የሳቅ ዘመን ይሁንልን !

19

 እናስቃለን ባዮች ሰው እያሳቀቁ ቀልድ ከሳቅ ምንጭነት ተራ ንግግር ወደ መሆን ተሸጋግሯል። እንዲያውም ሳቅ ከተነገረው ነገር ይልቅ ከተናጋሪው ጋር መያያዝ ጀምሯል። መሪ፣ አለቃ፣ አከራይ፣ አበዳሪ … “ቀልድ ነው” ብሎ በተናገረው ነገር በደንብ ይሳቃል። አብዛኞቹን የዘመናችንን “ቀልደኞች” ቀልደኛ የሚያ ሰኛቸው በቅጡ መቀለድ ሳይችሉ የቀልደኞች ማህበር ማቋቋማቸው ነው። ደግሞ ታዳሚዎቻቸው እያማጡ ሳል መሰል ሳቅ የሚስቁት “ቀልዶቻቸው” ባለማሳቃቸው መሆኑን ለማመን አይፈልጉም። “ምነው ረጃጅም የጋራ ሳቆች ከሳቅ መድረኮች ጠፉ?” ተብለው ሲጠየቁ “ለመሳቅ ተዘጋጅቶ የመጣን ሰው ማሳቅ ከባድ ነው” የሚል የመከላከያ ሀሳብ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ። ራሱን በመዝናናት መንፈስ ውስጥ አኑሮ ጊዜ ገዝቶ ለመሳቅ የተገኘ ታዳሚን ማሳቅ ምጥ ከሆነባቸው ኑሮን ለማሸነፍ ላይ ታች ሲል የሚውለውን ባተሌማ ማስለቀስ ነው የሚቀላቸው።

ሰው እኮ ለመሳቅ አንዳች ኮርኳሪ ነገር ይፈልጋል። ያልተኮረኮረ አይስቅማ! በእውቀቱ ስዩም እንዳለው በዚህ ዘመን ያለምክንያት መሳቅ የሚችለው ብቸኛው የሰው ፍጡር “የዓለም የሳቅ ንጉስ” እየተባለ የሚጠራው በላቸው ግርማ ነው። ይህ ሰው ከሦስት ሰዓት ተኩል በላይ መሳቁ ሳይበቃው በአፍሪካ ብቸኛ የሆነውን የሳቅ ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ ለመክፈት በቅቷል። ለራሱም ሆነ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን እንግዳ በሆነ መስክ የሥራ ዕድል በመፍጠሩ አድናቂው ነኝ። ግን ሰው እንዴት ያለምክንያት ይንከተከታል? እርግጥ ነው ዓለም አቀፍ እውቅናና ዳጎስ ያለ የሽልማት ገንዘብ ማግኘት ወፍራም ምክንያት ነው። በበኩሌ ግለሰቡን እንደ “የሳቅ ንጉስ” ከማየት ይልቅ የጉልበት ሠራተኛ አድርጎ መቁጠር ይቀለኛል። የ80 ኪሎ ሜትር የምጥ ሳቅ የፊት ጡንቻዎችን ያዳብር እንደሆን እንጂ አእምሯዊ ምቾት የሚሰጥ አይመስለኝም።

በአንድ ወቅት እንስሳት ሁሉ ትልቅ ጫካ ውስጥ በጠዋት ስብሰባ ተቀምጠው ሳለ ቆይታቸው አሰልቺ እንዳይሆን የሚያኝኩት ነገር ስላስፈለገ ገዝቶ የሚመጣ አንድ እንስሳ መላክ አስፈለገ። በዚህ ጊዜ ሁሉም ለመሄድ ስለሰነፉ ኤሊ ገዝታ እንድትመጣ በአብላጫ ድምጽ ወሰኑ። ኤሊ ውሳኔውን ተቀብላ ጉዞ ስትጀምር የተቀሩት እንስሳት በየተራ ሀሳብ እየሰጡ ስብሰባው ቀጠለ። ቀኑ እየተጋመሰ ሲመጣ እንስሳቱ የሚያኝኩት ነገር ባለመምጣቱ ማማረር ጀመሩ። አንዳንዶችም “ቀድሞውንም ይህች ቀርፋፋ መላክ አልነበረባትም” እያሉ ኤሊን መራገም ያዙ። በዚህ ጊዜ ኤሊ “እንዲያውም አልሄድም” አለች። የዘመናችንን “ቀልደኞች”ንም መውቀስ ልክ ሲቀልዱ እንደኖሩ ሁሉ “እንዲያውም አንቀልድም” ብለው እንዲቀልዱ በር መክፈት ነው።

