ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት እንዴት ተመጋግበው ይጓዙ?

41

ስልጣንን ለህዝብ አሳልፎ የሚሰጠው የዴሞክራሲ ስርዓት የህዝቦች ያልተገታ ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚረጋገጥበት ስለመሆኑ ይነገራል። ይሁን እንጂ ይህን መሰል ዴሞክራሲ እውን ከማድረግ አኳያ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን የሚገቱ አካሄድና አሰራሮችን ፈር የሚያሲይዝ የሕግ ማዕቀፍ ስለማስፈለጉ፤ የሕግ ማዕቀፍ መኖር ብቻም ሳይሆን የሕጉ ገዢነትና ተፈጻሚነት ኖሮ የሕግ የበላይነት መረጋገጡ የግድ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በኢትዮጵያም ዴሞክራሲ ስር እንዲሰድ እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ የሕግ የበላይነት ለነገ ሊባል የሚገባው ስራ አለመሆኑንም እነዚህ ምሑራን ያስገነዝባሉ። እኛም በዛሬው እትማችን ዛሬ የሚከበረውን አገራዊ የዴሞክራሲ ቀን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓቱ ስር ይሰድ ዘንድ መከናወን ስላለባቸው ተግባራትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ካለው አገራዊ ሁኔታ አኳያ የዘርፉን ባለሙያዎች ሀሳብና አስተያየት በሚከተለው መልኩ ይዘን ቀርበናል።

ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት

አቶ እንዳለ ንጉሴ፣ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለማቀፍ ግንኙነት መምህር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው። ዴሞክራሲ ሲባል፣ በሕዝብ የተመረጠና የህዝብ ይሁኝታ ያለው መንግስት ያለበት፤ የተሰጠውም የመንግስት ስልጣን ውስን የሆነበት፤ ወሳኙ የስልጣን ምንጭ ህዝብ የሆነበት፤ ባጠቃላይ የህዝብ አስተዳደር ያለበት አካሄድ ነው። ዋናውን ውሳኔ የሚወስነው ግለሰብ ወይም ቡድን ሳይሆን ህዝብ የሆነበትም ነው።

አንድ አገር ትልቅም ይሁን ትንሽ፣ በኢኮኖሚ ያደገም ይሁን ያላደገ፣ በዛ አገር ላይ ዴሞክራሲ አለ ለማለት እንደመመዘኛ የሚታዩ የዴሞክራሲ መርሆዎች አሉ። ከዴሞክራሲ መርሆዎች ደግሞ የመጀመሪያው የስልጣን ምንጭ ህዝብ ነው ብሎ ማመን ነው። ሁለተኛው የሕግ የበላይነት ነው። ስለዚህ የሕግ የበላይነት የዴሞክራሲ አንዱ መርህ ነው። የሕግ የበላይነት በሌለበት ዴሞክራሲ አይታሰብም። ይሄ በጠነከረ ወይም ደከም ባለ መንገድ ሊሆን ቢችልም በዴሞክራሲ ውስጥ የሕግ የበላይነት ሊኖር ይገባል።

ምክንያቱም ዴሞክራሲ ከመጀመሪያውም የእኩልነት ጉዳይ ነው። እኩል እድል የማግኘት ጉዳይም ነው። የሕግ የበላይነት ማለት ደግሞ የሚወጡ ሕጎች በሁሉም ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑበት ነው። ይህ ሲባል አንድ ሕግ የሚወጣው ለሆነ ቡድን ሲባል ሳይሆን ሁሉንም እኩል ለማገልገልና ለህዝብ ጥቅም ሲባል መሆን ይገባዋል። የህዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ፤ ከፍ ለማድረግ ነው ሕግ መውጣት ያለበት። ለሁሉም እኩል መስራትና ተፈጻሚ መሆን መቻልም አለበት።

