ገዳይ እንቀይር!

5

Uስለአባባሉ በኋላ እናወራለን! አሁን አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁ፣ ባለፈው ሳምንት ነው። ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ እየመጣን ሻሸመኔን አልፈን ይሁን ሳናልፍ ባላረጋግጥም ከሻሸመኔ ከተማ በቅርብ ርቀት የትራፊክ አደጋ ደርሶ ተመለከትን። ሐበሻ የተባለ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ከዋናው መስመር ወጥቶ ተገልብጧል። ዙሪያውን ሰው ከቧል። የአውቶብሱ አወዳደቅ አስደንጋጭ ስለሆነ መኪናችንን ዳር አስይዘን ሁላችንም ወረድን። በሰው ወደተከበበው የተገለበጠ አውቶብስም ተጠጋን። ፈጣሪ ይመስገን የሆነው ነገር ሁላችንም እንደፈራነው አይደለም! በወቅቱ የሞት አደጋ አልነበረም! የአካል ጉዳት ነበር።

ልነግራችሁ የፈለኩት ስለትራፊክ አደጋው አይደለም። በአደጋው ምክንያት ያየነውን ነገር ነው። በነገራችን ላይ እዚያው ቦታ ላይ እያለሁ ብዙም አልገረመኝም ነበር። የገረመኝ ጉዳዩ አጀንዳ ሆኖ ምሳ ስንበላ በሰፊው ስለተወራበት ነው። ነገሩ እንዲህ ነው።

አደጋው የደረሰው ከከተማ ወጣ ብሎ ስለሆነ ገጠር አካባቢ ነው። የአደጋውን መድረስ የሰሙ የአካባቢው ሰዎች በድንጋጤ ወደተሰበሰበው ሰው ይጎርፋሉ። እናቶች ከቤት ሲወጡ የመኪናውን መገልበጥ አይተው እንባ ይተናነቃቸዋል። እንደተጠጉም ከፊት ለፊታቸው ያገኙትን ሰው ‹‹የሞተ አለ የእኔ ልጅ?›› ብለው ይጠይቃሉ፤ ‹‹አይ! የሞተ እንኳን የለም እማማ!›› ሲባሉ እጆቻቸውን ወደላይ ዘርግተው ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ። ወዲያውም ወደቤታቸው ገብተው ምንጣፍ፣ ሸራ፣ ፍራሽ እየያዙ ይመጣሉ። ጉዳት ለደረሰባቸው የሚበላ የሚጠጣ ነገር እየያዙ ይመጣሉ። ይሄ ሁሉ ሲሆን ‹‹የተማሩ›› የተባሉት ከመኪና የወረዱት (ለማየት ማለት ነው) ከበው ፎቶ ያነሳሉ።

የቆየነውን ያህል ቆይተን ወደመኪናችን ገባንና ጉዞ ጀመርን። ለምሳ የወረድንበት ቦታ ምግቡ እስከሚመጣ እየተጨዋወትን ነው። በጨዋታችን መሃል የእነዚያ እናቶች ነገር ተነሳ። የእናቶችን ነገር ያስገረማቸው ሰዎች ምክንያታቸው፣ እነዚህ እናቶች ከየቤቱ ሲወጡ የማን ብሄር እንደሆኑ፣ ከየት እንደመጡ፣ የምን ቋንቋ ተናጋሪ እንደሆኑ ሳያውቁ ሰው በመሆናቸው ብቻ የተደናገጡ መሆናቸው ነው። አዎ! እነዚያ እናቶች ጉዳቱ የደረሰባቸው ሰዎች ከየት እንደመጡ፣ የምን ብሄር እንደሆኑ፣ የምን ቋንቋ ተናጋሪ እንደሆኑ አያውቁም። እነርሱን ያስደነገጣቸው ሰው መሆናቸው ብቻ ነበር። መቼም በአገር አቋራጭ አውቶብስ በዚያ የሚያልፍ የአካባቢያቸው ሰው እንዳልሆነ ያውቃሉ። የሩቅ አካባቢ ሰው እንደሆነ ይገነዘባሉ፣ የእነርሱ መስፈርት ግን ሰው መሆናቸው ብቻ ነበር። እነዚያ እናቶች እንባቸው ሲረግፍ የጎረቤታቸው ልጅ እንዳልሆነ ስተውት አይደለም!

