ሜዳ ሳር ብቻ ሳይሆን ሰው ያበቅላል

11

ከሳምንት በፊት ነው። ከጓደኛዬ ጋር ከስራ በኋላ በእግራችን እየተጓዝን ነበር። የእግር ጉዞ ለጤናም ለጨዋታም ይጠቅማል አይደል የሚባለው። በአጋጣሚ ለብዙ ጊዜ እየተመለከትኩት ያላስተዋልኩትን አንድ የእግር ኳስ ሜዳ ጋር ስደርስ ድንገት ቀልቤን የሳበው ነገር አጋጠመኝ እና ቆም አልኩ። ቢያንስ ከ30 የሚበልጡ ሰዎች ሙሉ የእግር ኳስ ትጥቅ ለብሰው ልምምድ ያደርጋሉ። ታዲያ ይሄ ምን ይገርማል? ትሉ ይሆናል። እኔን የገረመኝ ሰዎቹ ያላቸው ተክለ ሰውነት አንድ እግር ኳስ ተጫዋች ሊኖረው የሚገባ አቋም ባለመሆኑ ነበር። ቢሆንስ ታዲያ ለጤናቸው እየሰሩ ነዋ! ትሉ ይሆናል። እውነት ነው ለጤናቸው ነው የሚሰሩት። ግን ስነምግባራቸው እና ያላቸው ሞራል ከማስገረምም አልፎ ቀልብን ይስብ ነበር።

ልምምዳቸውን ከመመልከት ባለፈ የቡድን መሪያቸውን ጠጋ ብዬ አናገርኩት። የእግር ኳስ ጤና ማህበር እንደሆነ አጫወተኝ። ሜዳው ቀበና አካባቢ የሚገኘው «የቤሌር እግር ኳስ ሜዳ ነው» ። «ይህ ስፍራ አንተ ከምታስበው በላይ ታዋቂና አንጋፋ እግር ኳስ ተጫዋቾችን አፍርቷል። ነገር ግን ለበርካታ ጊዜያት ተረስቶ የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ነበር። ታዳጊዎችም ማዘውተሪያ ስፍራ አልነበራቸውም» ብሎኝ ላለፉት አራት ዓመታት ሜዳው የነበረውን የቀድሞ ስም ለመመለስ፣ ማህበራቸውም ጤናን መሰረት አድርጎ ስፖርትን ከማበረታታት ባለፈ ለታዳጊ ወጣቶች ተስፋ የሚፈነጥቁ ስራዎች ለመስራት እየለፋ መሆኑን ነገረኝ። በሰፊው ለመጨዋወት ተቀጣጥረን በሳምንቱ ተገናኘን።

ዳዊት ግርማ ይባላል። በቀበና 15 ሜዳና አካባቢ እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ነዋሪ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ በአካባቢው «ቤሌር» እየተባለ በሚታወቀው ሜዳ ከጓደኞቹ ጋር ኳስን እያንከባለለ ነው ያደገው። በግል ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ጎልማሳ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እግር ኳስን በተለየ ሁኔታ ይወዳል። በአሁኑ ወቅት ከአብሮ አደጎቹ ጋር በጋራ በመሆን «የአስራ አምስት ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበር» መስርተዋል። እርሱም የማህበሩ ሰብሳቢ በመሆን ያገለግላል።

«የእግር ኳስ ማህበሩ ከተመሰረተ አራት ዓመታትን አስቆጠሯል» በማለት በዋናነት ምስረታው በርካታ አላማዎችን አንግቦ እንደሆነ የሚናገረው ዳዊት፤ የቤሌር ሜዳ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ያበረከተው አስተዋጽዖ ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራል። ሆኖም ለብዙ ዓመታት «የቆሻሻ መጣያ እና መፀዳጃ» ሆኖ የአካባቢውን ሰው ለጤና ችግር ሲያጋልጠው ቆይቷል። የአካባቢው አብሮ አደጎችም ይህንን በመገንዘብ የቀድሞውን ዝና ለመመለስ፣ ህብረተሰቡንም ለጤና ችግር የሚያጋልጡ ቆሻሻዎችን ለማስወገድ እና ሌሎች በጎ አላማዎችን ለመስራት በአንድ ጥላ ስር ተሰባስበዋል። በሳምንት ሶስት ጊዜ ልምምድ እንዲሁም በየጊዜው የተለያዩ ውድድሮችን በማድረግ ጤናቸውን ይጠብቃሉ።

