የማያረጁ የትምህርት ቤት ትዝታዎች

5

አራት ዓሠርት ዓመታት ካለፉ በኋላ በወርቃማና በልዩ ልዩ ቀለማት በተዋቡ አለላዎች በተሸመነ የትዝታ ሙዳይ ውስጥ “የተሰነዱ” ገጠመኞችን ለማስታወስ ሰበብ የሆነኝ አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ በተመለከተ የሚደረጉ ሰሞንኛ ውይይቶች ናቸው። በግሌ በትምህርቱ ሪፎርም ላይ የሀገሬ የትምህርት ሚኒስቴር ከወሰዳቸው ጠንካራ የማሻሻያ ሃሳቦች መካከል የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ያስከተለውን ሀገራዊ ጉዳት ጠንከር አድርጎ በመተቸት በወጣቱ ትውልድ ሕይወት ውስጥ ለተፈጠረው ውጥንቅጥና ቀውስ ሰበብ እንደነበር ማመኑንና ይቅርታ መጠየቁን አድንቄያለሁ።

ምናልባትም ከሀገራችን ሚኒስቴር መ/ቤቶች መካከል በ2011 ዓ.ም “ይቅርታ!” በመጠየቅ ሪከርድ የሰበረው የትምህርት ሚኒስቴራችን ሳይሆን እንደማይቀር እገምታለሁ። በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለተፈጠረው ስህተት፣ ለምን አራት ትምህርቶች ብቻ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ እንደተመረጡ ወዘተ… ደጋግሞ ሕዝቡን በይቅርታ ተማጥኗል። ይቅርታው ክፋት ባይኖረውም ለወደፊቱ ግን መሰል “ብሔራዊ ስህተቶች” እንዳይደገሙ አጥብቆ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁሞ ማለፉ ይገባ ይመስለኛል። ስህተቶቹ ውለው አድረው የከፋ ውጤት እንዳያስከትሉም በአግባቡ መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል። ስለ ዝርዝር ጉዳዮቹ ትንተናና ሂስ መስጠቱ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስላልሆነ እንዳስፈላጊነቱ ወደፊት መለስ ብሎ ለመፈተሽ ቀጠሮ ማስያዙ አይከፋም።

“ሳይቃጠል በቅጠል” እየተባለ ገና በማለዳ የተጮኸለት መላው የትምህርት ሥርዓታችን በልብ ድንዳኔና እምቢታ ለዓመታት ታብዮ ቢጓዝም የማታ ማታ ጀንበር ስታዘቀዝቅም ቢሆን እንደገና መቃኘቱና መቃናቱ የሚያስመሰግን ጅምር መሆኑ ሊበረታታ ይገባል። ፍኖተ ካርታው ስላለው ምልዓት ወይንም ጉድለት ብዙ ሀገራዊ ውይይቶች እየተደረጉበት ስለሆነ ሰነዱ “ለእኛ ለተራ ዜጎች” ታትሞ በእጃችን ሲገባ ወይንም በቴክኖሎጂ አጋዥነት ወደ ኮምፒዩተራችን ሣጥን ውስጥ ሲላክ አገላብጠን እናየዋለን።

ለሀገራዊና ሞራላዊ ሥነ ምግባር ባዕድ ሆኖና ተፋትቶ መረን ለለቀቀ የፖለቲካ ፈረስ መፈናጠጫ በመሆን ሲጋለብበት የነበረው ሥርዓተ ትምህርታችን ትቶብን የሄደው ጠባሳ እንዳያመረቅዝ ደግሞ ደጋግሞ ሊመከርበት እንደሚገባ በማሳሰብ ወደተነሳሁበት ዋና ሃሳብ አቀናለሁ። የእስካሁኑ ጥረትም እንደሚበረታታ እግረ መንገዴን አስታውሼ ማለፍ እወዳለሁ።

