ዴሞክራሲ እንዲጎለብት መብትና ግዴታችንን እንወቅ

20

ኢትዮጵያ በተለያዩ ስርዓቶች ውስጥ አልፋለች። እነዚህ ስርዓቶች ደግሞ የየራሳቸውን አሻራ ጥለው አልፈዋል። አሁን ለምንገኝበት ስርዓት መነሻ ተደርጎ የሚወሰደው የፊውዳል ስርዓትም የራሱን ዳና አኑሮ ያለፈ ነው። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የዴሞክራሲ እጦት ነው።

በፊውዳሉ ስርዓት ዴሞክራሲ ፈጽሞ የሚታሰብ አልነበረም። ሰዎች በሰውነታቸው ሳይሆን በመጡበት የዘር ሃረግ ብቻ አንዱ ጨቋኝ፣ ሌላው ተጨቋኝ አድርጎ የኖረ አምባገነናዊ ስርዓት ነበር።

በዘመኑ ንጉሱም ሆኑ ሌሎች የበታች ሹማምንት የሚያነሷቸው ሃሳቦችም ሆኑ የሚያወርዷቸው መመሪያዎች በቀጥታ ወደታች ከመውረድ ውጭ ለምን ብሎ ጥያቄ የሚቀርብባቸው አልነበሩም። በየደረጃው ያሉት የመሬት ከበርቴዎችና ባላባቶችም መሬትን በጅምላ በመያዝ ቁጭ ብለው አብዛኛውን ህዝብ ጭሰኛ አድርገው የሚበዘብዙበት ነባራዊ ሁኔታ በመኖሩ አብዛኛው ህዝብ የኢኮኖሚም ተጠቃሚ አልነበረም፤ በበደል እየቆዘሙ ከመኖር ውጪ ይህንና ሌሎች ጥያቄዎችንም የማንሳት ዴሞክራሲያዊ መብት ፈጽሞ የሚታሰብ አልነበረም።

ይህ አጠቃላይ የዴሞክራሲ እጦት ያስከተለው ቅሬታ ታዲያ ቀስ በቀስ ህዝብን ለምሬትና ብሎም ለአመፅ በመዳረጉ የፊውዳል ስርዓቱ እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል። ጥሮ ግሮ ባፈራው ሃብትና ንብረት ተጠቃሚ መሆን ያልቻለው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በባላባቶቹና መኳንንቱ ላይ የጀመረው አመጽ ተቀጣጥሎ ስርዓቱን እስከመናድ ደርሷል።

እሱን የተካው የደርግ መንግስትም ቢሆን ህዝቡ የፈለገውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊያጎናጽፈው አልቻለም። ይባስ ብሎ በህዝቡ ላይ አምባገነን በመሆን አፈናና ጭቆና ብሎም የጅምላ ጭፍጨፋ ማድረግ የደርግ መንግስት መገለጫ ሆነ።

ከመሬት ባላባቶችና ከበርቴዎች ተገላገልኩ ያለው ደሃው የህብረተሰብ ክፍልም በአዲስ መልኩ በመጡ አፋኝና ጨቋኝ ካድሬዎች ዳግም የመብት ረገጣ ደረሰበት። የደሃውን ልጅ በአደባባይ መረሸን እና ያለፍላጎቱ በሰፈራ ሰበብ እያፈናቀሉ ማሳደድ የደርግ መገለጫ ሆነ።

በዚህ የተነሳም ውሎ ሳያድር ህዝብ ዳግም ለትግል ተነሳ። ከ17 ዓመታት መራር ትግል በኋላም የደርግ መንግስት ወደቀ። ኢህአዴግም መንበረ ስልጣኑን ተቆጣጠረ። ኢህአዴግ ወደስልጣን ሲመጣ ቀደም ሲል ከነበሩት መንግስታት በተሻለ መልኩ የዴሞክራሲን መንገድ የተጓዘበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በዚህ ወቅት በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ መድረክ ተገናኝተው ለመወያየት በቅተዋል። ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት ለመግለፅም የተሻለ እድል አግኝተዋል። አገራችንም የዴሞክራሲዊ ህገ መንግሰት ባለቤት ሆናለች። ዴሞክራሲ የሚል ቅጥያ የያዙ በርካታ ድርጅቶችም ተፈጥረው በይፋ ሃሳባቸውን መግለፅ ችለዋል።