«አሁን በራሳችን ጥረት እና በአንዳንድ በጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶች የሜዳውን ፅዳት መጠበቅ እና ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ለማድረግ ጥረት አድርገናል» የሚለው የማህበሩ ሰብሳቢ አሁንም ድረስ በስፍራው ላይ መሰራት ያለባቸው ቀሪ ተግባራት መኖራቸውን ይናገራል።

የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር የሚመራቸው በከተማዋ የሚገኙ ከ30 በላይ ማህበራት አሉ። ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ጤናን መጠበቅ እና ማህበራዊ ግንኙነትን ማጠናከርን ታሳቢ አድርገው የተመሰረቱ ናቸው። የአስራ አምስት ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበርም ከነዚህ መካከል የሚመደብ ነው። ከሌሎች ማህበራት ልዩ የሚያደርገው ግን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ተጫዋቾችን ማፍራት የቻለው «የቤሌር ሜዳ» ቀድሞ የነበረውን ስም እና ዝና በመመለስ አሁንም ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች እንዲያፈራ ለማስቻል በሚያደርገው ብርቱ ጥረት ነው።

የማህበሩ አባላት ከልጅነታቸው ጀምሮ በዚህ ሜዳ ላይ እየተፎካከሩ አንዳንዴም እየተጣሉ በአንዳንድ ምክንያት ሲለያዩ ደግሞ እየተነፋፈቁ ለረጅም ዓመታት አሳልፈዋል። ከሁሉም ከሁሉም ይህን ማህበር በቁርጠኝነት መስርተው የሜዳውን የቀድሞ ዝና ከዚያም አልፎ የአብሮ አደግነታቸውን ፍቅር ለመመለስ ያነሳሳቸው የአንድ ጓደኛቸው ሞት ነበር። የዚህ ሰው ሞት ከምንም ነገር በላይ ያስቆጫቸው ደግሞ በህክምና መዳን በሚችል ህመም ደጋፊ በማጣቱ ብቻ በመሞቱ ነበር። ክስተቱ የእነርሱ አለመሰባሰብ በአንድነት አለመረዳዳት ምን ያክል ጉዳት እንዳለው በይበልጥ አስረድቷቸዋል።

አባላቱ «እግር ኳስ» ሁላችንንም በአንድነት የማሰባሰብ እና እንድንደጋገፍ የማድረግ ሀይል አለው የሚል እሳቤ አላቸው። ተዳፍኖ የቆየውን የቤሌር ሜዳ በድጋሚ እንዲያንሰራራ ከማድረግ እና ተስፋ ያላቸው እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለአገሪቷ ከማበርከትም በላይ በአካባቢው የተቸገሩ ነዋሪዎችን መርዳት እንድንችል ስፖርቱ ትልቅ ሀይል ይሆነናል ይላሉ።

አራት ዓመታትን ያስቆጠረው የጤና ስፖርት ማህበራቸው ሲጀመር ትንሽ ሆኖ ጊዜያት በረዘሙ ቁጥር ደግሞ አቅሙን እያጠናከረ የአባላት ቁጥሩን እየጨመረ መጥቷል። አሁን ከ90 በላይ አባላቶችን ይዞ ይንቀሳቀሳል። ለረጅም ዘመናት የአካባቢው ተወላጆችን ጨምሮ በሜዳው ፍቅር ተይዘው ኳስን ለማንከባለል ከአጎራባች ሰፈሮች የሚመጡ ልጆችን ያለ ልዩነት ሲቀበል የነበረውን ሜዳ ባላቸው አቅም ለማስተካከል ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

