«የማታ ስጦታ»

9

ዕድሜ ሲመሽ አካላዊ ብርታትን ስለማሳጣቱ አስረጂ አያሻም። እንደወትሮው ሰውነትን ማቀላጠፍ፣ ያለ ድካም ስራን ማከናወን እንዲሁም እንደ ወጣትነት የፈለጉትን ለማድረግ መነሳትም የማይጠበቅ ነው። የጡንቻዎች መሟሸሽ፣ የመገጣጠሚያዎች አለመታዘዝ፣ ብርድ ብርድ ማለት እንዲሁም በትንሽ በትልቁ በህመም መቀሰፍም በእርጅና ጊዜ የሚመጣ ለውጥ ነው። በሴቶች ላይ ደግሞ እድሜን ተከትሎ ተፈጥሮአዊው ጸጋ ልጅ ወልዶ መሳምም የማይታሰብ ይሆናል።

«ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም» አይደል የሚባለው የሚያስደንቅ እና ግርምትን የሚያጭር ነገር ሲገጥም። በትንሿ ወር ጷጉሜ «አጀብ» የሚያሰኝ ነገር ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧልና ነው እንዲህ ማለታችን። አንዳንዴም ተፈጥሮ ከጸጋዋ እንዲሁም ከህግጋቷ እንደምታፈነግጥ ማሳያ እንዲሆንም ማሳያ ነው። «የ74 ዓመቷ ባልቴት የመጀመሪያ ልጃቸውን ከሰሞኑ በመገላገል በዓለም ትልቋ እናት ተሰኝተዋል» የሚለው ዜና (ጉድ ሳይሰማ… አትሉም)።

ነገሩ እንዲህ ነው በህንድ አንታር ፕራዴሽ ከተባለ ስፍራ ነዋሪ የሆኑት ማንጋያማ የተሰኙ ሴት፤ ኔላፓርታሂፑዲ ከተባለ አካባቢ ከተገኙት ወጣት አርሶ አደር ጋር እአአ በ1962 በትዳር ይጣመራሉ። የአንድ ጎልማሳ እድሜ ባስቆጠረው የትዳር ዘመናቸውም እንደ ወጉ ወልደው መታቀፍ ቢፈልጉም አልተሳካላቸውም። በልጅ አምሮትም ለዓመታት ያልሄዱበት ሃኪም ቤት ያልረገጡት የሃይማኖት ስፍራም አልነበረም። ትዳራቸው በልጅ ላለመባረኩም የአካባቢው ሰው አንዳች ሃጢያት አሊያም መርገምት ቢኖርባቸው ነው ሲል መጠቋቆሚያ አድርጓቸው ቆይቷል።

ሌሎች እንዲያ ይበሉ እንጂ ባላቸው ግን ማንጋያማን በማጽናናት እና በማጠንከር ዓመታትን አብረው ዘልቀዋል። ተስፋ ለመቁረጥ ሩቅ የሆኑት ጥንዶቹ ከ25ዓመታት በፊት በህክምና እርዳታ ልጅ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም ነበር። ያለፈው ዓመት ታዲያ አንዲት የ55 ዓመት ጎረቤታቸው ህክምናውን አግኝታ ማርገዟን ተከትሎ ጥንዶቹ በእርጅናቸው ሳያቅማሙ ወደ ህክምና ይሄዳሉ። ባለሙያዎችም በማንጋያማ እድሜ ህክምናውን እስካሁን ያልደፈሩት ቢሆንም አስፈላጊውን ምርመራ ሁሉ እንዲያደርጉ ያዛሉ።

የምርመራው ውጤትም ባልቴቷ ጤነኛ ስለመሆናቸው የሚመሰክር ቢሆንም፤ በእርግዝና ወቅት የሚኖረውን ድካም እንዲሁም አእምሯቸው ዝግጁ ስለመሆኑ መጠየቃቸው አልቀረም። ይህ ከሆነ በኋላም ህክምናው ቀጠለ። ላለፉት ዘጠኝ ወራትም አስር ዶክተሮች የወይዘሮ ማንጋያማን ጤንነት እንዲሁም እርግዝናው በትክክለኛ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ይቆጣጠሩ ነበረም ብሏል ዘገባው። በመጨረሻም ተስፋቸው ፍሬ አፍርቶ ጤነኛ እና መንትያ ሴቶችን መገላገል ችለዋል።

ይህም ባልቴቷን በ74 ዓመታቸው ወልደው የሳሙ የዓለማችን አዛውንቷ እናት አድርጓቸዋል። ከዚህ ቀደም የክብረወሰን ባለቤት የነበሩት ሴት ዳልጂንደር ካኡር እአአ 2016 በዚሁ ህክምና ወንድ ልጅ በ70 ዓመታቸው በመገላገላቸው ነበር። ማንጋያማ ስለሆነላቸው ነገር ሲገልጹም «በጣም ደስተኛ ነኝ፤ አምላክ ለጸሎታችን ምላሽ ሰጥቶናል። አሁን የራሳችን ልጆች ስላሉን በዓለም ላይ ደስተኞቹ ጥንዶች ነን» ብለዋል። «በፈጣሪ ክብር እና በዶክተሮቹ ጥረት የሁለት ሴት ልጆች አባት ሆኛለው፤ በዚህም ኩራት ይሰማኛል። አምላክ ከ54 ዓመታት በኋላ ለልመናችን ምላሽ ሰጥቶናልና ደስተኛ ነኝ» ያሉት ደግሞ የ80 ዓመቱ ባለቤታቸው ናቸው።

ዶክተሮች በበኩላቸው ህክምናውን አስተማማኝ የሚያደርገው የእናትየዋ አካላዊ ጤንነት መሆኑን ነው የሚገልጹት። ዜናው በህንድ ከተሰማ በኋላም በስኬትነት የተጠቀሰላቸው ቢሆንም፤ በዚህ ዕድሜ ህክምናውን እንዲያገኙ እንዴት ሊፈቀድ ቻለ የሚለውም አጠያያቂ ጉዳይ ሆኗል። ሌሎች በበኩላቸው በዚህ ዕድሜ ያሉ እናቶች ለምን ያህል ጊዜ ልጆቻቸውን ሊንከባከቡ ይችሉ ይሆን ሲሉም ጥያቄ ያነሳሉ። ዜናውን የሰማነው እኛስ የሆነውን «የማታ ስጦታ» ብንለው አይገልጸው ይሆን?

 አዲስ ዘመን ጳጉሜ 4/2011

 ብርሃን ፈይሳ