የ ››ላስብበት›› መፅሀፍ ሀሳቦች

42

የመድረክ አጋፋሪዋ ‹‹ዛሬ የተሰባሰብነው ህይወት በአዲስ ትውልድ ላይ ያሳረፈው ማህተም ይፋ ለማድረግ ነው›› ስትል ‹‹ላስብበት›› የተሰኘውን መፅሃፍ ተመርቆ አንባቢያን እጅ የሚደርስበት ይፋዊ እለት መሆኑን አበሰረች። ይህ መፅሀፍ በማህተብነት የመመሰሉ ጉዳይ የትውልዱን ኑረት የሚያሳይ በመሆኑ ነበር። የመፅሃፉ ደራሲ የሆነችውን ሴት በቅርብ ለሚያውቋት እና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በጉልህ ስትሳተፍ ለተመለከቷት፤ ለንባብ ያበቃችው ማህበራዊ አሻራ በፍጥነት በእጃቸው አስገብተው ከሃሳቦቿ በረከቶች ለመቋደስ ጉጉት እንዳሳደረባቸው ያሳብቅባቸው ነበር። ይህ የሆነው ከ15 ቀን በፊት በስካይ ላይት ኢንተርናሽናል ሆቴል የምረቃ ስነስርዓት ላይ ነበር።

በእለቱ የዝግጅት ክፍላችን በስፍራው ተገኝቶ የመፅሃፉ ይፋዊ ምረቃን ለአንባቢዎቻችን በዜና መልክ ማድረሱ ይታወሳል። በዛሬው የኪነ ጥበብ መፅሃፍ ዳሰሳ አምዳችን ደግሞ በሰላ ሂሳቸው እና ሙያዊ ምክረ ሃሳባቸው የሚታወቁ ባለሙያዎች ስለ ‹‹ላስብበት›› ምን ምልከታ ሰነዘሩ የሚለውን ጉዳይ ይዘንላችሁ ቀርበናል። ከዚያ በፊት ግን ለመነሻ ያህል እንዲሆነን ከመፅሀፉ የተቀነጨበ ኮርኳሪ ሃሳብ እናቀብላችሁ።

የመፅጽሃፏ ደራሲ ልጅ እናቷ በእቃዎች ላይ የሚፃፉ መመሪያዎችን ለምን አንብበን አንጠቀምም የሚል ጥያቄ ባነሳችላት ወቅት የተፈጠረውን አጋጣሚ እንዲህ በማለት ትተርከዋለች። ‹‹እኔ ባደኩበት አገር እቃዎች እና የምግብ ማሸጊያ እቃዎች ላይ የሚፃፍ የአጠቃቀም መመሪያዎች ማንበብ የተለመደ አይደለም። ማንም ከቁም ነገር አይቆጥራቸውም። አዲስ ነገር ከመጣ አጠገብ ያለ ሰው አሊያም ጎረቤት ተጠይቆ ነው የሚሰራው። በአንድ ወቅት አንድ አዛውንት ዘመዳችን መድሃኒት ታዞላቸው በመድሀኒቱ ላይ የተፃፈው ማስጠንቀቂያ በእንግሊዘኛ ስለነበር እኔን አስጠርተው አንብቤ እንድተረጉምላቸው ሲጠይቁኝ አስታውሳለሁ››