እንደ አቶ እንዳለ ገለጻ፤ በአንድ አገር ውስጥ ዴሞክራሲ ጀምሯል ወይም አለ ለማለት ሁሉም ሀሳቦች በሕግ መሰረትና ሕገ መንግስቱን አክብረው መንሸራሸር አለባቸው። ይህ ሲባል ግን ሕዝቦችን ወደ ግጭትና ወዳልተገባ ቀውስ የሚከቱ ሀሳቦች ሁሉ ይንሸራሸራሉ ማለት ሳይሆን፤ ለህዝብ አዎንታዊ ጥቅም ያላቸው የትኞቹም ሀሳቦች በነጻነት ሊነገሩና ሊደመጡ ይገባቸዋል ማለት ነው። ይህ ሀሳቦች ያለ ጫና በሰላማዊ መንገድ እንዲስተናገዱ መፍቀድ ነው፤ የእኔ ሀሳብ ብቻ ይደመጥ አለማለት ነው። ይህ የሚፈቀድበት መንገድ ደግሞ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት(መልቲ ፓርቲ ሲስተም) ነው። ምክንያቱም የመድበለ ፓርቲ ስርዓት የተለያዩ ሀሳቦች በሰላማዊ መንገድ እንዲንሸራሸሩ የሚፈቅድ በመሆኑ ነው።

ሌላው በአንድ አገር የዴሞክራሲ መኖር መገለጫ፣ በህዝብ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ የተመረጠው የአሸናፊዎች አስተዳደር በድምጽ የወደቁ የተሸናፊዎችን መብት ማክበር(ማጆሪቲ ሩል ማይኖሪቲ ራይት) ሲከበር ነው። አሸናፊው የተሸናፊዎችን መብት ማክበር ብቻም ሳይሆን ተሸናፊዎችም ላሸናፊው እውቅና መስጠትንም ይመለከታል። ተጠያቂነትም አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ ሲሆን፤ ይሄም ማንኛውም አካል ወይም ሰው ለሚሰራውና ለሚወስነው ነገር ተጠያቂነት እንዳለበት ያሳያል።

ግልጸኝነት፣ የዴሞክራሲ ሌላው መገለጫ ሲሆን፤ ማንኛውም ውሳኔ ባለና በወጣ ሕግ፣ ደንብና መመሪያ ነው መወሰን ያለበት። ጉዳዮችንና ሰዎችን አይቶ ወይም የሆነ ሰው ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት ተብሎ ሕግ መውጣት የለበትም። ለሁሉም ሰው እኩል እድል የሰጠ፣ ሰላማዊ፣ ነጻና የተረጋጋ ምርጫ መኖርና ማካሄድም የዴሞክራሲ መኖር ማሳያ ነው። በዚህ ሂደት ደግሞ የሕግ የበላይነት የዴሞክራሲ ሂደቱ አንዱና ወሳኝ አካል ሲሆን፤ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነትም ተደጋጋፊና ተመጋጋቢ እንጂ የሚቃረኑ አይደሉም።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሑርና የሰብዓዊ መብት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ስለ ዴሞክራሲ ሲወራ ሕዝብ በአስተዳደር ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሚሆንበት፤ በቀጥታ ወይም በውክልና በመረጣቸው መሪዎች የሚተዳደርበት፤ ምርጫ በየጊዜው የሚካሄድበት ሁኔታን ታሳቢ ያደርጋል። ሰዎች ሀሳባቸውን በነጻ የሚገልጹበት፤ የሚፈልጉትን የሚደግፉበትና የማይደግፉትን የሚቃወሙበት፤ ከዛም አልፎ የወደዱትን መርጠው የሚጠሉትን ደግሞ የሚያወርዱበት የፖለቲካ ስርዓት ሲኖር ዴሞክራሲ አለ ማለት ይቻላል።

