ከባህር ዳር ሰማይ ስር በዋልያዎቹ የተመሰለው ብሄራዊ ኩራት

20

ስፖርታዊ ክንዋኔዎች ከመዝናኛነት ባሻገር ጥልቅ የሃገር ፍቅር መውጫ የጦር አውድ መሆኑን በርካቶች ሲናገሩ ይደመጣሉ። «የአትሌቶች ሀገር» ሲል አለም የመሰከረላት ኢትዮጵያችን ለዚህ ንግርት ማረጋገጫ በመሆን ትጠቀሳለች። በአትሌቶቿ በአለም አቀፍ መድረኮች ዘመን ተሻጋሪ የድል ታሪክ በማስመዝገብ አለም የአትሌቶች ሃገር የሚል ተቀጽላን አክሎ እንዲጠራት አድርጓል። ኢትዮጵያን በጀግንነት ለማስጠራት እነዚህ ጀግና አትሌቶች አድካሚና ፈታኝ መንገድ መጓዝ ግድ ይላቸዋል። ፈተናዎቹንም በአሸናፊነት በጣጥሶ ማለፍ ይጠይቃል።

ከአትሌቶቹ ጽናት በተሞላው የድል መዳረሻ ጀርባ «የሃገር ክብር»የሚባል ጥልቅ የሃገር ፍቅር ብርታትና ጉልበት ሲሆናቸው ታዝበናል። በአትሌቶቹ ድል በአለም ፊት አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ቀይ ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ ተውለብልቧል። የድሉ ባለቤት የሆኑት አትሌቶቻችን የሃገር ፍቅር፣ ክብርና ነጻነት ትርጓሜን ያዘለው ሰንደቅ ከፍታ፤ጥልቁን የሃገር ፍቅር ለመግለጽ እንባቸውን መገደብ በተሳነው ሁናቴ ሲገልጹ ተመልክተናል።

የኢትዮጵያ ክብርና አርማ በሆነው ኃይሌ ገብረስላሴ፣ በእንስቷ ንግስታችን ደራርቱ ቱሉ የ2001 የሲድኒ ኦሎምፒክ የዘላለም ምስክር ናቸው። በተለያየ የእድሜ ክልል የሚገኘው ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የአትሌቶቹ በጥልቅ የሃገር ፍቅር ተሞልቶ ድልን የመሻት እሩጫን በማበረታታትና በማገዝ ረገድ ሚናውን ይወጣል።

በድሉ ግኝት በሃገር ፍቅር ስሜትና አብሮነት ደስታውን ያጣጥማል። በአንድነት ብሮ ወሸባዬን ይጨፍራል። በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም ሰንደቅ አላማውን በክብር ከፍ አድርጎ በአንድነት ይሰቅላል። በስፖርቱ ድል የሃገር አሸናፊነትን ስሜቱን ይወጣል።

በአትሌቲክሱ ድል የሚቀዳው ሃገራዊ ስሜት በእግር ኳሱም ቢሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲንጸባረቅ ታዝበናል። እኤአ በ2013 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ ዋንጫ ማለፏን ተከትሎ በህዝቡ ልብ ውስጥ የነበረው ደስታ ከጥልቅ የሃገር ስሜት እንጂ ሌላ ምክንያት አልነበረውም።

ዋልያዎቹ ከ31 ዓመት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የህዝቡ ብሄራዊ ስሜት እንዲገነፍል አድርጎት ታይታል። የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ከገባበት ሰመመን በመቀስቀስ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር በአንድነት አስተሳስሯል፣ አስፈንጥዟልም። የልዩነት ነጋሪት ጉሰማውን ድምጽ በመዋጥ፤ የአንድነቱን ድምጸት አጉልቷል። ይህም በአትሌቲክስ ስፖርት የተገነባው ብሄራዊ ስሜትን ዳግም እንዲያንሰራራ ያደረገ ትልቅ አጋጣሚ ከመሆን በተጓዳኝ ብሄራዊ መግባባት የፈጠረ ልዩ አጋጣሚ እንደነበርም ይታወሳል።

ከትናንት በስቲያም ዋሊያው በቀጣዩ አመት ኳታር ለምታዘጋጀው የአለም ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከሌሴቶ ጋር ሲያከናውን ከባህር ዳር ሰማይ ስር የሆነውም ይህን የታሪክ አጋጣሚ ዳግም ያስመለከተ ነበር። ብሄራዊ ቡድኑን ለመደገፍ ከባህርዳርና አካባቢዋ የሚገኝ የሃገር ስሜት የኮረኮረው ደጋፊ ወደ ስታዲየም ማልዶ ነበር መትመም የጀመረው።

