ከአንድ ሺ በላይ ለሚሆኑ ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጎላቸዋል

38

አዲስ አበባ፡- የፍትህ ወሩንና የፍትህ ቀኑን አስመልክቶ ቁጥራቸው ከአንድ ሺ በላይ ለሚበልጡ ታራሚዎች ይቅርታ የተደረገላቸው መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ገለፀ፡፡ ጳጉሜን አራት 2011ዓ.ም ደግሞ በማረሚያ ቤቶች በመገኘት ከአንድ ሺ በላይ ከሚሆኑ ታራሚዎች ጋር ውይይት እንደሚኖርም ተናገሩ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ‹‹እኔ ለህግ ተገዢ ነኝ›› በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ያለው የፍትህ ቀን በዋናነት የመከበሩ ምስጢር ተቋሙ የሰራውን ሥራ ወደህዝብ በመውሰድና ለህዝብ በማስተዋወቅ ያጋጠሙትን ችግሮች ደግሞ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለመረዳዳት እንዲያመች ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከአንድ ሺ በላይ ለሚሆኑ ታራሚዎች ይቅርታ የተደረገላቸው ሲሆን፣ ጳጉሜን አራት ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አመራሮች፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮች እንዲሁም ፌዴራል ፖሊስ እና የማረሚያ ቤቶች አመራሮች ባሉበት ከአንድ ሺ ከሚበልጡ ታራሚዎች ጋር ውይይት ይካሄዳል፡፡

እንደ አቶ ብርሃኑ ገለፃ፣ በዕለቱ ለታራሚዎች በዓል መዋያ የሚሆን ስጦታ ይበረከትላቸዋል፡፡ የታራሚዎች መኝታም በምን አይነት ይዞታ ላይ እንዳለ ለማየት ያስችል ዘንድ የሚጎበኝ ይሆናል፡፡ በማግስቱ ጳጉሜን አምስት ደግሞ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ይከበራል፡፡ በዕለቱ ከ15ሺ በላይ የሚሆኑ የበዓሉ ታዳሚዎች በሚሊኒየም አዳራሽ ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን ጨምሮ በታዋቂ ሰዎችም ፅሁፎች የሚቀርቡ ይሆናል፡፡

በቀጣይ ህዝቡን የማሳተፍና በተለይ በፍትህ ስርዓቱ ላይ የመጡ ለውጦች ህዝቡ አውቆ ለተጨማሪ ሥራ ከእነርሱ ጎን እንዲሆን ለማድረግም ጭምር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ማዕከላዊ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ኤግዚቢሽን መከፈቱና ለህዝብ እይታ የመቅረቡ ዋናው ዓላማ ማዕከላዊ አልተዘጋም ለሚሉ አካላትም መዘጋቱን በግልፅ ለማሳየት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በስፍራው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈፀምበት የነበረ ቦታ ስለነበር እስር ቤቱንና አጠቃላይ ይዘቱ ምን እንደሚመስል ሰዎች እንዲያዩትና እንዲገነዘቡት ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ሥፍራውን መንግሥት ‹‹ሙዚየም አደርጋለሁ›› ብሎ ስለወሰነ ከወዲሁ እሱንም ለማሳየት በማሰብ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የፍትህ ቀን ‹‹እኔ ለህግ ተገዢ ነኝ›› በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ሲሆን፣ በትናንትናውም ዕለት ማዕከላዊ ለዕይታ ክፍት ሆኖ መዋሉ ታውቋል፡፡ ጳጉሜን 5 ደግሞ የፍትህ ቀን ተብሎ ተሰይሟል፡፡

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011

አስቴር ኤልያስ