው ዝምድና

ነጻነት የሌለው ህዝብ የበለጸገች አገር ሊፈጥር አይችልም። ህዝብ ሀሳቡን በነጻነት በመግለፅ፣ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሁሉም አካባቢ በነፃነት መንቀሳቀስና ሰርቶ መኖር ሲችል አገርን ለማበልፀግ የድርሻውን ይወጣል። በነፃነት እጦት ስጋት ውስጥ የገባ ህዝብ ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ ማህበረሰቡንና አገሩን ለማበልፀግ ይቸገራል። አእምሮው ከስጋት ነፃ የሆነ ህዝብ ባለው አቅም ሁሉ በመንቀሳቀስ የብልፅግና ጉዞው አካል ስለሚሆን ለህዝብ ነፃነትን ማጎናፀፍ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ተወያዮቹ ይገልፃሉ።

ህዝብ በፈለገው አካባቢ ተዘዋውሮ ሀብት ማፍራት ካልቻለ እና በስጋቶች የተሸበበ ከሆነ፤ አገርም ለመበልፀግ የሚፈጅባት ጊዜ ረጅም ይሆናል። የብልፅግና ሂደቱ ውጣ ውረድ የበዛበት እና ፈታኛ በሆኑ መሰናክሎች የተከበበ እንዲሆን ያደርገዋል። አሁን በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ መፈናቀሎች ከነፃነት እጦት ጋር ቁርኝት ያላቸው እና በቶሎ ሊፈቱ የሚገባቸው ናቸው። ህዝብ ነፃነቱን ሲጠይቅ እና መንግስት የነፃነት ነጋሪቱን ሲጎስም አብሮ የመልማትና የመበልፀግ አዋጅ ይታወጃል።

የደህንነት ስጋት የሌለባት አገር መገንባት ወደ ብልፅግና የሚደረግ ጉዞን የማሳጠር ዋነኛው መንገድ ነው። በመሆኑም መንግስትና ህዝብ አገርና በነፃነት መምራትና አስተማማኝ ፀጥታን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።

ባለፀግነት ከባለሀብትነት ይለያል !

ባለፀግነት ሀብትን ብቻ ሳይሆን ሰላምን፣ ደህንነትን፣ ፍቅርን፣ ለሌሎች መኖርን፣ በጎነትን፣ አገልጋይነትን፣ ነፃነትና የመልካም አስተሳሰብ ባለቤትነትን ሁሉ የሚይዝ ስለሆነ ከባለሀብትነት ጋር እንደሚለያይ ተገልጿል። ባለሀብቶች ሁሉ ባለፀጎች አይደሉም፤ ሀብትን ወደ ፀጋ ለመቀየር የመልካም አስተሳሰብና አርቆ አሳቢነት መኖርን ይሻል። በተወያዮቹ ባለፀጎች የብልፅግና መሰረቶችና ቁልፎች ስለመሆናቸውም በውይይቱ ወቅት ተብራርቶ ቀርቧል። ባለፀግነት ቁሳዊ ሀብት ከማከማቸት ይዘላል። ብልፅግና አእምሮ ውስጥ የሚፈጠርና ልብን የሚገዛ እውነት ሲሆን ህዝብ ሲተጋ ደግሞ ብልፅግናን እውን ያደርጋል።

እውቀትና ጥበብን ያጣ ትውልድ መበልፀግን ሊያስብም ሊያልም አይችልም። ለባለሀብትነት ብቻ ሳይሆን ለባለፀግነትም ጭምር መስራት እና መንቀሳቀስ የሚጀምር ህብረተሰብ የብልፅግና ጉዞ አንቀሳቃሽ ሞተር ተደርጎ ሊታሰብ እንደሚችልም በውይይቱ ተነስቷል።

ሌሎች እንዲኖሩ የማድረግ ብልፅግና

‹‹አንድ አገር እንድትበለፅግ ከተፈለገ ውስጣችን ያለው አስተሳሰብ ለእኔ ሳይሆን ለእኛ በሚል መንፈስ ሊቃኝ ይገባል። እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎችም እንዲኖሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ሲቻል ብልፅግናን እውን ማድረግ ይቻላል። የሌሎችን ደስታ በእኛ ስንመለከት እውነተኛ ብልፅግና መምጣቱን ማረጋገጥ እንችላለን። በሀገር ደረጃ የዚህ በጎ አስተሳሰብ ባለቤት መሆንም ያስፈልጋል። ›› በማለት አንድ የውይይቱ ተሳታፊ ተናግረዋል።