ወደ ትዝታዬ ላቅና። ጸሐፊው የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለበት የአራት ኪሎው ወወክማ (የዛሬው የአዲስ አበባ ወጣቶችና ሕፃናት ቴአትር) ከመላው አዲስ አበባ እየተመረጡ ዕድል ያገኙ ለነበሩ ጥቂት ተማሪዎች ትልቅ ባለውለታ ነው። እንደ ፓይለት ፕሮግራም ወጣቶችን በውስን ቁጥር እየተቀበለ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን ብቻ ሳይሆን በብሔራዊ ክብር፣ በሀገራዊ ኩራት፣ በአፍቅሮተ ሕዝብና በአእምሮና በዕውቀት ልህቀት ተማሪዎችን እየቀረፀ ያወጣ የነበረው የያኔው ወወክማ ለማስፈጸም የቆመለት የተከበረ ዓላማና መርህ የሚከተለው ነበር፤

“ወወክማ በዓላማው ኢንተርናሽናል ቢሆንም በሚሠራበት ሀገር ሁሉ ነፃና ብሔራዊ ነው። በሚያካሂደውም ፕሮግራም ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ ለልጆችና ለወጣቶች ትክክለኛ የሆነ ሰብዓዊነትን ለማስገኘት የሚሠራ ነው። የወወክማ የመጨረሻው ግብ በአእምሮ፣ በመንፈስና በአካል የጠነከሩ ወጣቶችን ሰብዕና ገንብቶ ለሀገራቸው ታማኝ ዜጋ እንዲሆኑ ማብቃት ነው።” በእርግጥም የተቋሙ ህልም በብዙ ወጣቶች ሕይወት ውስጥ ፍቺ ማግኘቱን ጸሐፊውም የዚሁ ተቋም ውጤት ስለሆነ አስረግጦ ለመመስከር አይከብደውም። በዚህ ተቋም ውስጥ ያለፉ በርካታ የዘመኑ ታዳጊዎች ዛሬ ከሀገራችንም አልፈው ተርፈው በተለያዩ ዓለማት ተበትነው በታላላቅ የስኬትና የተመራማሪነት ደረጃ ላይ አንቱታን እያተረፉ ይገኛሉ።

“የነገይቱ ኢትዮጵያ ታላላቅ ተስፋዎች” በሚል መሪ ዓላማ ሕፃናትን በፈተና አወዳድሮ በመቀበል እስከ 1ኛ ደረጃ አስተምሮ ከፍ ወዳሉት ትምህርት ቤቶች ያሸጋግር የነበረው ወወክማ የቀለም ትምህርቱን ፕሮግራም ያካሂድ የነበረው እንደ ዋነኛ ተልዕኮ በመያዝ ሳይሆን በቀዳሚነት ትኩረት ይሰጥበት ከነበረው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎን በተጓዳኝነት በማስኬድ ነበር። ከቀለም ትምህርቱ በላቀ ደረጃ በስፖርቱ ዘርፍ ያበረከታቸው ሀገራዊ አስተዋጽኦዎች በእጅጉ የሚያስመሰግኑ ነበሩ።

አዲሱ ፍኖተ ካርታ ሊያጤንበት ከሚገቡ የወወክማ ተሞክሮዎች መካከል አንዱን በዋቢነት ልጥቀስ። ወወክማ በዘመኑ የማስተማር ተግባሩን ያከናወን የነበረው ከአንዱ ወይንም ከሁለቱ በስተቀር ቋሚ መምህራን ተቀጥረው አልነበረም። አስተማሪዎቻችን በሙሉ ከተለያዩ ተቋማትና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጭምር በበጎ ፈቃደኝነት ለአንድ ሴሚስተር ለማስተማር የውዴታ ግዴታ ገብተው ሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ ቃል የሚገቡ ስለነበሩ ከእነርሱ እናገኝ የነበረው የዕውቀት ትሩፋት ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። በትጋት፣ በብሔራዊ ፍቅርና በዜግነት ኃላፊነት ልክ እንደ ተከፋይ መምህራን በማስተማሩ ሥራ ይተጉ የነበሩ እነዚያን ሞዴል የሕዝብ ልጆች ዛሬ ላይ ቆሜ የማስታውሳቸው በከፍተኛ አክብሮትና ፍቅር ነው። ትውልዴን ወክዬ ወወክማና መምህራኖቻችንን በታላቅና በማይደበዝዝ አክብሮት አመሰግናለሁ።

