የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የግብርና ምርቶች በሸማች ማህበራት መቅረባቸው ተገለጸ

16

አዲስ አበባ፦ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የፌዴራል ህብረት ሥራ ማህበር ከግብርና ህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመቀናጀት የተለያየ የግብርና ምርት ውጤቶችን ማቅረቡን ገለጸ፡፡

የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በትናንትናው ዕለት በሰጡት ጋዜጣ መግለጫ በከተማዋ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ኤጀንሲው በክልሎች ካሉ አምራች ህብረት ሥራ ማህበራት ጋር ቀጥተኛ የገበያ ትስስር በመፍጠር ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የግብርና ምርቶች በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አረጋ በበኩላቸው ሸማቹ ህብረተሰብ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ባሉ 143 የሸማች ማህበራት በኩል የቀረቡትን የግብርና ምርቶች በመጠቀም ከአላስፈላጊ ወጪ መዳን ይችላል ብለዋል፡፡

በማህበራቱም የአትክልት ውጤቶች፣ ጤፍ፣ የስንዴ ዱቄት፣ የእርድ እንስሳት፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ቅቤና አይብ በተመጣጣኝ ዋጋ የቀረቡ ሲሆን ወደ ማህበራቱ በመሄድ መሸመት እንደሚቻል አቶ ሲሳይ አስታውቀዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 እፎይታ የሸማች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት መንግሥቱ እንደተናገሩት፣ ለሸማቹ ማህበረሰብ በዓሉን አስመልክቶ የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ የቀረቡ በመሆኑ ህብረተሰቡ እንዲጠቀምባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንደ አቶ ጌትነት ገለፃ አሁን በከተማዋ ያለውን የዋጋ ንረት ከማረጋጋት አንፃር በሸማች ማህበራት በኩል ዘይት፣ ዱቄት፣ፓስታ፣ ማካሮኒ እና ሌሎችም ምርቶች በመቅረባቸው ሸማቹ ከማይገባ ወጪ እየታደጉት ነው ብለዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሸማቶች ማህበር ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሙሉ ነጋሽ እንደተናገሩት፣ በዓሉን አስመልክቶ በሸማች ማህበራት የአትክልት ውጤቶች በስፋት መቅረባቸውንና ይህ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ደርቤ ተሾመ እንዳሉት ሸማች ማህበራት የጀመሩት ገበያን የማረጋገት ተግባር የሚበረታታ በመሆኑ በቀጣይም በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ደርቤ እንዳሉት ሌሎች ነጋዴዎች ጋር 190 ብር የሚሸጠው አምስት ሊትር ዘይት ከሸማች ማህበራት 128 ብር እየተገዛ ነው፤ ጤፍም በኪሎ የአስር ብር ልዩነት አለው ይህን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተረድቶት ወደ ማህበራቱ እየመጣ ቢገበያዩ አትራፊ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ኤጀንሲ በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ባህል ማዕከል ውስጥ የግብርና ውጤቶች አውደ ርዕይ (ባዛር) ከፍቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያደረሰ እንዳለም በመግለጫው ላይ ተገልጿል፡፡

አዲስ ዘመን ጳጉሜ 6/2011

ሃይማኖት ከበደ