የህብረተሰቡ አስተሳሰብ ሲቀየር ከግለኝነት ይልቅ ማህበረሰባዊነት ቅድሚያ ያገኛል። በዚህ ወቅት ደግሞ ሌሎች በእኛ ውስጥ እንዲኖሩ የማስቻል መልካም አስተሳሰብን በመላበስ ሁለንተናዊ ብልፅግናን እውን ማድረግ ይቻላል። ሌሎች እንዲኖሩ ለማድረግ የግድ ባለሀብት መሆንን የማይጠይቅ ሲሆን፤ አንድ ሰው ባለው ነገርና መልካም አስተሳሰብ ሌሎችን በማኖር ህልውናው እውን ሊደርግ ይችላል ተብሏል።

መልካም የስራ ባህልና ብልፅግና

የበለፀጉ አገራት መልካም የስራ ባህል ያላቸው ህዝቦች ባለቤቶች ናቸው። የሚሰራውን ስራ እንደራስ ንብረት በመቁጠር በታማኝነት መፈፀም ወደ ብልፅግና ያሻግራል። የአገር ንብረትን በፍትሀዊነት መጠቀምና ማስጠቀም፣ በስራ ቦታ በሀቀኝነት በመስራት እያንዳንዱን ስራ የብልፅግና ማሳያ አድርጎ መቁጠር ይችላል። የስራ ባህልና ልምድን በማሻሻል ጊዜውን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለመበልፀግ የምናደርገው ጉዞ በአጭር ጊዜ እውን እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

መልካም የስራ ባህልን ለማዳበር ደግሞ ከራስ ጀምሮ የተነሳሽነት መንፈስን ማሳደግና ስራን ባህል አድርጎ መቁጠርን መልመድ ያስፈልጋል። ስራውን ባህሉ ያደረገ ህብረተሰብ በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልግ አይደለም። በአቋራጭ መክበር ደግሞ የሌሎችን መብትና ጥቅም የሚጋፋ በመሆኑ መልካም ሰሪዎችን ያኮስሳል፤ አጭበርባሪዎችን ያጠናክራል። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን መልካም የስራ ባህላችንን በማዳበር ብልፅግናችንን ማፋጠን ለነገ የማንለው የቤት ስራ ሊሆን እንደማይገባም በውይይቱ ላይ ተገልፆዋል።

ተተኪ ትውልድን ማነፅ

ተወያዮቹ እንደተነጋሩት፤ አገር እንዳትበለፅግ እንቅፋት ከሚሆኑ ነገሮች ዋነኛው ተተኪ ትውልድ ላይ አለመስራት ነው። ትውልድ የእርስ በእርስ ትስስሩ እንዲጠናከር፣ የግለኝነት አመለካከትን እንዲያስወግድ እና አሻጋሪ እንዲሆን ማነፅ ያስፈልጋል። ትምህርት ቤቶች ላይ የሚሰራ ስራ የነገ የብልፅግና ራዕይን እውን ለማድረግ ድርሻው የጎላ በመሆኑ ብልፅግናን ለተተኪው ትውልድ ማሳየት ተገቢም ግዴታም ነው።

በትውልድ መካከል የሚፈጠር የግብረ ገብነት ልዩነት አንዱ ሌላውን እንዲወቅስ በማድረግ የሚያስማሙ ሳይሆን የሚያለያዩ ሀሳቦች እንዲጎሉ ያደርጋል። በስነምግባር የታነፀና በጎነትን የተላበሰ ትውልድ መፍጠር ነገን የተሻለ ማድረግ ብቻም ሳይሆን ብልፅግናን እውን ለማድረግ የሚያስችል መሳሪያ ማስታጠቅ ነው። ስነምግባሩ በወጉ የታነፀ ትውልድ አገራዊ አንድነቱን አስጠብቆ ለጋራ ጥቅምና ብልፅግና በአብሮነት ይሰራል። በጎነትን በልቡ የያዘ ተተኪም ከራሱ አልፎ ሌሎችን ለመጥቀም ወደ ኋላ አይልምና አብሮ በማደግና በመበልፀግ ትልም ይጓዛል። ስለዚህ ተተኪ ትውልድ ላይ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ እስከ ላይኛው ድረስ በርትቶ መስራት ያስፈልጋል።