ከማስተማር ኃላፊነታቸው በተጓዳኝም መምህራኖቻችን አንድ ለእናቱ በነበረው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ እየወሰዱን “ነገ ለከፍተኛ ትምህርታችሁ የሚቀበላችሁ ይህ ተቋም ነው” በማለት ያሰረፁብን ተስፋ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሆኖ በውጤት ተረጋግጧል። ይህንን መሰሉ የበጎ ፈቃደኝነት ተግባር ዛሬ የዘመኑ ዐውድ በሚፈቅደውና ጊዜው “ይሁን በሚለው” መልኩ በየትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ተግባራዊ ቢሆን ነገ ሊተረክለት የሚችል እጅግ ፍሬያማ ውጤት ስለሚያስገኝ ትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን ቢያስብበት አይጠቅም ይሆን?

ወወክማ ዛሬ ስሙ እንጂ ተግባሩ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለመመስከር ያዳግታል። በርካታ ስፖርተኞችንና ተማሪዎችን በማፍራት የሀገር በረከት የነበረው ያ ስመ መልካም ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋም እጅግ አድጎና ሰፍቶ ብዙዎችን መታደግ ሲገባው ሀብቱና ሕንፃዎቹ ተቀምተው እንደ በርካቶቹ ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ወደ ኋላ እንጂ ወደ ፊት ለመዘርጋት ያለመቻሉ ቁጭት ውስጥ ይከታል። በርካታ ተመራማሪዎች፣ ፕሮፌሰሮች፣ ስፖርተኞችና የተለያዩ ባለሙያዎችን ያፈራው ወወክማ እንደገና አንሰራርቶ ወደ ቀድሞ አገልግሎቱ እንዲመለስ ውለታ ውሎልናል የምንል ዜጎች ተቀዳሚውን ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባ አምናለሁ።

ሌላውና ጸሐፊው ከልቡ የሚመሰክርለት የትምህርት ቤቱ ትዝታ በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት የቆየባቸው ሦስት ያህል ዓመታት የሚጠቀሱ ናቸው። ይህ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረው የሀገራችን አንጋፋ ትምህርት ቤት በተማሪዎች አያያዝና በአስተዳደር አመራሩ ከዕድሜው እኩል ገዝፎ ቢጠቀስ ያንስበት ካልሆነ በስተቀር ይበዛበታል ለማለት ያዳግታል። የትምህርት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ለትምህርት ሪፎርሙ ትግበራ ምናልባት የሚያግዛቸው ከሆነ ቀጥዬ የማስታውሳቸውን አንዳንድ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተው ቢያስቡበት አይከፋም።

የስድስተኛ ክፍልን ብሔራዊ ፈተና አልፈው ወደ ሰባተኛ ክፍል የሚዘዋወሩ የወወክማና የአካባቢው ትምህርት ቤት ተማሪዎች በቀጥታ ይመደቡ የነበረው ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ነበር። የወቅቱ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የነበሩት ተወዳጁና ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ ሊያስታውሳቸው የሚገባው አቶ መኮንን ሸገነ በመጀመሪያው ቀን ያደረጉልን አቀባበል በእውነቱ የሚገርምና ዛሬም ድረስ በእኔና በዕድሜ እኩዮቼ አእምሮ ውስጥ ሳይደበዝዝ እንደፀና ይኖራል።

እኒህ ርዕሰ መምህር ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተመድበን የሄድነውን ተማሪዎች በሙሉ በክፍል ደረጃና ዕድሜ ገደብ ሳያደርጉ በሰንደቅ ዓላማው ፊት ለፊት ካሰለፉን በኋላ በትልቅ ፍቅርና አክብሮት “የእንኳን ደህና መጣችሁ” መልዕክት በማስተላለፍ የትምህርት ቤቱን ዝርዝር ሥርዓት ካብራሩልን በኋላ የተመደብንበትን ክፍል እንድናውቅ ተደረገ።