የማህበሩ ሰብሳቢ ዳዊት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረገው ቆይታ( እጁን ወደ ሜዳው እየጠቆመ) «ይህቺ ሜዳ ለብዙ ሰዎች ባለውለታ ነች» በማለት የቤሌር ሜዳን ታሪካዊ ባለውለታነት ይናገራል። በንግግሩ ለመረዳት የሞከረ ሰው «ታዲያ ውለታ ለሰራችልን ሜዳ ብንሰባሰብላት እና የቀድሞውን ስም እና ዝና ለመመለስ ብንሞክር ምን ይገርማል፤ ሜዳዋ እኮ ሳር ብቻ ሳይሆን ሰውም አብቅላለች» የሚል ድምፀት የተደበቀ ይመስላል። ለመሆኑ ይህቺ ሜዳ እነማንን አፍርታ ይሆን? መልሱ ዳዊት እና ጓደኞቹ ጋር አለ።

አሰልጣኝ ንጉሴ ገብሬ

አስረኛው የአፍሪካ ዋንጫና በ1974 በሊቢያ በተዘጋጀው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ያስቻሉ ተጠቃሽ ተጫዋቾችን አገራችን አፍርታለች። ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ውለታ ከሰሩት ተጫዋቾች መካከልም መንግስቱ ወርቁ፣ ይድነቃቸው ተሰማ ߹ ንጉሴ ገብሬ በቀዳሚነት የሚጠሩ ናቸው። በእነዚህ ሁለት የመጨረሻዎቹ የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው ውስጥ አንዱ የሆነው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋችና በአሁን ሰዓት በፕሮጀክት አሰልጣኝነት እየሠራ የሚገኘው ንጉሴ ገብሬ በታሪካዊቷ «የቤሌር ሜዳ ላይ ኳስን ካንከባለሉት» ውስጥ የሚጠቀስ ነው።

በ1948 ዓ.ም የተወለደው ንጉሴ ገብሬ በአዲስ አበባ ቀበና አካባቢ ተወልዶ አድጓል። ለንጉሴ ስኬት የቤሌር ሜዳ ትልቅ ትርጉም ነበራት። እርሱም «በልጅነቴ እንደ ማንኛውም ታዳጊ ሰፈር ውስጥ እግር ኳስ እጫወት ነበር፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታዬም ኳስ ተጫውቻለሁ» በማለት ይናገራል። ታዲያ የልጅነት የእግር ኳስ ጨዋታው የሚጀምረው በዚችሁ ሜዳ ላይ ነበር። ንጉሴ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ከ1967 እስከ 1983 ዓ.ም ለ16 ዓመታት ያህል ተጫውቷል።

ባዩ ሙሉ

ሌላኛው በቤሌር ሜዳ ተጫወተው ለሰኬት ከበቁ ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋቾች ውስጥ ባዩ ሙሉ ተጠቃሽ ነው። በኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪ ልብ ውስጥ ያለው ባዩ «የቤሌር ሜዳ» እድል ቀንቶት በታዋቂው የቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ለመጫወት በር ተከፍቶለታል። ባዩ የመጀመሪያውን የምሥራቅ አፍሪካ የታዳጊዎች ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ይዘው ከመጡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሲሆን የእርሱ ድርሻ ጉልህም ነበር። ከዚህም ሌላ ኬንያ ባዘጋጀችው «የሴካፋ ሻምፒዮና» ላይ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ለመመረጥም በቅቷል። የምሥራቅ አፍሪካ ውድድር ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ውጪ በሩዋንዳ ዋንጫ ስታነሳ በፍፃሜው ጨዋታ ላይ የማሸነፊያዎቹን ሁለት ግቦች አስቆጥሯል። ባዩ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ዓመት በዋናው ክለብ ተሰልፎ ተጫውቷል። የእግር ኳስ ህይወቱ ከማብቃቱም በፊት በቤልጂየም አገር ለረጅም ጊዜ ተጫውቷል። የቀበናዋ ቤሌር ሜዳም ካበቀለቻቸው የአገር ባለውለታዎች ተርታ አሰልፋዋለች።

የቀድሞው ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እና በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአሁኑ ሰዓት ተሳትፎ የሚያደርገውን መቀሌ ከተማ በማሰልጠን ላይ የሚገኘው ዮሐንስ ሳህሌ በዚህች ታሪካዊ ሜዳ ላይ እግራቸውን አሟሽተዋል። ጌቱ ተሾመ «ድክሬ»፣ ጳውሎስ ማንጎ የመሳሰሉት በትንሿ ሜዳ ላይ ኳስን ሲያንሸራሽሩ ነበር። የወደፊት እንጀራቸውንም የወሰነችው ይህችው ሜዳ ነበረች። በቅርብ ጊዜም ይህቺ ታሪካዊ ሜዳ እንደ ቀድሞው ባይሆን እንኳን ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የሚጫወተውን ናትናኤል ዘለቀን አፍርታለች።