እነዚህ ደግሞ የሚደገፉት በሕግ እንደመሆኑ እያንዳንዱ ነገር ሕግና ስርዓት ሊኖረው ይገባል። ዴሞክራሲም ቢሆን በሕግ መደገፍ አለበት። በተለያየ መልኩ የሚወጡ የተለያዩ ሕጎች፣ ደንብና መመሪያዎች ወደ ተግባር ሲቀየርና ሕግ ሲከበር፤ ዴሞክራሲያዊ መብቶችም በሕግ ድጋፍ አግኝተው በተግባር ሲውሉና ሲረጋገጡ የሕግ የበላይነት ሰፈነ ወይም የሕግ የበላይነት ተረጋገጠ ሊባል ይችላል። ስለዚህ ሁለቱ ጉዳዮች (ዴሞክራሲና የሕግ የበላይት) ተደጋጋፊና አንዱ ያላንዱ ብዙም ትርጉም የሌላቸው የሚሆኑበት አግባብ ነው ያለው።

መደጋገፋቸው እንዴት ይገለጻል

እነዚህ ሁለቱ ተቃርኖ አላቸው የሚባል ሀሳብ ካለ ትክክል አይመስለኝም›› የሚሉት ዶክተር ሲሳይ፤ ‹‹መጀመሪያ እዚህ አገር ውስጥ ሁለቱም የት አሉና?›› ሲሉ ይጠይቃሉ። እንደእሳቸው አባባል ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲም አለ ለማለት አይቻልም፤ የሕግ የበላይነትም ገና አልተረጋገጥም። በመሆኑም እነዚህ ሁለቱም በሌሉበት ይቃረናሉ ማለት ስህተት ይሆናል። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ካለ ሕጎችና ደንቦች የበለጠ የህዝብን መብትና ጥቅም፣ የአገርንም ሉላዊነት የሚያስከብሩ፤ የበለጠ መግባባትን፣ በልዩነት ውስጥም ሆኖ አንድነትን የሚያሰፍን አሰራር እንደሚኖር፤ ይሄን ወደ ተግባር ለመቀየር ደግሞ ሕጎቹ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ያብራራሉ።

እንደ ዶክተር ሲሳይ ገለጻ፤ አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት በሕግ እየመራ ነው ያለው እንጂ የሕግ የበላይነትን እያሰፈነ አይደለም። ምክንያቱም በሕግ መምራት እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይለያያል። በሕግ ለመምራት አምባገነን መንግስታትም ሕግ እያወጡ ሊመሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ አፄ ሃይለስላሴ ሕገመንግስትን ጨምሮ ሌሎች ሕጎችን እያወጡ ህዝቡን ይገዙ ነበር፤ ደርግም በተመሳሳይ አዋጅ እያወጀ ያፍንና በአንድ ወታደራዊ አገዛዝ ህዝቡ እንዲሰቃይ ሲያደርግ ነበር። ኢህአዴግም በተወሰነ መልኩ መድበለ ፓርቲ ስርዓት የሚፈቅድ ሕገመንግስት ቢኖርም የኋላ ኋላ ለስልጣኑ እየሰጋ ሲመጣ የፀረ ሽብር ሕግ፣ የፀረ ሙስና ሕግ፣ የበጎ አድራጎትና የሲቪክ ማህበራትን ነጻነት የሚጋፋ ሕግ፣ ወዘተ አውጥቶ ማፈን ጀመረ።

ይሄን አይነት አካሄድ ደግሞ የሕግ የበላይነትን ማስፈን ሳይሆን በሕግ መምራት/መመራት ነው። ምክንያቱም ሕግ ስላለ መንግስት በሕግ ይመራል፤ ሕጉ ግን ህዝብን የሚጠቅምና አገርን ወደፊት የሚያራምድ አልነበረም። የሕግ የበላይነት ሲባል ግን መንግስትም ለሕግ ተገዢ መሆን መቻል አለበት። ሆኖም እስካሁን ባለው ሁኔታ መንግስት በራሱ ለሕግ ተገዢ አልነበረም። ሌላው ቀርቶ ለሰብዓዊ መብቶች እውቅና የሰጡ ዓለማቀፍ ድንጋጌዎችን ያካተተ ሕገ መንግስት አለን እየተባለ መንግስት የሰብዓዊ መብቶችን የሚጥሱ ስራዎችን ሲያከናውን ነበረ። በመሆኑም መንግስት በራሱ ለሕግ ተገዢ ባልሆነበት ሁኔታ የሕግ የበላይነት ሊረጋገጥ አይችልም።

የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከሆነ ሕጉ ሲወጣ ጀምሮ ሕዝቡን ያሳተፈ ሊሆን ያስፈልጋል፤ የአብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ፍላጎትና ስሜት ያገናዘበም ይሆናል። ይህ ሲሆን ብዙሃኑ የሚደግፉት ሕግ ስለሚወጣ ያን ሕግ ህዝቡ ያከብረዋል፤ ይተገብረዋል። መንግስትም በራሱ ይገዛበታል። ከዚህ ወጥቶ የሚሰርቅ ወይም ሌላ ተግባር የሚፈጽም ባለስልጣንና አካል ካለም ተጠያቂ ይሆናል። አሁን ግን ይሄ አይታይም። ለዚህም ነው የሕግ የበላይነት እየታየ ያልሆነው፤ ዴሞክራሲውም እስካሁንም በተሟላ መልኩ ስራ ላይ ያልዋለው።

አቶ እንዳለ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ሁለቱ ተቃርኖ የላቸውም፣ ተመጋጋቢ ናቸው ሲባል፤ የሕግ የበላይነት የዴሞክራሲ ምሰሶ ነው፤ ዴሞክራሲም የሕግ የበላይነትን ያሰፍናል ማለት ነው። ስለዚህ የሕግ የበላይነት እንዲኖር ዴሞክራሲ መኖር አለበት። የሕግ የበላይነት ደግሞ የዴሞክራሲ አንድ መርሆ ነው። ሕግ ደግሞ ለአንድ ሰው መብትም ግዴታም የሚሰጥ እንደመሆኑ፤ ዴሞክራሲ በዚህ ላይ ተመስርቶ የሚተገበር ይሆናል። ይህ የሚሆነው ደግሞ ህዝቡም ሆነ የመንግስት ኃላፊዎች በሕግ ስለመገዛት ማመን፤ ሕጉም ለእኔ ይጠቅማል ብለው ማመን ይጠበቅባቸዋል። ያለው ችግር ግን የሆነ ጉዳይ ሲፈልጉ የሕግ የበላይነቱን ገሸሽ ያደርጉታል፤ ሌላ ጉዳይ ሲሹ ደግሞ የሕግ የበላይነትን ይፈልጉታል። ይህ ደግሞ በመንግስት አካላት ጎልቶ የሚታይ ነው።

ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ለሕግ የበላይነት አትመችም ማለት አይደለም። ምክንያቱም በተለይ ህዝቡ ቀደም ሲል ለሕግ ከፍተኛ ትርጉም ያለው ቢሆንም፤ በማበረታታት አልታጀበም። አንድ ሰው እያጠፋና እየሰረቀ በሄደ ቁጥር ደግሞ የሕግ የበላይነቱን ይሸረሽረዋል፤ ስርዓት አልበኝነትን ያሰፍናል። ስለዚህ መንግስት መጀመሪያ የራሱን ቢሮክራሲ በደንብ ማሳመን፤ ተጠያቂነት ስላለበትም በሕግ የበላይነት ላይም አለመደራደር ይኖርበታል። አሁን እየተንጸባረቁ ያሉትም ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮች ሲሆኑ፤ ይህ ደግሞ የከተማ፣ የወረዳ ወይም ዞን አስተዳዳሪ ስርዓት አልበኝነትን የሚፈልጉትና እንዲሆን የሚፈቅዱት ደግሞ ‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል›› እንደሚባለው በማምታታት የራስ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ነው።