በማስከተልም በየስማችን የተዘጋጀልን ባለ 24 ገጽ የትምህርት ቤቱ ደንብ በዝርዝር የሰፈረበትን መታወቂያ ደብተር ልክ እንደ ዲፕሎማ በታላቅ ክብር አስረከቡን። የመታወቂያው ደብተር እንደማንኛውም መታወቂያ መጠኑ አነስተኛ ሆኖ እጅግ ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተተ ነበር።

ዝርዝሩ መግለጫ፣ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ከሚለው ይጀምርና 18 የዳይሬክተሩ ጠቃሚ ምክሮች፣ ስለ ነባር ተማሪዎች፣ ተማሪዎች ሊፈጽሟቸው የሚገቡ ዐበይት ተግባሮች፣ የፈተና ጊዜያት፣ የፈተና ነጥብ ድልድልና የማለፊያ ደንቦች፣ ስለ ፈተና ሕጎች፣ ከትምህርት ቤት የሚያስወግዱ መጥፎ ተግባሮች፣ የተማሪዎች የክፍል እልቅና ተግባራት፣ ስለ ሽልማት፣ መልቀቂያ ስለሚጠይቁ ተማሪዎች፣ በየደረጃው ያሉ የትምህርት አመራሮችና የመምህራን ኃላፊነቶች ከእነ ስማቸው፣ ማዕረጋቸውና የቢሮ ስልክ ቁጥራቸው ከዝርዝር ኃላፊነታቸው ጋር፣ የዕቃ ግምጃ ቤት፣ የቤተ መጻሕፍትና የክሊኒክ አጠቃቀም ወዘተ… ዝርዝር መመሪያዎች በመታወቂያው ውስጥ ተጠቃሎ ቀርቧል። በግሌ ይህን በመሰለ የተከበረ ት/ቤት ለመማር በመቻሌ ዕድለኛ ነኝ ብዬ ከማመን ባለፈም እንደዚያ ዓይነት አደረጃጀት ያላቸው ት/ቤቶች ዛሬም ድረስ ቢኖሩልን ኖሮ ሀገራችን የት በደረሰች እያልኩ መመኘቴ አልቀረም።

በየትምህርት ቤቱ የሚማሩ ተማሪዎች ዕለት በዕለት ከኪሳቸው የማይለዩትን መታወቂያ በነጠላ ገጽና በውሱን ይዘቶች ብቻ አሳትሞ ከመስጠት ይልቅ የዘመኑን ዐውድ በጠበቀ መልኩ እንደ ቀድሞው የዳግማዊ ምኒልክ የተማሪዎች መታወቂያ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዙ አንድ ወጥ ብሔራዊ ወይንም ክልላዊ መታወቂያዎች ቢሆኑ እያልኩ እመኛለሁ። በታጣፊው መታወቂያ ወረቀት ውስጥ ጥቂት ገፆችን ጨምሮ ከላይ የተዘረዘሩትን መሰል መመሪያዎች እንዲይዙ ማድረጉ ጠቀሚነቱ የጎላ ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች ግዴታና ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲገነዘቡም ጭምር የሚያግዝ ይመስለኛል።

ስለ ወቅቱ የዳግማዊ ምኒልክ ዳይሬክተር ስለ ተወዳጁ መኮንን ሸገነ የግል ምስክርነቴን ልስጥ። እኝህ ዳይሬክተር ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ተዘዋውረው የመጡት ከልዑል መኮንን ት/ቤት ይመስለኛል። ምክንያቱ ደግሞ የዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ተማሪዎችን የተደጋገመ አመፅና ረብሻ አደብ እንዲያስገዙ ነው እየተባለ ይወራ እንደነበር አስታውሳለሁ። መኮንን ሸገነ በአጭር አገላለፅ ለመምህርነትና ለትምህርት አስተዳደር የተፈጠሩ ትክክለኛ ሰው መሆናቸውን በግሌ ሳላመነታ እመሰክራለሁ። ቀደም ሲል በደረሰባቸው የባቡር አደጋ ምክንያት ቀኝ እጃቸውና እግራቸው ክፉኛ ስለተጎዳ የሚሄዱት እያነከሱ ነበር። እንደሚመስለኝም አርቴፊሻል ሰው ሠራሽ አካል ሳይገጠምላቸው አልቀረም። በእሳቸው ዘንድ የሚያለምጥና አለበቂ ምክንያት ክፍል የሚዘጋ መምህር ይቅርታ አልነበረውም።