ስርዓተ ትምህርት ተቀርፆና ትኩረት ተሰጥቶ ከተተገበረ ውጤት የሚታፈስበትና ዘላቂ የብልፅግና መስመር የሚያዝበት ቀን ረጅም እንዳልሆነ ተወያዮቹ አንስተዋል። አገር ትምህርት ቤቶችን ትመስላላች ያሉት አስተያየት ሰጪዎች በትምህርት ቤቶች የሚሰራ መልካም ስራ አገርን ለመገንባት የሚቀመጥ የብልፅግና መሰረት ድንጋይ ሆኖ ሊቆጠር እንደሚችል አስረድተዋል።

የዕለቱን ሳይሆን የነገና የወደፊቱን የሚያስብ ትውልድ መገንባት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ሲሆን፤ ይህንን እውን ለማድረግ መስራት ደግሞ ብልፅግናን ለማምጣት የሚደረግ ጉዞ ጅማሬ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

በግብረገብነቱ ብቁ የሆነ ትውልድ ማህበረሰቡን በበጎ አድራጎት ስራዎች ያገለግላል። የበጎነት ስራ ደግሞ ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የብልፅግና በር ከፋች ሆኖም ያገለግላል። ሰብአዊ አገልግሎት የሚሰጥ የበቃ ትውልድ መፍጠር ሲቻል እና የተቆርቋሪነት መንፈስ ሲኖር የጋራ ዕድገትን እውን ለማድረግ ትውልድ ያለውን እምቅ ኃይልና እውቀት ለዚህ በጎ ተግባር እንዲያውለው በርትቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ተወያዮቹ።

የተቋማት እና የስርዓት ግንባታ ለብልፅግና

በአገሪቷ ብልፅግናን እውን ለማድረግ የሚያግዙ ተቋማት እምብዛም አልተገነቡም። የተገነቡትም ቢሆኑ የተገነባላቸው ስርዓት ከብልፅግና ለመድረስ በሚደረግ ሩጫ ውሃ የሚያነሱ ሆነው አልተገኙም። የህዝብን መብትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እንዲሁም ሰርቶ ለመቀየር በሚደረግ እንቅስቃሴ መደላድሎችን የሚያመቻቹ ተቋማት ያስፈልጋሉ። ተቋማቱ የተጠናና የተረጋጋ ስርዓት ሲበጅላቸው ደግሞ ብልፅግናን እውን ለማድረግ አላስፈላጊ ቢሮክራሲን ያስወግዳሉ።

ተቋማቱ ለሁሉም ህዝብ እኩል እድልና ነፃነትን በማጎናፀፍ ህዝብ ከመንግስት ጋር እጅና ጓንት

በመሆን ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚደረግ ግስጋሴን ያፋጥናሉ። በአቅርቦት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ እና ፍትሀዊነት የተቃኙ ተቋማት ሲኖሩ መንግስት ባለፀጎችን ይፈጥራል፤ ባለፀጎች ደግሞ መንግስትንና ህዝብን ያበለፅጋሉ። አቃፊ ተቋማት ወደ ውጪ የሚያማትር አይንን የመመለስ አቅም ስለሚኖራቸው የሀገር ልጅን እውቀትና መዋእለ ነዋይ በአገር በማፍሰስ ብልፅግናን ወደ ፊት ፈቀቅ ማድረግ ይቻላል።

ተቋማቱ የሚመሩበት ግልፅ ስርዓትም የብልፅግና አንደኛው ቁልፍ ጉዳይ ነው። ተቋማትን መገንባት ብቻውን ውጤት ሊያስገኝ አይችልም፤ ውጤቱ የሁለቱም የተሰናሰለ ድምር ሲሆን ለተገልጋይ እርካታን የሚያጎናፅፉ ይሆናሉ።