የቀድሞውን ታሪክ ለማስቀጠል

የአስራ አምስት ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበር የአካባቢያቸውን የቀድሞውን ስም ለማስቀጠል፤ ለአገሪቷ እግር ኳስ እድገት ጉልህ ሚና የሚኖራቸው ታዳጊዎችን ለማፍራት ቆርጠን ተነስተናል ይላሉ። ሜዳውን ደረጃውን በጠበቀ መንገድ አዘጋጅተው ከዚህ በኋላ ለሚተኩ ህፃናቶች ለማበርከት ፍላጎት አላቸው። የአካባቢያቸው ወረዳ ስፖርት ፅህፈት ቤትም በጉዳዩ ላይ ፈቃደኛ ሆኖ ሜዳውን እንዲጠቀሙበት አድርጓል። ነገር ግን የአራዳ ክፍለ ከተማ ትብብር አነስተኛ እንደሆነ ነው የማህበሩ አባላት የሚናገሩት። አንዴ «በስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች ሊሰራ ነው» ሌላ ጊዜ ደግሞ «መንግስት ራሱ በጀት ይዞ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ሊገነባው ነው» የሚሉ ምክንያቶች ማህበሩ አቅዶ ሊያከናውነው ያሰበውን ሰፊ ስራ እንዳያከናውን እንቅፋት እንደሆነባቸው ይናገራሉ።

አቶ ሽመልስ ተስፋዬ በቀበና መድኃኒአለም አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው። እግር ኳስን እንደ ሙያ አድርጎ ባይዘውም ለረጅም ጊዜያት ተጫውቷል። ኳስን ያስተዋወቀው ይህ ሜዳ ነው። ከጊዜያት በኋላ ግን ሜዳው የቆሻሻ መጣያ መሆን ጀመረ። በሀላፊነት የሚያስተዳድረው አካል ባለመኖሩም ለዓመታት በዚያ ስፍራ ኳስን ማንከባለል ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ ይዞት የሚመጣው የጤና መዘዝ ከባድ ሆነ። እሁድ እሁድ ጤናውን ለመጠበቅ እግር ኳስን የሚያዘወትረው አቶ ሽመልስም ከአካባቢው ርቆ በካዛንቺስ «መብርቅ» በሚባል የጤና ቡድኑ ውስጥ ተካቶ መጫወት ጀመረ። ሆኖም ግን ሁሌም አንድ የሚቆጨው ነገር ነበር። እርሱ በሚኖርበት ሰፈር ለብዙሀን የእግር ኳስ ህይወት በር የከፈተው ሜዳ እያለ ካዛንቺስ ድረስ እየሄደ መጫወቱ ያሳዝነው ነበር።

ሽመልስ ላይ ቁጭት የተፈጠረበት በሜዳው ላይ አለመጫወቱ ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ያሉት ወጣቶች የቀድሞዎቹን አንጋፋ ተጫዋቾች ፈለግ ተከትለው ውጤታማ የእግር ኳስ ህይወት እንዳይመሩ እና ለአገሪቷ የኳስ እድገት አበርክቶ እንዳይኖራቸው እንቅፋት ስለሆነ ብቻ ነው።

ለአንድ ዓመት ያክል በካዛንችስ የመብረቅ የጤና እግር ኳስ ቡድን ውስጥ የተጫወተው ሽመልስ በተፈጠረበት ቁጭት ምክንያት ከቡድኑ መልቀቂያውን ወስዶ በአካባቢው ተመሳሳይ ቡድን ለመመስረት አሰበ። ከአብሮ አደጎቹ ጋር ተመካክሮም አሁን ያለውን ማህበር እውን አደረጉት። ከምንም ነገር በላይ ለእነ ሽመልስ እግር ኳስ እየተጫወቱ የራሳቸውን ጤና መጠበቅ ብቻ ሳይሆን አላማቸው ቀድሞ «የቤሌር ሜዳ» ወጣት ተጫዋቾችን በማፍራት የሚታወቅበትን ስም በድጋሚ መመለስም ጭምር መሆኑን ይናገራል።