ብሄራዊ ኩራቱን የተሸከሙለትን ዋልያዎቹን ለማበረታታት ከረፋዱ 5 ሰዓት ጀምሮ በህብረ ቀለማት ደምቆና ታጅቦ የተለያዩ ትዕይንቶች ያሳየበት ሁኔታም እጅጉን ደማቅ ነበር። አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀዩ ሰንደቅ በባህር ዳር ጎዳናዎች በድምቀትና በክብር ሲውለበለብ የነበረበት ሁናቴ ታሪክ ራሱን የደገመበት ነበር።

ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ከሁለት አመት በፊት ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በባህር ዳር ስታዲየም ጨዋታቸውን ማካሄዳቸውና በዋልያዎቹ 2 ለ 1 አሸናፊነት መቋጨቱ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ በስታዲየም ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልቶ በተጋጣሚው ቡድን ትልቅ የስነ ልቦና ችግር መፈጠር የቻለው ደጋፊ፣ ለዋልያዎቹ ተጨማሪ አቅምና ጉልበት ሆኖም ነበር።

የትናንት በስቲያም ፍልሚያ ምንም እንኳን በውጤት ሲቃኝ ታሪክ ራሱን ደግሞ ባይታይበትም፤ ደጋፊው ግን በጥልቅ የሃገር ፍቅር ብሄራዊ ኩራቱ የሆነውን ብሄራዊ ቡድን ከማበረታታት አኳያ ታሪክን ደግሞ ሰርቶታል። ከማለዳ ጀምሮ በባህር ዳር ጎዳኖዎች የነበረው ከአገር ወዳድነት የሚፈለቀቀው ጥልቅ ስሜትም፤ ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ ይበልጥ ተጋግሎና ከፍ ብሎ ተሰምቷል።

ሙሉ ዘጠና ደቂቃ በተለያዩ ህብረ ዝማሬዎች በማጀብ ብሄራዊ ኩራት ለሆኑት ዋልያዎቹ ብርታት ሲሆኑ ታዝበናል።”…ዋልያ… ዋልያ…” “… ድሌ ማታ ነው ድሌ…” የደስታ ማጣጣሚያ ሆነው ሲሰሙ የነበሩ የባህር ዳር ስታዲየም ድምጾች ነበሩ።

በእለቱ ከአፍ እስከ ገደፍ በሞላው ስታዲየም የነበረው ትዕይንት በእርግጥም፤ ከባህር ዳር ሰማይ ስር በዋልያዎቹ ተመስሎ ብሄራዊ ኩራት በከፍታ ላይ ሲውለበለብ ለመታዘብ ተችሏል። ምንም እንኳን በብሄራዊ ስሜት ብሄራዊ ቡድኑን ለማበረታታት የተሄደበት ርቀት ታሪክ ራሱን ቢደግምም በውጤት ደረጃ ግን ራሱን መድገም የቻለ አልሆነም። በጨዋታ እንቅስቃሴ ብልጫ ማሳየት የቻሉት ዋልያዎቹ የሌሴቶን መረብ ለመድፈር ሳይችሉ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ተጠናቋል። መከላከልን መሰረት ያደረጉት ሌሴቶዎች ግባቸው ሳይደፈር ነጥብ እንዲጋሩ አድርጓቸዋል።

ከጨዋታው በኋላ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ «ከምንግዜውም በተሻለ ጥሩ ተጫውተናል፤ በርካታ የግብ እድሎችንም መፍጠር ችለናል፤ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎላ የመጣው የአጥቂ መስመር ክፍተት ጎል ሳናስቆጥር እንድንወጣ አድርጎናል። በቀጣይ ጊዜ ግብ የማስቆጠር ችግራችን ለመቅረፍ በርትተን እንሰራለንም» ብለዋል። «90 ደቂቃ ያለእረፍት ከጎናችን በመሆን ያበረታንን ደጋፊ ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ።» ሲሉም በከፍተኛ ድጋፍ ለታጀቡት ዋልያዎቹ በተጋጣሚውን ቡድን ላይ የጨዋታ የበላይነት እንዲያሳይ ሞራል እንደሆናቸው አስምረውበታል። የሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች የመልሱ ጨዋታም የፊታችን ጳጉሜን 3 ቀን ቀጠሮ ተይዞለታል።

አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2011

 ዳንኤል ዘነበ