የግል ትምህርት ቤቶች የስርዓተ ትምህርት ጥሰት

104

 መንግሥት ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ የነበረውን የትምህርት ሥርዓት ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል። ይህ የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታ በይፋ ሥራ ላይ ሲውል ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሰባት ዓመታቸው ጀምረው በ18 ዓመታቸው ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ተማሪዎች በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ለስድስት ዓመታት፤ በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ለሁለት ዓመታት እንዲሁም በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እንደ ቀድሞው የአራት ዓመታት ቆይታ ይኖራቸዋል። በቀጣዮቹ ዓመታት ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ በሚጠበቀው የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ መሠረት የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተና ይወስዳሉ። የስምንተኛ ክፍል ፈተናንም ብሔራዊ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን ላለፉት 18 ዓመታት ይሰጥ የነበረው የአስረኛ ክፍል አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንዲቀር ያደርጋል።

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ በሰጠው መግለጫ በፍኖተ-ካርታው ተለይተው ከቀረቡት ውሳኔ የሚያሻቸው ጉዳዮች መካከልም የቅድመ መደበኛ ትምህርትን መንግስት በሙሉ ኃላፊነት እንዲተገብር፣ የአንደኛ ክፍል መግቢያ እድሜ 7 ዓመት እንዲሆን፣ የአጠቃላይ ትምህርት ማጠናቀቂያ እድሜ 18 ዓመት እንዲሆን የሚሉና የአጠቃላይ ትምህርት መዋቅር 6-2-4 ሆኖ እንደሚዋቀር ነው የገለፀው። የትምህርት አሰጣጡ ከአሃዳዊነት ወደ ትምህርት ክፍል (ዲፓርትመንት) እንዲቀየር፣ ነጻና የግዴታ ትምህርት ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ 8ኛ ክፍል እንዲሁም ነጻ ትምህርት እስከ 12ኛ ክፍል እንዲሆን፣ የግብረ ገብ ትምህርት እስከ 6ኛ ክፍል ራሱን ችሎ እንዲሰጥ፣ የልዩ ፍላጎትና ተሰጥኦ ያላቸው ህጻናት የሚለዩበትና የሚደገፉበት ስትራቴጂ በመቅረጽ እንዲተገበር የሚጠይቁ መሆናቸው ታውቋል።

በአሁን ወቅት ስራ ላይ የሚገኘው የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ ከመንግስት ትምህርት ቤቶች ውጭ በግል ትምህርት ቤቶች በብዛት ሲተገበር አይታይም። ይህ ደግሞ አዲሱ የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ- ካርታ በግል ትምህርት ቤቶች ተግባር ላይ ላይውል ይችላል የሚል ግምት አሰጥቷል። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የግል ትምህርት ቤቶች ምን ያክል የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲው በግል ትምህርት ቤቶች እየተተገበረ ስለመሆኑ ክትትል ያደርጋል። በክትትሉም ብዙ የግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲውን የጣሰ አሰራር እየተከተሉ መሆኑን ይናገራል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ የስነ ዜጋና ስነምግባር ትምህርት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አስራት ሽፈራው እንደሚናገሩት፤ መንግስት አገራዊ በሆነ መልኩ አንድ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ አውጥቷል። ፖሊሲው ከሚያካትታቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ይገኝበታል። የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት በመላ አገሪቱ በተመሳሳይ መልኩ የሚተገበር ነው። በየትምህርት ቤቶቹ ስርዓተ ትምህርቱ በአግባቡ እየተተገበረ እንዳለ ክትትል ይደረጋል። በአዲስ አበባ በርካታ የግል ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። የግልም ሆነ የመንግስት ትምህርት ቤቶች በስርዓተ ትምህርቱ ገዢነት ተግባራቸውን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል።