‹‹መድሀኒቱ በቀን አንድ ጊዜ ማታ ማታ የሚቀባ ነበር። ማታ ይቀቡት ጠዋት ሞቅ ባለ ውሀ ይታጠቡት፣ ልጆች በሚደርሱበት ቦታ እንዳይቀመጥ፣ ልጆችም እንዳይቀቡት” ይላል የሚለውን መልዕክት ተርጉሜ ለአዛውንቱ አስረዳኋቸሁ። እሳቸውም “በይ ተይው ልጆቼ የማይቀቡትን መድሀኒት ነው እንዴ ለኔ የሚያዙልኝ የኔ ቆዳ እኮ ከህፃን የለሰለሰ ነው በይ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ወስደሽ ጣይው” አሉኝ። እኔም ትዕዛዙን ተቀብዬ የተባልኩትን ፈፀምኩ እያለች ትቀጥላለች። በተለይ ልጆች የሚያነሷቸው ድንገተኛ ጥያቄዎች ምን ያህል ተገቢ እንደሆኑ በመገንዘብ ማህበረሰባችን ጥያቄ አለመጠየቁ ምን ያህል እንደሚጎዳው ለማስገንዘብ ትሞክራለች። ‹‹መልሱ የሚከብደን ለዛ ይሆን›› ስትልም ለራሷ ጥያቄውን መልሳ ትጠይቃለች።

ላስብበት የተሰኘው የበርካታ ሃሳቦች ውቅር መፅሃፍ በይፋ ለአንባቢዎች ተመርቆ በወጣ እለት ሶስት የስነ ፅሁፍ፣ የስነ ልቦና እና የማህበራዊ ሳይንስ ሙያተኞች በየራሳቸው ምልከታ በየምእራፎቹ የተቀመጡ ሀሳቦች ላይ ዳሰሳዊ ትንታኔ ማቅረብ ችለው ነበር። የዚህን መፅሃፍ ይዘት በሙያዊ እይታ አጮልቀው የተመለከቱት የስነ ልቦና ባለሙያው እና ‹‹የስነ ልቦና ውቅር›› ማይንድ ሴት የማነቃቂያ መድረክ አዘጋጅ ዶክተር ምህረት ደበበ፣ የደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ደራሲና ጋዜጠኛ አበረ አዳሙ እና አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ ነበሩ።

‹‹መፅሃፉ ክብሪት ነው››

መፅሃፉ ክብሪት ነው በሚል አስገራሚ ሃረግ የጀመሩት እና የወፍ በረር ዳሰሳ ያደረጉት የስነ ልቦና ባለሙያው ዶክተር ምህረት ደበበ ነበሩ። ይህን ያሉበትን ምክንያት ሲያስቀምጡ ‹‹ጫካ ላለው ሰው ብዙ ደን የሚያቃጥል ምንም ለሌለው ደግሞ ነዶ በዚያው የሚጠፋ›› በማለት የአንበሳውን ድርሻ ይሰጡታል። ይህ ብቻም ሳይሆን በጥቂት ቃላቶች እና ውቅር ሀሳቦች በርካታ ጉዳዮችን የሚዳስስ እና ማህበረሰቡም እነዚህን ሀሳቦች የራሱ እንዲያደርጋቸው እንደ ክብሪት መጫሪያ ጉዳይ መሆኑን በምልከታቸው ላይ ያስቀምጡታል።

‹‹ፍሬ አለም ይህን መፅሃፍ ስትከትብ አነስ አድርጋ የፃፈችው የሃሳብ መጫሪያ ኮርኳሪ ለማድረግ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ›› የሚሉት ዶክተር ምህረት ስለሰራችው የሃሳብ ክብሪት ምስጋና ይገባታል ሲሉ የድጋፍ ሂሳቸውን ይሰጣሉ። ሌላው ከመፀሃፉ ውስጥ በሁለተኝነት ያተኮሩት ላስብበት የሚለው የጥቅል ፅሁፉ ርዕስ ላይ ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ምልከታ ሲያስቀምጡ ‹‹ሃሳብ ሲያነክስ ሰበብ ይሆናል ›› በማለት ማሰብ ከሰበበኝነት መውጣትን የሚያመለክት በመሆኑ እና በመፅሃፉ ውስጥ ያሉት ጥቅል ሃሳቦችን መሸከም የሚችል ሳቢ አርዕስት እንደሆነ ይናገራሉ።