ይሁንና በዚህ የአገዛዝ ዘመንም በሚፈለገው ደረጃ ዴሞክራሲን ማረጋገጥ አልተቻለም። በተለይ የዴሞክራሲ ምህዳሩ ጠቧል በሚሉ ወገኖችና በኢህአዴግ መካከል በሚነሱ መካረሮች ቀስ በቀስ ፓርቲዎች  እየተዳከሙና ኢህአዴግ ብቻ አውራ ፓርቲ ሆኖ የመጣበት ሁኔታ እንዲፈጠር አደረገ።

የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና ሂደቱም እየተሸረሸረ መጣ። ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል የሚለው የዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብም እየተናደ ሄደ። ይህ ደግሞ በአገሪቷ ውስጥ የታየው የዴሞክራሲዊ ስርዓት ጭላንጭል እንዲጠፋ በር ከፈተ።

እነሆ ይህ ከሆነ ከ27 ዓመታት በኋላ በህዝቦች መሪር ተቃውሞ መነሻነት ኢህአዴግ በውስጡ ባካሄደው ተሃድሶ ራሱን ፈትሾ ለውጥ አደረገ። ይህ ለውጥ ገና ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ያልዘለለ ቢሆንም ያስመዘገባቸው በርካታ ለውጦች ግን እንዳሉ አይካድም። በተለይ የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ዋነኛ መነሻ የሆኑትን የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ እውን ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎች በተጨባጭ ለውጥ ያመጡና የሚያመጡ ናቸው።

ከዚህ አንጻር የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግን ገለልተኛ በሆኑ አካላት ዳግም ለማዋቀር የተከናወነው ስራ ተጠቃሽ ነው። ከዚህም ባሻገር ቀደም ሲል በዴሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ ውስጥ ትልቅ እንቅፋት የፈጠሩ የተለያዩ ህጎችንና አዋጆችን በማሻሻል የተከናወነው ስራም የዚሁ የዴሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታ አንድ አካል ነው።

በተለያዩ ምክንያቶች በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ላይ እንቅፋት ፈጥሮ የነበረውን የፀረ ሽብር አዋጅ በአዲስ መልኩ በማሻሻል የዴሞክራሲ ምዕራፉን ለማስፋት የተከናወነው ስራ ተጠቃሽ ነው። በሰብ አስባቡ ብዛት ታስረው የነበሩ ታራሚዎች በምህረት መለቀቃቸውም ለዴሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታው መልካ መደላድል የሆነ ነው።

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የዴሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚገዳደሩ ክስተቶች አልጠፉም። ከነዚህም ውስጥ የህግ የበላይነትን የሚጣረሱ ድርጊቶች ይጠቀሳሉ። በተለይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ዜጎችን ከቀዬአቸው የማፈናቀል እና በየቦታው የሰው ህይወት መጥፋት ዴሞክራሲው በአግባቡ እንዳያድግ የራሳቸውን አሉታዊ ጫና ፈጥረዋል።

ከዚህም ባሻገር ከህግ አግባብ ውጭ በማህበራዊና ሌሎች ሚዲያዎች የብዙሃኑን ህዝብ መብት የሚጋፉ ድርጊቶች የሚከናወኑበት፣ የርስ በርስ ግጭቶችን ለመፍጠር የሚሰሩ እንቅስቃሴዎችና መሰል ድርጊቶች በወቅቱ መታረም ያለባቸው የዴሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታ እንቅፋቶች ናቸው።

በመሆኑም አሁን የተጀመረውና አጓጊው የዴሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታ እውን እንዲሆንና የአገራችን ዴሞክራሲ ጎልብቶ ወደምንፈልገው ጠንካራ ዴሞክራሲዊ ስርዓት እንድንሸጋገር በመንግስት በኩል የተጀመሩ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

ከዚህም ጎን ለጎን ህብረተሰቡም መብትና ግዴታውን በአግባቡ መለየትና ለመብቱ ዘብ መቆም፣ በአንጻሩ ደግሞ ግዴታውን በአግባቡ የሚወጣበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል። መብትና ግዴታው አውቆ በዚያ የሚመራ ማህበረሰብ ዴሞክራሲዊ ስርዓትን ለመገንባት ትልቅ አቅም ነውና።  

አዲስ ዘመን ጳጉሜ 4/2011