ማህበራዊ ግንኙነት እና ብልፅግና

ማህበራዊ ግንኙነቱ የተጠናከረ ህብረተሰብ የሚያልመው በጋራ ሰርቶ አብሮ ስለመበልፀግ ነው። ማህበራዊ ትስስሩ ጠንካራ የሆነ ህብረተሰብ የግለኝነትና አግላይነት መንፈስ የተጠናወተው አይደለም። ይህን መሰሉ አስተሳሰብ የሚመነጨው ደግሞ የማህበረሰቡ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ስሜት ተጠብቆ መቆየት ሲቻል ነው። ብልፅግና ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች መኖርን የሚጠይቅ በመሆኑ እንደአገር እውን ለማድረግ ሲታሰብ ማህበራዊ ግንኙነትን ማጠናከር ላይ መሰራት እንዳለበትም ተወያዮቹ አንስተዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ማህበራዊ ግንኙነት እጅግ የጠበቀባት አገር ወደ ብልፅግና የሚደረግ ጉዞን ለማመቻቸት ቀላል ቢሆንም የዚያን ያህል ግን ትልልቅ ስራዎችን መስራትም ይጠይቃል። ግንኙነቱን አጥብቆ ማስቀጠል እና የአንድነት መንፈሱ የማይፈረካከስ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረትን ይጠይቃል።

ከራስ የሚጀመረው ብልፅግና የሚያመራው ወደ ማህበረሰቡ በመሆኑ የጋራ ራእይና ግብ ያለው ጠንካራ ቁርኝት መፍጠር መንገዱን ቀና ያደርገዋል። እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር የማህበረሰቡ ትስስር አንድ በሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች የተገመደ በመሆኑ እድሉን በመጠቀም አገርን ከድህነት እና ከመከፋፈል ወደ ብልፅግና ማሻገር ይቻላል። ይሁን እንጂ አሁን አሁን እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ መለያየቶች እና መከፋፈሎች የብልፅግናን ጉዞ የሚገቱ፣ ግለኝነትንና ምን አገባኝነትን የሚነግሱ በመሆናቸው መስተካከል እንዳለባቸው ተነስቷል።

የበርካታ ሰብአዊና ባህላዊ እሴቶች ባለፀጋ በሆነችው አገር ማህበራዊ ግንኙነትን ይበልጥ በማጠንከር የፀጋዎቿ ተቋዳሽ መሆን ብቻም ሳይሆን የፀጋዎቿ ምንጮች መሆንም ይጠበቅብናል።

ወደ ብልፅግና ማምራት ያልቻልነው ለምን?

ኢትዮጵያ ወደ መበልፀግ ልታመራ ያልቻለችባቸው በርካታ ችግሮች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ግለኝነት፣ ሙስና፣ ጠባቂነት፣ ብዙ ፈላጊነት፣ ገፊነት፣ የአስተሳሰብ አለመለወጥ እና ሌሎችም ለዚህ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ለረጅም ዘመናት ያሳለፍናቸው ጨቋኝ ስርዓቶችም ለዚህ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ለራስ ያለ ግምት የወረደ ሲሆን ለለውጥ መነሳሳትን ከማዳከሙ ባሻገር አገር ወደ ብልፅግና እንዳታመራም ያደርጋታል።

ካለ ነገር ላይ አለማካፈል የስግብግብነት መንፈስን አላብሶ የእኔነት ስሜትን ብቻ ያነግሳል። ሙስና የአገርን ሀብት በመበዝበዝ ለራስ ጥቅም የማዋል አባዜ በመሆኑ የህዝብን ተጠቃሚነት እየሸረሸረ ግለሰቦችና ቡድኖችን ብቻ ያፈረጥማል። የጠባቂነት መንፈስ ሳይሰሩ ማግኘትና የተረጂነት መንፈስን ስለሚያሰፍን ሰርቶ ለመለወጥ የሚደረግ ጉዞን በአጭር ያስቀራል።

ብዙ ፈላጊነት በራስ ጥረት ብቻ ሳይሆን አግባብ ባልሆነ መንገድ በመበልፀግ መደልደልን ይፈጥራል። የተቸገሩትን ከመደገፍ ይልቅ መግፋትን ያስቀድማል። በማህበረሰቡ ዘንድ ወደ ብልፅግና ለማምራት ያለ የአስተሳሰብ ክፍተትም ሌላኛው መንስኤ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። አገር ከድህነት እንደማትላቀቅና የተወሳሰበ ችግርን ዘላለማዊ አድርጎ የመሳል አዝማሚያዎች ወደ ብልፅግና መራመድ እንዳይቻል የሚያደርጉ ናቸው። በአብሮነትና በጥረት ሌሎች የደረሱበት ቦታ ለመድረስ እንደሚቻል የሚያምን ህብረተሰብን ለመለወጥ ዝግጁ ሲሆን፤ ለጉዞው የመጀመሪያውን እርምጃ እንደተራመደ መቁጠር ይቻላል።