ዶክተር ምህረት ሌላኛው የመፅሃፉን በጎ ጎን ሲያነሱ የጠቀሱት በውስጡ የተካተቱት ፅሁፎች በጠቅላላ በጥያቄ ጀምረው በጥያቄ ማለቃቸውን ነው። በተለይ ደራሲዋ መልስ የመስጠት እና የማብራራት ስራ ሳይሆን የሰው ልጆችን እውነቶች በጥያቄዎች ውስጥ ለመጫር ነው የሚሞክሩት ሲሉ ያነሱታል። እንደ ዶክተሩ ምልከታ አብዛኛው ማህበረሰብ መልስ የማግኘቱ ችግር ሳይሆን የሚያንገላታው የተንሻፈፉ እና የጎደሉ ጥያቄዎች ብዛት ነው በማለት ፍልስፍናዊ ይዘቱን ለማብራራት ይሞክራሉ። እንደ እርሳቸው ምልከታም ይህ መፅሃፍ የተስተካከለ ጥያቄን እንዴት ማንሳት እንደምንችል መንገድ አመላካች መሆኑን ያነሳሉ።

‹‹ጥያቄ ማለት መልሱ ሲመጣ በአእምሯችን ውስጥ የምንከፍትበት መሳሪያ ነው›› ያለውን አንድ የታወቀ የስነ ልቦና ባለሙያ በመጥቀስ የጥያቄን አስፈላጊነትና ምንነት ለማብራራት ሞክረው የደራሲ ፍሬ አለም ሺባባው ስራም ይህንኑ ጎን ለማህበረሰባችን ለማሳየት ጥረት የሚያደርግ መፅሃፍ መሆኑን ይናገራሉ። የማይጠይቁ ሰዎችም ዝግ ጭንቅላት ያላቸው መሆኑን ጠንከር አድርገው ያስቀምጣሉ። ከዚህ መነሻ መፅሃፉን የሚመለከት ሁሉ የሃሳቡን አስፈላጊነት ተረድቶ የተስተካከለ ጥያቄ እንዲጠይቅ እና የመፍትሄው ምላሽ ቁልፍን እንዲያገኝ ይረዳል በማለት ያነሳሉ።

በሌላው ጎን ደግሞ በላስብበት መፅሀፍ ውስጥ በርካታ ህፃናት ቦታ ተሰጥቷቸው። ታሪኮቻቸው እና የሚያነሷቸው አስገራሚ ጥያቄዎች ተካተዋል። ዶክተር ምህረት ይህን የመፅሃፉን ክፍል እንደ መልካም ጎን ያነሱታል። ‹‹ህፃናት በአገራችን ውስጥ በቁጥር ብዙ ሆነው ሳለ እንደ አናሳ ይታያሉ›› በማለት ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ትኩረት አለመስጠትን ጨምሮ በበርካታ ነገሮች መገለል እንደሚደርስባቸው ይገልፃሉ። ላስብበት መፅሃፍም የነዚህን ህፃናት ድምፅ እንዲሰማ በጠንካራ ብዕር የሚሞግት ስል ሃሳቦችን የሚያነሳ መሆኑ ሊደነቅ ይገባዋል የሚል እሳቤን ያንፀባርቃሉ።

ከራስ ታሪክ የተመዘዙ ሰበዞች

በእለቱ የመፅሃፉ ይፋዊ ምርቃት ላይ ተገኝተው የግል ሃሳባቸውን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ደራሲና ጋዜጠኛ አበረ አዳሙ ነበሩ። እርሳቸው ይህን መፅሀፍ ከስነ ፅሁፋዊ ይዘቱ እና ሃሳቡ ጋር በማዛመድ የግል ምልከታቸውን እና አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር። በተለይ የመፅሀፉ ደራሲ ከራስ ታሪክ የተመዘዙ ሰበዞች ስብስብን በመፅሀፍ ማቅረብ መቻላቸው በህይወት መንገድ ላይ ሌሎች ተሞክሮ እንዲወስዱ ስለሚያስችል ተገቢነቱ ከፍተኛ ነው በማለት አሞካሽተዋቸዋል።

