በጎ በጎ ታሪኮቻችንን በማሰብ ለሠላም እንቁም

21

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው።በሀገር መኖር፤ የሚቻለው ወጥቶ መግባት፤ ተምሮ እራስንና ቤተሰብን መርዳት፤ ሰርቶ መክበር፤ ወልዶ መሳም፤ ዘርቶ መቃም የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው።ሰላም በሌለበት ሁሉም ነገር ከንቱ ነው።እንኳንስ ለሌላው ለራስም መሆን አይቻልም።

በሰላሟና በጸጥታዋ የምትታወቀው ሀገራችን ዛሬ ሰላም ርቋታል።በብሄር፤ በሃይማኖት፤ በጎሳ ተቧድነን የሰላም አየሩን አደፍርሰነዋል።ለራሳችንም ሰላማችንን አጥተን ሌሎችንም ሰላም እየነሳን እንገኛለን።በማያልቅና አታካች በሆነው እሰጥ እገባችን ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅን መርጠናል። ከመወያየት ይልቅ መዘላለፍን አስቀድመናል። ከመደማመጥ ይልቅ መጯጯህን ልምድ አድርገነዋል። ሰላማችን በመታወኩም ሀገራዊ ጥሪታችን ተዳክሟል። ዕዳ ተጭኖናል። በአጠቃላይ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ገጥመውናል። ስለዚህም ዛሬ ቆም ብለን የምናስብበት ቀን ሊሆን ይገባል።

ከ20 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ዛሬ ስራ ይፈልጋሉ። ከ30 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ፍጹም ከሆነ የድህነት አረንቋ ውስጥ መውጣት ይሻሉ።200 ሺህ የሚጠጉ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደ ሰው ቤት ቀልሰው መኖርን ያልማሉ።በየዓመቱ ሀገራቸውን ጥለው የሚሰደዱት ከ40ሺ በላይ ስደተኞች በሀገራቸው ሰርተው መኖርን ይናፍቃሉ።

እነዚህ ሁሉ ቁልል ችግሮች መፍትሄ ይሻሉ።ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ለማውጣት በፖለቲካ፣ በፍትሕና በዴሞክራሲ  መስኮች ወደፊት መራመድ ይጠበቅባታል።ለህዝብ እናስባለን የሚሉ ልሂቃንና አክቲቪስቶች እራሳቸው ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋባ አጀንዳ ከመወርወር ተቆጥበው ሰላም ሰላሙን ሊያስቡ ይገባል።

በኢትዮጵያ የተፈጠረውን አዲስ ለውጥ ተከትሎ የተከሰቱት አደናቃፊና አዋኪ ተግባራት የ2011 ዓ.ም ትዝታ ከመሆን አልፈው ወደ 2012 ዓ.ም እንዲሸጋገሩ ልንፈቅድላቸው አይገባም። ሰላም የሚረጋገጠው በምልዓተ ህዝቡ ተሳትፎ ቢሆንም መንግስትም የማይተካ ሚና አለው። ግጭቶች ስር ከመስደዳቸው በፊት ቀድሞ የመቆጣጠር፤ አዝማሚያዎችን በመመልከት ጥፋት ሳያስከትሉ የማረምና የተሳሳቱትን በግልጽ በመገሰፅና አለፍ ሲልም በመቅጣት ሰላምን ማስጠበቅ ዋነኛ ስራው ሊሆን ይገባል።

ከልዩነቶቻችን ይልቅ የጋራ የሆኑ ጉዳዮቻችን በርካታ ናቸው።ችግሩንም ደስታውንም በጋራ አልፈን ዛሬ ላይ ደርሰናል።በጋራ ሆነን ከራሳችን አልፈን የሌሎችንም ሰላም ለማስጠበቅ በተለያዩ ሀገራት ዘምተናል፤ መስዋዕትም ሆነናል።በኮርያ፤ በኮንጎ፤ በርዋንዳ፤ በላይቤሪያ፤ በሶማሊያ፤ በደቡብ ሱዳን የሰላም ዘብ ሆነን ደምቀን ታይተናል።ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ኖረናል።ስለዚህም ዛሬ የሰላም ቀንን ስናስብ አብረው ያኖሩንን በጎ በጎ ታሪኮቻችንን በማሰብ ሊሆን ይገባል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011