በዚህ መልኩ ችግሮች ሲታዩ ደግሞ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት የሚጋጩ መስለው ሊታዩ ይመስላል። ምክንያቱም የፖለቲካ መሪው፣ አስተማሪው፣ ሐኪሙ፣ የእምነት መሪው፣ ወዘተ. ሞዴል ሆነው መታየት ካልቻሉና የዚህ አይነት ድርጊት ተባባሪ ሆነው ሲታዩ ነው በሁለቱ ተደጋጋፊነት ላይ ብዥታን የሚፈጥረው። እናም ኃላፊነት የወሰዱ ሰዎች ስራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ፣ ተጠያቂነት እንዲኖራቸው፣ የህዝብ ውሳኔ ሰጪነት እንዲረጋገጥ፣ ሀሳቦች በነጻነት እንዲሸራሸሩ ለማድረግና መሰል የሕግና ዴሞክራሲ መገለጫ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያግዙ ጣምራ ጉዳዮች ናቸው። ምክንያቱም የሕግ የበላይነት ለዴሞክራሲ፤ ዴሞክራሲም ለሕግ የበላይነት አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው። ለዚህ የሚመች ቢሮክራሲ ሲፈጠር ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ተደጋጋፊነታቸው ይረጋገጣል።

ተደጋጋፊነታቸውን ጠብቀው ባይጓዙስ

አቶ እንዳለ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ በየትኛውም እምነትና ባህል፣ በየትኛውም አካባቢ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ መከባበርን፣ መተሳሰብና መተባበርን የሚቃረን እሴት የለም። ችግሩ ይሄን ተጠቅሞ የመምራት በተለይም የመንግስት ኃላፊዎች ችግር ነው። በሌላ በኩል ዴሞክራሲ ሲባል እንደፈለጉ የመሆን፤ የሕግ የበላይነት ሲባልም ሁሉንም የማሰር አድርጎ የማየት አዝማሚያ አለ። ስለዚህ ይሄ ሊታረም ይገባል፤ በሀሳብ ብዝሃነት ማመንም ያስፈልጋል። ይሄን ማድረግ ካልተቻለ ዴሞክራሲን ማስረጽ፣ የሕግ የበላይነትንም ማረጋገጥ ስለማይቻል ከባድ ችግር ይፈጠራል።

ምክንያቱም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በግድ ተይዞ የሚኖር ህዝብ አይኖርም። ከአሁን በኋላ ዴሞክራሲ ከሌለ መስራት ሳይሆን ወጥቶ መግባት እንኳን የሚቸግርበት እድል ይፈጠራል። በመሆኑም ዴሞክራሲም ሆነ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የመንግስት ቀዳሚ ስራ ሊሆን ይገባል። በዚህ መልኩ ከአሰራር የሚወጣን አካል ወይም ቡድን ወደ መስመር ማስገባት ሲቻል ህዝቡም ደስተኛ ይሆናል። የሕግ የበላይነት በመከበሩ የሚቆጣ ቡድን ሊኖር ይችላል፤ የሚቆጡ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ፤ የሚቆጣ ህዝብ ግን የለም። እነዚህ ቡድኖችና ግለሰቦች ቢቆጡ ደግሞ ለህዝብ ጥቅም ሳይሆን ስርዓት አልበኝነት በመፍጠር ባቋራጭ ተጠቃሚነታቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ነው። ይህ ደግሞ ሁል ጊዜ የሚኖር ሲሆን፤ እንደዚህ ያሉ አካላት ላይ ማስተካከያ አትውሰድ የሚል የዴሞክራሲ ስርዓት የለም። በመሆኑም ዴሞክራሲ እንዲዳብር፣ የሕግ የበላይነትም እንዲረጋገጥ በሚወሰዱ እርምጃዎች የሚቆጡ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ቢኖሩም ዴሞክራሲንም ሆነ የሕግ የበላይነትን በሚነኩ ነገሮች ላይ መደራደር አይገባም።

መንግስት በፖለቲካ የሚመድባቸው ሰዎችም በዚህ ሊለኩ ይገባል። በሕግ የበላይነት ላይ የሚደራደር፤ አሁን እንደሚታየው በወረዳና ዞን አካባቢ ስርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን የሚሰሩ አካላት ካሉም ሀይ ሊባሉ ይገባል። ምክንያቱም የአንድና ሁለት ኃላፊዎች ችግር የበርካታ ህዝቦች መረበሽ ምክንያት በመሆኑ በሌሎች ነገሮች ላይ የሚታይ መታገስ በሕግ የበላይነት ላይ መታየት የለበትም። ለዚህ ደግሞ ከትምህርት ቤቶች፣ የእምነት ተቋማት፣ የመንግስት ተቋማትና ሌሎችም ትውልድና ህዝብጋ የሚደርሱ አካላት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል።

