ብሔራዊ አንድነት በፖለቲካ ፓርቲዎች ዕይታ

81

በኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ቢኖርም በሕዝብ ስምምነት የተፈጠረ ብሔራዊ አንድነት አለመኖሩን አንዳንድ የፖለቲካ አባላት ገለፁ። ገዥዎች የፈጠሩት እንጂ ሕዝቦች ተመካክረው በስምምነት ያመጡት አስተዳደራዊ መዋቅር እንደሌለም ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጀላ መርዳሳ፤ ‹‹ኢትዮጵያ እንደአገር የተመሰረተችው ቅርብ ጊዜ ነው። ከተመሰረተች በኋላ የግዛት አንድነት ቢኖርም በሕዝብ ስምምነት የተፈጠረ ብሔራዊ አንድነት የለም። ሕዝቦች ተመካክረው በስምምነት ያመጡት አስተዳደራዊ መዋቅርም የለም። ገዥዎች ለራሳቸው እንዲመቻቸው ያደረጉት ነው›› ብለዋል።

እንደ አቶ ቀጀላ ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ለሕዝብ በጉርብትናና በአንድነት አብሮ መኖር እንጂ በመዋቅር ደረጃ ብሔራዊ አገራዊ አንድነት የለም። በ1983 ዓ.ም ሕዝቦች ቁጭ ብለው በመወያየት ብሔራዊ አንድነት ለማምጣት ሞክረዋል። ሆኖም የተሟላ አልሆነም። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አልተፈጠረም። ኢኮኖሚውና ፖለቲካው በአንድ ቡድን እጅ የወደቀ ነበር።

አቶ ቀጀላ አገራዊ አንድነት ለማምጣት በሕዝቦች መካከል እኩልነት መስፈን እንዳለበት፤ ዴሞክራሲ ሥርዓት መፈጠርና የብሔረሰቦች መብት መከበር እንደሚኖርበት፤ ይህ ከሆነ አብሮ መኖር እንደማያስቸግር፤ ይህን ማድረግ የእያንዳንዱ ብሔረሰብና ዜጋ ኃላፊነት እንደሆነ፤ አንድነት እንዲመጣም የዜጎች ኃላፊነት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

‹‹ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ የአንድ ቡድን አስተሳሰብ አይሰራም፤ አገሪቱን ይበትናል፤ ሁሉም ሰላምን፣ ነፃነትና አንድነትን ማዕከል በማድረግ የአገሪቱን አንድነት መስመር ማስያዝ ይገባል። ይህን ለማድረግም ተስፋው በሕዝብ እጅ ነው››ሲሉም አክለው ይናገራሉ።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት እንደሌለ፤ በታሪክ አረዳድ፣ በትርክቶች፣ በብሔራዊ ጀግኖችና በምልክቶች መግባባት ላይ እንዳልተደረሰ፤ ለዚህ ትልቁ ችግርም ያልተስተካከለ የታሪክ ምልከታና ብያኔ መሆኑን ያስረዳሉ።

እንደ ዶክተር ደሳለኝ ማብራሪያ፤ ሕዝቦች ለዘመናት አብረው አንፀባራቂ ድሎችን አስመዝግባዋል። በግንኙነታቸው ውስጥም መልካምም መጥፎም ገጠመኞችም ነበሯቸው። ከ1960ዎቹ ወዲህ የተፈጠሩ ብሔረተኞች የችግሮቹ መንስዔና በዳይ አድርገው ጨቋኝ ተጨቋኝ በማለት የተሳሳተ የታሪክ ብያኔ ይሰጣሉ። ይህ በስህተት ላይ የተመሰረት ብያኔ አገራዊ መግባባት እንዳይፈጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ዶክተር ደሳለኝ ‹‹አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር የታሪክን አረዳድ ማስተካከል። በአገሪቱ የተፈጠረው ልማትም ሆነ ጥፋት የሁሉም ሕዝቦች የጋራ አድርጎ መውሰድ ይገባል። በውሸት ላይ የተመሰረቱና የተመረጡ የታሪክ ንባቦችን ማረም። ፖለቲከኞች ባለፈ ታሪክ ከመነታረክ ወጥተን ለልጆቻችን መልካም አገር ለማውረስ የቀጣይ የ50 ዓመታት የጋራ ርዕይ በማስቀመጥ ወደ ሥራ መግባት አለብን፤ ታሪክን ለፖለቲካ መሣሪያና ትርፍ ከመጠቀም መቆጠብ ያስፈልጋል›› ብለዋል።

ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ባለድርሻዎች አሉ። የፖለቲካ ኃይሎች ግን ያለፈ ታሪክ ላይ ከመነታረክ ወጥተን የኢትዮጵያ መጽዒ ዕድል ላይ በጋራ መፍትሄ መፈለግ አለብን ያሉት ዶክተር ደሳለኝ፤መንግሥት፣ የታሪክ ምሁራንና የማህበረሰብ አንቂዎች የተሳሳቱትን አካሄዶች ማስተካከል ላይ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ‹‹በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት የለም። የዚህ መንስዔ ሊሂቃኑ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ጥያቄ ቢያነሱም ወደ ብሔራዊ መግባባት አልደረሱም። አገርን የሚመሩ ድርጅቶችና ተቀናቃኝ ኃይሎች ብሔራዊ መግባባት ላይ አልደረሱም። ልሂቃኑ ህልማችውን ይዘው ፍጅትና ግጭት በመፍጠር ከመቆዘም ያለፈ ራሳቸውን ለውጠው ሕዝብን በመለወጥ ብሔራዊ መግባባት ማምጣት አለመቻላቸው ዋና ምክንያት ሆኗል›› ይላሉ።

እንደ ፕሮፌሰር መረራ ገለፃ፤ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሁሉም የቤት ሥራውን መስራት አለበት፤ በቀዳሚነት አገርን የሚመሩ አካላት ሕዝብን በማቀራረብ ብሔራዊ አንድነት መፍጠር አለባቸው፤ ከሴራ ፖለቲካ መውጣትና የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ይኖርባቸዋል፤ ተቀዋሚዎችም ቢሆኑ ህልማቸውን እያስታመሙ አገሪቱን ከመበጥበጥ የሰከነ ፖለቲካ በማራመድ በደረጃ የቤት ሥራቸውን መስራት አለባቸው፤ ዳር ቆሞ ፖለቲካውን እየቆሰቆሱ አገርን ከመጉዳት ወደ ሀቀኛ የፖለቲካ ድርድር መግባት አለባቸው፤ ዳር ቆሞ እያራገቡ ሕዝቡን ለግጭት ከመዳረግ መቆጠብ አለባቸው፤ ሁላችንም ኃላፊነት መወጣት አለብን፤ ከፖለቲካ ውጪ ያሉ ልሂቃንም ሕዝቡን የማስተባበር፣ የማንቃት፣ የማደራደር ሥራ መስራት አለባቸው፤ ለሥልጣን ብሎ አገሪቱን ከመተብተብ ከችግር ለማውጣት በመስራት አገራዊ መግባባትን መፍጠር ይገባል።

የአፋር ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ሊቀመንበር መሀሙድ ጋአስ፤ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ጽንፍ የወጡ አካሄዶች መታረም እንዳለባቸው፤ ጽንፈኝነት ለማንም እንደማያዋጣ፤ በተለያዩ ጽንፍ ያሉ አካላት ሰጥቶ በመቀበል መርህ ወደ መሀል በመምጣት ብሔራዊ አንድነት መፍጠር እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

ሊቀ መንበሩ ‹‹ጽንፍ የወጡ አስተሳሰቦችን ለማለዘብ ሕገ መንግሥቱን፣ ህብረ ብሔራዊነትንና የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የሚያከብሩ አካላት ወደ አንድ መምጣት አለባቸው፤ የአገሪቱን መጻዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግም በጋራ መስራት ያስፈልጋል›› ብለዋል።

አዲስ ዘመን ጳጉሜ 6/2011

አጎናፍር ገዛኸኝ