«የዚህ ሜዳ በአካባቢያችን መኖር ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው» የሚለው ሽመልስ በዋናነት ሜዳው ለጤና ማህበሩ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ይልቅ ታዳጊዎች በማፍራት እና በአገሪቷ እግር ኳስ ላይ ለውጥ ማምጣት ይችላል በማለት ይናገራል። በመሆኑን ማዘውተሪያ ስፍራውን ሁሉም የአካባቢው ህብረተሰብ እና መንግስት ትኩረት ሰጥቶት ሊጠብቀው ይገባል የሚል መልእክት አለው።

ሚኪያስ አምባቸው ሌላኛው የስፖርት ማህበሩ አባል እና ምክትል ሊቀመንበር ነው። በቤሌር ሜዳ ላይ ከልጅነቱ ጀምሮ ከአብሮ አደጎቹ ጋር ይጫወት ነበር። እርሱ እግር ኳስ ከጨዋታም በላይ ነው ይላል። በአካባቢው ላይ የሚኖሩት ወጣቶች ብሎም ጎልማሳዎችን በአንድ ጥላ ስር በማሰባሰብ ማህበራዊ ህይወታቸው እንዲጠናከር የሚጫወተው ሚና ይህነው ተብሎ የሚገለፅ አይደለም ።

«ማህበሩ ከተመሰረተ አንስቶ ባለን አቅም የተቸገረን እና የታመመን እንጠይቃለን» የሚለው ሚኪያስ ይህን ማድረግ የቻልነው ይህ ታሪካዊ ሜዳ እስካሁንም ድረስ በዚህ ስፍራ በመኖሩ ነው ይላል። ታዋቂ ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ከማበርከት ባለፈ ሜዳው ማህበራዊ ህይወትን በማጠናከር ያለው ፋይዳ ሊታወቅ ይገባል የሚል መልእክት አለው። በዚህ የተነሳ ማዘውተሪያ ስፍራውን የመጠበቅ እና ወደ ተሻለ ደረጃ የማሳደግ ሀላፊነቱ የሁሉም መሆን አለበት።

የአስራ አምስት ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበር በየወሩ አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች እንዲውል መዋጮ ያደርጋሉ። ድጋፍ አድራጊ አካላትን በማስተባበር ሜዳውን ለማሻሻል ይጥራሉ። በሳምንት ሶስት ቀን የልምምድ መርሀ ግብር ሲኖራቸው እሁድ እሁድ ደግሞ ከሌሎች ቡድኖች ጋር የአቋም መለኪያ ውድድር ያደርጋሉ። በቤሌር ሜዳ የማህበሩ አባላት ብቻ አይደለም ጨዋታ የሚያደርጉት። በፕሮጀክት ታቅፈው የሚሰሩ ታዳጊ ህፃናትም አሉ። ትርፍ ጊዜያቸውን ኳስ በመጫወት ማሳለፍ የሚፈልጉ የአካባቢው ነዋሪዎችም በዚሁ ሜዳ ላይ እንደየፈርጃቸው ይሳተፋሉ። ጨዋታውን ማየት የሚፈልጉ ሰዎችም በሜዳዋ ዙሪያ መመልከት አሁን አሁን እየተለመደ ነው። ለዘመናት ሳትሰስት እራሷን የሰጠችው ሜዳም ጥቁር ከነጭ፣ ትንሽ ከትልቅ ሳትል ሁሉንም ተቀብላ ታስተናግዳለች። እርሷ የባረከችው ደግሞ እንደ ንጉሴ ገብሬ እና ሌሎች አንጋፋ ተጫዋቾች ተባርኮ የህይወት መስመሩን ይዟል።

አሰልጣኙ ምን ይላል

ኤሊያስ ኢብራሂም ይባላል። በደደቢት እግር ኳስ ቡድን ውስጥ ምክትል አሰልጣኝ ነው። የአስራ አምስት ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበር በበጎ ፍቃድ ያሰለጥናል። ለሶስት ዓመታት ያህል በቤሌር ሜዳ ቡድኑን ሲያሰለጥን ቆይቷል። በእድሜ ከእነርሱ ትንሹ ቢሆንም ባለው የማሰልጠን ክህሎት ሁሉም አባላቱን አስፈላጊውን ሳይንሳዊ የእግር ኳስ መርህ ያሰራቸዋል። እነርሱም ቢሆኑ በመልካም ስነ ምግባር ከኤሊያስ ጋር ልምምዳቸውን ያደርጋሉ።

