የፍቺው ጥቁር ጥላ በተወዳጁ ሊግ ላይ

5

 በርካታ እግር ኳስ አፍቃሪያን የዓለማችን ምርጡ ሊግ ሲጠቁሙ ‹‹የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን በማስቀደም የሚስተካከለው የለም›› በማለት ሽንጣቸውን ይዘው ይሞግታሉ። ምንም እንኳን የግል የምርጫ ልዩነት እንደተጠበቀ ቢሆንም አንዱን በመለየት ሂደት በመላው ዓለም የሚገኙ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ በመሳብ፣ አንድም የገቢ ምንጭ አንድም የመዝናኛ አማራጭ ሆኖ ብዙዎችን እያዝናና ስለመሆኑ ምስክር በማቅረብ ሊጉን ከማንኛውም ሊግ ያስበልጡታል።

ባሳለፍነው አመት በአውሮፓ ታላቅ የእግር ኳስ መድረኮች በሻምፒንስ ሊጉና የዮሮፓ ዋንጫም የፍፃሜ ተፋላሚዎች ከእንግሊዝ መሆናቸው ዋቢ በማድረግም ሊጉ የጠንካራ ክለቦች ባለቤትና የአለማችን ምርጡ ስለመሆኑም ያሰምሩበታል።

በተጫዋቾች የአልሸነፍ ባይነት የታጋይነት ስሜት ፈጣን፤ መከላከልንና በአብዛኛው አካላዊ ጥንካሬን መሰረት ያደረገው ሊግ፣ በእያንዳንዱ ውድድር አመት አስቀድሞ ከማይገመቱና በደረጃ ግርጌ ያሉ ክለቦች በደረጃው አናት የሚገኙ ከለቦችን ሲያሸንፉ የሚታይበት መሆኑም የደጋፊዎቹን ቀልብም ለመግዛቱና ዓለምዓቀፍ ትኩረት ለመሳቡ ዋነኛው ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል።

በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የቴሌቪዥን ስርጭት ተደራሽነትና ጨዋታዎች የሚተላለፍበት ሰዓትም ይበልጥ ምቹ መሆንም የብዙዎች ምርጫ እንዲሆንና በርካታ የስፖንሰር አድራጊ ተቋማትን ቀልብ እንዲስብ ስለማድረጉም ይታመናል።

ብሪታኒያ እኤአ በ2016 ‹‹ከአንድነት ይልቅ ልዩነቱ ይበጀኛል›› በሚል በህዝበ ውሳኔ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ለመፋታት ከወሰነች ማግስት አንስቶ ታዲያ የፍቺው አጀንዳ በአገሪቱ እግር ኳስ በተለይ በተወዳጁ ፕሪሚር ሊጉ ውድድር እጣ ፈንታ ላይ ከፍተኛ ስጋትን አጭሯል።

በእርግጥ አገሪቱ ባለፉት ሶስት ዓመታት በብሬግዚት ጣጣ ስትቃወስ ብትቆይም ከህብረቱ የመፋታት ፍላጎትን ግን እንዳቀለለችው አልቀለላትም። በአገሪቱ ታሪክ ሁለተኛ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ቴሪሳ ሜይም የፍቺ አጀንዳ ማስፈፀም አልሆነላቸውም።በጉዳዩ ላይ ከፓርላማ አባላት ጋር ከስምምነት መድረስ ተስኗቸው በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለመልቀቅም ተገደዋል። ስልጣናቸውንም ለሃምሳ አምስት አመቱ ቦሪስ ጆንሰን አስረክበዋል።

የብሬግዚት አቀንቃኙ የቀድሞ የለንደን ከተማ ከንቲባና የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንም የለንደንን ከህብረቱ የመፋታት ውጥን እንደሚያሳኩና የሀገሪቷን አንድነት እንደሚያስጠብቁም ቃል ገብተዋል። ካለስምምነት ከህብረቱ መፋታትን አዋጭ አድርገው የሚመለከቱት ጆንሰን፣ በመጪው የፈረንጆቹ ጥቅምት መጨረሻ አገራቸውን ከህብረቱ ለማፋታት ቆርጠው ተነስተዋል። ጉዳዩንም የሞት ሽረት አድርገው ገፍተውበታል።

 ምንም እንኳን የፍቺውን ፍላጎት የሚደግፉት ቢኖሩም፤ ‹‹ያለምንም ስምምነት ፍቺውን የመፈፀም አደጋ ከባድ ነው፤ ይሕን ለማስቀረትም አማራጮችን መቃኘት ያስፈልጋል›› በሚል ስጋታቸውን የሚያስቀመጡ በርካቶች ሆነዋል። በአለም ኢኮኖሚ እድገት አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠቸውን አገር ኢኮኖሚ በእጅጉ እንደሚጎዳ የሚያሳስቡም አልጠፉም። ገና ከወዲሁ የፓውንድ አቅም መዳከምና ታላላቅ ኩባንዎችም በፍቺው ጣጣ መተማመኛ ማጣታቸውን ሲገልፁ መደምጣቸውም ለዋቢነት ይነሳል።