በእናቶች ድርጊት ለምን ተገረምን?

የነበርነው ሰዎች ‹‹የተማረ›› የምንባለው ነን። የተማረ ማለት እንግዲህ መስፈርቱ ምን እንደሆነ ወሰኑ ባይታወቅም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀን የወጣን ነን። ይሄ የተማረ ክፍል ነው እንግዲህ ያ! የእናቶች ድርጊት ያስገረመው። ዶክተርና ፕሮፌሰር የሚሉ ማዕረጎችን የደራረበውም እንደዚሁ ነው። መስፈርቱ ብሄር ሆኗል። የተገረምንበት ምክንያትም የተማረ የሚባለው አገር የሚያጠፋ ሥራ ሲሰራ እነዚህ ‹‹ያልተማሩ›› የሚባሉ እናቶች እንዲህ አይነት አገር የሚያቀና ሥራ መሥራታቸው ነው። ከዚህ በግልጽ የምንረዳው ነገር የአገሪቱ ችግር ፈጣሪ የተማረ የሚባለው አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍል መሆኑን ነው።

በታደሉት አገሮች የተማረ የሰው ኃይል የሚያስፈልገው፣ ለጥናትና ምርምር፣ ለቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ ለሰላምና ዴሞክራሲ መበልጸግ ነው። በእኛ አገር ግን የተማረ የሚባለው ብሄርን ከብሄር የሚያጋጭ ሆነ፣ ሰውን የሚለካበት መስፈርት ብሄር ሆነ! መገናኛ ብዙኃን አውታር ላይ የሚሰብከው እንደነዚያ እናቶች አይነት ፍቅር ሳይሆን የዓመታት ቂም እያመጣ ማቋሰል ነው።

የእነዚያን እናቶች ድርጊት የተመለከተ አንድ ‹‹ያልተማረ›› የሚባል ሰው ምንም ላይገርመው ይችላል፣ ምክንያቱም ሁሌም የሚያየው ድርጊት ነው። ለእርሱ ይሄ የዕለት ከዕለት ክንዋኔ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም። የተማረ ለሚባለው ለምን አዲስ ሆነበት?

የሚውለው ፌስቡክ ላይ ነው። ፌስቡክ ላይ ያለው ነገር ደግሞ ያው የምታዩት ነገር ነው። ያንን ሲያይ የኖረ ሰው ታዲያ የእነዚያ እናቶች ድርጊት እንዴት አዲስ አይሆንበት?

እሺ ፌስቡክ ይቅር! ጋዜጦችና መጽሔቶች ምንድነው እያደረጉ ያሉት? አንድ የተማረ የሚባል ሰው ፌስቡክን ንቆ ቢተወው እንኳን በጋዜጣና መጽሔት የሚያነበው እኮ ጥላቻና ዘረኝነትን ነው። ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን ቢከፍት የሚሰማውና የሚያየው የዩኒቨርሲቲ መምህር የተባለ ሰው ጥላቻ ሲዘራ ነው፣ ታዲያ የእነዚያ እናቶች ድርጊት እንዴት ብርቅ አይሆንበት?

ለመሆኑ ግን ‹‹የተማረ›› ማለት ምን ማለት ይሆን? ምንም እንኳን ሰፊ የትርጉም ትንታኔ ለመስጠት ሊቅ መሆንን ቢጠይቅም ለሁላችንም ግልጽ የሆነው ትርጉም ደግሞ አለው። አዋቂ፣ አስተዋይ፣ አመዛዛኝ፣ ነገሮችን የሚረዳ… ነው። በተደጋጋሚ በሚባለው ትርጓሜም የሰው ልጅ ከእንስሳት የሚለየው ማሰብ በመቻሉ ነው። እነዚህን መስፈርቶች ይዘን ዲግሪ የደራረቡ ሰዎችን ልብ እንበል! እውነት በትምህርት ቤት በር ያላለፈ አርሶ አደር አይበልጣቸውም? ይሄ ትምህርት ቤት ያልገባ አርሶ አደር፣ አስተዋይ ነው፣ አመዛዛኝ ነው፣ ለሰው ልጅ ክብር ያለው ነው። የተማረ የሚባለው ግን እንስሳ እየሆነ ነው!

