ዕንቁ – ለጣጣሽ/ ዕንቁጣጣሽ!

12

ለኢትዮጵያውያን የዘመንን መቀየር አብሳሪው ዐውደ-ዓመት ዕንቁጣጣሽ፤ የቀኖች ሁሉ ደማቁ፣ የደስታ ቀኖች ሁሉ ታላቁ ሆኖ፤ የዘመን ሽግግር “አንደኛ ቀን” ሆነ። የሰው ልጅ የዘመን ሽግግር ፍላጎት፣ የሰለቸን የማደስ ሰበብ፣ እና ተፈጥሯዊ ሂደት፤ “ዐውደ-ዓመት” ነው፡፡ ይሁን እንጂ፤ ‘ዘመን’ ዕለቱ ስለተቆጠረ ብቻ አይሻገርም። 365 ቀናት በውስጡ ስላለፉ ብቻ ‘ዘመን’ አይቀየርም። ዘመኑ ዕለቱን ጠብቆ ሲቀየር “የዙር ዑደቱን መሠረት አድርጎ በቀመር ተቀየረ” ይባል ይሆናል እንጂ፤ በሰው ሃሳብ ውስጥ ያለው የዘመን ዑደት ሽግግር አደረገ ለማለት ግን ሌላ አጽዳቂ ይፈልጋል፡፡

ዘመን መቀየሩን ለሰው አእምሮ የሚያበስረው የተፈጥሮና የባህል አጀብ በሌለበት፤ “አዲስ” የተባለው ቀን ብቻውን “አንደኛ ቀን” ሆኖ አይደምቅም፡፡ ይህንን ዕለት የሚያስናፍቅ ሽር-ጉድ፣ ይህንን ቀን “ደረሰ”… “ደረሰ”… የሚያሰኝ የሚያውድ መዓዛ፣ የሚደልቅ ከበሮ፣ “ቀን ተቆጠረ 365 ዕለት ሞላ” ከሚለው ስሌት ጋር፤ ስሌቱን “እውነት ነው” ብሎ የሚያረጋግጥ የተፈጥሮ አጽድቆት ይፈልጋል፡፡ ዐደይ ብቅ የምትለው እዚህ ጋር ነው፡፡ የመስከረም ፀሐይ መውጣት የሰበሰበው የሰው ትርምስ፣ ለበዓል ዝግጅት፣ የሚትጎለጎለው ጭስ፤ የተፈጥሮንና የሰውን የሃሳብ ስሌት ስምምነት ያመለክታል፡፡

እንደ “ዕንቁጣጣሽ” በተፈጥሮ ምስክርነት ዐውደ ዓመት መሆኑን ያስመሰከረ የዘመን መለወጫ ዕለት በዓለም የተለያዩ አቆጣጠሮች ውስጥ መኖሩ ያጠራጥራል። ‘ዐደይ’ በበጋም በክረምትም ያልታየ የጠፋ ሥሯ ብቅ የሚለው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ‘የመስቀል ወፍ’ የላባውን ጌጥ አድምቆ ለመውጣት ከዚህ ጊዜ ውጪ የሚጠብቀው ሌላ ጊዜ ያለው አይመስልም፡፡

“ዘመን አለፈና ዘመን ተለወጠ፣

ደመናው ተሸኘ ሰማዩ ገለጠ፣

ምድራችን ባበባ በልምላሜ አጌጠ፤

እንዲህ ተንቆጥቁጦ የሚታየው መሬት፣

ራቁቱን ነበር በጋ ልብሱን ገፎት፤

አምላክ ግምጃ ቤቱን ከፈተለትና፣

አማርጦ ለበሰ አገኘ ቁንጅና፤”

(በጸሐፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ እና በሊቁ ያሬድ ገብረ ሚካኤል፤ ለንጉሠ ነገሥቱ ከተበረከተ ግጥም የተወሰደ የዘመን መወድስ፡፡)

አበባ’የሽ ወይ?