ያልተገባ የተማሪዎችን ባህርይና ረብሻም በትዕግስት አያልፉም ነበር። መኮንን ሸገነ ከቢሯቸው ይልቅ አዘውትረው የሚገኙት በሜዳ ላይና ክፍሎችን እየተዘዋወሩ በመጎብኘት ነበር። አስተማሪ የጎደለበት ክፍልም እየገቡ ያስተምሩ እንደነበር ደጋግሞ አጋጥሞናል። ለታታሪና ጎበዝ ተማሪዎች ያላቸውን ልዩ አክብሮትና ስስትም በግሌ አጋጥሞኝ ተመልክቻለሁ። እጅግ አድርጌ የማከብራቸው እኒህ ታላቅ ሰው በትምህርት ሥራቸው ላይ እንዳሉ በደም ጥማተኛ ነፍሰ ገዳዮች ሕይወታቸው ያለፈው በፈረቃ ሽግግር መሃል በተማሪዎቻቸው መካከል ቆመው ተግባራቸውን ሲከውኑ ነበር። ዛሬ “ያ ትውልድ” በማለት ራሱን የሚያንቆለጳጵሰውና በተለያዩ ቡድኖች ተፈራርጆ “በስመ ትግል” ሲፋጅና ሲፈጅ ትኩስ ዕድሜውን በከንቱ ያባከነው “ያ ወጣት” ይህንን መሰል ታሪክ ሲያነብ ህሊናው ምን እንደሚለው አላውቅም። ከዘመናት በኋላ መሰል የሞት ዜና በየትምህርት ተቋማት ሲደመጥ መስማት ምን ያህል እንደሚያሳምም ለመረዳት አይከብድም።

ዛሬም ድረስ ከማስተማር ሥራቸው ያልተለዩት ሌላው የማከብራቸው የሰባተኛ ክፍል የአማርኛ መምህሬ አቶ ሰውነት ጥበቡም ቢታወሱ መልካም ይሆናል። መምህር ሰውነት ጥበቡ በቀለም ዕውቀት መጋቢነታቸው ብቻ ሳይሆን በቅንነት የሚገለፀው አባታዊ ባህርያቸው ያለምንም መሳቀቅ ተማሪዎች በቀላሉ የሚቀርቧቸው የቀለም አባት ነበሩ። ስናናግራቸውም እንደ መምህር ሳይሆን እንደ መልካም አባት ተጠግተንና በግልጽነት ነበር። በግሌ ዛሬም ድረስ ያልተለያየነው እኒህ ትጉህ መምህር ያሳደሩብኝ በጎ ተጽእኖ በቀላሉ የሚገለጽ ብቻ አይደለም። በአጭሩ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ እንድበቃ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት እርሳቸው ናቸው።

በትምህርት ቤት ውስጥ ያለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ሀገርም ጭምር የምትሰራው እዚያው ትምህርት ቤት ውስጥ ነው። የትምህርት ሥርዓታችን በፖለቲካ ንክር በደመቀባቸው ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ያፈራነው ትውልድ ምን መልክና ይዘት እንዳለው ቤታችን ቢመሰክር ይሻላል። “ከዚህ ከማይሞተው የሰው ልጅ ማደጊያ ስፍራ ግቡ!” የሚለውና በአንዳንድ ት/ቤቶች ዋና መግቢያ በር ላይ የተጻፈው ጥቅስ የሁሉም ት/ቤቶች መለያ ቢሆን መልካም ይመስለኛል። “ትዝታ አያረጅም ይሉ የለ!?” መልካም የትምህርት ዘመን!

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ጳጉሜ 6/2011

(በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)