በርግጥ አንዳንድ መሻሻሎች አሉ። የስታንዳፕ ኮሜዲን ምንነት ሳይረዱ መድረክ ላይ ወጥተው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በጎደለው መንገድ የግለሰቦችን ገበና አደባባይ ላይ ያሰጡ ዘርጣጮችን ተመልክተን አንገታችንን የደፋንበት ጊዜ ነበር። ዛሬ የህብረተሰቡን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጎዳዮችን የሚዳስሱ አዝናኝና አስተማሪ የስታንዳፕ ኮሜዲ ትዕይንቶችን ማየታችን ይበል የሚያሰኝ ነው።

አባቶች “በራስ መቀለድ ጨዋነት፤ በእንስሳትና ግዑዝ ነገሮች (በአሊጎሪ ዘይቤ) መቀለድ ደግሞ ብስለት ነው” ይላሉ። ከአባባላቸው ተነስቼ ቀደም ባለው ጊዜ ስለቀልድ እንዴት ዓይነት ግንዛቤ እንደነበር የማወቅ ጉጉት አድሮብኝ መጽሐፍትን ሳገላብጥ ማህተመ ስላሴ ወልደመስቀል በ1961 ዓ.ም “ባለን እንወቅበት” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ ቧልት ብለው የሚጠሩትን ቀልድ አስመልክተው የከተቡትን አገኘሁ። እንዲህ ይነበባል፡-

“እንደ አሽሙር፣ አግቦ፣ ሽሙጥ፣ ፌዝ፣ ሾርኔ ፣ ተረብ ፣ቀልድና ዋዛ የመሳሰሉት ሁሉ ቧልት ይባላሉ። እነዚህም በንግግር በሰላምታና በጨዋታ ሰዓት በአንድ ሰው ላይ ሲሰነዘሩ እንደ ፍላጻ ልብን የሚወጉ ቃላት ናቸው። ነገር ግን ትርጉማቸው ለማንም ሰው በቀላሉ ቶሎ የሚገባ አይደለም። ሁልጊዜ ሁለትና ሦስት ፍቺዎች ስለሚገኙባቸው ተራው ሕዝብ የሚረዳው መጋረጃ ሆኖ ጎልቶ የሚገኘውን ሰም የምንለውን ድብቅ ያልሆነውን ክፍል ብቻ ነው። … እንደ እነ አለቃ ገብረሃና፣ አለቃ መልካሜ፣ መምህር እዝራ ፣ ዐራት ዓይና ጎሹ ፣ ነጋአድራስ ተሰማ እሸቴ … ከመሳሰሉት የአማርኛ ባለቤቶች ጋር በነገር ለመቋቋም በጣም ከባድና አስቸጋሪ እንደነበር ያውቋቸው የነበሩ ይናገራሉ። ተናጋሪው ምንም እንኳን ቀናውን መንገድ የተከተለ ቢሆንም ከሚሰሙትም ሆነ ከአንደበታቸው ከሚፈልቀው ነገር ሁልጊዜ እጥፍና አሻሚ ሆነው ድርብ ትርጉም የሚሰጡ ቃላትን ለማግኘትና ለማሰማት የተለየ ችሎታ ነበራቸው። … እንደ ዘበት ጣል አድርገው የሚያልፉት ቃል ልብ አድርጎ ለሚሰማውና ውስጡን ለሚመረምረው ሰው ውስጠ ወይራ የሆነ ዘለፋ ወይም ምስጋና ይዞ ይገኛል። ደረቅ ስድብ ነው ለማለት ግን አይቻልም፤ በነገር የተጎነጠው ሰው የተዘለፈ ቢሆንም ቅሉ ለመከራከር አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይወድቃል። አንደኛውን ትርጉም ይዞ እንዲህ ተባልኩ ቢል፣ አይደለም እኔ እንዲህ ነው ያልሁት ብሎ በሁለተኛው ፍቺ ሊያሸንፈው ይችላል። ”

ጽሑፉ በዘመኑ ይነገሩ የነበሩ ቀልዶች ትኩረታቸውን የቃላት ጨዋታ ላይ ያደረጉ ውስጠ ወይራዎች እንደነበሩ ያሳያል። አልፎ አልፎም ቢሆን አሁንም እንዲህ ያሉ ሳቅ የሚያጭሩ ቀልዶችን እንሰማለን። በጣት የሚቆጠሩ ቢሆንም እውነተኛ ሳቅ ደጋሽ ኮሜዲያን አሉን። በቀልዶቻቸው ዘዋሪነት ውጥረት በመላ በት በእኛው አኗኗር ላይ ለአፍታም ቢሆን ሳናምጥ እንድንፈግግ ምክንያት እየሆኑን ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት ሰሞኑን ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው በየዓመቱ ስምንት መቶ ሺ ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ። ጥናቶች እንደሚ ያረጋግጡት ሰዎች በራሳቸው ላይ መሰል እርምጃዎችን የሚወስዱት ከልክ ባለፈ ጭንቀት ምክንያት ነው። ሳቅ ደግሞ ጭንቀትን ይቀንሳል። የሳቅ ዘመን ይሁንልን !

አዲስ ዘመን ጳጉሜ 6/2011

 የትናየት ፈሩ