የባሕላችንን ወግ ጥቂት ከመረመርነው፤ ወላጆች፣ ልጃገረዶች ልጆቻቸውን ካለምንም ምክንያት በየሰዉ ደጃፍ እየቆሙ እንዲታዩ፣ በዚህ ዕለት የፈቀዱበት ምክንያት ምን ይሆን? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ትልቅ ሃሳብ ወደ አእምሯችን ይመጣል፡፡ አንዳች መንፈሳዊ ወይም ባሕላዊ ስምምነት ይህንን ፈቃድ እንዲሰጡ ካላስገደዳቸው በስተቀር፤ ልጆቻቸው በየመንደሩ እንዲዞሩ ሊፈቅዱ አይችሉም፡፡ አለቃ ነቢየ ልዑል ዮሐንስ፤ “የታሪከ-ነገሥትን” እና “የክብረ ነገሥትን” የታሪክ ጭብጥ ይዘው ስለ ልጃገረዶቹ ጨዋታ ምክንያት ሲያብራሩ፤

“ንግሥቲቱ ሳባ ወደ ንጉስ ሰሎሞን ዘንድ ስትሄድ፤ አምስት መቶ ደናግል ተከትለዋት ነበር።” ይላሉ። “የእልፍኝ አሽከሮቹም እነርሱው (ልጃገረዶቹ) ሲሆኑ፤ የአበባው (የዕንቁጣጣሽ) አሰጣጡም በእነዚሁ ልጃገረዶች ለንግስቲቱ ክብር የተደረገ ነው፡፡” ሲሉ ያመሰጥሩታል፡፡

በመሆኑም ዛሬ ልጃገረዶቹ፣ በየሀገሩ በተለይም በሰሜናዊው የኢትዮጵያ ባሕል ውስጥ ዐደይ አበባ ቀጥፈው እንግጫ ነቅለው፣ በተለያዩ ጌጣጌጦች ተሸልመው፣ በየዓመቱ የሚቀርቡት፤ ይህንን የሳባ ዘመን ‹‹ሥርዓተ-ደናግል›› ወግ አድርገው ነው ማለት ነው፤ እንደ ሊቁ አተራረክ፡፡

ዕንቁጣጣሽ የሚለው የበዓሉ ሥያሜም፣ ልጆቹ ከሚይዙት “ዕንቁጣጣሽ” ወይም “ግጫ” ከተሰኘው ሣር የወጣ ሥያሜ ነው፡፡ አለቃ ነቢየ ልዑል ዮሐንስ፤ በብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ላይ በወጣው ቀደም ሲል በተጠቀሰው ጽሑፋቸው፤ ስለ ልጃገረዶቹ ጨዋታ ሰበብና ስለ ዕንቁጣጣሽ ትርጉም በሰጡት ትንታኔ ላይ እስከ ዛሬ የሚታመንበትን “ዕንቁጣጣሽ” የሚለውን ቃል ተለምዷዊ ትርጓሜ ጠንከር አድርገው ይሞግታሉ፡፡

“አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት፤ ‘ዕንቁጣጣሽ’ ማለት፤ ንግሥተ-ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም በሄደች ጊዜ ሰሎሞን ‘ለችግርሽ’ ወይም ‘ለጣጣሽ ይሁንሽ’ ብሎ ዕንቁ ስለሰጣት በጊዜ ብዛት ‘ዕንቁ-ጣጣሽ’ ወደሚል ሥያሜ እንዲመጣ ሆኗል ወይም ‘ዕንቁጣጣሽ’ ተብሏል፤ ይላሉ። ይህም ግን አከራካሪ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም፤ ሰሎሞን የሚናገረው በዕብራይስጥ፣ ሳባ ወይም ንግሥተ-አዜብ የምትናገረው ደግሞ በሳባ ቋንቋ በመሆኑ፤ ‘ዕንቁ’ የሚባለው ቃል በዕብራይስጥ ቢኖርም፤ ‘ጣጣሽ’ የሚለው ቃል ግን በአማርኛ እንጂ በሌላ ስለሌለ ነገሩን ልክ ሊያደርገው የሚችል አይመስልም፤” ይላሉ፡፡

የምክንያታቸው ሚዛን የሚያጋድለው “ዕንቁጣጣሽ” የሚለው ሥያሜ፣ ልጃገረዶቹ ከሚይዙት “ዕንቁጣጣሽ” ከተሰኘው ቄጠማ መሰል ሣር መገኘቱን ወደ ማጽናቱ ይመስላል፡፡ ይህንን ቄጠማ በየሰዉ ደጃፍ እየቆሙ መስጠታቸውና ዕንቁጣጣሽ ማለታቸው፤ ትልቅ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ሲሆን፤ በኖኅ ርግብ አምሳያ እንዲታሰቡ አድርጓቸዋል፡፡ የያዙት መልዕክት “የደስታ ብስራት” መሆኑ፣ ለኖኅ የጥፋትን ውሃ መጉደል ካበሰረችው ርግብ ጋር ተምሳሌታዊ ትስስር እንዳለው የሚተርኩ የሊቃውንት ትርጓሜዎችም አሉ፡፡ ልጃገረዶቹ ይህንን የመሰለ ታላቅ ሃይማኖታዊ ተምሳሌት ወክለው መቆማቸውን አወቁትም፤ አላወቁትም፡፡ የሥርዓተ ባሕሉን ተምሳሌታዊ ወግ የሚተነትነው የሊቃውንቱ ተዋስዖ ግን፤ ይህንን እና ሌሎች ብዙ ሃይማኖታዊነታቸው የሚያመዝኑ አንድምታዎችን ያስቀምጡላቸዋል፡፡