እንደ አሰልጣኙ አመለካከት «አካባቢው ላይ ተዳክሞ የነበረውን እግር ኳስ ለማንሳት» የዚህ ማህበር መመስረት ትልቅ ፋይዳ ነበረው። ጎልማሶች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በዚህ ሜዳ ላይ ማድረጋቸው በቀዳሚነት የራሳቸውን ጤና እንዲጠብቁ እረድቷቸዋል የሚል አመለካከትም አለው። ከዚህ አንፃር ማህበራቸው ግቡን እያሳካ ነው። በሌላ መልኩ በመሰረታዊ ሁኔታ ታዳጊዎች ሞራል ሰንቀው በተሻለ ተስፋ እና ምቹ በሆነ ሜዳ እንዲጫወቱ ስብስቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።

ኤሊያስ ለቡድኑ አባላት በሳምንት ሶስት ጊዜ ስልጠና ይሰጣል። በኮሚቴዎቹም ላይ በመሳተፍ ያለውን ሙያ ሳይሰስት ያካፍላል። ምክንያቱም ተጫውቶ ያደገባት ሜዳ ትወቅሰዋለችና። ከዚህም ሌላ ታሪካዊው ስም ወደ ቀድሞው ስፍራ ተመልሶ አሁንም ታዋቂ እና አንጋፋ ተጫዋቾች ከአካባቢው እንዲወጡ ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ሙያዊ እገዛ ማድረጉ የውዴታ ግዴታው ይሆናል።

ኤሊያስ የእግር ኳስን ክህሎት ያዳበረው እና ፍቅሩን ያገኘው አሁን በአሰልጣኝነት ከሚመራው የጤና ቡድን አባላቶች ነው። በሰፈር ውስጥ እነሱን እየተመለከተ ነው ያደገው። ከዚያ ባለፈ ግን አሁን ስብስቡን በመልካም ስነምግባር የታነፀ እግር ኳስን ለጤናና ለማህበራዊ ሀላፊነት ለመወጣት የሚጫወት አድርጎ የማሰልጠን ሀላፊነቱን ተቀብሏል። የእግር ኳስ እና የአሰልጣኝነት ክህሎቱ ደግሞ የጤና ማህበር ቁንጮ አሰልጣኝ ሆኖ እንዲመረጥ አድርጎታል።

አሰልጣኙ ቡድኑ ከጤና አኳያ ምን አይነት ሳይንሳዊ የእግር ኳስ ልምምድ ማድረግ እንዳለበት ይወስናል። እነርሱም ይህንን ተከትለው ልምምዳቸውን ያደርጋሉ። በዚህ ረገድ አሰልጣኝ ኤሊያስ ስኬታማ እንደሆነ ይናገራል። «በሁለት ቡድን የተከፈሉት የማህበሩ አባላት እንዲያውም ክለቦች ከሚሰሩት ልምምድ በላይ ነው የሚሰሩት» በማለት ያላቸውን ተነሳሽነት ይመሰክራል። እርሱም አካላዊ ጤንነታቸው የተስተካከለ እንዲሆን ከማድረጉም ባለፈ የቡድን እና የአጋርነት መንፈስ እንዲኖራቸው እገዛ አድርጎላቸዋል።

ኤሊያስ አብዛኛውን የልጅነት ጊዜውን በቤሌር ሜዳ እግር ኳስን በመጫወት እንዳሳለፈ ይናገራል። ወደኋላ መለስ ብሎ የልጅነት ጊዜውን ሲያስታውስ የማዘውተሪያ ስፍራው ለአካባቢው ወጣቶች በቃላት የማይገለፅ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው በቅድሚያ በአዕምሮው ላይ የሚከሰትለት። ከዚያም በዘለለ «አሁን ላለሁበት ደረጃ ሜዳው የህይወቴ መሰረት ነው» በማለት እርሱ እና እግር ኳስ ሜዳው ያላቸውን ቁርኝት ይገልፃል።