የብሬዚዳት ቀውስ የአገሪቱን በርካታ ኢንዱስትሪዎች እንደመነካካቱ ተወዳጁ የአለማችን ፕሪሚየር ሊጉም ከሰለባዎቹ መካከል ዋነኛው ስለመሆኑ የሚያስገነዝቡ ባለሙያዎች ቁጥርም ከፍተኛ ነው። በተለይ የፍቺው ቀነ ቀጠሮ እየቀረበ በመጣ ቁጥር ስጋቶችም አብረው ከፍ ሲሉ እየተስተዋለ ይገኛል።

አገሪቱ በመጪው የፈረንጆቹ ጥቅምት መጨረሻ ከህብረቱ ከተፋታች በተወዳጁ የአለማችን ፕሪሚየር ሊግ ላይ ከሚስተዋሉ ጥቁር ጥላዎች መካከል አንዳንዶቹ ከወዲሁ ተገምተዋል።፡

የሊጉ ተሳታፊ ክለቦችና የተጫዋቾች ዝውውር ላይ የሚያደርሰው ጫናም ከሁሉ ቀድሞ ተጠቅሷል። በተለይ ‹‹በሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ ከወገብ በላይ ሆነው የሚያጠናቀቁና በተጫዋቾች ዝውውር ገበያው ቀንደኛ ተዋናይ በመሆን ስኬታማ የሚሏቸውን ተጫዋቾች በማስፈረም የሚታወቁ ክለቦች፣ ከፍቺው በኋላ ፍላጎታቸውን በቀላሉ ለማሳካት ይቸግራቸዋል››ተብሏል።በሰዎች ላይ የሚደረጉ ማናቸውም በነፃነት ተንቀሳቅሶ የመስራት ገደቦችም የክለቦቹ ዋነኛ ፈተና እንደሚሆኑም ተመላክቷል።

ከብሬግዚት በኋላ ማንችስተር ዩናይትድና አርሰናልን የመሳሰሉ ክለቦች ምርጫ የሆኑት የጀርመን፣ ፈረንሳይና ስፔን ተጫዋቾች እንግሊዝ ምድር እግር ኳስን ለመጫወት የስራ ፈቃድ ማግኘትና መስፈርቶችን ማሟላት ግድ እንደሚላቸውም ታውቋል።ይሕም በተጫዋቾች ብቻ የማይወሰንና አሰልጣኖችንም የሚመለከት ይሆናል።

በአለም በኢኮኖሚ እድገት አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠቸው አገር ኢኮኖሚ በእጅጉ ተንገጫግጮ በተለይ የፓውንድ የመግዛት አቅም የሚዳከም ከሆነ ደግሞ ክለቦች የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች ፊርማ ለማግኘት እንዲቸገሩ ማድረጉ አይቀሬ ነው።

የመገበያያ ገንዘቡ አቅም ማጣትን ተከትሎም ተጫዋቾች ልፋታቸውን የሚመጥን አቅም ያለው ገንዘብ አለማግኘታቸውን ታሳቢ በማድረግ በእንግሊዝ ምድር እግር ኳስን ለመጫወት ፍላጎት እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ለመጫወት እንዲወስኑ ለማግባባት ደግሞ የፕሪሚር ሊጉ ክለቦች ተጨማሪ ገንዘብን ለመክፈል ኪሳቸው መግባት ግድ ይሆንባቸዋል።

ተጫዋቾች ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለመምጣትና ለመቆየት ዳተኛ ከሆኑ ደግሞ በአልሸነፍ ባይነት ተጋድሎ በሚታወቁት ክለቦች መካከል የተፎካካሪነት ስሜት እንዲቀንስ በማድረግ የሊጉን ተወዳጅነት ያደበዝዘዋል። ምርጥነቱን ሊያስነጥቀውም ይችላል።

ይሕም በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የቴሌቪዥን ስርጭት ተደራሽነት ምክንያት የሰበሰባቸውን በርካታ የስፖንሰር አድራጊ ተቋማት ቀልብ በማስነፈግ፣ አስተማማኛና ከፍተኛ የገንዘብ አቅሙን በእጅጉ ያዳክመዋል። ዋጋውንም ዝቅ ያደርገዋል።

የብሬግዚት ጣጣ ክለቦች የውጭ አገር ተጫዋቾች ለማስፈረም እንዲቸገሩና ሂደቱንም ውስብስብ በማድረግ በተጓዳኝ የውጭ አገራት ተጫዋቾች ቁጥር ለመቀነስ ሊያስገድዳቸውም ይችላል።መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ እኤአ በ1992 በፕሪሚር ሊጉ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች መካከል 70 በመቶ እንግሊዛውያን ነበሩ።ይሕ አሃዝ እያደር አሽቆልቁሎ ባሳለፍነው ውድድር አመት ከ26 እስከ 27 በመቶ ደርሶም ታይቷል።

የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር (ኤፍ.ኤ) በአንድ ክለብ ከ25 ቡድን አባላት ውስጥ የሚገኙ አገር በቀል ተጫዋቾች ቁጥር ከፍ እንዲል ሲተጋ ቆይቷል።የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦችም 12 አገር በቀል ተጫዋቾችን ማስመዝገብ እንዳለባቸውም በፖሊሲው ያስቀምጣል።

ይሕ ህግ በተቀመጠበት የሊጉ ክለቦች በፍቺው ጥቁር ጥላ ምክንያት እንደቀድሞው የውጭ ተጫዋቾችን በቀላሉ ለማስፈረም ካልቻሉም ወደ አገር በቀል ተጫዋቾ ማተኮሩና ለታዳጊዎች ልማት ትኩረት መስጠታቸው አይቀሬ ነው። ይሕ ደግሞ በሊጉ የሚጫወቱ እንግሊዛውያን ተጫዋቾችን ቁጥር ከፍ እንዲልለት ፍላጎት ላለው ማህበር ዋነኛ ፍላጎት ነው።

አዲሱ የማህበሩ የቴክኒክ ዳይሬክተር ለስ ሪድም የብሬግዚት ጣጣ በርካታ እንግሊዛውያን ተጫዋቾች በተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ የመጫወት እድልን እንደሚሰጥ እምነት አላቸው። በአሁን ወቅት በሊጉ የሚጫወቱ እንግሊዛውያን ተጫዋቾች ቁጥር ከ32 እስከ 34 በመቶ ከፍ ማለቱን የሚጠቁሙት ዳይሬክተሩ፣ ማህበሩ ይሕ አሃዝ ይበልጥ እንዲጎለበት ፍላጎት እንዳለውም ያስምሩበታል።

‹‹ጠንካራ ፕሪሚየር ሊግ ያስፈልገናል፤ ይሕ እንዲሆን የምንፈልገውም ለአገሪቱ እግር ኳስ ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ስለሆነ ነው›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ሊጉ የአለማችን ጠንካራና ምርጡ ሆኖ እንዲቀጥል፣ ሳቢና ማራኪ ከመሆኑ ባሻገር በምጥጥንም የተሻለ እንዲሆን ፍላጎታቸው ስለመሆኑም አፅኖት ሰጥተውታል። ለዚሕ ውጥን እውን መሆን ደግሞ ሊጉ ለወጣት እንግሊዛውያን ተጫዋቾች እድል መስጠቱ ግድ መሆኑን አስ ምረውበታል።

በአሁን ወቅትም ክለቦች ታዳጊዎችን ለማፍራት እየታተሩ ሰለመሆኑና በቼልሲ ክለብ ላይ ለአንድ አመት የተወሰነው የተጫዋቾች ዝውውር ቅጣት በእስታንፎርድ ብሪጅ የነበረውን ባህል በእጅጉ እንደቀረው የሚጠቁሙት ዳይሬክተሩ፣በአሁኑ የፍራንክ ላምፓርድ የቼልሲ ቡድን አባላት ውስጥ ታሚ አብረሃም ማሶን ማውንትን የመሳሰሉ ወጣቶችን መተዋወቃቸውም አንድ ጅምር ሰለመሆኑ ነው ያስገነዘቡት።

በአጠቃላይ በብሬግዚት ጣጣ ክለቦች የውጭ ተጫዋቾችን በቀላሉ ማግኘት ሊያስቸግራቸው ቢችልም፤ በተቃራኒው ትኩረታቸውን ወደ አገርው ውስጥ እንዲመልሱ ስለሚያደርጋቸው በርካታ እንግሊዛውያን ተጫዋቾች በሊግ የመጫወት እድልን እንደሚያገኙም ተማምነዋል።

በርካታ የእግር ኳስ ሳይንስ ባለሙያዎች በአንፃሩ በአገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ የሚካሄድ ሊግን መናፈቅ አግባብ አለመሆኑንና ለተወዳጁ ሊግ ተወዳጅ ሆኖ መዘልቅ አዋጭ አለመሆኑን አስገንዝበዋል።የሊጉ አስተዳዳሪ አካላትም ከዚህ የተሳሳተ እሳቤ መውጣት እንዳለባቸው አፅኖት ሰጥተውታል።

ምንም እንኳን በአሁን ወቅት የብሬግዚት አጀንዳ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ከፊት ቢደቀኑበትን በርካቶች ግን ከወዲሁ ከፍቺው በኋላ የሚሆነው አስግቷቸዋል። ተወዳጁ የአለማችን ሊግም ዕጣ ፈንታውን የሚወስንለት የፍቺው ቀነ ቀጠሮ እስኪደርስ ተወዳጅ ሆኖ ይዘልቃል።

አዲስ ዘመን  ጳጉሜን 5 /2011

 ታምራት ተስፋዬ