ብሔራዊ አንድነታችን ለሰላማችንና ብልጽግናችን!

29

 ያሳለፍናቸው የጳጉሜን አምስት ቀናት የብልፅግና፣የሰላም፣የአገራዊ ኩራት ፣የዴሞክራሲ፣የፍትህ ቀን ተብለው በመሰየማቸው አኩሪና ይበል የሚያሰኝ ተግባራት ተከናወኖባቸው አልፈዋል። የዛሬው የመጨረሻውና የአዲስ ዓመት ዋዜማ ጳጉሜን ስድስት ቀን 2011ዓ.ም. ደግሞ የብሔራዊ አንድነት ቀን በማለት እያከበርነው እንገኛለን። በርግጥም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብሔራዊ አንድነት በእጅጉ ያስፈልገናል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብሔራዊ አንድነትን ስንመኝ አንዳንዶች «ብሔራዊ እርቅ ነው የሚያስፈልገን!» ሲሉን፤ አንዳንዶቹ «ማን ከማን ተጣልቷል እርቅ የሚያስፈልገን?» ሲሉ ቀለዱ። እውነታው ግን የተለየ ነበር።

በሕዝቦች መካከል መሠረታዊ ጥላቻና አንድነትን የሚያጠፋ ቂም ባይኖርም፤ ለሕዝቦች መለያየት አድብተው ሲሰሩ የነበሩ ኃይሎች መኖራቸው ግን በገሀድ ታይቷል። ይህ በመሆኑም ባሳለፍናቸው ሁለት ዓመታት፤ በተለይም እያገባደድነው በምንገኘው በዚህ ዓመት በአገሪቱና በሕዝቦቿ ላይ የደረሰው መከራ ለሰሚው ከባድ ነበር።

በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ታስረው፣ ጥፍራቸው ተነቅሎ፣ ተኮላሽተው፣ ብልታቸው ላይ የውሀ ላስቲክ ተንጠልጥሎ ተሰቃይተው፣ ተደብድበው አካላቸው ጎድሎ ከሞት የተረፉት ሁሉ ከእስር ተፈቱ፤ ፍትህና ዴሞክራሲ በመጠየቃቸው ከአገር ተሰድደው፣ ጭቆና አንገፈገፈን ብለው ጠመንጃ አንስተው በረሃ ገብተው፣ ከፖለቲካ ተሳትፎ ተገልለው አኩርፈው በዝምታ የተቀመጡ ሁሉ በአገራቸው በሰላም በመረጡት መስክ እንዲሳተፉ ጥሪ ተደርጎላቸውና አገር ውስጥ ገቡ።

ይህ እርምጃ በፈጠረው መልካም ዕድል ተሰባስበን ብሔራዊ አንድነታችንን ማጠናከር ሲኖርብን፤ በአንዳንዶቹ እየተረሳ ጥቃቅን ነገሮችን ለግጭት ማራገቢያ ሲያደርጉ መስተዋሉ ያሳዝናል።

«መገናኛ ብዙሃኑን የመጠቀም መብት አጥተናል፤ እንዳንጠቀምበት ተደረግን» ሲሉ የነበሩም ዕድሉ ሲመቻችላቸው የነበሩበትን ረስተው ድል አድርገው የመጡ ያህል መረን በወጣ መንገድ ካለምንም ይሉኝታና ሀፍረት የአፍራሽ ተልዕኳቸው ማሰራጫ ሲያደርጉት ማየቱም የተለመደ ሆነ።

 በተሻለ ሁኔታ ተዋድዶና ተከባብሮ ይኖር የነበረ ዜጋችን በመካከሉ በተሰገሰጉ የአንድነት ጠንቆች ሰላሙ ተናግቶ፣ ከቀዬው ተፈናቅሎ፣ ሕይወቱን አጥቶና ለጎዳና ሕይወት ተዳርጎ ተመልክተናል። ይህ ሁሉ ጥፋት አንድነታችን ተሸርሽሮ እርስበርስ እንድንጠፋፋ ከሚፈልጉት መጥፎ አሳቢዎች በስተቀር ማንን ሊያስደስት ይችላል?

የፖለቲካ ተንታኝ ነን የሚሉ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ነን የሚሉ ፖለቲከኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን የሚሉ ቋሚ ጠበቃዎች፣ አክቲቪስት ነን የሚሉ ጽንፈኞች፣ የእከሌ ቡድን ጠበቃ ነን የሚሉ ስውር መልዕክተኞች ሁሉ ለጊዜው የቆሙለት ዓላማ የዕለት ጉርሳቸው ከሆነ የጦዘው ፖለቲካ ሲረግብ ለሆዳቸው ማደራቸው ተሰምቷቸው የሀፍረት ካባ ይከናነባሉ።

በወገናቸው ደም መፍሰስ፣ መሰቃየትና ንብረት መውደም እነርሱ የህሊና ስቃይ ውስጥ ይገባሉ፤ የአገራቸው እድገትም ወደ ኋላ መጎተት የእነርሱም መጎዳት መሆኑን ይገነዘባሉ። ይህ ስሜት የሚሰማቸው ግን ህሊና ያላቸው ከሆኑ ብቻ ነው።

ይህ ሁሉ ምስቅልቅል ሁኔታ በአገሪቱ ሲከሰት መንግሥት በታጋሽነት የተመለከተው የታመቀው ወጥቶ መጪው ጊዜ የተሻለ ይሆናል ብሎ በማሰብ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተገልጿል። የታመቁ ስሜቶች እንዲተነፍሱ፣ ሁሉም ያሻውን እንዲናገር የመወያያ መድረኮች ተመቻችተው ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል፤ ልዩነቶችም አንድነቶችም ያለምንም ገደብ ተሰብከዋል። እንዲህም ሆኖ ጥቂቶች ካፈርኩ አይመልሰኝ ብለው በለመዱት የመከፋፈል ፅንሰ ሃሳብ ላይ ተቸክለው ሊቆዩ ይችላሉ።

ሚዛናዊ የሆነውና የአንድነቱ መኖር እንደሚጠቅመው የሚረዳው ሕዝብ ግን አገራዊ አንድነቱን ጠብቆ ማቆየቱ የአገሪቱ ታፍሮና ተከብሮ መቆየት የእርሱ ክብር መሆኑን ስለሚገነዘብ ነው። መላው ሰላም ወዳዱ ሕዝብ አንድነቱና ሰላሙ በመጠበቁም የአገሩ ማደግ የእርሱም ማደግ መሆኑን በማወቅ ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን ሊያስጠብቅ በቁርጠኝነት መነሳት ይኖርበታል። ለዚህ ነው የዛሬው የብሔራዊ አንድነት ቀን የሁሉም ቀናት መደምደሚያ የሆነው።

አዲስ ዘመን ጳጉሜ 6/2011

 ወንድወሰን መኮንን