በመንግስት ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ስርዓተ ትምህርቱ እየተተገበረ ሲሆን በግል ትምህርት ቤቶች ስርዓተ ትምህርቱን የሚጣረሱ ነገሮች ይስተዋላሉ። የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት የስርዓተ ትምህርት አተገባበር ምን እንደሚመስል በሚያካሂደው የክትትል ስራ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ የስርዓተ ትምህርት ጥሰት በብዛት እንደሚታይ ይገልጻል። የክትትል ስራው በሶስት ደረጃ የተከፈለ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ የሚተገብሩ፣ በከፊል የሚተገብሩና በጭራሽ ተግባር ላይ የማያውሉ ተብሎ መከፋፈሉን አቶ አስራት ያስረዳሉ።

እንደ አቶ አስራት ገለፃ፤ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተማሪዎች መውሰድ የሚገባቸው ትምህርቶች ተጠቅሰዋል። በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሚታዩት የስርዓተ ትምህርት ጥሰቶች መካከል ለምሳሌ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ መማር የሚገባቸው አራት የትምህርት አይነት ሆኖ ሳለ እስከ ስምንት የትምህርት አይነት ያስተምራሉ። ሌላኛው ደግሞ የትምህርት አይነቶቹን በአማርኛ ማስተማር ሲገባቸው በእንግሊዘኛ ቋንቋ የመስጠት ሁኔታዎች ይበዛሉ። በግል ትምህርት ቤቶች ከአንደኛ ክፍል እስከ አራተኛ ክፍል የአካባቢ ሳይንስና ሂሳብ ትምህርት በእንግሊዝኛ እየተሰጠ ይገኛል።

የስርዓተ ትምህርት ጥሰቶች ለማሻሻል በክትትል ሂደቶች የተገኙትን ጥንካሬዎችና ድክመቶች በመለየት በተለይ በግል ትምህርት ቤቶች የተጣሱት ምንድናቸው፤ በምን ደረጃ ነው የተጣሱት የሚለውን ነገር መለየት ስራ እንደሚከናወኑ ይናገራሉ። የተለዩት ችግሮች እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለአዲስ አበባ አጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ሪፖርት ያደርጋል። ኤጀንሲው ዋነኛ ተግባሩ ለግል ትምህርት ቤቶች ፈቃድ መስጠት፣ ማደስና አጥፍተው ሲገኙ ደግሞ ፈቃድ የመሰረዝ መብት እንዳለው ይጠቅሳሉ። በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ተናቦ መስራት ያስፈልጋል። በየዓመቱ በሚደረጉ የክትትል ስራዎች የታየ ነገር ቢኖር ሁልጊዜም የስርዓተ ትምህርት ጥሰት እንደሚስተዋል ያመለክታሉ።

በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የእንግሊዘኛ ቋንቋን እንደ ግዴታ በመውሰድ መንግስት ያስቀመጠውን ስርዓተ ትምህርት እየጣሱ ይገኛሉ የሚሉት አቶ አስራት፤ በዚህ ደግሞ ህፃናት ተማሪዎች ላላስፈላጊ መጨናነቅ እየተዳጉ እንደሚገኙ ይገልፃሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርት ቤቶቹ የራሳቸውን መፅሀፍት የማሳተምና የመሸጥ ነገሮች የነበሩ ሲሆን በአሁን ወቅት በተወሰነ መንገድ እንዲቀረፍ ተደርጓል። አብዛኛው የግል ትምህርት ቤት ትኩረት ቋንቋ ላይ ሲሆን በተለይ እንግሊዘኛ ቋንቋን እንደ ግዴታ በመውሰድ እየሰሩና እያስተማሩ እንደሚገኙ ያስረዳሉ።

ችግሩን ለመፍታት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮና የአዲስ አበባ አጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ተናበው መስራት ሲጠበቅባቸው እስካሁን ችግሩ ሳይፈታ የቆየው መስሪያ ቤቶቹ ተናቦ መስራት ላይ ችግሮች በመኖራቸው መሆኑን ይጠቁማሉ። ለዚህ ደግሞ ማሳያው የግል ትምህርት ቤቶች ተደጋጋሚ የስርዓተ ትምህርት ጥሰት መፈፀማቸውና እርምጃ አለመወሰዱ መሆኑን ይናገራሉ።