እንደ ዶክተር ሲሳይ ማብራሪያ የለውጡ አመራር እንደመጣ ከፍተኛ ድጋፍ ነበረው። ሆኖም ዴሞክራሲያዊ ሁኔታው በአግባቡ ስላልተመራና የሕግ የበላይነትም የማስከበር ሂደቱ ስላልተሳካላቸው ሲደግፋቸውና ሲያደንቃቸው የነበረው ህዝብ ወደ ቅሬታ እንዲመለስ፣ በመንግስቱም ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸርና ድጋፉ እየቀነሰ እንዲሄድ አድርጎታል። ከዚህ በተጓዳኝ ሲደግፉ የነበሩ ሚዲያዎችና ተፎካካሪ ፓርቲዎችም መቃወም በመጀመራቸው እንደገና በየምክንያቱ መታሰር ጀመሩ። ይህ ደግሞ አገራዊ መግባባት እንዳይፈጠር ያደርጋል።

በ2012 በሚዛናቸው እንዲጓዙ

ዶክተር ሲሳይ እንደሚሉት፤ ጳጉሜ አራት የዴሞክራሲ ቀን ስለተባለ የዴሞክራሲ ስርዓት ይገነባል ማለት አይደለም። ነገር ግን የመንግስትን ቁርጠኝነት ማሳያ አንድ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የማዕከላዊ እስር ቤት ክፍት መሆንም የዚህ አንድ አብነት ሊሆን የሚችል ነው። ለበዓሉ ዝግጅት ሲባል በሚከናወኑ መርሃ ግብሮች በሰፊው መነጋገርና ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣት ብሎም በችግሮቹ መነሻነትም መንግስት ዴሞክራሲን ለማስፈን በዕለቱ ቃል የሚገባበትን እድል ይሰጠዋል። ለዴሞክራሲ መስፈንና የሕግ የበላይነት መከበርም በጎ መልዕክት ሊተላለፍበት ይችላል።

ምክንያቱም በአገሪቱ ትልቅ ችግር የሆነው እዚህም እዚያም የነገሰው ስርዓት አልበኝነት ነው። በዚህ ምክንያት የሰላም እጦት አለ፤ የፖለቲካ ቡድኖች ማፈንገጥም ተስተውሏል። እነርሱ የሚፈጥሩች ችግር ደግሞ የበለጠ ሰላሙን የሚያናጋ ይሆናል። ስለዚህ በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያው ስራ መሆን ያለበት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ነው። ሰላም የሚመጣው ደግሞ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በማሳተፍና ሀሳባቸውንም ግምት ውስጥ በማስገባት፤ ሁሉንም ክልሎች በአግባቡ እንዲደመጡ በማድረግና በፌዴራል መንግስት ውስጥ ተገቢ ውክልና እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ በማከናወን፤ ብሎም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር በማድረግ ጭምር ነው።