መስከረም

ዶ/ር ሀብተማርያም አሰፋ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባሕሎች›› በሚሉት መጽሐፋቸው መስከረምን እንዲህ ገልጸዋታል፡፡

መስከረም ‹‹ምስ-ከረም›› ከከረመ በኋላ ወይም ክረምት ካለፈ በኋላ ማለት ነው፡፡ የመስከረም ወር ዝናብ የሚቆምበት ፀሐይ የምትወጣበት የወንዞች ንጹሕ ውሃ ጽሩይ ማይ የሚጎርፍበት፣ አፍላጋት የሚመነጩበት፣ አዝርዕት ማለት የተዘሩት አድገው ማሸት የሚጀምሩበት፣ ሜዳዎችና ተራራዎች ሸለቆዎችም በአበባ የሚያሸበርቁበትና የሚያቆጠቆጡበት ነው ይሉታል፡፡

እንዲህም በመሆኑ የጨለማ የችግርና የአፀባ ጊዜ የሚያበቃበት የብርሃን፣ የደስታ የእሸት፣ የፍሬና የጥጋብ ጊዜ የሚጀምርበትና የሚተካበት ነው ብሎ ሕዝቡ ስለሚያምንበትም የዕንቁጣጣሽ በዓልን ከሁሉ አብልጦ ግምት ስለሚሰጠው በእሳት ብርሃንና በእሳት ቡራኬ በየቤቱ እንደ ሁኔታው እንስሳ አርዶ፣ ደም አፍስሶ ይቀበለዋል፡፡ ያከብረዋል ሲሉም አክለውበታል፡፡

በወርኃ መስከረም መሬቷ በአደይ አበባ አሸብርቃ ስለምትታይና በተለይም ዕንቁ የመሰለ አበባ ስለምታወጣ መሬቷን ዕንቁጣጣሽ፣ ዕንቁ የመሰለ አበባ አስገኘሽ ለማለት ዕንቁጣጣሽ መባሏን የቅርስ ባለሙያው መምህር ዓለሙ ኃይሌ ይገልጻሉ፡፡ አያይዘው አቧራ፣ ቡላ የነበረው መሬት በዝናቡ ኃይል ለምልሞ ተመልከቱኝ፣ ተመልከቱኝ የምትል ያሸበረቀች፣ በአበባ የተንቆጠቆጠች ሆነች የሚል ለዕንቁጣጣሽ ስያሜ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡

መስከረም አንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያጠመቀው የቅዱስ ዮሐንስ መታሰቢያ ዕለትም ነው፡፡ መስከረም ሁለት ደግሞ ይህ አባት አንገቱን የተቆረጠበት ቀን ነው፡፡

በገሊላ ሀገር የነገሠ ሄሮድስ የሚባል ሰው ነበር፡፡ እርሱም የወንድሙን የፊልጶስ ሚስት ሄሮድያዳን ስላገባ ቅዱስ ዮሐንስ ሳይፈራ ንጉሡን «የወንድምህን ሚስት ልታገባት አልተፈቀደልህም» ብሎ ይነግረው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ንጉሡ ተቆጥቶ ዮሐንስን አስሮት ነበር፡፡ ሊገድለውም ፈልጐ ሕዝቡ ዮሐንስን በጣም ስለሚወዱት እነርሱን ፈርቶ ተወው፡፡

አንድ ቀን የሄሮድስ የልደቱ ቀን በሆነ ጊዜ ታላቅ ድግስ ተደግሶ እንግዶች ተጋባዦች ተሰብስበው ሲበሉና ሲጠጡ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ገብታ ለንጉሡ ዘፈነችለት ደስም አሰኘችው፡፡ ስለዚህ የምትለምነውን ሁሉ ሊሰጣት ማለላት፡፡ እርሷም እናቷን አማክራ የመጥምቁ የዮሐንስን ራስ አሁን በሰሀን ስጠኝ አለችው፡፡ ንጉሡም ወታደሮቹን ልኮ በእስር ቤት ሳለ የዮሐንስን ራስ አስቆረጠው፡፡ ራሱንም በሰሀን አምጥተው ለዚያች ልጅ ሰጡአት እርሷም ወስዳ ለእናቷ ሰጠቻት። እግዚአብሔርም ለቅዱስ ዮሐንስ አንገት ክንፍ ሰጣት እየበረረችም ለ15 ዓመት አስተማረች፡፡