በ2010 ዓመተ ምህረት ኢንስፔክት ከተደረጉት አንድ ሺ 407 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ደረጃ አንድ፡ 41፣ በደረጃ ሁለት፡ 560 ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃ አንድ፡ 10፣ በደረጃ ሁለት፡ 409 እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃ አንድ፡ 6፣ በደረጃ ሁለት፡ 80 በድምሩ አንድ ሺ 106 (78 ነጥብ 6 በመቶ) ትምህር ቤቶች ስታንዳርዱን ያላሟሉ (ደረጃ አንድ እና ደረጃ ሁለት) መሆናቸውን ያሳያል። ቀሪዎቹ በቅድመ መደበኛ 108፣ በመጀመሪያ ደረጃ 125 እና በሁለተኛ ደረጃ 66 በድምሩ 299 (21 ነጥብ 3 በመቶ) ትምህርት ቤቶች ደረጃ ሶስት ናቸው።

በ2010 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ 363 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች የእውቅና ፈቃድ እድሳት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በተደረገው ምዘና፣ 309 ትምህርት ቤቶች ታድሶላቸዋል፤ 28 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ስታንዳርዱን በሚጠበቀው መጠን ባያሟሉም በማስጠንቀቂያ ለአንድ ዓመት ብቻ እንዲቀጥሉ ተደርጓል፤ 26 ትምህርት ቤቶች ከስታንዳርድ በታች በመሆናቸው እንዲዘጉ ተደርገዋል። ከተዘጉት ተቋማት ውስጥ ከቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ቦሌ ቡልቡላ፣ ሳሊተ ምህረትና ቶምናጄሪ። በየካ ክፍለ ከተማ፣ ገነተ እየሱስ አዲስ ሰው፣ ኤሎን፣ ሀመር፣ ሙሴ፣ ሜሲሚዶ ናቸው። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ብራስዩዝ ሲሆን ከንፋስ ስልክ፣ ንጋት፣ አሀዱ ቤተሰብ እና ደብል ይገኙበታል። ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፣ አፍሪካ ስድሪም፣ ባቤጅ፣ ብሪሊያንት፣ አልአፊያ ቁጥር አንድ፣ ጂኤች፣ ኢስት አፍሪካ፣ ቅዱስ ዮሃንስ ናቸው። ጉለሌ ክፍለ ከተማ አጼ ተክለጊዮርጊስ፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ደግሞ ሳም ፋሚሊ፣ ኒው ዩኒክ። ከልደታ ክፍለ ከተማ፣ ብራይት መሆናቸውን አብራርተዋል።

ትምህርት ቤቶቹ የተዘጉበት ምክንያት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተቋም ሊኖሩት የሚገባ የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አለመኖር፣ የመምህራንና የሠራተኞች የትምህርት ደረጃ አለመሟላት፣ የመምህራንና ሠራተኞች ብዛት ማነስ፣ የሕፃናት ማሸለቢያ ክፍል ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው ቁሳቁሶች አለመኖር፣ ቋሚ የውጭ መጫወቻ መሳሪያዎች እጥረት፣ የመምህራን ማረፊያ ክፍል ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው ቁሳቁሶች አለመኖር፣ የትምህርት ማበልፀጊያ ማዕከል (work shop) አለመኖር፣ የሚያስፈልግ የሰው ኃይል አለመቅጠር፣ ለሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት የሚያስፈልጉ የትምህርት መሳሪያዎች አለመሟላት፣ የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አለማዘጋጀትና የስርዓተ ትምህርት ጥሰት ተጠቅሰዋል።

አዲስ ዘመን ጳጉሜ 4/2011

 መርድ ክፍሉ