ወጣቱ የስራ እድል እንዲያገኝና በተለያዩ መስኮች ተሰማርቶ እንዲሰራ በማድረግ አዕምሮው ስራ እንዳይፈታና ራሱን በስራ እንዲወጥር በማድረግ ለተንኮል እሳቤዎች ተገዢ እንዳይሆን ማስቻልም ይገባል። በህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ ተገንዝቦ መመለስ፤ ለሚገለጹ ቅሬታዎች የሚሰጡ ምላሾች ለሌላ ሁከትና ብጥብጥ በር እንዳይከፍቱ መጠንቀቅም ያስፈልጋል። ባለው ሁኔታ መንግስት ለተወሰኑ የአክቲቪስት ቡድኖችና የማህበራዊ ሚዲያ ሽፍቶች ተንበርካኪ እየሆነ ያለበትን ሂደትም በህዝቡ ዘንድ ጉርምርምታን እየፈጠረ በመሆኑ ማረም ይጠበቅበታል። በተመሳሳይ፣ አንዱን እንዳሻው ለቅቆ በህዝቦች መካከል ግጭት ሲቀሰቅስ ዝም እያሉ ሌላውን የማሳደድና የማሰር አካሄዱም ሊታረም ያስፈልጋል። ብስለት በተሞላበት አመራርም በፓርቲው ውስጥ ያለው መጠራጠርም መልክ ሊይዝ ይገባል። እነዚህንና መሰል ግድፈቶችን በማረም ዴሞክራሲያዊ አሰራሩም፤ የሕግ ተገዢነቱም ለሁሉም በእኩል መልኩ እንዲሆን መስራት ይገባል።

አቶ እንዳለ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ዓለም ያደገው በዴሞክራሲ ነው። በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያላደጉ አገሮች ተመልሰው ችግር ውስጥ ሲገቡ እየታየ ነው። ምክንያቱም አስገድዶ ማስቆፈር፣ ደሴትም ማሰራትና እድገት ማምጣት ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን እድገቱ ዘላቂ አይሆንም። ዘላቂ እድገትና ሰላም የሚመጣው በዴሞክራሲ ነው። ከዚህ አኳያ የዴሞክራሲ ቀን መከበሩ መልካም ነው። ነገር ግን በባዶ የሚከበር ከሆነ ትርጉም የለውም። ለዴሞክራሲ ዓመቱን ሙሉ ሰርቶ ነው ቀኑን ማክበር የሚገባው።

ዴሞክራሲ ደግሞ የአንድ ቀን በዓል ማክበርና ስራ ውጤት ሳይሆን የ365 ቀናትን ስራ የሚጠይቅ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ መከበሩ ለዴሞክራሲ ትኩረት እንደተሰጠው የሚሳይ ነው። ቀኑ ሲከበር ግን ለሕግ የበላይነት ትልቅ ትኩረትና ቦታ ሰጥቶ ሊሆን ይገባል። ለምን ቢባል፣ ቀደም ሲል በተለያዩ ምክንያቶች ብዙ ችግሮች ነበሩ፤ የመብት ጥሰቶችና አፈናዎችም ነበሩ። ይህ ቀውስ ደግሞ የአንድ ቀን ውጤት አይደለም፤ ሂደቱም የቆየ የቤት ስራን ማከናውን የሚጠይቅ ነው። ስለዚህ ቀኑ ሲከበር ከዴሞክራሲ መርሆዎች መካከል አንዳንድ (ሁሉንም በአንድ ጊዜ መፍታት ስለማይቻል የሕግ የበላይነቱን ወይም መድበለ ፓርቲውን ወይም የአሰራር ግልጸኝነቱን ወይም ሌላ አንዱን) እየሰጡ ለመፍታት ለመስራት ቃል በመግባት ነው።

ቃል ከመግባት ባለፈም ለስራው ራስን ማዘጋጀትና በዛው ልክ መትጋትን የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ ነው። ለዚህ ደግሞ ለአመራሩ ግንዛቤ መፍጠር፣ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ማከናወን፣ ካለፈው ሂደት ተምሮም የተሻለ መስራት የሚችል ሁሉን አቀፍ አቅም መፍጠር ይገባል። ከዚህ በተጓዳኝ አመራሩ፣ ህዝቡ፣ ነጋዴውና ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ሰርቶ መብላት፤ ወጥቶ መግባት፤ የውጭ ዲፕሎማሲው ስኬት፣ የኢኮኖሚው እድገትና ሌላውም ሊረጋገጥ የሚችለው ዴሞክራሲ ስር ሲሰድ፤ የሕግ የበላይነትም ሲረጋገጥ መሆኑን ተገንዝቦ የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል።

አዲስ ዘመን ጳጉሜ 4/2011

ወንድወሰን ሽመልስ