ደራሲ አበረ የቅርፅ ይዘቱን ሲገመግሙ ባስቀመጡት ሀሳብ በመጀመሪያ ያነሱት የሽፋን ገፁን ነበር። በዚህም የኢትዮጵያውያንን የአሳሳል ጥበብን መነሻ በማድረግ የገፅ ሽፋኑን ትርጉም ለመስጠት መሞከሩ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል። በተለይ ፀሃፊዋ ከወጣችበት አካባቢ ጎጃም የሚዘወተሩ የሴት ልጅ አፍሮዎችን የያዘ ምስል መሆኑ ልዩ ውበትን የደረበ እንደሆነ ነበር በምልከታቸው ላይ ያስቀመጡት። ከዚህ መነሻ የመፅሃፍ ሽፋኑ ኢትዮጵያዊነትን አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን አንስተዋል። የገፅ ቅንብሩ በጥሩ መልኩ መቀናጀቱንም አንስተዋል።

የመፅሀፉ ይዘት

እንደ ደራሲ አበረ አዳሙ ምልከታ መፅሀፉ ‹‹ሜሞ›› ወይም ከራስ የትውስታ ሰበዝ የተመዘዘ መሆኑን ጠቅሰው ዘውጉ ከግለ ታሪክ የአፃፃፍ ስልት ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ያነሳሉ። ሆኖም ግን የራሱ የሆነ ስልት እንዳለው ያስቀምጣሉ። በአንደኛ መደብ የተፃፈው ላስብበት በተለይ ጥቃቅን ከሚመስሉ የትውስታ ሀሳቦች ውስጥ ጥልቅ ጥያቄን የሚያጭሩ በርካታ ቁምነገሮች የሚዳሰሱበት እንደሆነ ይነግሩናል። የአፃፃፍ ስልቱ ሜሞ ዘውግ እንዲሆን ማስቻሉን ያስረዱናል። ከዚህ አኳያ ደራሲዋ የተሳካ መፅሃፍ ለአንባቢያን ማድረሳቸውን ነው የሚመሰክሩት።

ማጠቃለያ

በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ውስጥ እውቅ ከሆኑት ሙዚቀኞች መካከል በቀዳሚነት የምትጠቀሰው እጅጋየሁ ሺባባው ‹‹ጂጂ›› ታላቅ እህት የሆነችው ፍሬ አለም ሺባባው ለአንባቢያን እንዲደርስ የፃፈችው መፅሃፍ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል። ደራሲዋ መፅሃፉን እንካችሁ ከማለቷ ቀደም ብሎ ለበርካታ ዓመታት ህፃናት እና ታዳጊዎችን በተመቻቸ መንገድ እንዲያድጉና መልካም ትውልድ እንዲፈራ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ትታወቃለች። በተለይ በተገቢው መንገድ ምግብ ማግኘት የሚችሉ ህፃናትን በትምህርት ቤት ውስጥ እንዲመገቡ የሚያስችለውን የሰቆጣ ቃልኪዳን በመንደፍ መንግስት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የበኩላቸውን እንዲያግዙ የጀመረችው ፕሮጀክት ስኬታማ ከሚባሉት ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።

ከዚህ ባሻገር ፍሬአለም በባህርዳር ከተማ ትምህርት ቤት በመክፈት በርካታ ህፃናትን በማስተማር ላይ ትገኛለች። የ2011 ዓ.ም መጠናቀቂያ ላይ ደግሞ በርካታ ጠቃሚ ሃሳቦችን የያዘ ‹‹ላስብበት›› የተሰኘ መፅሃፍ ለአንባቢዎች አድርሳለች። የዝግጅት ክፍላችንም በዘርፉ አሉ በሚባሉ ፀሃፍት እና ባለሙያዎች አድናቆትን ያተረፈውን የስነ ፅሁፍ ውጤት እንድትጋበዙልን በዚህ መንገድ ዳሰሳውን አቅርቦላችኋል። ሰላም!

አዲስ ዘመን ጳጉሜ 3/2011

ዳግም ከበደ