እንግጫ

እንግጫ የሣር ዓይነት ነው፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ልጃገረዶች መስክ ወርደው የሚነቅሉት ነው። የዕንቁጣጣሽ ብሥራት ነጋሪ ነው፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባሳተመው ‹‹በሰሜን ሸዋ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች የተመዘገቡ የማይዳሰሱ (ኢንታጀብል) ባህላዊ ቅርሶች›› መድብል ላይ ስለ እንግጫ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡

በዘመን መለወጫ ዋዜማ እንግጫ ሳር በልጆች እየተነቀለ ‹‹እንደቋጨራ›› እየተጎነጎነ ጣራ ላይ ተወርውሮ ያድርና ጠዋት ላይ ለዘመን መለወጫ እየተጎነጎነ ራስ ላይ፣ ቡሃቃ አንገት ላይና ሌማት ክዳን ላይ ይታሰራል፡፡ ቡሃቃ እና ሌማት ላይ የመታሰሩ ምልክትነት ለረድኤትና ለበረከት ሲባል የሚደረግ ነው፡፡

ራስ ላይ የታሰረው ደግሞ ለመስቀል በዓል ተቀምጦ ይቆይና ደመራው ላይ ይታሰርና እንዲቃጠል ይደረጋል፡፡ ለራስ ምታትና ለጤንነት ሲባል በማኅበረሰቡ የሚከወን ነው፡፡ እንግጫ ነቀላ ዘመን ሲለወጥ የሚከወን ባህላዊ ሥርዓት ነው፡፡ በዋዜማው ያላገቡ ሴቶች ወደ መስክ ወርደው እንግጫ ይቆርጣሉ፡፡ ምሽቱን ደግሞ እንግጫውን ሲጎነጉኑ ይቆያሉ፡፡ ሲነጋ ደግሞ በጠዋት ተጠራርተው በመሰባሰብ በየሰው ቤት እየዞሩ የተጎነጎነውን እንግጫ ከቤቱ ምሰሶ ላይ ያስራሉ፡፡ እንግጫ የአዲስ ዓመት የምሥራች ምልክት ነው፡፡ በመድበሉ እንደተወሳው፣ እንግጫ ነቀላው በዜማ የታጀበ ነው፡፡

«እቴ አበባዬ ነሽ

አደይ ተክለሻል

አደይ ተቀምጠሻል

ባሶና ሊበን

አዋጋው ብለሻል

ባሶና ሊበን

ምነው ማዋጋትሽ

አንዱ አይበቃም ወይ››

በዚህ ጊዜ ወንዶች ደግሞ ያዘጋጁትን ዳቦት (የችቦ ስም) በእሳት ለኩሰው እያበሩ በመምጣት እንግጫ ለሚጎነጉኑት ሴቶች ያበሩላቸዋል፡፡ ዳቦታቸውን እያበሩ ወደ ሴቶቹ በሚያመሩበት ጊዜ የሚያዜሙት ዜማ አላቸው፡፡

«ኢዮሃ ኢዮሃ

የቅዱስ ዮሐንስ

የመስቀል የመስቀል

አሰፉልኝ ሱሪ

ኢዮሃ›› በማለት ያዜማሉ፡፡

በከተሞች አካባቢ እንግጫ ነቀላው እየቀረ አበባየሆሽ የሚለው ጨዋታ በመስፋፋት ላይ ይገኛል። ልጃገረዶቹ ወደየሰው ቤት ሲሄዱ ሎሚ ይሰጣቸው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን የእንግጫው ሴቶች ራሳቸው ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› እያሉ ሎሚ ሲሰጡ ገንዘብ ይሰጣቸዋል፡፡

ተቀጸል ጽጌ›› (አበባን ተቀዳጅ)

‹‹ተቀጸል ጽጌ›› አበባን ተቀዳጅ ማለት ሲሆን፣ በዘመነ አክሱም በስድስተኛው ምዕተዓመት በነበሩት አፄ ገብረ መስቀል ዘመን የክረምት መውጫ በሆነው መስከረም 25 ቀን የሚከበር የወቅት ሽግግር በዓል ነበር። ለንጉሠ ነገሥቱ የአበባ አክሊል/ጉንጉን ይበረከትለት ስለነበር ‹‹ተቀጸል ጽጌ፤ ገብረ መስቀል ሐፄጌ›› (አፄ ገብረ መስቀል አበባን ተቀዳጅ) እየተባለ ይዘመር ነበር፡፡ ከ15ኛው ምዕተዓመት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ግማሽ ክፍሉ (ግማደ መስቀል) መምጣቱን ተከትሎ በዓሉ ወደ መስከረም 10 ቀን ዞሯል። እስከ መጨረሻው ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ (1923 – 1967) ድረስ በዓሉ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ሲከበር ቆይቷል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ወዲህ በዓሉ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐውደ ምሕረት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አማካይነት የአበባውን በዓል ማክበሩና ለበዓሉ ታዳሚዎችም አበባን ማደሉ ቀጥሏል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ

መስከረም 1 በክረምት ውስጥ የምትገኝ ያመት መነሻ ናት፡፡ ሰኔ 26 ቀን የገባው ክረምት የሚወጣው መስከረም 25 ቀን ላይ ነው፡፡ የስድስተኛው ምዕተዓመት የነገረ መለኮት ሊቁ (ቲኦሎጊያን)፣ መዝሙረኛውና ዜማ ቀማሪው ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፈ ድጓው ‹‹ኀለፈ ክረምቱ ጸገዩ ጽጌያት ቆመ በረከት!›› – ክረምቱ አለፈ አበቦችም ፈኩ፣ በረከትም ቆመ ይለናል፡፡

ከዓመት አውራ መነሻ (ርእሰ ዐውደ ዓመት) መስከረም አንድ ቀን እስከ መስከረም ሰባት (ስምንት) ቀን ያለው ‹‹ዮሐንስ›› ሲባል፣ ከመስከረም ዘጠኝ እስከ 15 ዘመነ ፍሬ ይባላል፡፡ ‹‹ዮሐንስ›› የሚለው ቃል የተወሰደው በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ከሚገኘውና ኢየሱስ ክርስቶስን ካጠመቀው የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ ነው፡፡ መስከረም አንድ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕለተ ዮሐንስ መባሉ በተምሳሌታዊ ፍች የመጣ ነው፡፡ ከአሮጌው ብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን፣ ወደ ዓመተ ምሕረት መሸጋገሪያ ላይ የመጣው መንገድ ጠራጊው ዮሐንስ ስለሆነ፤ ባህሉ/ ትውፊቱ ካሮጌው ዓመት ወዳዲሱ መሸጋገሪያዋን ዕለት፣ መስከረም አንድ ቀንን በዘይቤ ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› ‹‹ዕለተ ዮሐንስ›› እያለ ይጠራዋል፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ባገልግሎት ላይ ይገኛል፡፡

ሊቁ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ የዛሬ 54 ዓመት በአዲስ አበባ ራዲዮ ጣቢያ የዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ ላይ፣ ባደረጉት ንግግር ማሰሪያቸውን እንዲህ ገልጸውት ነበር፡፡ ‹‹በዘመን መለወጫ በዓል አሮጌው አልፎ አዲስ ሲተካ የክረምት ጭለማ አልፎ ብርሃን ሲመጣ ሁሉም ‹በተውሳከ መብልዕ ወመስቴ› (ምግብና መጠጥን በመጨመር) እየተደሰተ፣ ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላው መሻገሩን ያከብራል፡፡

ገጣሚ ነብይ መኮንን መስከረምን በፍቅር ይመስላታል፣ ይቀኝላታል፤ እንዲህ እያለ፡፡

የመስከረም ፍቅር

የመስከረም ጸሐይ ጥርሷን ለመፏቋ

ዕድል ለመንቃቷ ዓለም ለመሳቋ

ሕይወት ለመፍካቷ

ጭቃው ለመድረቁ

ዝናብ ለማቆሙ

ዓመት ለማለፉ

ዘመን ለማበቡ

ቀንሽና ቀኔ ነዶ ለመፋሙ

የናፈቅሽው እኔ

የጓጓሁት ፍቅርሽ

ደርሶ ለመጣሙ፡፡

ልብሽ ለመዝፈኑ ልቤ ለማዜሙ

ምን ይሻል ምስክር ለዓለም ዘልአለሙ

መስቀል ወፍና ዐደይ ከተፈጣጠሙ፡፡

በመጨረሻም

አዲሱ ዓመት የሠላም፣ የጤና፣ የፍቅር፣ የብልጽግና፣ የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የመደማመጥ እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡ (ማጣቀሻዎች፡- ሪፖርተር፣ አዲስ አድማስ፣ የማኀበረ ቅዱሳን ድረገጽ፣ ከአጥናፍ እስከአጥናፍ ድረገጽ…)

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ጳጉሜ 6/2011

(ፍሬው አበበ)