አሁን አሁን እየገነነ የመጣው የዘረኝነት መንፈስ ብልፅግናን የሚጎዳ፣ ሰላምን የሚያደፈርስ፣ የደህንነት ስጋት ውስጥ የሚከት፣ የአገር መልካም ስምን በማጉድፍ ገቢን የሚያሳጣ፣ ውስጣዊ መፈናቀልን የሚፈጥር እና የሚያባብስ እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን የሚፈጥር ነው። ስለዚህ የዘረኝነት አስተሳሰብ ተወግዶ የአንድነት መንፈስ ቦታውን ካልተረከበ በስተቀር አገር የምታደርገውን ጉዞ በመግታት ከብልፅግና ሀዲድ እንድትወጣ ያደርጋታል።

ብልፅግናን ለማምጣት ምን ይሁን?

ብልፅግና በቀላሉ ሊመጣ የማይችልና በርካታ ስራዎችን መስራት፣ ፈተናዎችንም በፅናት መቋቋም የሚጠይቅ ነው። አሁን በአገሪቷ ባለው ሁኔታ ወደ ብልፅግና ለማምራት አስቻይ ሁኔታዎች የጠበቡ ቢመስልም መንገዱ ጨርሶ የተዘጋ አይደለም። ጉዞውን ለመጀመር እንደ አገር ቀድሞ መግባባትና አንድ የጋራ ራዕይ ላይ መድረስ ያስፈልጋል። በመቀጠል ወደ ራዕያችን የሚያደርሰንን መስመር ተከትለን መስራት ባሰብነው ቦታ ላይ ያደርሰናል። በጉዟችን ከእኛ አጠገብ ሌላ ሰው እንዳለ መረዳትና በጋራ ወደ ሚያሻግረን ዘመን መሸጋገር ያስፈልጋል።

የዕለት ሲሳይ ከማግኘት ጋር ሁለንተናዊ ሰላምና ደስታን አብሮ ማስኬድ፣ ለእኛ የምንፈልገውን ነገር ለሌሎች መመኘት፣ ወጥና ሁሉን የሚያስማማ አገራዊ የብልፅግና ትልም መትለም ወደ መዳረሻው ሊወስዱን የሚችሉ ጠቋሚዎች ናቸው። ከምንም በላይ ደህንነቱ አስተማማኝ የሆነና ከስጋት የተላቀቀ ህብረተሰብ መገንባት አስፈላጊ ነው። ደህንነት ሲረጋጋጥ ሰላም ወጥቶ በሰላም መመለስ፣ በመክሊት መስራት፣ ነፃነት፣ ሀብት፣ ስኬት፣ ትርፍ፣ ዕድልና ቱሩፋትን ሁሉ ማግኘት ስለሚቻል በደህንነቱ የሚተማመን ዜጋን ዕውን ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው።

ብልፅግና የጥቂቶች ሳይሆን የአገር ሲሆን ጠቀሜታው ስለሚጎላ አገራዊ ስሜትን የተላበሰ የአብሮነት ስራ መስራት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ የማትበለፅግበት ምንም መንገድ እንደሌለ በተወያዮች የተገለፀ ሲሆን፤ ፍርሃትን ማስወገድና ብሔራዊ ስሜትን ማጠናከር ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ አስምረውበታል።

ተወያዮቹ በመጨረሻ ኢትዮጵያ የማትበለፅግበት ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለ ገልፀው ብልፅግናውን እውን ለማድረግ ግን ያልተቆጠበ ጥረት እና ትግል እንደሚስፈልግ ለዚህ ደግሞ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ፣ በአዲሱ ዓመት መላው ህብረተሰብ ፍቅርን የማስቀደም እና ጥላቻን የማራቅ፣ አንድነትን የመስበክ እና መለያየትን የማውገዝ፣ ግንኙነትን የማጠናከርና መራራቅን የማስወገድ ስራ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባ መክረዋል።

ችግርን በመነጋገር የመፍታት ባህልን በማዳበር እርስ በእርስ ሊያጋጩ ከሚችሉ ነገሮች መራቅ የሁሉም ህብረተሰብ የአዲሱ ዓመት እቅድ ሊሆን እንደሚገባ ያነሱት ተወያዮቹ ከጥላቻ የሚገኝ ምንም ትርፍ ባለመኖሩ ፍቅርን የህይወት መርህ በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ማሻገር የሁሉም የቤት ስራ ይሁን !

አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2011

ድልነሳ ምንውየለት