ለኤሊያስ ቤሌር ከእግር ኳስ ሜዳም ባለፈ እራሱ እግር ኳስ ምን እንደሆነ ያስተዋወቀው ነው። ስለዚህ ሁሌም ለዚህ ስፍራ የተለየ ክብር አለው።

«ከመሰረታዊ የእግር ኳስ የታዳጊዎች ፕሮጀክት አንስቶ ክለብ እንድመሰረት የዚህ ታሪካዊ የማዘውተሪያ ስፍራ መኖር ጠቅሞኛል» በማለት ይገልፃል። የጤና ስፖርት ማህበሩ እና እርሱ በግል የጀመረው የታዳጊዎች ፕሮጀክት ቤሌርሜዳ እንዲሁ የቆሻሻ መጣያ ሜዳ ሆኖ እንዳይቀር ትልቅ ትግል አድርገዋል። ታሪካዊነቱን ጠብቆ እንዲቆይ ከማድረግም በዘለለ ታዳጊዎች በዚህ ስፍራ ውጤታማ ስፖርት ተጫዋች ሆነው እንዲያድጉ ይህን ማዘውተሪያ ስፍራ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደጉ ተገቢ በመሆኑም ጭምር ነው።

ኤሊያስ በእርሱ እድሜ በዚህ ስፍራ ከልጅነታቸው ጀምሮ እግር ኳስን በመጫወት ትልቅ ስፍራ ደርሰዋል∷ ለአገራቸውም ስፖርት አበርክቷቸው ሰፊ ነው∷ ያላቸውን እነ ጌቱ ተሾመ፣ ባዩ ሙሉ፣ ደብሮም ሀጎስ፣ መስፍን ደምሴ «ድክሬ» እና ቻይና አድማሱ የመሳሰሉ ሰዎች በድጋሚ በዚህኛው ትውልድ፤ በዚህች ታሪካዊ ሜዳ ላይ ማፍራት ይኖርብል ይላል። ለዚያም ነው በርካታ ታዳጊዎችን በፕሮጀክት አቅፈው በማሰልጠን ላይ የሚገኘው። ለልጆቹ መልካም ስነምግባር መቀረፅ ደግሞ «የጤና ቡድኑን» ራእይ እንዲከተሉ መንገዱን በመክፈት ላይ የሚገኘው።

ኤሊያስ «ራእይ ታዳጊዎች የእግር ኳስ ፕሮጀክትን» ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ አቋቁሞ በዚሁ ቤሌር ሜዳ ላይ እያሰለጠነ ቆይቷል። ሶስት ቡድኖችንም በተለያየ ዓመት በማሰልጠን ለተለያዩ የእግር ኳስ ክለቦች እንዲመለመሉ አስችሏል። ይህ ሜዳ ባይኖር አሁንም እነዚህን ወጣቶች ማብቃት አይቻልም ነበር የሚል አመለካከት አለው። የረጅም ዓመት እቅዶችን በማውጣትም እየሰራም ነው።

ኤሊያስ የሚመራው የታዳጊዎች ፕሮጀክት እና «የአስራ አምስት ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበር» በርካታ እንቅፋቶችን እንደሚያጋጥማቸው ያነሳሉ። ሆኖም የተነሱበትን አላማ ለማሳካት ካላቸው ፍላጎት እና ጉጉት አንፃር ለረጅም ዓመታት መፍትሄ ሲፈልጉላቸው እና ጎንበስ ብለው ሲያልፏቸው ነበር። ነገር ግን ይህን ችግር ይፈቱልናል ያሏቸው አካላት ድጋፍ ቢያደርጉላቸው መንገዳቸው ቀና ስለሚሆን ተባበሩን የሚል ጥሪ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ያስተላልፋሉ። በዚህም ታሪካዊውን ሜዳ ዘመናዊ ለማድረግ ብሎም የእግር ኳስ ማህበሩን እና ፕሮጀክቱን በገንዘብ አቅም ለመደገፍ የሚፈልጉ ባለሀብቶች እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው ይላሉ። ምክንያቱም «ሜዳው ሳር ብቻ ሳይሆን ሰውም ያበቅላልና»∷

አዲስ ዘመን ጳጉሜ 3/2011

ዳግም ከበደ