የሰው ልጅ ተዘቅዝቆ ሲሰቀል ታይቷል፣ ያንን ያደረገው (ያስደረገው) የተማረ የሚባለው መሀይም ነው። ያ! ድርጊት ለግጭትና ለብጥብጥ ይሆን ዘንድ ሲያራግበው የነበረው ይሄው የተመራኩ ነኝ የሚለው መሀይም ነው። እገሌ ብሄርና እገሌ ብሄር ላይታረቁ ተቆራርጠዋል እያለ የሚነዛው ይሄው የተማረ የሚባለው ነው። የተባሉት ብሄሮች ውስጥ የሚኖሩት ህዝቦች የሚባለው ነገር መፈጠሩንም ያልሰሙ ናቸው። ለእነርሱ መስፈርታቸው ሰውነት ብቻ ነው!

‹‹የተማረ ይግደለኝ!›› የሚለው አባባል የተለመደና ተደጋግሞ ሲጠራ የምንሰማው ነው። የተማረ ይግደለኝ ማለት፤ የተማረ አዋቂና አስተዋይ ስለሆነ እንኳን የሚጠቅም ነገር የሚጎዳ ነገር (መግደል) እንኳን በተማረ ያምራል ለማለት ነው። ብሞት እንኳን የተማረ ቢገለኝ ይሻላል ለማለት ነው። ምን ዋጋ አለው! አሁን ግን ትርጉሙ ተገለባብጧል። ያልተማረ ይግደለኝ ለማለት ተገደናል። አሁን ገዳይ መምረጥ አለብን! የተማረ የሚባለው መሀይም ሆኖ ስለተገኘ ያልተማረ ቢገለን ይሻላል!

የአገሪቱን ሁኔታ ያበለሻሸው የተማረ የሚባለው መሆኑን ብዙ ማሳያዎች አሉን። ያልተማሩ የሚባሉት ባህላቸውና ሃይማኖታቸው ራሱ ለጥፋትና ለክፋት የሚሆን አይደለም። እንደየሃይማኖታቸውና ባህላቸው የበለጠ ክብር የሚሰጡት እንዲያውም ከሌላ አካባቢ ለመጣ ሰው ነው። ‹‹ቤት ለእንግዳ›› የሚለው አባባል ገዥ ህጋቸው ነው። ቤቱ የሚያገለግለው ከቤተሰቡ ይልቅ ለእንግዳ ነው ማለት ነው። እንግዳ ማለት ደግሞ ከሌላ አካባቢ የሚመጣ መሆኑ ግልጽ ነው። ቤት ተስተናግዶ የሚወጣውም ‹‹የአብርሃም ቤት ይሁን›› ብሎ ይወጣል። የእንግዳ ቤት ይሁን ማለት ነው።

እንግዳ ቤት ውስጥ ሲመጣ አልጋ እና ምንጣፍ ይለቀቃል። ቤት ውስጥ ዘወርት ሽሮ የሚበላ ከሆነ ሥጋ የሚፈለግ ወይም ሌላ ለየት ያለ ወጥ የሚሰራው እንግዳ ሲመጣ ነው። እንግዲህ ይሄንን ህዝብ ነው የተማረ የሚባለው ያበላሸው። የተማረ ታሪክ፣ ወግና ባህል ይጠብቃል ሲባል አውዳሚ ሆኖ አረፈው!

ይሄንን ነው ታዲያ ‹‹የተማረ ይግደለኝ!›› እያልን የምናንቆለጳጵሰው? በሉ ገዳይ እንቀይር!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011

 ዋለልኝ አየለ