ቦርጭን በአራት ደቂቃ

63

 ቦርጭ ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ በሆድ ውስጥ በሚከማች ስብ አማካኝነት የሚፈጠር ውፍረት ነው። ታዲያ ቦርጭ የሰውነትን ቅርፅ የሚያበላሽና ልብስ ለመልበስም የሚያሳቅቅ በመሆኑ አብዛኛው ሰው ይጠላዋል ማለት ይቻላል። ቦርጭን ለማጥፋት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ከማድረግ አንስቶ የአመጋገብ ሥርዓትን እስከማስተካከል የሚደርሱ መንገዶች አሉ።

በሕክምናና በመድኃኒትም ቦርጭን ማጥፋት እንደሚቻል በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በእኛም ሀገር በሕክምና ዘዴ ቦርጭን እናጠፋለን የሚሉ አልታጡም። በየታክሲውና በየስልክ እንጨት ላይ ማስታወቂያቸውን እስከመለጠፍም ደርሰዋል።

ቦርጭን ከማጥፊያ መንገዶች ውስጥ አንዱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ መሆኑ ይታወቃል። ይሁንና ቦርጭን በዚህ መንገድ ለማጥፋት ያለማቋረጥ በተከታታይ ለበርካታ ጊዜያት ያለማቋረጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን መስራት ይጠይቃል። ለዚሁ አላማ የተመረጡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማከናወንም ያስፈልጋል። በዚህ መልኩም በርካቶች ቁልል ቦርጫውን አስወግደው ሸንቃጣ ለመሆን በቅተዋል።

ከሰሞኑ ኦዲቲ ሴንትራል ያወጣው ዘገባ ደግሞ ቦርጭ በአራት ደቂቃ ብቻ ይጠፋል ይለናል። እንደዘገባው ከሆነ፤ መምህር ሂራጊ የሚል ስያሜን ያተረፈው ጃፓናዊው ግለሰብ በቀን ለአራት ደቂቃዎች ብቻ ከባድ የሆነ ልምምድ በማድረግ በተለይ በእስያ የተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች መነጋገሪያ ሆኗል።

የዚህ መምህር ታሪክ ሰዎችን መሳብ የጀመረው ባለፈው መጋቢት ወር ወፍራም ቦርጩን የሚያሳይ ፎቶውን በቲዊተር ገፁ ከለቀቀ ወዲህ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ቦርጩን በማጥፋት ሰውነቱን በጡንቻ እንደሚገነባ ቃል ገብቶ ነበር። ከአምስት ወር በኋላም ሸንቃጣ ሰውነቱን የሚያሳየውን ፎቶ ምን ያህል መለወጡን በንፅፅር ለማሳየት እንዲረዳው ቀደም ሲል ቦርጫም ሆኖ ከሚያሳየው ፎቶ ጋር በቲዊተር ገፁ ይለቀዋል።

በምስሉ ላይም ቦርጩ ሙሉ በሙሉ ጠፍቶና የእጁና የደረቱ የጡንቻ ቅርፅ ጎልቶ ይታያል። ለዚህም በየቀኑ ለአራት ደቂቃዎች ብቻ በተደጋጋሚ የሚያከናውነውና ለአምስት ወራት የዘለቀው ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሆኑን ተናግሯል።

የበፊቱንና የአሁኑን ተክለሰውነቱን የሚያሳየውን ፎቶ በቲዊተር ገፁ ከለቀቀ ወዲህም በርካታ አስተያየቶችን የተቀበለ ሲሆን፣ ከ10 ሺ በላይ የሚሆኑ የማህበራዊ ድረገፅ ተጠቃሚዎች ሥራውን ወደውለታል። የእርሱን ሥራ በምሳሌነት በመውሰድ ማከናወን ለሚፈልጉ ሰዎችም በዩቲውብ አማካኝነት መልዕክት አስተላልፏል።

በአንደኛው የዩቲውብ ቪዲዮም ሲሰራ የቆየውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አሳይቷል። በአራት ደቂቃ ውስጥ በየቀኑ የሚሰራው እንቅስቃሴ በጂምናዚየም ውስጥ በአንድ ሰዓት ውስጥ ከሚሰራው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እኩል ጥቅም እንዳስገኘለትም ገልጿል።

በዚሁ የአካል ብቃት እንቅስቃሴም 13 ኪሎ ግራም ማቃጠል የቻለ መሆኑንና በሰውነቱ ውስጥ የሚገኘውን የስብ መጠን 18 ነጥብ 2 በመቶ መቀነስ እንደቻለም ተናግሯል። የሰውነቱ ክብደትም በፊት ከነበረበት 72 ኪሎ ግራም ወደ 59 ዝቅ ማለቱን ጠቅሷል። ከዚህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጎን ለጎንም አትክልቶችንና የተጠበሰ ስጋ ሲመገብ እንደቆየም ጠቁሟል። ለዚህ ስኬት ያበቃውም አመጋገቡን ለማስተካከልና የአካል ብቃት እንቅስቃሴውን በየጊዜው ለማድረግ የደረሰበት ቁርጠኛ ውሳኔው መሆኑን ገልጿል።

አዲስ ዘመን  ጳጉሜን 5 /2011

 አስናቀ ፀጋዬ